በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 90(1) ላይ የተደነገገው የዜጐች የማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት ለማረጋገጥ መንግሥት የፖሊሲ መነሻ ሐሳብ ቀርጾ ሽፋኑን ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች በማስፋት፣ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 አውጥቷል፡፡ መንግሥት ምንም ዓይነት የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሌላቸው የግል ድርጅት ሠራተኞች ይህንን ዋስትና እንዲያገኙ በማሰብ ያወጣው ይህ አዋጅ እጅግ ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡ መንግሥት ዋናው ሥራው ሕዝብን ማገልገልና ለሕዝብ ማሰብ እስከሆነ ድረስ፣ ምንም ዓይነት የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሌላቸው ዜጐች በዚህ ሽፋን ውስጥ እንዲጠቃለሉ ማድረጉ ይበል የሚያሰኘው ነው፡፡
ይህ የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን አዋጅ በወጣበት ወቅት የዚህ ሽፋን አንዱ አካል የሆነውና በርካታ የግል ድርጅት ሠራተኞች የሚጠቃለሉበት የፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ነበር፡፡ በመሆኑም በወቅቱ መንግሥት ይህን አዋጅ ሲያወጣ በፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ውስጥ ተካተው የነበሩ ሠራተኞች እንዴት መቀጠል እንዳለባቸው? የሚለው ሐሳብ ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህ የግል ሠራተኞች በፕሮቪደንት ፈንድ ዕቅድ ይቀጥሉ ወይስ በጡረታ ይታቀፉ? በሚለው ሐሳብ ላይ የሚመለከታቸው የግል ድርጅት ሠራተኞች ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ መሠረት በፕሮቪደንት ፈንድ መቀጠል የሚፈልጉት እንዲቀጥሉ፣ በጡረታ መታቀፍ የሚፈልጉት እንዲታቀፉ በራሳቸው መርጠዋል፡፡ ይህ ትክክለኛ አካሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ከመወያየታቸው ባሻገር፣ በጉዳዩ ላይ አማራጮች ቀርበው ዜጐች የሚሻላቸውን መርጠዋል፡፡
አሁን ግን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዲሱ የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ማሻሻያ አዋጅ እንዳይፀድቅ የምንቃወምባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
- ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ አይደለም!
ለፓርላማው የቀረበው ይህ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ያስፈለገባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆንም፣ የሚያተኩሩት ግን በአገሪቱ ያለው የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ላይ ልዩነት እንደይኖርና አንዳንድ ድንጋጌዎች ለትርጉም ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የማሻሻያ አዋጅ ያስፈለገበት ሌላው ምክንያትን ሲገልጽ፣ የግል ድርጅት ሠራተኞችንና ተተኪዎቻቸውን የዘለቄታ የማኅበራዊ ዋስትና ጥቅም ስለሚያሳጣ ነው ይላል፡፡ በረቂቅ አዋጁ የቀረቡት ምክንያቶች ላይ ግን አሁንም ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡
ከአራት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ያሉ ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን እንዲያገኙ ያስቻለው አዋጅ በራሱ የፈጠረው ሥርዓት ነበር፡፡ በወቅቱም ሁሉም የባለድርሻ አካላት ተወያይተው የወሰኑት ውሳኔ ተቀባይነት ነበረው፡፡
እንደሚታወቀው በፕሮቪደንት ዐቅድ ውስጥ የታቀፉ የግል ድርጅት ሠራተኞች የሚያጠራቀሙትን ገንዘብ የሚጠቀሙበት ያንን ድርጅት ሲለቁ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ሠራተኞቹ ለምሳሌ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጥቶላቸው ክፍያ መክፈል ሲኖርባቸው፣ አልያም ራሳቸውን ለማሻሻል ትምህርት መማር ሲፈልጉ ወይም ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው እንደ ሕክምና ያሉ ወሳኝ ነገሮችን ለማከናወን ነው፡፡ እዚህ ላይ እንደታየው እነዚህ የግል ድርጅት ሠራተኞች ይህንን የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘብ የሚጠቀሙበት ለሕይወታቸው ወሳኝ ለሆኑ ጉዳዮች ነው፡፡
እነዚህ ሠራተኞች አሁን ላሉ ወሳኝና ለዘለቄታዊ ኑሯቸው ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ላይ ገንዘቡን እንዳያውሉ ተደርጐ፣ ለእናንተና ለተተኪዎቻችሁ ዘለቄታዊ የማኅበራዊ ዋስትና ጥቅም አመጣለሁ ማለት የትም አያስኬድም፡፡ ከዚህም ባሻገር የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋኑን አንድ ለማድረግ ከታሰበ ለምን ሁሉንም ሠራተኞች በፕሮቪደንት ፈንድ እንዲታቀፉ አይደረግም? በአገሪቱ ያለው የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ሥርዓት ወጥ እንዲሆን በሚል የዜጐች መብት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ረቂቅ አዋጁ ከላይ የተነሱትን ሐሳቦች ተገቢ ምላሽ ስላልሰጠባቸው እንዳይፀድቅ እንቃወማለን፡፡
- ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ላይ ተገቢ ውይይት አልተካሄደም!
ከዚህ በፊት የወጣው ተመሳሳይ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ውይይት ተቀምጠው ነበር፡፡ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን አካል የሆነው ፕሮቪደንት ፈንድ በአንዳንድ የግል ድርጅቶች የነበረ በመሆኑም፣ የእነዚህ ድርጅት ሠራተኞች እንዴት መቀጠል አለባቸው? በሚለው ሐሳብ ላይ ተገቢ ውይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም መሠረት ሠራተኞቹ መታቀፍ የሚፈልጉበትን ዐቅድ መርጠው በዚያው ቀጥለዋል፡፡
አሁን ግን ምንም ዓይነት ውይይት ሳይካሄድ፣ ረቂቅ አዋጁ በጠቀሳቸው ምክንያቶች ብቻ ሁሉም የግል ሠራተኞች ወደ ጡረታ መዘዋወር አለባቸው መባሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ማንም ዜጋ ለራሱን የሚጠቅመውን ከመረጠ በኋላ ‹‹አንተ የመረጥከው ሳይሆን እኔ የመረጥኩልህ ይሻላል›› በሚመስል አካሄድ ይህን ረቂቅ አዋጅ ማቅረብ፣ ‹‹ከባለቤቱ ያወቀ…›› የሚለውን ቢህል ስለሚያመጣ፣ አሁኑኑ ሕዝብ ይወያይበት እንላለን፡፡ በመሆኑም ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገቢ ውይይት ያልተካሄደበት በመሆኑ እንዳይፀድቅ እንቃወማለን፡፡
- ረቂቅ አዋጁ አማራጮች አልቀረቡበትም!
የቀድሞ አዋጅ የግል ድርጅት ሠራተኞች በማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን ሊጠቃለሉ የሚችሉበት አማራጮች ነበሩት፡፡ ዜጐችም እነዚህን አማራጮች ከራሳቸው ሁኔታ በመነሳት መርጠው ቀጥለዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች በአርዓያነት የሚጠቀሱና ሊበረታቱ የሚገባቸው ናቸው፡፡ አሁን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን ሁሉም የግል ድርጅት ሠራተኞች ወደ ጡረታ እንዲዞሩ የሚያስገድድ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የግል ድርጅት ሠራተኞች ወደ ጡረታ እንዙር ካሉ አማራጩ ያለ በመሆኑ በዚያው መቀጠል ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ሌሎች አማራጮችን ያላቀረበ በመሆኑ እንዳይፀድቅ እንጠይቃለን፡፡
እንግዲህ ከላይ እንደማሳያ በጠቀስናቸው ሦስት ነጥቦች ምክንያት ረቂቅ አዋጁ የግል ድርጅት ሠራተኞች መብትን የሚጋፋ በመሆኑ፣ የተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን በማጤን ረቂቁን እንዳያፀድቀው እንጠይቃለን፡፡