Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

‹‹ሰው በዜና ውኃ በደመና››

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደው አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት ግንቦት 19 ቀን በገለጸበት ወቅት የተገኙት ጋዜጠኞች ገጽታ (ፎቶ በታምራት ጌታቸው)

**********

ባማራት!

ላዲስ እጮኛዬ

ፍጹም ለወደድኳት

ነፍሷ ያሳሻትን

ጥሬ ላቀርብላት

ይዞኝ አዲስ – ፍቅር

ስለወዘወዘኝ

ላሞላላት ሳለግም

ልቧ ሲፈቅድልኝ

ምን አማረሽ ፍቅሬ

የኔ ውዷ ክብሬ

ብዬ ብጠይቃት

ኖሮ ያዋለላት

. . . አለች . . .

‹‹ጥቁር – ወተት›› እንድፈተንበት

ከልዬ አጥናፍ ካጥናፍ

ፍቅርዬ ላማራት

እንጂ ነጭ ወተት

ላም ጥቁር የት አላት?

ባሰምር ደክሜ

ብትቀይርልኝ

ከፋፍታ አፎቿን – አለች

‹‹ነጭ-ኑግ›› አርግልኝ

ገባኝ’ና ግራ

እንዲህ ለጦፍኩላት

በምድር ስላጣሁ

ፍል-ገቷን ለመሙላት

ጀርባ – በጀርባ ሆን

ፍቅርዬ – ባማራት!

  • ማሙሽ ላቀው ‹‹ብቸኝነት›› (2005)

 

**********

ስብራት ከድርድር ያላገዳቸው ጆን ኬሪ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በደረሰባቸው የብስክሌት አደጋ እግራቸው ቢሰበርም ከኢራን ጋር በኒውክሌር ጉዳይ የሚደረገው ድርድር እንደማይቆም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች አሳውቀዋል፡፡ የቱዳ ፍራንስ ውድድር በሚካሔድበት መስመር ስዊዘርላንድ ውስጥ አደጋው ከደረሰባቸው በኋላ ጄኔቫ ወደሚገኝ ሆስፒታል በሒሊኮፕተር ተወስደዋል፡፡

የ71 ዓመቱ ኬሪ ለብስክሌት ከፍተኛ ፍቅር አላቸው፡፡ በአደጋው ለተጐዳው እግራቸው ሕክምና እየተደረገላቸው ቢሆንም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ቦታ ጉዳት ስለደረሰባቸው ቶሎ ላያገግሙ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር የሚጠናቀቅበት ቀን መቃረቡ ጥያቄ ቢያስነሳም የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ‹‹ኬሪ በቶሎ ያገግማሉ›› ብሏል፡፡

አደጋው የደረሰባቸው ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሐመድ ዣቫድ ዛሪፍ ጋር ለስድስት ሰዓታት ከተወያዩ በኋላ ነበር፡፡ አሶሽየትድ ፕሬስ የአሜሪካ ስቴት ሴክሬተሪ ዲፓርትመንትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ድርድሩ በተያዘው ቀን እንዲጠናቀቅ እየሠሩ ነው፡፡ ኬሪ አደጋው ከደረሰባቸው ከደቂቃዎች በኋላ በቶሎ ወደ ሥራ ለመመለስ ያላቸውን ጉጉት በትዊተር ገጻቸው አስፍረው ነበር፡፡ 

********************

ከክፍያ የበለጠው ጉርሻ

ለአንዳች አገልግሎት የሚከፈል ገንዘብ ተጠቃሚው ለመስተንግዶ ከሚሰጠው  ጉርሻ (ቲፕ) ማነሱ የተለመደ ነው፡፡ ከአሜሪካ ዋሽንግተን ሰሞኑን የተሰማው ዜና ግን ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

ማንነቱ ያልተገለፀ ግለሰብ ብሉ ፎርቲፎር የተባለ ሬስቶራንት ውስጥ የ93 ዶላር ምግብና መጠጥ ተጠቅሞ የ2,000 ዶላር ጉርሻ ሰጥቷል፡፡ ግለሰቡ አንድ ቢራና ጋምቦ (የሰሜን ሉዊዝያና ባህላዊ ምግብ) ያዛል፡፡ ከሬስቶራንቱ ሲወጣ ‹‹ስለ ጋምቦው አመሰግናለሁ፤ 1,000 ዶላር ለሼፉ፣ 500 ዶላር ለአስተናጋጇና 500 ዶላር ለሬስቶራንቱ ባለቤት ይሰኝልኝ፤›› የሚል ጽሑፍ ትቶ ነበር፡፡

