Saturday, October 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልስደተኛ ወፎችን ለማዳን

  ስደተኛ ወፎችን ለማዳን

  ቀን:

  ከአህጉረ አፍሪካ ውጪ ያሉ አገሮች በበረዶ በሚሸፈኑበት ወቅት አንዳንድ ወፎችን ምግብ ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ የክረምቱን ቅዝቃዜ መቋቋም የማይችሉ የወፍ ዝርያዎች ለጥቂት ወራት ወደ አፍሪካ ይመጣሉ፡፡ ቅዝቃዜውን አሳልፈውም ወደየአገራቸው ያቀናሉ፡፡ ከሚተላለፉባቸው አገሮች በአንዷ በኢትዮጵያ ከመስከረም እስከ መጋቢት ይቆያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ኢትዮጵያን መሸጋገሪያ አድርገው ወደሌላ የአፍሪካ አገር ይሄዳሉ፡፡ ስደተኛ ወፎች (ማይግራቶሪ በርድስ) ለጉዟቸው የሚጠቀሙት የበረራ መስመር ስምጥ ሸለቆን ይከተላል፡፡ ሙቀቱ ከመሬት እጅግ ከፍ ብለው እንዲበሩ ስለሚያደርጋቸው እንደሚመርጡት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

  ዕድሜ ዘመናቸውን ዓለምን እየዞሩ የሚያሳልፉበት ስደተኛ ወፎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶችን ይስባሉ፡፡ ከአገር አገር ሲጓጓዙ በአንድ አካባቢ የሚቆዩባቸው ቀናት ስለሚታወቁ ብዙዎች ይጠባበቋቸዋል፡፡ ጉዟቸው የአንድ አገር ነዋሪዎችንና የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስብ ትዕይንት ነው፡፡ ስደተኛ ወፎችን ለመመልከት ወደ ኢትዮጵያ ሰማይ የሚያማትሩ ጎብኚዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ወፎቹ እንደየዝርያቸው ባህሪ በሚያዘወትሯቸው ቦታዎች ይጎበኛሉ፡፡ የሐዋሳና ዝዋይ ሐይቅ ከባሌ ተራሮች ፓርክ ደግሞ የሳነቴ ተራራ ይጠቀሳሉ፡፡

  ስደተኛ ወፎች ከአገር ወደ አገር የሚያደርጉት ጉዞ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ እንደየአገሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዐውድ ልዩ ልዩ ችግሮች ይገጥሟቸዋል፡፡ በሰዎች ሠፈራና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ምክንያት መጠለያቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥና ያልተገባ ቆሻሻ አወጋገድም አደገኛ ናቸው፡፡ ወፎችን የማደን ልማድ ያላቸው አገሮችም አሉ፡፡

  በወፎቹ የኢትዮጵያ ቆይታ ከሚፈታተኗቸው ዘርፎች መካከል ግብርናና የኃይል ማመንጫ ዘርፍ ይጠቀሳሉ፡፡ ባሙያዎች እንደሚናገሩት፣ በግብርና ፀረ ተባይ ነፍሳትን ለመከላከል የሚረጩ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ወፎቹን ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡ በኃይል ማመንጫ ዘርፍ የሚጠቀሰው የነፋስ ኃይል ማመንጫ (ዊንድሚል) ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ታሪክ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ ወንድአፍራሽ፣ ስደተኛ ወፎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖራቸውን ቆይታ ከሚያውኩ ዋነኛ ተጠቃሽ እየሆነ የመጣው የነፋስ ኃይል ማመንጫ እንደሆነ በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡

  የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እየናረ ነው፡፡ በአገሪቱ እየተስፋፉ ካሉ ኃይል አመንጪ መሣሪያዎች አንዱ የነፋስ ኃይል ማመንጫም ፍላጎቱን ለማሟላት ያለመ ነው፡፡ ለአገሪቱ ከፍተኛ ኃይል የሚያመነጩት ዊንድ ሚሎች ግንባታ የስደተኛ ወፎችን ህልውና ምን ያህል ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ አቶ መንግሥቱ ይጠይቃሉ፡፡

  በተለያዩ አገሮች የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች በወፎቹ የበረራ መስመር በሚተከሉበት ወቅት ለህልውናቸው ያሰጋሉ፡፡ በነፋስ ኃይል ማመንጫ አካባቢ የሚኖረው ተረፈ ምርትም ወፎቹ ላይ አደጋ ያስከትላል፡፡ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በሚሽከረከርበት ወቅት ወፎች ለማለፍ ሲሞክሩ ተመትተው ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ ስደተኛ ወፎች በነፋስ ኃይል ማመንጫ አካባቢዎች ለመመገብ ወይም ለማረፍ ወርደው ተመልሰው ሲበሩ በእሽክርክሪቱ ይመታሉ፡፡ የአንድ አገር ዕድገትና የብዝኃ ሕይወት ጥበቃን ጎን ለጎን ማስኬድም የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡  

  ኢትዮጵያ ውስጥ ዊንድሚል ወፎችን ማወኩን የሚያሳይ ጥናት አለመሠራቱን የሚናገሩት አቶ መንግሥቱ፣ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመመርኮዝ ዘርፉ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ፡፡ በሌሎች አገሮች በነፋስ ኃይል ማመንጫዎች መስፋፋት ቁጥራቸው እየተመናመኑ የመጡ ወፎች እንዳሉ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይጠብቃት የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያሻዋል ይላሉ፡፡

  የኃይል ማመንጫ ዘርፍ የስደተኛ ወፎችን ህልውና ታሳቢ እንዲያደርግ ለማሳሰብ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የስደተኛ ወፎች ቀን ‹‹ኢነርጂ፤ ሜክ ኢት በርድ ፍሬንድሊ›› በሚል መሪ ቃል ግንቦት 14-15/ 2007 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ በኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ በዓለም ለአሥረኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የስደተኛ ወፎች ቀን የኃይል ማመንጫ ዘርፍ የወፎችን የበረራ መስመር ያማከለ እንዲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ መልዕክት ተላልፎበታል፡፡

  የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ታሪክ ማኅበር የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ይልማ ደለለኝ እንደሚናገሩት፣ ስደተኛ ወፎች ክምችት ከፍተኛ የሆነበት አካባቢ ተለይቶና የበረራ መስመራቸው ተጠንቶ የነፋስ ኃይል ማመንጫ መገንባት አለበት፡፡ ያደጉ አገሮች የተከሏቸው በርካታ ነፋስ ኃይል ማመንጫዎች የወፎች ሀብታቸውን ያመናመኑበተን አጋጣሚ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹መሣሪያው በኢትዮጵያ አልተስፋፋም፡፡ በወፎች ላይ ያደረሰው ጉዳትም አልተጠናም፡፡ የነፋስ የኃይል ማመንጫዎች በሚሠሩበት ወቅት ግን ከወፎቹ ጉዞ አንፃር መታሰብ አለበት፤›› ይላሉ፡፡

  አቶ መንግሥቱና አቶ ይልማን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች በክብረ በዓሉ ወቅት ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቱ የተካሄደው ስደተኛ ወፎች ከሚጎበኙባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው ቢሾፍቱ የሚገኘው ጨቅለቃ ሐይቅ አቅራቢያ ነው፡፡ ከከተማው በጥቂት በኪሎ ሜትሮች ርቀት በቅርቡ የተመረቀው የአዳማ ሁለት የነፋስ ኃይል ማመንጫ ይገኛል፡፡

  የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያ አቶ ምሕረት እውነቱ እንደሚናገሩት፣ ወፎቹ በተለያዩ አገሮች ሲዘዋወሩ ብዝኃ ሕይወትን በማመጣጠን ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ በየዓመቱ የስደተኛ ወፎች ቀን ሲከበር የሚመረጡ መሪ ቃሎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመጠቆም መፍትሔ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ዝርያዎቹ በተፈጥሮ የሚጠፉበት አጋጣሚ ቢኖርም ሰው ሠራሽ መንስዔዎችን መቀነስ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

  አቶ ይልማ የሚያስቀምጡት የመፍትሔ ሐሳብ የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ሲተከሉ ከወፎች የበረራ መስመር ጋር እንዳይጋጩ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ የሚረዳ ካርታ (ሴንሲቲቪቲ ማፕ) በባለሙያዎች ይዘጋጃል፡፡ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ቢተከልባቸው የወፎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ የማይጥሉ ቦታዎችን ይጠቁማል፡፡ ‹‹ስደተኛ ወፎች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በተፈጥሮ ሀብትና በማኅበራዊ ሕይወት  የተለያዩ አገሮችን በጉዟቸው የሚያስተሳስሩ ‹አምባሳደሮች› ናቸው፡፡ ለየአገሮቹ ቱሪስት በመሳብም ከፍተኛ ገቢ ያስገኛሉ፡፡ ለአንድ አገር ዕድገትም ብዝኃ ሕይወትንም ያስፈልገዋልና ማጣጣም መቻል አለብን፤›› ይላሉ፡፡

  አቶ መንግሥቱ የኃይል ማመንጫ ዘርፍ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት እንደሆነ አስረግጠው፣ ‹‹እኛ የምንለው ዘርፉ ይቋረጥ ሳይሆን የብዝኃ ሕይወት ሀብታችንን ታሳቢ ያድርግ ነው፤›› ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ሳቢያ የጎላ ችግር ተከስቷል ባይባልም ከጊዜ በኋላ ዘርፉ ሲስፋፋ የበለጠ አስጊ ይሆናል፡፡

  ባለሙያዎቹ የሚስማሙበት ነጥብ የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ከመሠራታቸው በፊት ስለስደተኛ ወፎች የበረራ መስመር የተሠሩ ጥናቶች ማጣቀስን ነው፡፡ የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ከተተከሉ በኋላም ቢሆን ባለሙያዎች ጥናት የሚያደርጉበት መንገድ መመቻቸት አለበት ይላሉ፡፡ ስደተኛ ወፎቹ በተለይ በቱሪዝም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚያስገኙ ከመሆናቸው ባሻገር የአገሪቱም የዓለምም ብርቅዬ ሀብቶች በመሆናቸው ቸል መባል እንደሌለባቸው ያሳስባሉ፡፡

  አቶ መልካሙ አበበ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ዩቲሊቲ ኢንቫይሮመንት ሔልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኃላፊ ናቸው፡፡ መሥሪያ ቤታቻው ስለ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ያፀደቀው መርህ ‹‹አቮይዳንስ፣ ሚኒማይዜሽንና ሚቲጌሽን›› የተባሉ መርሆች እንዳሉት ይገልጻሉ፡፡ አንድ ፕሮጀክት በብዝኃ ሕይወት ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ከታወቀ እንደማይካሄድ ይናገራሉ፡፡

  በኃይል ማመንጫ ዘርፍ ሥራዎችና በብዝኃሕይወት ጥበቃ መካከል መጣረስ መፈጠሩ አይቀሬ ነው ብለው፣ መሥሪያ ቤታቸው የጉዳት መጠንን ለመቀነስ ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሲወጥኑ በብዝኃ ሕይወት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ እንደሚጠና አቶ መልካሙ ያስረዳሉ፡፡ ወፎች ከሌሎች የብዝኃ ሕይወት ሀብቶች ተነጥለው ጥናት ባይሠራላቸውም በዘርፉ ይካተታሉ ይላሉ፡፡

  ወፎቹ በጉዟቸው ወቅት ከመሬት በጣም ከፍ ብለው ስለሚበሩ በነፋስ ኃይል ማመንጫ የሚመቱበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው ይላሉ፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዝቅ ብለው በሚበሩበት ወቅት ወይም መሬት ላይ ወርደው ዳግም ሲበሩ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል ብለን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ኃላፊው መላ ምቱ እንዲጣራ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በተተከሉባቸው አካባቢዎች ጥናት ያስፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹የአገሪቱ የኃይል ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው፤ በቀጣይ ዓመታት የበለጠ ስለሚጨምር አሁን ካለው በላይ ለወፎች ህልውና አስጊ ይሆናል፤›› የሚሉት ኃላፊው፣ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ታሳቢ ተደርጎ ቢሠራም ከተከላው በኋላም ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ከባለሙያዎች ጋር ይስማሙበታል፡፡

  ከወፎች ጋር በተያያዘና በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ስምምነቶች አንዱ ኮንቬንሽን ኦን ማይግራቶሪ ስፒሲስ (ሲኤምኤስ) ነው፡፡ አግሪመንት ፎር ኮንሰርቬሽን ኦፍ ወተር በርድስ (አኤዋ) እና ኮንቬንሽን ኦን ባዬሎጂካል ዳይቨርሲቲ (ሲቢዲ) ይጠቀሳሉ፡፡ አቶ ይልማ ኢትዮጵያ የተፈራረመቻቸውን ስምምነቶች በመተግበር በኩል ድክመት እንደሚታይ ይናገራሉ፡፡ አቶ መንግሥቱ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ስምምነቶቹን መፈረሟ የብዝኃ ሕይወት ሀብት ጥበቃን ግዴታዋ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ‹‹ኃላፊነቱ የመንግሥት ቢሆንም እኛ ክፍተቶችን በማሳየት መስተካከል ያለበትን እየጠቆምን ነው፤›› ይላሉ፡፡

  አቶ መልካሙ እንደሚናገሩት፣ የመሥሪያ ቤቱ ሥራዎች የብዝኃ ሕይወት ጥበቃን ታሳቢ ቢያደርጉም ከሚመለከታቸው ተቋሞች ጋር የጋራ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት፡፡ ‹‹ዕድገትን መግታት አይቻልም፤ የወፎች ሕይወትም መጠበቅ  አለበት፤›› የሚሉት ኃላፊው፣ በሚመለከታቸው ተቋሞች መካከል የመግባቢያው ሰነድ ቢፈረም ለለውጥ ይረዳል ብለው ያምናሉ፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img