Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የገባውና ያልገባው!

እነሆ መንገድ ከጎሮ ወደ መብራት ኃይል  ልንጓዝ ነው። “እስኪ እረክ እረኩን ደግሞ ልመልከተው፣ የሐረር ባቡር ቢሄድ አይታክተው” ሜሪ አርምዴ ጊዜ በማይሽረውና በማይጠግበው ድምጿ ትለዋለች። “እንዲህ በባቡር ሲገጠምና ሲዘፈን እንዳልኖረ ዛሬ ሐዲድ ብርቅ ሆኖብን ተሰቃየን እኮ? ግን መቼ ነው ባቡሩ ሥራ የሚጀምረው ወንድም? አታውቅም? አንተም እንደኛው ነህ? ጎሽ፤” ትላለች ከምትቆረጥመው ገብስ ቆሎ ካላካፈልኩህ የምትለኝ ወይዘሮ። “በቃኝ” ስላት ንዴት እየቃጣት “አቤት ጉራ። የዘንድሮ ሰው ርካሽ መጠጥና ርካሽ ምግብ ሲፀየፍ ፆሙን አለቀ እኮ እናንተ። እኔን ስማኝ ዝም ብለህ ያገኘኸውን ብላ። ከዚያም ሲመክሩህ ስማ። ምክሩን ብትንቅም ድምፅ ግን አትናቅ። ድምፅ ነው እናቴ መንግሥትን ፓርላማ ያስገባው፤” ትላለች። ምን የማትለው አለ?

 ጉልበቱ ሁሉ ክንዱ ላይ የተከማቸ የሚመስል ፈርጣማ ወያላ መጣ፡፡ “እስኪ ለእኔ ስጪኝ?” አላት። “ያንተው ባሰ” ብላ ከት ብላ ሳቀች። ተገርሞ ሲያያት፣ “ወይ እንደዚህ ዓይናማ ኮራ ቀብረር እያልክ የፈለግክ መስለህ ሳትፈልግ፣ ቀላውጠህ፣ እስክትጋበዝ መጠብቅ አለብህ። ከናጠህ ግን አየህ ቀስ ብለህ አድብተህ፣ አባብለህ፣ አሽኮርምመህ ነው ሴት ልጅ የምትጠየቀው። ዝም ተብሎ ስጪኝ አለ? ለነገሩ አንተ ምን ታደርግ? ማስታወቂያው ሁሉ የሞዴስና የወሊድ መቆጣጠርያ ቢሆንብህ ነው። ዘፈኑ ሁሉ በውስጥ ልብስና በጡት ማስያዣ ቢቀመርብህ ነው፤” ብላ ወደ አፏ የገብስ እንክብሎች ወረወረች። “ምንድነው የምታወሪው? ቆሎ ስጪኝ አልኩሽ እንጂ ሌላ ምን አልኩሽ? ያማታል እንዴ ሴትዮዋ?” ብሎ ተራውን ወደ እኔ አፈጠጠ። “ትልቅ ሰው አይደለሽም እንዴ አንቺ። ሰው በቅንዝር ሊያብድ ነው እንዴ?” እያለ ሁለት ሰው ሊሞላ የእግረኛው መንገድ ላይ መንጎማለል ያዘ።

“አበደ እንጂ ምን ሊያብድ ነው ትላለህ? እንዲያው በመድኃኔዓለም ቆሎ ስጪኝ ሲል ሰምተኸዋል? (ዞራ ወደኔ) ምናምን ስለቆላው ምን ስጪኝ እንዳለም አላወቀውም እኮ። አይ ስምንተኛው ሺሕ። ምነው ፈጣሪ በዘመን አተላ ሆዳችን ሳይሞላ ደግሞ ኑሩ ብለህ በቅንዝር ታሳብደናለህ? ምነው?” ስትል ጤነኝነቷን በመጠራጠር ተሳፋሪዎች አተኩረው ዓይን ዓይኗን ማየት ጀምረዋል። “ዳሩ ምን ያድርግ? በሴቱ ሲገርመን ወንዱ ጭምር ቡታንታው እየታየ የመቀመጫውን ሸለቆ እንደ ጌጥ ላላፊ አግዳሚው እዩልኝ እያለ ታክሲ ሲሳፈር ሲወርድ ይውላል። ነገርኩህ እኮ ሰው ርካሽ ምግብና ርካሽ መጠጥ እየተፀየፈ ለአጓጉል ውበትና ውድነት ሥጋውን ያረከሰበት ዘመን ነው። ያዝ?” አለችኝ ደግማ። የግዴን ተቀበልኩ። ሌላ ሐተታ፣ ሌላ ጉንተላ ከእንቢታዬ እንዳይመዘዝ ስለሠጋሁ። ወይ መንገድና የመንገደኛ አመል። አይጣል እኮ ነው!

መንቀሳቀስ ጀምረናል። ጋቢና አባትና ጎረምሳ ልጃቸው ተቀምጠዋል። ለጊዜው ሁለቱ ብቻ ናቸው የሚያወሩት። አባት፣ “ነግሬሃለሁ እንግዲህ ደጋግሜ። እኔ የማወርስህ ምንም ነገር የለኝም። ራስህ ኑሮህን ታሸንፍ እንደሆን ከዛሬ ጀምሮ ነው የሚለይልህ። አይ ካልክ አንተ ታውቃለህ። ምን አበላው ምን አለብሰው ብዬ የምጨነቅበት ነገር የሚኖረኝ እንዳይመስልህ ከእንግዲህ ወዲህ። ታልፍ እንደሆነ ይኼን ፈተና እለፍ። ነገርኩህ፤” ይላሉ፡፡ ጎረምሳው ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ መሆኑ ነው። አቀርቅሮ ያዳምጣቸዋል። ከፈተናው ይልቅ አባቱ የሚፈጥሩበትን ሰቀቀን ማለፍ የከበደው ነው የሚመለስለው። ጥቂት ሄድ ከማለታችን ዩኒፎርም የለበሱ ሴት ተማሪዎች ታክሲያችንን አስቁመው ገቡ። ለወሬው አላደርስ ብሏቸው ጎማው ላይ አቧራ ለብሶ ከተጋደመው አግዳሚ ላይ ዘፍ አሉ። ያወራሉ።

“እና (የጓደኛቸውን ስም እየጠሩ) በአንቺ በኩል ከተቀመጠች አንቺ እንደተባባልነው መልሱን ለእኔ ትልኪያለሽ። እይው ብቻ ባለፈው ‘ሞዴል’ ስንወስድ ተንበጫብጨሽ ፈታኙ እንደነቃብሽ ዛሬም ብታስነቂ ጓደኝነታችን አበቃ፤” ትላለች አንደኛዋ። “አብደሻል ዛሬማ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። ፊልም ላይ መሞትና የምር ድብን ማለት አንድ ነው?” ትጠይቃለች የወዲያኛዋ። “እኮ!” ትመልሳለች የፊተኛዋ። “ደግሞ አሥረኛ ላይ ማትሪክ ብወድቅ ማዘር እንዴት እንደ ሥጋ ዘልዝላ ቋንጣ እንደምታደርገኝ እያወቅሽ? የትምህርት ሚኒስቴር ፀረ ኩረጃ ፉከራና የፈታኝ ማስጠንቀቂያ ትፈራለች ብለሽ አታስቢ፤” ብላ የወዲያኛዋ ወዲያው በሹክሽኩታ የኩረጃ  ‘ስትራቴጂያቸውን’ መከለስ ጀመሩ። ከተጠና ከሚሠራው ብሔራዊ ፈተና ይልቅ ለጥናት የማይመቸው ወላጅ የሚፈጥረው ከባድ ጫና የትውልዱ ዋነኛ ‘ማትሪክ’ ሳይሆን አልቀረም። የሞት ሽረት ሲሉ አትሰሙም እንዴ?

ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ነው። መካከለኛው የጥንዶች ረድፍ ላይ አንድ ጎልማሳና ቆንጅዬ ወጣት በቀስታ ይጫወታሉ። በተለይ ጎልማሳው ወዲያና ወዲህ ባዳመጠው የተማሪና የኩረጃ ጉዳይ ተገርሟል። “መውለድ መከራ ነው አንዳንዴ!” ይላል። “ያውስ ልጆች ምኑን ያውቁታል?” ትላለች ወጣቷ። “እሱን  ነው የምልሽ። ግን አንዳንዴ ሳስበው ዋናው ችግር ያለው ወላጅ ላይ ይመስለኛል። ልጆቹን የሚገለውም የሚያስነሳውም ወላጅ ነው፤” ይላታል። “እንዴት?” ታሰፋዋለች ወጣቷ። “በቃ ሁሉን ነገር ገና ከለጋነታቸው አንስተን ፉክክር እናደርግባቸዋለን። ምግብ አልበላ ሲሉን ‘እኔ ቀደምኩህ በላሁብህ’ እያልሽ ታበይዋለሽ። አስቢ እንግዲህ። ትምህርት ቤት ስትልኪው ‘የእኔ ልጅ አንደኛ ነው የሚወጣው ሰነፍ መሰላችሁ’ እያልሽ ደረጃን ታለማምጂዋለሽ። አንደኛ ወጥቶ ሲመጣ ከእሱ በላይ ሰው እንደሌለ ደምድሟል። አንቺም አፅድቀሽለታል። እንግዲህ እኩልነት ቀስ በቀስ እንዴት እየከሸፈች ሙሉ ሰው እስኪሆኑ ኢ ፍትሐዊነት እንዴት እንደምትገነባ አስተውይ። ከዛማ በቃ። ኅብረተሰቡን ሲቀላቀል ለግሉ አፅድቆት የነበረውን የበላይነት ወደ ቡድን የበላይነትና ኃያልነት ሊቀይረው ሲፈልግ ‘የእኛ ሃይማኖት ከእናንተ ይበልጣል፣ እዚህ ሠፈር የምንኖር ነዋሪዎች እዚያ ሠፈር ከሚኖሩት ጋር አንወዳደርም’ የሚሉ ፈንገሳዊ አስተሳሰቦች ይመጣሉ፤” ካላት በኋላ፣ “ለመሆኑ ወልደሻል?” ብሎ ያልተጠበቀ ጥያቄ አቀረበላት፡፡ መቼስ የሰውን የጓዳ መጋረጃ ካልገላለጥን አይሆንልም አይደል? “ሴት ልጅ አለችኝ” ስትለው፣ “አደራ እሷን የሚደግም ተመሳሳይ ተፈጥሮ እንደሌለ እየሰበክሽ አሳድጊያት። ይኼን በአክራሪነት ስሜት ተሰግስጎ ያለ ‘እኔ ብቻ ልሰማ! ልታይ! ልግነን!’ ባይ መንፈስ የሚወልድ የውድድር ነገር አታስለምጂያት። ሰው ሌላውን ተቀብሎ ራሱን መስሎ እንዳይኖር መንገድ የሚያስተውን የፉክክር ቀንበር መጪው ትውልድ ላይ ካልሰበርነው ቀድመን መሰበራችን ነው፤” እያላት በሐሳብ ጭልጥ አለ። መንገድ ከሚወስደን ሐሳብ የሚወስደን አልባሰም ትላላችሁ?!

ጉዟችን ቀጥሏል። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙ ወጣቶች ሥጋት አዘል ጨዋታ ይዘው የተሳፋሪውን የመኖር ተስፋ ያጨልማሉ። “አንተ ለካ አይኤስ የዓለምን መጨረሻ ለማምጣት ነው አሉ ከታሪክና ከሥልጣኔ ጋር ጠብ ይዞ ሕዝብ የሚፈጀው፤” ይላል አንደኛው። “ደግሞ በቅርቡ ኑክሌር ቦምብ ሊታጠቅ ይችላል ሲባል ሰምቻለሁ፤” ይላል ሌላው፡፡ “አይ ጉድ የዛሬ ልጆች የመጣባችሁ ጣጣ። እኛስ እንጀራ በአዋዜ ተምትመን በልተን፣ በባዶ እግራችን ተጉዘንም ከበቂ በላይ ኖረናል። የዛሬ ልጆች ግን በወዳጅ ታማኝነት እጦት፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በቤት እጦት ምኑ ቅጡ ሁሉ ነገር በቁም ገድሏችሁ ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር መጣባችሁ?” ብለው አንድ አዛውንት አንገታቸውን ወዘወዙ። “ኧረ በስንቱ እንወዝወዝ እናንተ?” ከአዛውንቱ አጠገብ የተቀመጡ ትልቅ ሴት ቀጠሉት። ‹‹በቁራሽ እንጀራ ለምትዘጋ ወስፋት እንዲህ ላይ ታች ስንል ኖረን ማለፋችን ሳያንስ ደግሞ ሌላ ጣር?” ሲሉ አጠገባቸው ጋዜጣ የያዘ ወጣት፣ “ለዚህ እኮ ነው ከመንግሥታችን ጎን በመሠለፍ ሽብርተኝነትንና አክሪነትን ፀንተን ማውገዝ የሚጠበቅብን፤” በማለት እያንዳንዳችንን በዓይኑ ቃኘን፡፡ ተሳፋሪዎች እርስ በርሳቸው ተገለማምጠው ሲያበቁ  አንዱ “የፓርላማው አልበቃ ብሎ ደግሞ ወደ ታክሲ ተዞረ? ለነገሩ በአምላክ ፀጋና ቸርነት ለሚኖር ሁሉን አሜን ብሎ መቀበል እንጂ ሌላ ምን ምርጫ አለው?” ብሎ አረፈው። ጉድ እኮ ነው። ወዲያው ደግሞ፣ “ታዲያስ ወገኛ ቀበሮ ሙክት ያባርራል አለ ያገሬ ሰው። አሁን ማን ይሙት እነ አሜሪካ አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ እያለፉ እንጂ፣ ዓለማችን እንዲህ በአጥፍቶ መጥፋት ትናጥ ነበር?” ሲል ጎልማሳው እርስ በርሱ የዶለቱ ይመስል ተሳፋሪዎች በአንድ ቃል ‘‘እኛ ምኑን አውቀን?” አሉ፡፡ አቤት ድንጋጤ? አቤት መርበትበት?

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ወደ ሥራ የሚጓዘው ሠራተኛ፣ ወደ ፈተና የሚሮጠው ተማሪ፣ ሊዘራ የወጣ አራሽ፣ ምርቱን ሊያጭድ የወጣ ባተሌ እየተርመሰመሰ መንገዱ ተዘጋግቷል። “እኔን የሚገርመኝ የዚህ ሁሉ ሰው በልቶ ማደር ነው፤” አሉ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ አዛውንት። “በልቶ ማደሩ ነው የሚገርምዎት ወይስ በቀን ሦስቴ መብላት እየተገባው አንድ የማትሞላ ጉርሻ ጎርሶ በሕይወት መኖሩ?” ብለው ሴትዮዋ አዛውንቱን ጠየቋቸው። “ሁለቱም” አሉ አዛውንቱ በአጭሩ ለመገላገል ይመስልባቸዋል። “አይዞን መንግሥታችን አሁን ሁለተኛውን ዙር የትራንስፎርሜሽን አቅድ ጀምሮልናል። አይደለም ሦስቴ በቅርቡ ዘጠኝ ጊዜ ባንበላ ቱ ከምላሴ ፀጉር . . .” ሲል ያ ጋዜጣ በእጁ የያዘ ወጣት ገባበት። “ኧረ ፀጉር ማብቀሉ ቀርቶ ምላስህ አርፎ በተቀመጠ። ምን ሊለን ነው እናንተ? ይኼ አንድ ፍሬ ልጅ አሁን እንባቸው አቅርሮ ‘ሕዝቤ በቀን ሦስቴ ሲበላ ማየት ነው የምፈልገው’ ካሉት ከሟቹ ባለራዕይ መሪ ሊበልጥ ያምረዋል እንዴ? የእኛን ሞራ እንኳን እንዳንተ ያለው ግራ የገባው መሪ ጌታውም አላነበበው እሺ?” ቀወጠችው አጠገቤ የተቀመጠችው ወይዘሮ።

“ዝም አትይውም ይልቅ እንደ ጓያ ነቃይ የፊት የፊቱን ማለት ብንጀምር ያዋጣን ነበር። አለባብሶ ማረስ በኋላ በአረም መመለስ እንጂ ሌላ ትርፍ የለውም፤” ጎልማሳው ‘ሌክቸሩን’ ሲያረዝመው ከጀርባው ከተቀመጡ ወጣቶች አንደኛው፣ “ቆይ ግን የትራንስፎርሜሽን ዕቅዶቻችን የተቀዱት ከትራንስፎርመር ፊልም ላይ ነው እንዴ?” ሲል ያኛው መልሶ፣ “ሳይሆን አይቀርም እባክህ። ሥራችን ሁሉ ሰውን ማዕከል ያላደረገ፣ ሰብዓዊነትና ማኅበራዊ እሴት ላይ ጭራሹኑ ዝር የማይል፣ ብቻ ቁስ በቁስ ላይ፣ ብረት በብረት ላይ፣ ብሎኬት በብሎኬት ላይ መቆለሉን ተያይዘነዋል። የባህል ዕድገት፣ የሥነ ጽሑፍ ዕድገት፣ የንቃተ ህሊና ዕድገት የታል?” ብሎ ሳይጨርስ ታክሲያችን ሥፍራ ይዛ ቆማለች። ወያላው “መጨረሻ” ሲለን ወጣቶቹ የጀመሩትን ወሬ እንደቀጠሉ ነጎዱ። እኛም በየፊናችን እየተራመድን አንዱ፣ ‹‹የሰው ልጅ ሥራ የሰውን ፍላጐት ካላማከለ ወይም ሰው ሰው ካልሸተተ ምን ይፈይዳል?›› ሲለን የተጀመረው ወግ መቋጫ መሆኑ ገብቶን ነበር፡፡  የገባን ላልገባን እንዲህ ካላስተላለፍን ዕውቀት ምን ይፈይዳል? የገባችሁ እንዲገባን ዕርዱን የሚባለው ይኼኔ አይደል? የገባውና ያልገባው ተደባልቆ እኮ ነው የሚኖረው፡፡ መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት