Wednesday, June 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢሕአዴግ ተመራጮች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?

በአገራችን በ2007 ዓ.ም. ከተከናወኑት ዓበይት የፖለቲካ ሥራዎች አንዱ አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት የምርጫ ቦርድ ምርጫን በሚመለከት ያከናወናቸው ተግባራት ካለፉት አራት ዓመታት ምርጫዎች አንፃር ሲታዩ ጥሩ ጎኖች ነበራቸው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ውድድር የሰፈነበት እንደሚሆን በአገሪቱ የሚገኙ ፓርቲዎችን በብዛት አሳምኖ ወደ ውድድር አቅርቧቸዋል፡፡ ምርጫው የተሳካ እንዲሆንም ከምርጫው ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችና ስብሰባዎች አካሂዷል፡፡ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችም ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ አቅርበዋል፡፡ ከኢሕአዴግ የሚለዩበትን የፍልስፍና አቅጣጫም ለማሳየት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህም ሆኖ በየትኛውም በማደግ ላይ እንደሚገኝ አገር ሁሉ በአገራችንም የአካሄድ ችግር አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ የችግሩ ምንጭና ሒደትም ዘርፈ ብዙ ነበር ብሎ በደፈናው ማለፍ ይቀላል፡፡ በመጨረሻ ግን እንደተጠበቀው ኢሕአዴግ ምርጫ ቦርድ በከፊል በገለጸው መሠረት መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን ድምፅ አግኝቷል፡፡

ዳሩ ግን የዛሬዎቹ ተመራጮች ከሁሉ አስቀድሞ ለመሆኑ ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበሩት ተመራጮች ሕዝብና የኢሕአዴግ የጣሉባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ተወጥተዋል? ምን ያህሉስ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከተመረጡበት ዓላማ ተቃራኒ የሆነ ተግባር አከናወኑ? ሕዝቡስ ባለፉት አምስት ዓመታት ምን ይላቸው ነበር? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ዛሬ ከጅምሩ ማለትም ወደ ሥልጣን ኮርቻ ከመውጣታቸው ወይም ለመውጣት በሚዘጋጁበት ዋዜማ ላይ ሆነው ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡

ሕዝብን ለመምራት ራስን ማብቃት ያስፈልጋል

በሥልጣን ላይ መሆን እንዲህ የዋዛ ሳይሆን ብዙ ማንበብን፣ ብዙ መስማትን፣ ብዙ ማየትን፣ ብዙ መንቀሳቀስን፣ ብዙ ማሰላሰልን ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን በዚህ የጥድፊያ አገርን የማልማት ሩጫ ጊዜ እንኳንስ አዲስ ሐሳብ ሊያመነጩ በአዋቂዎች ተረቆ የመጣው ሕገ-ደንብ ወይም መመርያ ከመፅደቁ በፊት እንዲገመግሙት ሲሰጣቸው፣ አንብበውት ወደ ስብሰባ አዳራሽ የማይገቡ ይኖራሉ፡፡ ባለማንበባቸውም አስተያየት መስጠት አይችሉም፡፡ ቢሰጡም ደግሞ ትክክል የመሆኑ ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡ ያፀደቁትን ሕግ፣ ደንብ፣ መመርያ፣ ወዘተ ምን እንደነበር ባለማወቅም ያወቁ መስሏቸው ሐሳብ የሚሰነዝሩ አይጠፉም፡፡ ተዘጋጅተው ያለመምጣታቸው ትልቁ ምክንያት አለማንበባቸው ቢሆንም፣ ያላነበቡትም ምክንያት የማንበቢያ ጊዜያቸውን በሌላ ተግባር ላይ አውለውት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ማንበብ፣ ንባብንም በተጓዳኝ ዕውቀት ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1900-1965 የኖረው አድላይ ሰቲፈንሰን፣ ‹‹ከመመረጥ ይልቅ አገርን ማስተዳደር የበለጠ ነው፡፡ የአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ ችሎታ የሚመነጨውም በሥልጣን ላይ ሲቀመጥ ነው፤›› በማለት ያስገነዘበው መመረጥ እጅግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡

