ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ሕፃናትና ተማሪዎች የሚሳተፉበት የምሥራቅ አፍሪካ ‹‹ፉት ቦል ኔት›› የተሰኘ ውድድር በሱዳን ካርቱም ከግንቦት 28 እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ሶማሊያ ተሳታፊ አገሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡
‹‹ፉት ቦል ኔት›› ከመደበኛው የእግር ኳስ ለየት እንደሚል፣ ዋነኛ ዓላማውም በታዳጊ ሕፃናት መካከል ውድድርን ወይም ፉክክርን ማዕከል አድርጎ የሚዘጋጅ እንደሆነም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ እንደ መግለጫው፣ ተሳታፊ አገሮችና አካላት መቻቻልን፣ ትጋትንና መከባበርን፣ ለማጎልበት በሚል በኢትዮጵያ የኦሊምፕአፍሪካና በሱዳን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ትብብር የተዘጋጀ እንደሆነ ጭምር አስታውቋል፡፡
ውድድሩ ከተለመደው የእግር ኳስ ጨዋታ የሚለይበት ባህሪ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ቡድን በስድስት ወንዶችና በአራት ሴቶች ተደራጅቶ መከናወኑ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በውድድሩ ለየት ያለ ክህሎትና ብቃት የሚያሳዩ ለሁለት ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች ነፃ የትምህርት ዕድል እንደሚመቻችላቸውም በመግለጫው ተካቷል፡፡
በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ታዳጊዎች በቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኙ 12 የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ተወዳዳሪዎቹም ቀደም ሲል የ‹‹ፉት ቦል ኔት›› ጽንሰ ሐሳብና አተገባበር ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውን ጭምር ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