ብሉ ፎርቲፎር ሬስቶራንት ከተከፈተ አራት ዓመቱ ሲሆን፣ ጋምቦ እጅግ የሚታወቁበት ምግብ ነው፡፡ የሬስቶራንቱ ባለቤት፣ ሼፍና ባርቴንደር ክሪስ ናርዴሊ ‹‹ጉርሻው እያንዳንዱን ሰው በደስታ አስፈንጥዟል፤›› ሲል ለሮይተርስ ገልጿል፡፡ የአጐራባች ሬስቶራንቶች ባለቤቶችንም በዜናው ተገርመዋል፤ ተደስተዋልም፡፡

*****************************

አታላይዋ ‹‹ዕጣ ፈንታ ነጋሪ››

የፔንስልቬንያ ተወላጇ ኤፕሪል ኡይንዊች፣ ጄነፈር ጋርድነር የተባለች ወጣትን ‹‹በላይሽ የከበበሽን የጽልመት ደመና አስወግድልሻለሁ፤›› ብላ ነበር የተዋወቀቻት፡፡ ኤፕሪል ዕጣ ፈንታ ነጋሪ እንደሆነችና የጄነፈርን ሕይወት አልጋ በአልጋ እንደምታደርግላት ቃል ትገባላታለች፡፡ ጄነፈርም ቃሏን አምና በሕይወቷ የሚገጥማትን ሳንካ እንድታስወግድላት ገንዘብ መክፈል ትጀምራለች፡፡ በሕይወቷ ተጨባጭ ለውጥ ሳይመጣ ሁለት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ጄነፈር ከአሥር ሺሕ ዶላር በላይ ከሰረች፡፡

በፔንስልቪንያ ፍርድ ቤት ኤፕሪል ከጄነፈር በተጨማሪ በርካቶችን አጭበርብራለች የሚል ክስ ተመሥርቶባታል፡፡

ክሶቹ እስካሁን 55 ደርሰዋል፡፡ ኤፕሪል ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ክስ ፍርድ ቤት ቀርባ ነበር፡፡ ‹‹እርግማንንና ፅልመትን ከሕይወታችሁ ላስወግድላችሁ›› በሚል ገንዘባቸውን የተቀበለቻቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ኤፕሪል በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተደጋጋሚ በማጭበርበር ከታሰሩ ‹‹ዕጣ ፈንታ ነጋሪዎች›› ቀዳሚ ልትሆን ትችላለች፡፡ በ55ቱ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘችም የዕድሜ ልክ እስራት ይጠብቃታል፡፡

************************

ከራሳችሁ ጋር ሰላም ሁኑ

ውስጣችሁ ያላችሁን ጉድፍ በማጉላት ሊወቅሳችሁና ተደጋጋሚ አሉታዊ ትችት ለማቅረብ በሚጥርበት ወቅት ጆሯችሁን አትስጡት፡፡ በተለይ ሴት ከሆናችሁ እነዚህ ዓይነት አሉታዊ ስሜቶችን በቀላሉ ለመለየት አትቸገሩም፡፡ ለበርካታ እንከኖች የተጋለጥን ነን፤ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ስንፍናን፣ አመለ ቢስነትንና መልከ-ጥፉነት ሊኖረን ይችላል፡፡ የምንከውነው ሁሉ በኛ ዕይታ ‹‹ጥሩ›› የሚለውን እርከን የማያሟላ ይመስለናል፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ አሉታዊ ውስጣዊ ስሜቶች ሕልውና አግኝተው እንዲቆሙ መፍቀድ የለብንም፡፡ አሁን ባላችሁና እየከወናችሁ ባላችሁት ነገር ላይ ጥሩ እንደሆናችሁ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ችግሩ በዚህ እውነት ካለማመን ይመነጫል፡፡

ማንኛውም ነገር የእምነት ጉዳይ ነው፡፡ እናንተ የምታስቡትን ናችሁ፡፡ የራሳችሁን ትክክለኛ እሴት ዋጋ የሚያውቁ ሰዎችን ስትመለከቱ በበጎ አትውስዱትም፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀና አሳቢ እንዲሆኑና ለራሳቸው ያላቸው ግምትና ክብር እንዲጎለብት አጥፊ የሆኑትን አሉታዊ ስሜቶቻቸውን በመጀመርያ ሊያስወግዱ ይገባል፡፡

– ሊንዳ ፌልድ፣ ‹‹ራስን መሆን››፣ (ትርጉም በበረከት ብርሃኑ 2001 ዓ.ም.)

******

የጥንቱ ማስታወቂያ

ስለ ሳሙና የንግድ ማስታወቂያ S.F. ይህ ምልክት ያለበት ሳሙና ጥሩ የሚበልጥ ሳሙና ነው፡፡ እሱ ብቻ ልብስ የማያገማ የማያቃጥል ጥሩ አዲስ አበባ ተሰራ፡፡ ይህ ሳሙና ረኪስም ጤናም ነው፣ በብር 14 ኪሎ ይገኛል፡፡ ይህ ሳሙና ለጤና እጅግ ማለፊያ ውስጡ የሚጨመረው ጥሩ የጤና የሚሆን መድኃኒት ተመርጦ ነው፡፡ ገላ ነክ ልብስ ቢያጥቡበት ጤና ይሆናል፡፡ ለጤና ገላ ቢያጥቡበት ይሆናል፡፡ ያንን የድሮውን የሚገማውን የሞራ ሳሙና አትግዙ ቆይቶ ይቆማምጣል አሉ፡፡

  • ‹‹የአማርኛ መድበለ ምንባብ›› (1916)

*********

ሞት አነሰው

በአንድ ወቅት ነብር መግደል የፈለጉ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ ነብሩም አይቷቸው ሲሮጥ በመንገዱ ላይ አንድ ገበሬ አገኘ፡፡

ገበሬውም እርሻውን እያረሰ እንዲህ እያለ ይዘፍን ነበር፤

እኔ እያረስኩ ነው
ደመናዎቹን እያየሁ
ዝናብ የሚያመጡልኝን፡፡

ነብሩም “የዘሩን ከረጢት አቀብለኝና ከአዳኞቹ አድነኝ እባክህ፡፡” ብሎ ገበሬውን ጠየቀው፡፡

ገበሬውም እሺ ብሎ ነብሩን የዘር መያዣው ውስጥ ደበቀው፡፡ ሁለቱም አዳኞች ገበሬው ጋ ሲደርሱ ቆም ብለው “አንድ ነብር አይተሃል” አሉት፡፡

ገበሬውም “አዎ በዚህ በኩል ሄዷል፡፡” አላቸው፡፡ አዳኞቹም ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡

በዚህ ጊዜ ገበሬው ነብሩን “ነብር ሆይ አዳኞቹ ስለሄዱ በል ሂድ፡፡” አለው፡፡

ነብሩ ግን “ወይ እገድልሃለሁ ወይም ምግብ አምጣልኝ፡፡” አለው፡፡

ገበሬውም “ለምን ስላዳንኩህ ነው የምትገድለኝ?” ብሎት “በል አህያዋ ጋ ሄደን ትዳኘን፡፡” አለው፡፡

አህያዋ ጋም ሄደው ገበሬው “እኔ ነኝ መበላት ያለብኝ?” ሲላት አህያዋም “አዎን፣ ለምን አትበላም?” አለችው፡፡

ከዚያም ወደ ቀበሮ ሄዶ ገበሬው “ይህንን ነብር ከሞት አዳንኩት፤ ሆኖም አሁን ሊበላኝ ይፈልጋል፡፡” አላት፡፡

ቀበሮዋም “እንዴት ነው የዳንከው” ስትለው ስለአዳኞቹና ነብሩ ስለተደበቀበት የዘር ክምር ነገራት፡፡

ከዚያም ቀበሮዋ “በል እንዴት እንደነበረ አሳየኝ፡፡” ስትለው ገበሬው ነብሩን እንደገና ደበቀው፡፡

በዚህ ጊዜ ቀበሮዋ ገበሬውን “በል አሁን አጥብቀህ እሰረው፡፡” ስትለው ገበሬው ነብሩን ጥፍር አድርጎ ካሰረው በኋላ ቀበሮዋ “በል አሁን ደግሞ ደብድበው፡፡” አለችው፡፡

ገበሬውም ነብሩን ደብድቦ ገደለው፡፡

ከዚያም ገበሬው ቀበሮዋን “ከሞት አድነሽኛልና ምን ላድርግልሽ?” አላት፡፡

እርሷም “አንድ ጥሩ በግ አምጣልኝ፡፡” አለችው፡፡

ገበሬው ግን አንድ ትልቅ ውሻ ሲያመጣ ቀበሮዋ አይታ “ለሰው ሞት አነሳው፡፡” አለች ይባላል፡፡

ተራኪው የማይታወቅ የትግራይ ተረት

  • ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ

 

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች