Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምግብ ነክ ምርቶች ዋጋ አሁንም እያሻቀበ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጥቂት ወራት ወዲህ በአንዳንድ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ለውጥ ሳይታይበት እየቀጠለ ነው፡፡ በተለይ የበርበሬ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ ከምግብ ነክ ምርቶች እንደ ሽሮና ምስር ክክ ያሉ ምርቶች እየታየባቸው ያለው የዋጋ ጭማሪ ከዚህ ቀደም ውድ ተብለው ይሸጡበት ከነበረው ዋጋ በላይ ደርሷል፡፡

ከቅመማ ቅመም ምርቶችም ዝንጅብልና ጥቁር አዝሙድ ዋጋቸው አልቀመስ ብሏል፡፡ ከአራት ወራት በፊት በተለያዩ የአዲስ አበባ የገበያ ስፍራዎች በ30 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ፣ ቀስ በቀስ ዋጋው እየጨመረ በአሁኑ ወቅት ከ120  እስከ 135 ብር ደርሷል፡፡ በሾላ ገበያ በርበሬና በተለያዩ ቅመማ ቅመም ምርቶች ንግድ ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ ሰላም እንደሚገልጹት፣ በተለይ ባለፉት አራት ተከታታይ ሳምንታት የበርበሬ ዋጋ ጭማሪ በየዕለቱ እየታየ ነው፡፡ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. አንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ በ120 ብር ሲሸጡ እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ ሰላም፣ ማክሰኞ ግንቦት 25 ግን የማከፋፈያ ዋጋው ራሱ 120 ብር ስለደረሰ አሁንም የችርቻሮ መሸጫ ዋጋው መጨመሩ እንደማይቀር ያስረዳሉ፡፡ በሳሪስ ገበያም አንድ ኪሎ በርበሬ 135 ብር ተሽጧል፡፡ ‹‹አንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ በዚህን ያህል ዋጋ ሸጬ አላውቅም፤›› የሚሉት የበርበሬ ነጋዴዋ፣ ሰሞኑን ያዩት የዋጋ ለውጥ ግን ከዚህ ቀደም በውድ ተሸጠ በሚባልበት ወቅት እንኳን ያልገጠማቸው ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ በሳሪስ ገበያ ያገኘናቸው ሌላ የበርበሬ ነጋዴም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ሁሌም ክረምት ሲገባ የበርበሬ ዋጋ በተወሰነ ደረጃ መጨመሩ የተለመደ ነው የሚሉት ወ/ሮ ሰላም፣ ‹‹የዘንድሮው ግን የተለየ ነው፡፡ አምና በዚህ ወቅት እንኳን አንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ ተወደደ ተብሎ 60 ብር ሸጠናል፤›› ብለዋል፡፡

እኚሁ በርበሬ ነጋዴ ከሰሞኑ የታየው የገበያ ለውጥ እንዳሳሰባቸው ይገልጻሉ፡፡ የአንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ ታኅሳስ 2007 ዓ.ም. ላይ ከ30 እስከ 35 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ የዛላ በርበሬ በከፍተኛ ደረጃ ዋጋው እየጨመረ መምጣት ታሸጎ በሚሸጠው የበርበሬ ዋጋ ላይም ተፅዕኖ እንዳሳደረ ያነጋገርናቸው የባልትና አዘጋጆች ይገልጻሉ፡፡ አንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ 30 ብር ይሸጥ በነበረበት ወቅት ተፈጭቶ የታሸገው በርበሬ ቢበዛ 60 ብር ይሸጥ እንደነበር የሚናገሩት የባልትና አዘጋጆች፣ ሰሞኑን ግን ዛላ በርበሬ በመወደዱ 130 ብር ለመሸጥ ተገደዋል፡፡ ይህም ቢሆን አዋጭ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

በግል ቤታቸው በርበሬና ሌሎች የባልትና ውጤቶችን በማዘጋጀትና በመሸጥ የሚተዳደሩት ወ/ሮ ዝናሽ መኮንን (ስማቸው ተለውጧል) ደግሞ የዛላ በርበሬ መወደድ በርበሬ ማዘጋጀት እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል፡፡ ከአራትና አምስት ወራት በፊት በ30 ብር የሚገዙትን ዛላ በርበሬ አዘጋጅተው አንዱን ኪሎ የተፈጨ በርበሬ ከ50 እስከ 60 ብር ይሸጡ ነበር፡፡ መወደድ ከጀመረ ወዲህም አንዱን ኪሎ ዛላ በርበሬ 80 ብር ገዝተው ያዘጋጁትንና የተፈጨው በርበሬ እስከ 90 ብር መሸጣቸውን ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ግን የዛላው ዋጋ ከ120 ብር በላይ በመሆኑ በዚህን ያህል ዋጋ ተገዝቶ ቅመማ ቅመም ጨምሮ ማዘጋጀቱ ስለማያዋጣ የተፈጨ በርበሬ ማዘጋጀት አቁመዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ዝናሽ ገለጻ ሥራው አድካሚና ለዝግጅቱ የሚያስፈልጉ ቅመማ ቅመሞች ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ገበያው እስኪረጋጋ ማቆሙ የተሻለ ነው ይላሉ፡፡ ወ/ሮ ሰላምም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ ዛላ በርበሬ ከመሸጥ ጎን ለጎን የተፈጨ በርበሬ እያዘጋጁ ለባልትና መደብሮች ያቀርቡ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ስለማያዋጣቸው ማቆማቸውን ይገልጻሉ፡፡

አንድንድ የባልትና መደብሮች በሰሞኑ ተፈጭቶ የተዘጋጀውን በርበሬ እስከ 140 ብር እየጠሹ ነው፡፡ የግል የባልትና አዘጋጆች በዛላ በርበሬ መወደድ በርበሬ ማዘጋጀት ቢያቆሙም፣ የተለያየ ቅምማ ቅመሞችን የሚያዘጋጁ ኩባንያዎች ግን የታሸገ አንድ ኪሎ የበርበሬ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋቸውን ከ90 እስከ 100 ብር አድርሰዋል፡፡ አንዱን ኪሎ ዛላ በርበሬ በ120 ብር እየተገዛ የተዘጋጀውን 90 ብር መሸጣቸው ግራ ያጋባል የሚሉም አሉ፡፡

ከሰሞኑ የበርበሬ ዋጋ መወደድ የተለያዩ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም፣ ዋነኛ ምክንያቱ የምርት እጥረት እንደሆነ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቅመማ ቅመም ምርቶች ተመራማሪና የቅመማ ቅመም አምራቾችና አቀነባባሪዎች ማኅበር አስተባበሪ አቶ አዲሱ ዓለማየሁ ይገልጻሉ፡፡ ለበርበሬ ዋጋ መናር የበርበሬ ምርት እርሻው ላይ በበሽታ መጠቃቱ ለምርት እጥረቱ ዋነኛ መንስዔ ነውም ይላሉ፡፡ ይህም እጥረት ለዋጋ ማሻቀብ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበርበሬ ዋጋ መናርና ለውጭ የቀረበውም በርበሬ መጠን በተወሰነ ደረጃ መጨመርም የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረ ይላሉ፡፡ ወቅታዊ የሆነው እጥረት ግን እንዳይቀጥል ተከሰተ የተባለውን በሽታ ሊቋቋም የሚችል አዳዲስ የበርበሬ ዝርያዎች የተዘጋጁ በመሆኑ፣ በቀጣይ የምርት ዘመን ችግሩ ይወገዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ አንዳንድ የበርበሬ ነጋዴዎች ግን የበርበሬ ዋጋ መወደዱን ተከትሎ ምርቱን ይዘውት እንዳልሆነ  ይጠቁማሉ፡፡

 በርበሬ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹ ቅመማ ቅመሞችም በተመሳሳይ መንገድ በበሽታ መጠቃታቸው፣ ገበያ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉም እየተነገረ ነው፡፡ ከቅመማ ቅመም ምርቶች በተለይ ዝንጅብልና ጥቁር አዝሙድ የመሸጫ ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ በተለይ ዝንጅብል ከጥቂት ወራት በፊት የአንድ ኪሎ ግራም ተወደደ ተብሎ አሥር ብር ይሸጥ ነበር፡፡ በአብዛኛው ግን ከስድስት እስከ ሰባት ብር ይሸጥ እንደነበር ወ/ሮ ሰላም ይገልጻሉ፡፡ አሁን ግን አንድ ኪሎ ዝንጅብል 35 ብር ደርሷል፡፡

ዝንጅብል በዚህን ያህል ደረጃ ዋጋው ሊጨምር የቻለው እንደ በርበሬው ሁሉ በበሽታ በመጠቃቱ ነው የሚሉት አቶ አዲሱ፣ የዝንጅብል እጥረት የአገር ውስጥ ተጠቃሚን ብቻ ሳይሆን የወጪ ንግዱንም ጎድቷል ይላሉ፡፡ በተለይ በቅመማ ቅመም ዘርፍ ሥር ሆነው ለውጭ ከሚቀርቡ ምርቶች ውስጥ አንዱ ዝንጅብል ሲሆን፣ ወደ ውጭ ከሚላከው ቅመማ ቅመም ምርቶች ውስጥ 43 በመቶውን የሚይዘው ዝንጅብል በመሆኑ የምርት እጥረቱ በወጪ ንግዱ ላይም የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል ተብሏል፡፡ ጥቁር አዝሙድም በአሁኑ ጊዜ የአንድ ኪሎ ግራም የመሸጫ ዋጋው 88 ብር ደርሷል፡፡ ከሦስት ወራት በፊት ግን ከፍተኛ ዋጋው 40 ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ በርበሬ አይሁን እንጂ የታሸገ ሽሮ ምርትም በተመሳሳይ ዋጋው ጨምሯል፡፡ ከሦስት ወራት በፊት በአዲስ አበባ የችርቻሮ መደብሮች በ28 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ምስር ክክ 48 እስከ 55 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ መንግሥት ጭማሪው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም በሚል ቢያስጠነቅቅም የተለወጠ ነገር የለም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች