ህንዳውያን አገሪቱ ባጋጠማት ያልተጠበቀና ያልተለመደ የሙቀት ማዕበል ሰላማቸውን አጥተዋል፡፡ የምድሩ ወላፈን በምሽት እንኳን የሚጋረፍ ቢሆንም ከቤታቸው ይልቅ ጐዳናውን መርጠዋል፡፡ ኃፍረታቸውን ብቻ ሸፍነው በየገላጣ ሥፍራው ለመተኛትም ተገደዋል፡፡ የአገሪቱን አንዳንድ ክፍሎች ከመታው የሙቀት ማዕበል ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ በየሰዓቱ ውኃ የሚነከሩ፣ በአየር ማቀዝቀዣ (ቬንትሌተር) ሥር ተቀምጠው ቀዝቃዛ አየር ለማግኘት የሚሞክሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ ግን ዕድሉ ላላቸው ነው፡፡ በህንድ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ውስጥ ላሉ ጐዳና ተዳዳሪዎች ወይም በቤት ላይ ቤት ደራርበው ለሚኖሩ ድሆች የሚታሰብ አይደለም፡፡
በተጨናነቁ አካባቢዎች ተፋፍገው የሚኖሩ ህንዳውያንን የሙቀቱ ማዕበል ከቤት እንዲወጡ አስገድዷቸዋል፡፡ በየወንዙ ዳርቻ እንዲተኙም አድርጓቸዋል፡፡ በተለይ ደሃ ለሆኑና በግንባታና በቀን ሥራ ለተሰማሩ ህንዳውያን ደግሞ የሞት ምክንያት ሆኗል፡፡
ህንዳውያን ከዚህ ቀደም በውኃ ማዕበል በተደጋጋሚ ተመትተዋል፡፡ አውሎ ንፋስም አጥቅቷቸው ያውቃል፡፡ አሁን ግን ከዚህ ቀደም ከነበራቸው የተፈጥሮ መዛባት በተለየ በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል እየተመቱ ነው፡፡ በአንዳንድ የህንድ ከተሞች ላለፉት ሰባት ተከታታይ ቀናት ተመዝግቦ የቆየው 48 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠን፣ እስከ ማክሰኞ ድረስ ለ2,330 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ በህንድ ከዚህ ቀደም ተመዝግቦ በማያውቀው ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሞቱት ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችልም የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
የሞንሱን ዝናብ መዘግየትን ተከትሎ ህንዳውያን አምላካቸው ዝናብ እንዲያወርድላቸው እየተለማመኑ ሲሆን፣ የአገሪቱ የአየር ትንበያ ባለሙያዎችም ከመደበኛ ወቅቱ የዘገየው የሞንሱን ዝናብ ከሦስት ቀናት በኋላ ሊጥል እንደሚችል ተስፋ ሰንቀዋል፡፡
በህንድ በተለይ ከፍተኛ ሙቀትና ሞት ባስመዘገበችው በደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው አንድህራ ፕራዴሽ ከተማ ብቻ በ24 ሰዓታት ውስጥ 42 ሰዎች ሲሞቱ እስከ ማክሰኞ ድረስ የሞት ቁጥሩ 1,719 ደርሷል፡፡ የከተማዋ የአደጋ መከላከል አስተዳደር ዳይሬክተር ዳሃናኒያ ሬዲን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደገዘበው፣ የአካባቢው የሙቀት መጠኑ 48 ዲግሪ ሴልሺየስ ወይም 118 ዲግሪ ፋራናይት ተመዝግቦ ሰንብቷል፡፡ አሁን የሙቀት መጠኑ በመጠኑ እየቀነሰ ቢሆንም ለሰባት ቀናት በተከታታይ በዘለቀው ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ምን ያህል የአካባቢው ነዋሪዎች ሊተርፉ ይችላሉ የሚለው ገና መልስ አላገኘም፡፡
በሙቀት ማዕበሉ በአብዛኛው ጉዳት የደረሰባቸው በተለይ ድሆችና የታመሙ ሰዎች ቢሆኑም፣ የአገሪቱ መንግሥት ሕዝቡ ጥላ እንዲጠቀም፣ ሙቀቱ በሚያይልበት ሰዓት እንዳይንቀሳቀስ፣ ውኃ በብዛት እንዲጠጣ መክሯል፡፡ ሕዝቡ ውኃ በነፃ እንዲጠቀምም በአገሪቱ የሚገኙ የውኃ መስመሮች ክፍት ተደርገዋል፡፡ ኩዌትና ሌሎች ሞቃታማ አገሮች ህንድ እንዳጋጠማት ከፍተኛ የሙቀት መጠን አስመዝግበው የሚያውቁና በየጊዜው የሚያስመዘግቡ ቢሆንም፣ ከሙቀት ጋር የተያያዘ ሞትን ተቆጣጥረዋል፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ ህንዳውያን በተጨናነቁ ሥፍራዎች መኖራቸው፣ የሕዝብ ቁጥሩ መብዛቱና ድህነት፣ ሰሞኑን ከተከሰተው ሙቀት ጋር ተደምሮ ለተመዘገበው ሞት ምክንያት መሆኑንም የሚገልጹ አሉ፡፡
