Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በ2007

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ 19 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውል ተፈጽሟል

በፌዴራል ደረጃ የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ የሚሳተፉ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ቁጥር እያደገ ቢሆንም፣ አሁንም የቻይና ኮንትራክተሮች ብልጫ ያላቸውን ሥራዎች በመውሰድ የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በየዓመቱ ለኮንትራክተሮች ከሚያስተላልፋቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ዘንድሮም አብዛኛውን የቻይና ኮንትራክተሮች ወስደውታል፡፡ ከባለሥልጣኑ የተገኘው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ2007 ዓ.ም. አሥር ወራቶች ብቻ ከ25.3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ 19 የመንገድ ግንባታ ውሎች ከኮንትራክተሮች ጋር የተፈጸሙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የቻይና ኩባንያዎች ከ15.1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁትን ስምንት ፕሮጀክቶች ወስደዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከስምንት የቻይና ኮንትራክተሮች ሌላ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ዘርፍ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ውል የፈጸሙ ሁለት የውጭ ኮንትራክተሮች ብቻ መሆናቸውም በዘርፉ የቻይና ኩባንያዎች ተሳትፎ የጎላ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ሁለቱ የውጭ ኩባንያዎች የወሰዱት ሁለት ፕሮጀክቶች 2.2 ቢሊዮን ብር የሚፈጁ ናቸው፡፡ እንደመረጃው በበጀት ዓመቱ በፌዴራል ደረጃ ለመገንባት ውል ከታሰረባቸው 19 ፕሮጀክቶች ውስጥ ዘጠኙን ደግሞ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ተረክበውታል፡፡

በአንድ የበጀት ዓመት ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው ፕሮጀክቶች ለአገር በቀል ኮንትራክተሮች ተሰጥቶ የማያውቅ መሆኑን የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአሥር ወሮች ለአገር በቀል ኮንትራክተሮችና ለውጭ ኮንትራክተሮች የተሰጡት ፕሮጀክቶች ቁጥር ተቀራራቢ ቢሆንም፣ በፕሮጀክቶቹ ይዘትና የግንባታ ወጪ አንፃር ሲታይ ግን የውጭዎቹ በተለይ የቻይና ተቋራጮች ከፍተኛ መዋለ ነዋይ የሚፈስባቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ወስደዋል፡፡ ቻይናዎቹና ሁለቱ የውጭ ኮንትራክተሮች በድምሩ የወሰዱዋቸው አሥሩ ፕሮጀክቶች ጠቅላላ ወጪ ከ17.3 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን የተረከቡዋቸው ስምንቱ ፕሮጀክቶች ደግሞ ጠቅላላ ወጪያቸው 7.8 ቢሊዮን ብር መሆኑ በዘርፉ የቻይና ተቋራጮች የያዙትን ከፍተኛ ድርሻ አመላክቷል፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ከባለሥልጣኑ ጋር በመዋዋል የመንገድ ግንባታ ሥራው ከተሰጣቸው ኩባንያዎች መካከል ቻይና ሬልዌይ ሰባተኛ ግሩፕ ሊሚትድ፣ ሲጂሲ ኦቨርሲስ፣ ቻይና ቴሱጂ፣ ሁናን ሁንዳ የመንገድና ድልድይ ኮርፖሬሽን፣ ቻይና ፈርስት ሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ኮ ሊሚትድ የተባሉት ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡

ከቻይናዎቹ ውጪ በበጀት ዓመቱ የኮንትራት ውል የፈረሙት ሁለቱ የውጭ ኮንትራክተሮች ደግሞ ዩቲኤ ኤልሳሜክስ ኤኮ አስፓልት ኢትዮጵያ 35 የተባለው የስፔን ኮንትራክተርና የዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትሱ አልአሰብ ጄኔራል ትራንስፖርት ኮንስትራክሽን ናቸው፡፡ በበጀት ዓመቱ ከባለሥልጣኑ ሥራ የተረከቡት አገር በቀል ኮንስትራክተሮች ውስጥ ደግሞ ሰንሻይን፣ መከላከያ ኮንስትራክሽን፣ አሰርና የማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የመከላከያ ኮንስትራክሽን አንድ ፕሮጀክት 2.66 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ነው፡፡ ይህም ከአገር በቀል ኮንትራክተሮች በከፍተኛ ወጪ የሚገነባ ፕሮጀክት መረከቡን ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች የወሰዱዋቸው የፕሮጀክቶች መጠን ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ነው ተብሏል፡፡ ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ በ2006  በጀት ዓመት በጠቅላላው 18.6 ቢሊዮን ብር የሚጠይቁ 15 የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች የግንባታ ውል ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ ውስጥ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የተሰጣቸው ሦስት ፕሮጀክቶች ብቻ በመሆናቸው፣ የዘንድሮው ተሳትፎ የተሻለ ነው ሊባል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ባለፈው ዓመት ለአገር በቀል ኮንትራክተሮች ከተሰጡት ሦስት ፕሮጀክቶች ውስጥ ሁለቱን ሱር ኮንስትራክሽን የወሰዳቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡

ከ15ቱ ፕሮጀክቶችም የቻይናዎቹ ተቋራጮች የወሰዱዋቸው ፕሮጀክቶች ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ አሥር ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ ቀሪዎቹ ለሌሎች ሁለት የውጭ ኮንትራክተሮች የተሰጡ ነበሩ፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን በመንገድ ግንባታ ዘርፉ ውስጥ የቻይና ኮንትራክተሮች ድርሻ ከዓመት ዓመት እያደገ መጥቷል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች በተለይም የቻይና ኩባንያዎች በመንገድ ልማት ዘርፍ በመሳተፍ ብልጫ ይያዙ እንጂ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተሳትፎ እንዲጨምር እየተደረገ መሆኑን አቶ ሳምሶን ይገልጻሉ፡፡

የውጭ ኩባንያዎች በተለይ ከፍተኛ መዋለ ነዋይ የሚጠይቁ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እንዲሠሩ የሚደረገው፣ ፕሮጀክቶቹ በውጭ አበዳሪዎች የሚሠሩ በመሆኑ እንደሆነም አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡ በውጭ አበዳሪዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ደግሞ የጨረታ መስፈርቶቻቸው አገር በቀል ኮንትራክተሮች ሊያሟላቸው የማይችሉ በመሆኑ፣ ሥራውን የውጭ ኮንትራክተሮች እንዲሠሩ በር በመክፈቱ እንጂ አገር በቀል ኮንትራክተሮች በሁሉም ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ ለመሆን የሚከለክላቸው ነገር እንዳልነበር ተጠቁሟል፡፡

መንግሥት የአገር በቀል ኮንትራክተሮችን አቅማቸውን በማጎልበት እየሠራ ነው ያሉት አቶ ሳምሶን፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በየዓመቱም ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው በአገር በቀል ኮንትራክተሮች ሊገነቡ የሚችሏቸው ሥራዎች እንዲመቻችላቸው በማድረጉ ጭምር ዕድል እየተከፈተላችሁ ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡

ወደፊትም በመንግሥት ፋይናንስ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች እየጨመሩ ስለሚሄዱ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ተሳትፎ አሁን ካለውም በላይ ይሄዳል ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ደረጃ በሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉና አቅማቸውን ያጐለበቱ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ቁጥር 93 እንደደረሰ የጠቆሙት አቶ ሳምሶን፣ ‹‹በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ በፌዴራል የመንገድ ግንባታ ላይ ሊሰማሩ የሚችሉ ብቁ አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ቁጥር 100 ለማድረስ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን 93 ደርሷል፤ ይህ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ግን በፌዴራል ደረጃ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ የመሳተፍ አቅም የነበራቸው 20 ኮንትራክተሮች ብቻ ነበሩ ተብሏል፡፡ 

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ መሠረት የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ቁጥር በ2006 ዓ.ም. ከነበረው ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች በመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን የሚጠቁመው የባለሥልጣኑ መረጃ፣ ከዚህ በኋላም የእነሱን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጿል፡፡ አቶ ሳምሶን እንደገለጹት በፌዴራል ደረጃ በሚገነቡ መንገዶች ላይ ልምድ የሌላቸው አገር በቀል ኮንትራክተሮች እየገቡ መሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ወራት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ውል ከፈጸሙት መካከል እንደ አሰር ኮንስትራክሽን ያሉ በፌዴራል ደረጃ ሥራ ሲሰጣቸው ዘንድሮ የመጀመሪያቸው መሆኑን ለአብነት ተጠቅሷል፡፡

በዲዛይንና በኮንስልታንት ደረጃ ግን የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ብልጫ ያለውን ሥራ እየወሰዱ ነው፡፡ በየዓመቱ ከሚገነቡ መንገዶች ውስጥ ከ90 በመቶው በላይ የሚሆኑት ዲዛይኖች በአገር ውስጥ  አማካሪ ድርጅቶች የተሠሩ ናቸው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ግን ተሳትፏው ይህን ያህል ያልነበረ ሲሆን፣ የአገር በቀል አማካሪ ድርጅቶች ቁጥርም 15 ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ ደርሰዋል፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ 50 አማካሪ ድርጅትን ለማድረስ የታቀደ ቢሆንም፣ በዘርፉ ከዕቅድ በላይ ማከናወን በመቻሉ በፌዴራል ደረጃ ተፎካካሪ የሚሆኑ የአማካሪ ድርጅቶችን ቁጥር 60 ማድረስ ተችሏል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች