Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፈጠራና ፈጣሪዎቹ

ፈጠራና ፈጣሪዎቹ

ቀን:

 ልዩ ልዩ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ወጣት ነው፡፡ በዓለም ላይ አስገራሚና አስደናቂ ሥራዎች የተከናወኑትም በአብዛኛው ከዋኞቹ በወጣትነት ዕድሜ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ስለሆነም ሀገራችንን ጨምሮ በሌሎች አገሮች ያሉና የነበሩ ወጣቶች ሕዝብ አስተባብረው አገራቸውንና ዓለማቸውን መርተዋል፡፡ በርካታ አሳሾች በመላው አለም የተንቀሳቀሱት በወጣትነት ዕድሜያቸው ነው፡፡ የዓለማችን የሃይማኖት መሪዎች እምነታቸውን፣ አመለካከታቸውንና ፍልስፍናቸውን ይዘው ብቅ ያሉት በወጣትነት ዕድሜቸው ነው፡፡ ጥንትም ሆነ ዛሬ ዓለም የወጣቶች ናት፡፡

በዓለማችን፣ በክፍለ አህጉራችን፣ በአገራችን ብሎም በክልላችን የሚገኙ ወጣቶች በአፍላ የጉርምስና ጊዜያቸው አንዳች ተግባር አከናውነው ለመታወቅ ይመኛሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ አነስተኛ የገጠር ቀበሌ የሚገኝ ወጣት አንድም በአካባቢው እንዳለ ሀብታም ገበሬ፣ ጀግና ነጭ ለባሽ፣ ወታደር፣ አስተማሪ፣ የሃይማኖት መሪ ወይም ሌላ ለመሆን ይመኛል፡፡ በዞንና በክልል ከተሞች የሚገኝ ወጣት ደግሞ በአካባቢው ከሚያየው፣ በሬዲዮ ከሚሰማው፣ በቴሌቪዥን ከሚመለከተውና በትምህርት ቤት አስተማሪው ከሚነግሩት ከሱ ዝንባሌ ጋር የሚሄደውን አንዱን ወይም ሁለት ሦስቱን በመምረጥና እንደአርአያ በመውሰድ «እኔም እንደሱ/እንደሷ እሆናለሁ» ብሎ ይመኛል፡፡ በመሠረቱ በየትኛውም አህጉርና አገራት ያሉ ታላላቅ ሰዎችም ታላላቅ የሆኑት በተመሳሳይ ሁኔታ ነው፡፡

በየትኛውም የዕውቀት ዘርፍ ታዋቂ ለመሆን የፈጠራ ችሎታን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ፈጠራ ማለት ደግሞ ከዚህ ቀደም ያልነበረውን ነገር ህልውና እንዲኖረው ማድረግ፣ ብዙ ሰዎች ሊያደርጉት የሞከሩት ነገር ግን የምሥጢሩን ቁልፍ አጥተው በጅምር የተውቱን እፍጻሜ ማድረስ ሲሆን የሚፈጠረውም ጉዳይ በሳይንስ፣ በኢንዱስትሪ፣ በምሕንድስና፣ በፖለቲካ፣ በኪነጥበብ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡

«የሥነ ባሕርይ መግቢያ» በሚል ርእስ ኧርነስት አር-ሂልጋርድና ሪቻርድ አርኪንሰን ስለፈጠራ በተነተኑበት ንዑስ ርእስ ውስጥ ‹‹ፈጠራ ሥነ ባሕርያዊና ፍልስፍናዊ ገጽታ ሲኖረው በሥነ ባሕርይ መልኩ ከግለሰቦች ኀሊናዊ አመለካከት ማለት ካካበቱት የሕይወት ገጠመኝ ልምድል የሚመነጭ ነው፡፡» ሲሉ ጄ.ዋላንስ ደግሞ ‹‹ፈጠራ ለመፍጠር የሚያስችል ሁኔታ ማመቻቸትን፣ መረጃዎችን መሰብሰብንና የተሰበሰበውን መረጃ አቀነባብሮ ለመግለጽ መቻልን ያጠቃልላል» ይላሉ፡፡

ዶክተር ጆን ደብሊው ጋርድነር እያንዳንዱ ትውልድ ለዓለማችን አንድ አዲስ ነገር ፈጥሮ ማለፍ እንዳለበት አበክረው ባሳሰቡበት ጽሑፋቸው ‹‹ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን አደራ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የራሱን ታሪክ እንዲሠራ የሚገጥመውን ውስብስብ፣ አዋኪና አስቸጋሪ ሁኔታ ማለፍ እንዳለበት መንገር አለብን» ይላሉ፡፡

የፈጠራ ሥራ ወጤቶች በተጠቃለለ መልካቸው ካልተስተዋሉ በስተቀር በተለያዩ ሰዎችና ጊዜያት የተገኙትን ከተመለከትን እንደሁኔታው የተለያዩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ አልበትር እንስታይን ገና የ16 ዓመት ወጣት ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ጥያቄውን ለመመለስ ለሰባት ዓመታት ያህል ጥረት ሲያደርግ፣ ሲዘጋጅና መረጃ ሲሰበስብ ቆይቷል፡፡ ማስረጃዎችን ካጠናከረና የአንፃራዊነት ጽንሰ ሐሳበ ካገኘ በኋላ ይህንን አብራርቶ ለመጻፍ አምስት ሳምንት ብቻ ወስዶበታል፡፡

ኤ.ኤች በክረል የዩራኒየም ውሕድ የፎቶግራፍ ማድረቂያ ቆርቆሮውን እንደጐዳው ሲመለከት ምንም ጥረት ሳያደርግ የሬዲዮ አክቲቭ ምሥጢር እንደተከሠተለት ሁሉ፣ አሌክሳንደር ፍሌሚንግም ቢሆን የፔኒሲሊንን ጠቃሚነት የተረዳው ባክቴሪያዎች ሲያሳድግ በአጋጣሚ ነው፡፡

ፈጠራ ሌላ ሳይሆን «ዛሬ ያለውን ነገር መለወጥ፣ ማሻሻል፣ ማሳደግ፣ የበለጠ ጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ» ማለት ሲሆን በሌላ መልኩም ዛሬ ትክክል የሚመስለው ነገ ስሕተት ሊሆን ስለሚችል ሁኔታዎችን በየጊዜው እየተከታተሉ ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ የሚያበቃ ነው፡፡

የሒሳብ ስሌት ጠቢቡና ሳይንቲስቱ ጃኮብ ብሮኖቭስኪ የዕውቀትና የምናብ ምንጭ በተሰኘው መጽሐፋቸው «ፈጠራ የተገኘው ይህ ልክ አይደለም እስቲ በሌላ መንገድ እንሞክረው በማለት ነው፡፡ ማንም ቢሆን ዕውነትን፣ ፈጠራን እንዳስቀመጠው ዕቃ ብድግ ሊያደርገው አይችልም፡፡ እንደዚህ ከሆነ ዓለምን የተሻለች ማድረግ አይቻልም›› በማለት ሰው ዓለምን ለመለወጥ ካለው ፍላጐት የፈጠራ ውጤት ሊያገኝ እንደሚችል እንደ ዶክተር ጋርድነር አጥበቀው የሳስባሉ፡፡ በ18ኛው ምዕተ ዓመት ለነበረው ኢማኑኤል ካንት «የፈጠራ ሥራ ከሰው ልጅ ግንዛቤ፣ ለአንድ ነገር ከሚያድርበት ስሜትና ያንን ጉዳይ ለማወቅ ከሚያደርገው ጥረት ጋር ተዋሕዶ በአዲስ መልክ እንዲፈጥር ያስችለዋል» የሚል ትንታኔ ይሰጣል፡፡

በአሥራ ዘጠነኛውና በሃያኛው ምዕተ ዓመት የነበሩት ሐሳባውያን ፈላስፎች ደግሞ ፈጠራ ሜካኒካልና ቴክኒካል ነው በማለት ለይተው አስቀምጠውታል፡፡ ስለ ሕይወት ከሚፈላሰፉት ውስጥ ኤች ቢርገሰን የተባሉት ሊቅ ‹‹ፈጠራ በሰው ንቃተ ኀሊና ውስጥ ያለማቋረጥ የሚወለድ፣ የሚያድግና በዚህም የእድገት ሒደት የሚበስል ነው» በማለት ያስረዳሉ፡፡

ፈጠራ በአጭሩ አዲስ ነገር መፍጠር ወይም የተጀመረውን እዳር ማድረስ ተብሎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡

ዛሬ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከመቼውም ጊዜ በፈጠነ ሁኔታ በመሮጥ ላይ ባለበት ዘመን ከመቶና ከሺ ዓመታት በፊት ከነበረው ያልተሻለ አድርገው እየሠሩ «ፈጠራ» ሲባልላቸው፣ ከገበያ ውጭ የሆኑ ፋብሪካዎችን እየተጠቀሙ ከኋላ ቀር ኢኮኖሚ ለመላቀቅ ጥረት ቢደረግ «ፈጠራ» የሚባለው «ቢወቅጡት እምቦጭ» ከመሆን ሊዘል አይችልም፡፡

የፈጠራ ሰዎች በኪነትና በሳይንስ ዘርፍ የፈጠራ ሥራ ለዓለማችን የሚያበረክቱ ናቸው፡፡ ሆኖም ሁሉም የፈጠራ ሰዎች እኩል የፈጠራ ውጤቶችን እያበረክቱም፡፡

ለወጣቶች ዓላማቸውን እግብ ለማድረሰ የሚያስችል መርሃ ግብር አውጥቶ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው፡፡ ችግር የሚሆነው ዓላማን በትክክል ያልተገነዘቡና ተገንዝበው ደግሞ እንደምን እግብ እንደሚያደርሱ ያላወቁ እንደሆነ ነው፡፡ ዳሩ ግን እንደዚህ ያለው ችግር የሚደርሰው በወጣቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙ መቶ ሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይም ነው፡፡ አር.ጀ. ሂይሶርን «በአንድ ሥራ ለመታወቅ መፈለግ ጥሩ ቢሆንም ዓላማን እግብ ለማድረሰ የሚቻለው ሐሳብን ያለመወላወል ወይም ከወዲያ ወዲህ ባለመርገጥ በቀጥታ ለመጓዝ የተቻለ እንደሆነ ሲሆን ወደ ፊት ለመሥራት የምናቅደውንም ካለፈው ትምህርት ተመርኩዘን መሆን እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡ በአእምሯችን መያዝ የሚኖርብን መርህም ጉዟችን በክብ ቀለበት ዙሪያ መሽከርከር ሳይሆን በቀጥታ መጓዙን ማረጋገጥ ነው፡፡ ዓላማችን ግቡን እንዲመታ በእርግጥ የምንፈልግ ከሆነም ፍላጎታችን የኛ ተገዥ እንጂ እኛ የፍላጎታችን ተገዥ እንዳንሆን ማስተዋል እጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህም ጋር ለአላማችን ግብ መምታት በወግ፣ በብልሃት፣ በሥርዓትና ሁኔታዎችን በቅደም ተከተል ለማከናወን በተፈጥሮ ችሎታችን መጠቀም ይኖርብናል፡፡

በመሠረቱ የዓላማችን ግቡን መምታት በሕይወታችን ውጤታማነታችንና ድል አድራጊነታችንን እንዲሁም ደስተኛነትን የሚያስከትል ሲሆን በሥራችን ክብረን፣ ዕድገትን፣ ታማኝነትን፣ አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉትን፣ ለሚቀርብልን ጥያቄ መልሰ መስጠትን፣ ካለንበት ማህበራዊ ሕይወት ወደ አዲስ ማኅበራዊ ሕይወት የመግባት ዕድልን ያጉናጽፈናል፡፡

ይሁንና ዓላማችን ግቡን ሊመታ የሚችለው ከተፈጥሮ ችሎታችን ከእውቀታችን ከየዕለቱ ማኅበራዊ ኑሯችንና ግንኙነታችን ጋር በጥብቅ የተሳሰረና ለዚህ ዓለማ ግብ መምታት ደከመኝ ሰለችኝ ሳይሉ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

ብዙ ሰዎች ውድቀት የሚያጋጥማቸው ምናልባት አሁን ካሉበት ተነስተው ባለመጀመራቸው፣ አሁን ለመጀመር ሲፈልጉ ደግሞ ምናልባት ለአላማው ግብ መምታት እሙን ያልሆነ ጊዜ ነው ብለው በመገመታቸው ነው፡፡ በእርግጥም በጣም አስፈሪና አስጨናቂ በሆነ ጊዜ አንድ የሚያስደስት ነገር ለመሥራት የሚከብድ ይመስላል፡፡ ነገር ግን አስፈሪና አስጨናቂ ሁኔታዎች ድል ሊያደረጉ የሚችሉት የሚያስደስት ነገር ለመሥራት በሚፈልጉና በሚሠሩ ሰዎች ያልተቋረጠ ትግል መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም ወጣቶች እንደሚያደንቋቸው ታላላቅ ሰዎች ትልቅ ለመሆን «ዓላማዬ ግቡን ቢመታ ተጠቃሚው እኔው ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ለኔ አለሁ፤» ብለው ዘወትር ለራሳቸው መንገር ይጠበቅባቸዋል፡፡

አንዳንድ ወጣቶች ፈጠራን ከሀብት ጋር በማያያዝ «ገንዘብ ቢኖረኝ ይህን አደርግ ነበር፡፡ ገንዘብ ስለሌለኝ ግን ላደርገው አልቻልኩም» ብለው ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ነገር ግን ይህ ስህተት መሆኑን ብዙ ምሳሌዎችን ጠቅሶ ማስረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ታላቁ የስኮትላንድ የታሪክ ሊቅና ብዙ ትምህርታዊ ጽሑፎችን ያበረከተው ቶማስ ካርላይል፣ ከመጀመሪያው አንስቶ ማንበቡን፣ ማጥናቱንና መመራመሩን በመቀጠል አእምሮውን በትምሕርት አበለጸገ፡፡ የ23 ዓመት ወጣት ሲሆንም ከአንድ ምሁር የሚጠበቀውን አስተዋጽኣ ማበርከት ጀመረ፡፡ በሚጽፋቸው የታሪክና የምርምር፣ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያው የሚያቀርባቸው ሕግ ነክ ትንታኔዎች አድናቆትን አተረፉለት፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ጋዜጠኛና ሳይንቲስት የነበረው ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ ለአባቱና ለእናቱ 5ኛ ልጅ ነበር፡፡ አባቱ ድሃ ስለነበረም በ17 ዓመቱ ፊላደልፊያ በሚገኝ አንድ ማተሚያ ቤት ተቀጠረ፡፡ ወዲያውኑም የራሱን የሆነ ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ፈለገ፡፡ ከጊዜ  በኋላም የሚፈልገውን የማተሚያ መሣሪያ ገዛና ወደ አሜሪካ በመመለስ ፔንሲልቫኒያ ጋዜት የሚል ጋዜጣ ማሳተም ጀመረ፡፡ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅም እራሱ ስለነበረ ተቀባይነትና የሥራው ተነባቢነት ከፍተኛ ሆነ፡፡ ቀጥሎም ዛሬ ዩኒቨርስቲ የሆነውን የፔንሲልቫኒያ ኮሌጅ አቋቋመ፡፡ በ40 ዓመቱ ላይም ስለኤሌክትሪክ ማጥናት ጀመረ፡፡ በ48 ዓመቱም የእንግሊዝ ሮያል ሶሳይቲ አባል የመሆን ዕድል አጋጠመው፡፡

ፈረንሳዊው የፍልስፍና ጸሓፊ ዣንዣክ ሩሶ የተወለደው እ.ኤ. አ. 1718 ጄኔቫ ውስጥ ነው፡፡ የሰዓት አዳሽ ልጅ ነው፡፡ ይሁንና እናቱ በሕፃንነቱ ስለሞቱ በዘመድ አደገ፡፡ ሩሶ ባበረከተው ከፍተኛ የፖለቲካና የፍልስፍና ሥራዎች የሚታወቅ ቢሆንም በልጅነትና በወጣትነት ዕድሜው ደልቶት የኖረ ሰው አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ ይመስላል ያደረበት ስሜታዊነትና የብስጩነት ባሕርይ ከሰዎች ጋር አላስማማውም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ የመሥራት ዕድል ሳይገጥመው ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው በመዞር አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን አሳልፏል፡፡ ሩሶ፣ መንግሥት በምክር ሕዝቡን መምራት እንደሚገባው፣ የመንግሥት አመራር አባላትም የሕዝብ አገልጋዮች እንደሆኑ፣ ለሕዝብ ደኀንነት መቆም እንዳለባቸውና ሕዝቡንም ከአደጋ ሊጠብቃቸው እንደሚገባ አጥብቆ ተከራክሯል፡፡

እስካሁን በተመለከትነው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዚህ ረገድ ለቀበሌያቸው፣ ለክልላቸው ብሎም ለሀገራቸው ምን ሠርተው ታላቅ ሰዎች መሆን ይችላሉ? ብለን ስንጠይቅ እጅግ በርካታ ያልተዳሰሱ ነገሮች በዓይነ ሕሊናችን መጥተው ይደነቀራሉ፡፡ ዳሩ ግን ፍለጋውን ለፈጠራ ለተነሳሱት ወጣቶች ለራሳቸው እንተወው፡፡ ይህ ሲሆን ያለ አንዳች ጥርጥር ኢትዮጵያ በወጣት የፈጠራ ልጆቿ ወደ ጥንታዊ ክብርና ዝናዋ ትመለሳለች፡፡

ይህ ጽሑፍ በከፊል የተወሰደው ታላላቅ ሰዎችና ጥቅሶቻቸው በሚል ርእስ በ2007 ዓ.ም. ከታተመ መጽሐፍ መሆኑን በአክብሮት እገልጻለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...