ባለሙያዎች ከሦስት እስከ አምስት ባሉት ቀናት ውስጥ ዝናብ ሊጥል ይችላል ብለው ቢተነብዩም፣ የአገሪቱ የሜትሮሎጂ ዲፓርትመንት ወቅቱን ጠብቆ መጣል የነበረበት የሞንሱን ዝናብ ሊዘገይ እንደሚችል ሥጋቱን ገልጿል፡፡ በሚያዝያ አጋማሽ የጀመረው የሙቀት ማዕበል ከዕለት ወደ ዕለት መጠኑ ጨምሮ መግደል የጀመረውም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ነው፡፡ ለዚህም ወቅቱን ጠብቆ መጣል የነበረበት ዝናብ አለመዝነቡ ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
አንድ አካባቢ በሙቀት ማዕበል ተመታ የሚባለው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያስመዘግብ ከነበረው የሙቀት መጠን ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሲጨምርና ይህም ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲዘልቅ ነው፡፡ እንደ ዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ማብራሪያ፣ ህንድ ከዚህ ቀደም ከተከሰቱ የሙቀት ማዕበሎች ከፍተኛውን ሞት በማስመዝገብ አምስተኛውን ደረጃ ትይዛለች፡፡ ሁለት በሙቀት ማዕበሎች የታጀቡ ሳምንታትን ማሳለፍም በርካታ ድሆች ለሚኖሩባት ህንድ መከራ ነው፡፡
የሙቀት ማዕበል ሲከሰት የደን ቃጠሎን፣ የሰብል ውድመትን፣ የኤሌክትሪክ ፍጆታ መጨመርን፣ የአስፋልት መቅለጥን፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስን የሚያስከትል ሲሆን፣ ለጊዜው ከህንድ የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩት የሰው ሞት ቁጥርንና የአስፋልት መንገዶች ቀልጠው መበላሸትን ነው፡፡
ከሙቀት ማዕበል ጋር የተያያዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን እ.ኤ.አ. በ1896 በዩናይትድ ስቴትስ በተከሰተ ከፍተኛ ሙቀት 1,500 ሰዎች ሞተዋል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ቴክሳስ፣ ሚዞሪ፣ ኤሊኖስ፣ ዊስኮንሲን፣ ኢንዲያና፣ ኦሃዮ፣ ኒብራስካ፣ ማኒሶታ 38 ዲግሪ ሴልሽየስ የሚደርስ ሙቀት በተደጋጋሚ የሚያስመዘግቡ ቢሆንም፣ በሙቀት ማዕበል ሳቢያ የሚመጣ ሞትን ተቆጣጥረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1987 በግሪክ በተለይ በአቴንስ አካባቢ በተከሰተ የሙቀት ማዕበል ከ1,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ በወቅቱ የተመዘገበው የሙቀት መጠንም 41.6 ዲግሪ ሴልሽየስ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1988 እስከ 2000 ባሉት ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ በተደጋጋሚ በድርቅና በሙቀት ማዕበል የተመታችበት ወቅት ነው፡፡ ሆኖም መረጃዎች እንደሚያሳዩት በእነዚህ 12 ዓመታት የሞቱባት ዜጐች ቁጥር ከ18 ሺሕ አይበልጡም፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ግዛቶች የሙቀት መጠን መደበኛ ከሚባለው የየግዛቱ የሙቀት መጠን ከአምስት በላይ መጨመር የተለመደም ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳና በአውሮፓ ከተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን በአውሮፓ የነበረው ከፍተኛ ሞት አስመዝግቧል፡፡ በአውሮፓ እ.ኤ.አ. በ2003 በተከሰተ ከፍተኛ ሙቀት በተለይ በፈረንሣይና በፖርቹጋል የተመዘገበውን ከፍተኛ የሞት ቁጥር ጨምሮ ከ46 ሺሕ ሰዎች በላይ ሞተዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2010 በኋላ ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ በተለይ ሰሜን ምሥራቅ ቻይና እንዲሁም ሩሲያ በከፍተኛ ሙቀት የተመቱበት ዓመት ነበር፡፡ ፓኪስታን በዚሁ ዓመት 53 ዲግሪ ሴልሺየስ በማስመዝገብ ከፍተኛውን ሪከርድ ይዛለች፡፡
እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 2015 ጀምሮ ደግሞ ህንድ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ማለትም እስከ 48 ዲግሪ ሴልሺየስ ያስመዘገበች ሲሆን፣ በዚህም ከ2,300 ዜጐች በላይ አጥታለች፡፡ በአገሪቱ አንዳንድ ከተሞችም የአስፋልት መንገዶች ቀልጠዋል፡፡