ለአንዳንድ ተመራጮች ኢሕአዴግ ስላስመረጣቸው ዓላማቸው ሁሉ የኢሕአዴግ የበላይ ባለሥልጣናት የሚሰጡትን መመርያ መጠበቅ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የኢሕአዴግ ዓላማ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት፣ ፍትሐዊ ሥርዓት መዘርጋትና ልማት ማስገኘት እስከሆነ ድረስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እየገነባ ተቀናቃኝ ኃይሎችን መጥላት ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ማራቅ፣ ኢፍትሐዊ አሠራርን ማራመድ፣ ጉቦኝነት፣ አድሎአዊነትና ሙስናን ማራመድ የኢሕአዴግ ዓላማ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፡፡ ድርጅታቸው በሕዝብ ስም ተነስቶ ለዕቅዱ መፈጸም ሲያስመርጣቸው ዓላማውን እንዲያራምዱለት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የተሰጣቸው ኃላፊነት የራሳቸውን ወይም የወዳጆቻቸውን ወይም የበላዮቻቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድሙበት መስሎ ከተሰማቸው ፖለቲከኛነታቸው እዚያ ላይ ያበቃል፡፡ ለምን? በአጭሩ ይህ አስተሳብ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ካልሆነ ደግሞ ዕድገትን ያቀጭጫል፣ ዕድገት ከሌለ የመናገር ነፃነት፣ የመደራጀት ነፃነት፣ የመሰብሰብ ነፃነት በአጠቃላይም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊኖር አይችልም፡፡

መሪዎቻችን የራሳቸው የሆነ ፍልስፍና ሊኖራቸው ይገባል

አንዳንድ ሊቃውንት ‹‹ያለፍልስፍና የሚያስተዳድር መሪ በዓይነ ስውር ፈረስ የሚጎተት ጋሪ ነው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ዛሬ የበለፀጉት አገሮች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኑሯቸው እጅግ በተሻለ የኑሮ ደረጃ የደረሱት መሪዎቻቸው ፍልስፍናን እንደ ዋነኛ መሣሪያቸው አድርገው በመነሳታቸው ሲሆን፣ የፍልስፍና ድህነት ባለባቸው አገሮች ጠበብት ‹‹መንግሥት እንደ ሳይንስ በፍልስፍና እጦት እየተሰቃየ ነው›› በማለት የሚያስጠነቅቁትም፣ የፖለቲካ መሪዎች ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ የራሳቸውን ዓላማ በጭፍን እንዳያራምዱ ነው፡፡ ያለሳይንስና ፍልስፍናም ፖለቲካው ብቻውን አፍራሽ ተፅዕኖ ያለው ባዶ ጩኸት ስለሚሆን ነው፡፡ አንዳንድ ታላላቅ መሪዎች ተብለው የሚነገርላቸው የፖለቲካ ሰዎች አንድም ራሳቸው ፈላስፎች ካለበለዚያም ፈላስፎችን ከጎናቸው ያደረጉ፣ ወይም ሁለቱንም ሁኔታዎች በማመቻቸታቸው እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ኧርቪን ኤድማን የተባሉ ፈላስፋ ‹‹ዘ ፊሎዞፊ ኩዌስት›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1947 ባሳተሙት መጽሐፋቸው ‹‹በፍልስፍና አዕምሮን ማንቃት ከጠባብነትና በምኞት ዓለም ከመኖር ያድናል፡፡ … (ፍልስፍና) ሰዎችን እርስ በርስ የሚያግባባ፣ አንዳቸው የሌላው አባል የአንድ ዓለም ዜጎችና ወንድማማቾች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤›› ሲሉን ቪክቶር ሁጎም ‹‹ፍልስፍና የሐሳብ አጉሊ መነጽር ነው›› በማለት አስፈላጊነቱን ያጎላዋል፡፡

እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 22 ቀን 1561 ዮርክሻር በሚባለው የለንደን ክፍለ ከተማ የተወለደው ዝነኛ ፈላስፋ ፍራንሲስ ቤከን፣ ‹‹እኔ የተወለድኩት ለሰው ልጅ መልካም አገልግሎት ለመስጠት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ሕዝብ መብት መጠበቅ ያሉ የሰው ልጅ የደስታ ምንጭ የመሳሰሉት መልካም ነገሮች ሁሉ ክብካቤ ሊደረግባቸው፣ እንደ ውኃና አየር ሁሉም እኩል ሊጠቀምባቸው እንደሚገባም አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም ለሰው ልጅ የሚበጁ ነገሮችን ለማከናወን እንደምን ተፈጥሮዬን ማስተካከል እንዳለብኝ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በዚህም ጥያቄ ሁኔታዎችን ስዳስስ ኪነ ጥበብን ከማሳደግና ከመፍጠር የተሻለ የሰው ልጅን ብልፅግና የሚያመጣ ሥራ አላገኘሁም፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ልጅን ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣ ሐሳብ የሚያመነጭ እውነተኛ ሰውን የዓለማችን የበላይ የሚያደርግ፣ የነፃነት ሻምፒዮንና በአሁኑ ጊዜ ባርያ አድርጎ ከያዘው ችግር (ፍላጎት) አስወጋጅ የሚል መጠሪያ ሊሰጠው ይገባል፤›› ያለውን እንደ ጸሐፊው ያለ ተራ ሰው ማስታወስ ይገባው ይሆን?

ስለሕዝብ ነፃነት አጥብቀው ከተከራከሩት ዕውቅ ፈላስፎች አንዱ የሆነው ጆን ሎክ እንደሚለው፣ ‹‹ከፍተኛ የሕዝብ ነፃነት ፍላጎት መንግሥት ከሚሰጠው እጅግ አነስተኛ ፍላጎት ጋር መታረቅ አለበት፤›› ሲል የመከረው ነፃነትና ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ሰፍኖ የተሻለ ማኅበራዊ ሕይወት እንዲገኝ፣ ሕዝብ የሚፈልገውን እንዲሾምና እንዲሽር ነው፡፡ ሕዝብን እንደፈለገ የሚነዳ የፖለቲካ ፓርቲ ሲኖር ግን በሌላው አገር ሁሉ አልፀደቀምና በእኛም አገር ደርሶ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ ዕውቁ ጸሐፊ ተውኔት ሼክስፒርም ‹‹ጁሊየስ ቄሳር›› በሚል ርዕስ በደረሰው ተውኔትም፣ ‹‹ሕዝቦች ሆይ ፓምፔም፣ ጁሊየስ ቄሳርም፣ ብሩተስም፣ ማርክ አንቶኒዮስም ያው አምባገነን መሪዎቻችሁ ናቸው፤›› ይለናል፡፡ ሞሎቫን ዲጂላስ የተባሉና የዩጎዝላቪያ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ ግለሰብ ‹‹ዘ ኒው ክላስ›› በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1958 ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣ ‹‹በራሺያም ሆነ በሌሎቹ የኮሙዩኒስት ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ሁሉም ነገር ሌኒን፣ ስታሊን፣ ትሮትስኪና ቡካሪን ከጠበቁት የተለየ ሆኗል፡፡ እነዚህ ሰዎች ዴሞክራሲ ተጠናክሮ የፈላጭ ቆራጭ መንግሥት አገዛዝ ይወገዳል ብለው ነበር፤ በመፈጸም ላይ ያለው ግን ግልባጩ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕድገት ተገኝቶ የሕዝብ ማኅበራዊ ሕይወት እንደሚሻሻል አምነው ነበር፡፡ ነገር ግን እንደጠበቁት ሊሆን አልቻለም፤›› ካሉ በኋላ ይህም የሆነው አዲሱ የወዛደር-ላብአደር መደብ ከፊውዳሉ መደብ እንደተነሳው ዘውዳዊ መደብ ልፍለጥ ልቁረጥ በማለቱ ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ የአዲሱ መደብ ሌላ ችግር ካፒታሊስትም፣ ወዛደርም፣ ላባደርም፣ ሠራተኛም ለመሆን የማይችል ነገር ግን በሠራተኛው ላይ የተለጠፈና በስሙ የሚገዛ እንደሆነም ያስገነዝባሉ፡፡ የአዲሱ መደብ ዕጣ ፈንታ ከ40 ዓመታት በኋላ ምን እንደሆነም ዛሬ ከአገራቸው ዩጎዝላቪያ የበለጠ ማስረጃ አይኖርም፡፡ ይህ ምሳሌ ግን የጥሩ ነገር ምሳሌ ሊሆን ከቶ አይቻልም፡፡ በዓሉ ግርማም ‹‹ኦሮማይ›› በተሰኘው መጽሐፉ የሚያስተምረን ይህንን ሀቅ ነው፡፡

‹‹ሁሉን ቢናነገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል›› እንደሚባለው ሁሉንም በአንድ ጊዜ ዘርዝሮ መናገር ይቸግራልና አሜሪካዊው ፈላስፋ ጆን ዲዩ (1859-1952) ‹‹ሪኮንስትራክሽን ኢን ፊሎዞፊ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ (1920 ገጽ 140) ያሰፈረውን ልብ ብለን እንመልከተው፡፡ ‹‹መጥፎ የሚባለው ሰው ምን ያህል ጥሩ የነበረ ቢሆን ከዕለት ወደ ዕለት ጥሩነቱ እየቀነሰ ሲሆን፣ ጥሩ ነው የሚባለው ሰው ደግሞ ምንም ያህል ፋይዳቢስ የነበረ ቢሆን፣ ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ጥሩነት እያደገ የሚሄድ እንደሆነ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ግንዛቤ ያለው ራሱንና ሌሎቹን ሊገመግም ይችላል፤›› ይላል፡፡ የዚህ ፈላስፋ አመለካከት ትክክል ነው ብሎ የሚያምን መሻሻልን ያመጣል፡፡ ካለማወቅ ባርነትም ራስን ማላቀቅና ራስን በተሻለ ሁኔታ መቅረፅ ነው፡፡ የሰዎች የወደፊት ብሩህ ተስፋ የሚመሠረተውም ከመጥፎ ወደ ጥሩ በመጓዝ እንጂ ከጥሩ ወደ መጥፎም ሆነ፣ ከመጥፎ ወደ መጥፎ በመሻጋገር ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ ደርግ መሬትን ላራሹ በማድረጉ በገበሬው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ በግድ በአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጁና በመንደር ተሰባሰቡ በማለቱ፣ አብዮቱ የመሬት ባለቤት አድርጎሃልና ለአብዮቱ ህልውና ዝመት ብሎ በማስገደዱ ወዶ እስኪጠላው ድረስ አንገፍግፎታል፡፡ የሕዝብ መንገፍገፍም ደርግን ከጥሩ ወደ መጥፎ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡

ወቅቱ ዛሬ ነውና የአሁኑ መንግሥትም በዚህ መነጽር ራሱን ይመርምር፡፡ ሕዝብን በእርግጥም ነፃ የሚያደርግ ፍልስፍና ይጨምር፡፡ እስካሁን ምን ሠራሁ? በዚህ የሥራ ሒደትስ ምን አለማሁ ብቻ ሳይሆን ምን አጠፋሁ? ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል፡፡  ትናንት ‹‹እንቢ አልገዛም›› ብሎ ጫካ ያስወጣው የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የትምህርት ብርሃን ስላልፈነጠቀ ነው? ለዘመናዊ ዕድገት በሩን ስላልከፈተ ነው? ደርግስ ዕድገትን የማይመኝ ነበር? ሁለቱም በጎ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ስህተታቸው እኛ ብቻ እንግዛ፣ ማንም ሊቀናቀነን አይገባም ነው፡፡ ስለሆነም ተቀናቃኝን ማንጓጠጥ ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት መሞከር የትም እንደማያደርስ የሚያውቅን ሕዝብ በፕሮፓጋንዳ ሞገድ ለማጥለቅለቅ ቢሞከርም ፍንክች እንደማይል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ‹‹ያለፍልስፍና የሚያስተዳድር መሪ፣ በእውር ፈረስ የሚመራ ጋሪ›› ተብሎ የሚመሰለውም ለዚሁ ነው፡፡  ሕዝብ የሚመራው በፍልስፍና ጥበብ ነውና ካለፈው ጥፋት ለመማር ያብቃን፡፡

አዳዲሶቹ ባለሥልጣናት

ሰዎች ሰላማችንን ለማደፍረስ የጦርነት ነጋሪት ሊጎስሙ፣ እንቢልታ ሊነፉና ሊያስተጋቡ ይችላሉ፡፡ ዳሩ ግን ደኅንነታችን የከፋ አደጋ ላይ የሚወድቀው እነዚህ ሰዎች ስለፎከሩም ሆነ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እጅግ በተራቀቀ መንገድ በመሠራቱ ከቶ አይደለም፡፡ የጦር መሣሪያዎች በሳይንሳዊ ዘዴ ተሠርተው ከሚያስከትሉት አደጋ ይልቅ፣ ኅብረተሰቡ አንዱ የሌላውን ነፃነት ለማደፍረስ ህልውናውን ደምስሶ የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ ምቾቱን በሌሎች ችግር ለማግኘት ጥረት ያደረገ እንደሆነ ነው፡፡ ኤልቶን ትሩብለድ የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ “ዲክሌሬሽን ኦቭ ፍሪደም” በሚል ርዕሰ ባሳተሙት መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ “ብዙዎቻችን የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንመኛለን፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ መናኛ ግጭቶችን ለማናርና በዚህ ችግር ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ኃይሎች አንድነትን ለመሸርሸርና ውህደቱን ለማደፍረስ ይጥራሉ፡፡ ከአንድ ይልቅ ለሁለትና ለሦስት የተከፈለ ልብ እንዲኖረንም ይወተውቱናል፤” ብለዋል፡፡ አንዲህ ያለው ከጦር መሣሪያ ይልቅ አንድነትን የመበተንና ውህደትን የመሸርሸር ችግር ሊወገድ የሚቻለው ግን ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ የሆነ አስተሳሰብ ያለ አንዳች ገደብ በሕዝብ ዘንድ የተናኘና የሰረፀ እንደሆነ ነው፡፡፡ እርግጥም “የእኔን አመለካከት አንጂ የሌላው አትመኑ፣ የኔን ድርጅት አምልኩ፣ የሌላው ሁሉ ፋይዳ ቢስ ነው…” የሚሉ ግለኛ አስተሳሰቦች ሲወገዱ የተሻለ ዘመን ይመጣል፡፡

ባሳለፍነው የሶሻሊስት ሥርዓት “ሰዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እኩልነታቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉት የወዛደር መደብ በአሸናፊነት የወጣ እንደሆነ ነው” የሚል ፕሮፓጋንዳ ይነፍስብን ስለነበረ፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ “ሌሎች መደቦች ጭምር በነፃ የሚንቀሳቀሱበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ይኑር” ባንል፣ ድሮውንም “ፓርቲያችን ያሸንፋል” በሚል አጉል አመለካከት ተጀቡነን ከተቀመጥን ዴሞክራትነታችንን አያመለክትም፡፡ ዳሩ ግን ለተፋጠነ ዕድገት ከነፃ ገበያ ሥርዓት የተሻለ እንዳልተገኘ ሕይወት ራሷ እየመሰከረች ነው፡፡ ነፃ ገበያ ደግሞ ከነፃ የፖለቲካ ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ “ያንተ ድርጅት፣ ድርጅቴ ሥልጣን በያዘበት አካባቢ ዝር እንዳይል” የሚያሰኝ ሳይሆን፣ “እንዲያውም የተቀናቃኝ ድርጅቶች በአካባቢው መኖር ለእኔ ህልውና ዋስትና ነው” የሚያሰኝ ነው፡፡ ነጋዴው ከነጋዴው፣ ምሁሩ ከምሁሩ፣ ገበሬው ከገበሬ፣ ፖለቲከኛው ከፖለቲከኛው በነፃ ካልተወዳደረ፣ ካልተቸና በዚህ ሒደት የተሻለ አመለካከት መንጭቶ ለዕድገት በር ካልተከፈተ፣ አማራጭ በሌለው መንገድ መጓዝ ይሆንና ለአምባገነን አገዛዝ መዳረግ ይሆናል፡፡ ኤልተን ትሩብለድ በግልጽ እንዳስፈሩት ደግሞ፣ “ነፃ ኅብረተሰብ የሚባለው ሁሉም  ነው፡፡ ጥቁሩም ሆነ ነጭ፣ ደሃም ሆነ ሀብታም፣ በአገሩ ተጠቃሚ መሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ ነው፡፡ መንግሥት የሚኖረው ለግለሰቦች እንጂ ግለሰቦች ለመንግሥት ሲሉ አይኖሩም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ ጠቃሚ በመሆኑ፣ የማንኛውም ሥርዓት ዴሞክራሲያዊነት የሚለካው መንግሥት ለዚያ ግለሰብ መብት መጠበቅ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ነው፡፡”

ልዩነትን በአንድነት መፍታት

ዛሬ በአገራችን የተለያዩ አመለካከቶች፣ አስተሳሰቦች፣ እምነቶች፣ ርዕዮቶችና ዴሞክራሲያዊ መንገዶች እየታዩ ናቸው፡፡ ይህም ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ልምዶች ጋር ሲደመር አንድነታችንን የበለጠ እንደሚያጠናክረው አያጠያይቅም፡፡ አንድነታችን ባለን ልዩነት ላይ የተመሠረተ መሆኑንም ከደሙ ጋር ተዋህዶ ለኖረው ሕዝብ እንደገና ማስተማር አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ማንኛውም በሥልጣን ላይ ያለ አካልም ሆነ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚሻ የፒራሚድ ቅርፅ ያለውን የፖለቲካ ሕይወት እያለፈ ሲሄድ ማስተዋል የሚኖርበት ይህንን ሀቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች በእርግጠኛነት ለአገር ዕድገትና ብልፅግና ለመሥራት ቁርጠኛ ዓላማ ካላቸው፣ እንደምንም ብለው በማለፍ ሥልጣን ኮርቻ ላይ መንጠልጥል ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብ ሌሎች አማራጮችም እንዳሉትና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲያውቃቸው ተወዳድረው ከተሸነፉበት ጊዜ ጀምሮ ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ በእነሱና በተቀናቃኞች መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርገው ማሳየት ቀዳሚ ተግባራቸው መሆን ይገባዋል፡፡ ተቀናቃኝን በተለያዩ መንገዶች በሕገወጥ ጭምር ካልጎዳሁት በስተቀር ሥልጣን ልይዝ አልችልም በሚል በጣም የተሳሳተ አመለካከት በመነሳት የሚያከናውት ተግባር፣ ራሱን ከፍተኛ የፖለቲካ ክስረት ውስጥ የሚጥልና ሕዝብን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1809-1865 የኖሩት አብርሃም ሊንከን፣ ‹‹ባሪያ ለመሆን እንደማልፈልገው ሁሉ ጌታ ለመሆን አልሻም፡፡ ይህ ዴሞክራሲያዊ አመለካከቴ ነው፤›› ያሉትም ዛሬ ለብዙዎቻችን አርዓያነት ያለው ይመስለኛል፡፡ በፖለቲካው መስክ የተሠሩ ሁሉ ሕዝብን ከጭቆና፣ ከሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ከድህነትና ከበሽታ ለማላቀቅ እንጂ ተቃራኒውን ለመፈጸም እንዳልሆነ በቀና አስተሳሰብ እንደገና እንዲያጤኑት ወቅቱ ይጠይቃቸዋል፡፡ አብረሃም ሊንከን እንዳሉት የሕዝብ ድምፅ የተሻለ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሥልጣን የሚወዳደሩበት ሥርዓት ከተዘረጋ ገና 20 ዓመት ብቻ ስለሆነ፣ ከአሮጌ አስተሳባብ ወደ አዲስ አስተሳሰብ መቀየር በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ይኼው ዴሞክራሲያዊ ጮራ ካለመለመዱ  የተነሳ የፀሐይ ጨረርን ቀና ብለን ስንመለከት እንደሚወጋን ሁሉ ዓይነ ህሊናችንን ሊወጋ ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ልናስተውለው የሚገባ አብይ ቁም ነገር ግን ከዴሞክራሲው የሚፈነጥቀው ጨረር ብቻ ሳይሆን፣ ጨረሩ በሕዝብ ላይ አርፎ የሚያሳየው ክስተት መሆን ይኖርበታል፡፡ ወትሮም ሰው የሚመለከተው ፀሐይን ሳይሆን ፀሐይ የምታሳየውን ነው፡፡ ይኼው የዴሞክራሲ ጮራ ሁነቶችን፣ አንድነትና ልዩነትን፣ መግባባትንና መስማማትን፣ የሰዎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር አለመከበራቸው በትክክል ለማሳየት የሚችለው ደግሞ፣ እንደ ደመና የሚከልል ወይም የመሬት ነውጥ ይመስል የሚያውክ፣ እንዲሁም እንደ ጎርፍ የሚያደፈርስ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊት የሌለ እንደሆነ ነው፡፡ “ጥሩን መጽሐፍ የሚያጠፋ ዕውቀት ራሱን እንደገደለ ይቆጠራል›› በማለት ዕውቁ እንግሊዛዊ የሥነ ጽሑፍ ሰው ጆን ሚልተን እንደገለጸው ሁሉ፣ ዛሬ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና ብለን በሀቅ ካልተነሳንና ዓለማችንን ዳር ለማድረስ ካልቆረጥን በስተቀር ሁላችንንም የምታናግረን፣ የምታሳስበን፣ የምታጽፈን፣ እንድንደግፍንና እንድንቃወም የምታደርገን አገራችን ልንጎዳት እንችላለን፡፡

ስለዚህም በዚች አገር ፍትሕ፣ ርትእ፣ ሰላምና አንድነት ተከብረው ለመቆየታቸውም ሆነ፣ ኢትዮጵያን ለአንዱ እናት ለሌላው እንጀራ እናት ሆና ከቆየችበት ዘመን ልትላቀቅ የምትችለውና ሕዝቡ በፍቅር ዓይን መተያየት የሚጀምረው ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነቱን ሲያጠናክር ነው፡፡ ሰዎች በፈለጉት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ኑሮ መስክ ሊያራምዱት የሚችሉት አንድ አገራዊ እምነት ሲኖራቸው እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ስለአንድነታችንና ልዩነታችን ለማስገንዘብ በየፊናችን ስንሰማራ ደግሞ የብዙ ዘመናት የብሔር ብሔረሰብ ጭቆናን አስወግደን፣ ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ አስተደደር ለመመሥረት ባለን ዓላማ እንጂ፣ በአሜሪካ ያሉት ሞንጎሎይድ፣ ካውካሶይድና ኔግሮይድ አሜሪካዊ እንደሆኑት ሁሉ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን በመዘንጋት አይደለም፡፡ አሜሪካን በምሳሌነት የጠቀስኩት የዘመናችን ትልቅ አገር በመሆኗ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከፍተኛ ማኅበራዊ ውህደት እንደተፈጠረ ለመተንተን መሞከር ደግሞ ለቀባሪው አረዱት እንደሚባል ይሆናል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አጎራባች አገሮችና ቀይ ባሕርን ተሻግረው ወደ አገራችን ከገቡ ዓረቦችም ተዋልደን ኖረናል፡፡ እንደሚታወቀው ለረጅም ዘመናት በአንድ ላይ ስለኖርን ልምዳችን፣ ባሕላችን፣ ባህሪያችንና ትውልዳችን ስለተዋሀደ ከዚህም አንፃር ብሔርና ብሔረሰብ እያልን የምናራምደው እንቅስቃሴ ዘመን የወለደው የፖለቲካ ስትራተጂና ጭቆና የፈጠረው ጥያቄ ስለሆነ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊነታቸው ያላቸውን መብት ከቶ የሚነካ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕዝቦች በፈለጉት አቅጣጫ ይደራጁ ልዩነታቸው አንድነታቸው ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በጦር መሣሪያ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መድረኮች ይገለጽ የሚል አስተሳሰብ ቢነሳም በአግባቡ ሊስተናገድ ይገባል፡፡ በአጭሩ አንድ ኢትዮጵያዊ የአገሪቱን ሕግና ደንብ እስካከበረ ድረስ፣ በፖለቲካ ፓርቲ፣ በብሔር ብሔረሰቦች ተደራጅቶ ቢንቀሳቀስ መብቱ እንደሆነ ሊታወቅለት ይገባል፡፡

የጥላቻ ፖለቲካን ማስወገድ

ጥላቻ የሰው ልጅ የገነባውን የሕይወት ድር ከመበጣጠሱም በላይ፣ ማኅበራዊ ይዘትና ቅርፅ ከያዘ መዘዙ በቀላሉ የማይነቀል መርዝ ነው፡፡ በጥላቻ መንፈስ የተመረዘ ኅብረተሰብም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮው ድርና ማግ እየተሸማቀቀ ወደ ድህነት ማዘቅዘቁ አይቀሬ ነው፡፡ ጥላቻ ከፍርኃት፣ ወይም ከመንፈስ መጎዳት የሚመነጭ የሚገልጽ ስሜት ነው፡፡ አንድን ነገር በመረረ ሀኔታ አለመውደድና ነገሩ ሥር ሰዶ ለመበቀል የሚያነሳሳ ድርጊት ነው፡፡ ጥላቻ በአንድ ነገር ውስጥ ጥሩ ነገር ቢኖር እንኳ ያንን መልካም ገጽታ የሚከልል ጠንካራ መጋረጃ ነው፡፡ ስሜቱ በጥላቻ የተጋረደም ለጥፋት እንጂ ለልማት ከቶ ሊነሳሳ አይችልም፡፡ አንዱን በመጥላቱ ምክንያት ሌላው ከእሱ (ከዚያ ከሚጠላው) ጋር የተያያዘ መሆኑን ጭምር ይረሳዋል፡፡ ለምሳሌ ወተት የማይወድ ሰው ከወተቱ ጋር የተያያዘውን ጥቅም ሁሉ ሊያስታውሰው እንደማይፈልግ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ይህም በወተት ውስጥ ምን ቢሆን ጥቅም ሊኖረው አይችልም ብሎ እንደማሰብ ይሆናል፡፡ ይሁንና አንድ ሰው በልዩ ልዩ ምክንያት ወተትን ቢጠላ ደግሞ ሌሎች እንዲጠሉት ማድረግ ለራሱም ቢሆን አይበጀውም፡፡ በማኅበራዊ ኑሮም ቢሆንም ግለሰብን በግል መጥላት አንድ ነገር ሲሆን፣ ኅብረተሰብን በጅምላ መጥላት ግን ለራስም ቢሆን ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ያለፈን፣ ያረጀንና ያፈጀን በግል መጥላት ይቻላል፡፡ የሚጠሉትን ነገር እየደጋገሙ መጥላት ግን ለመውደድ ይቻላል የነበረውን ጊዜ በከንቱ ማጥፋት ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ ከ500-250 የኖረው ሱታፒታክ እንዳለውም፣ “ጥላቻን በጥላቻ መንገድ ከቶ ማስወገድ አይቻልም፤›› ቢቻል ኖሮ የደርግ መንግሥት ለአሥራ ሰባት ዓመታት ያህል ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ወደፊት ያለውን ሁሉ እጅግ በመረረ ጥላቻ አይቶት ነበር፡፡ እርሱ ራሱ ጥላቻን ሲዘራ በሕዝብ የሚያስፈቅር ተግባር ለማከናወን ጊዜ ባለማግኘቱ ግን አይወድቁ አወዳደቅ ወደቀ፡፡

ነፃነትን ማረጋገጥ

አንዲት አገር ለመበልፀግና በትክክለኛ አቅጣጫ ለመጓዝ የምትችለው የፕሬስ ነፃነት፣ የሐሳብ ነፃነት፣ የመሰብሰብ ነፃነት፣ የመናገር ነፃነትና የእምነት ነፃነት የተረጋገጠ እንደሆነ ነው፡፡ እነዚህ መልካም ነገሮች ሁሉ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት በትክክል ሠፍረዋል፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥት ላይ መሥፈራቸው ብቻ መንግሥት የሕዝቡን ነፃነት አረጋግጧል ማለት እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም ኢሕአዴግ በ30ኛው የግዛት ዘመኑ መግቢያ ላይ ሆኖ የሕዝቡን የፕሬስ ነፃነት፣ የሐሳብ ነፃነት፣ የመሰብሰብ ነፃነት፣ የመናገር ነፃነት፣ የእምነት ነፃነት የተረጋገጠ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አሠራርን በሚገባ ገምግሞ የተሻሉ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የግሉ ሚዲያንም በጥላቻ ወይም በንቀት ዓይን ማየት፣ መጠራጠር፣ ወዘተ አስወግዶ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የማስቻሉ ኃላፊነት በመንግሥት ላይ የተጣለ ነው፡፡

የሃይማኖትንና የፖለቲካን መቻቻል እውን ማድረግ

Anchorስለሃይማኖትና ፖለቲካ መቻቻል ሲነሳ የአሜሪካ ፕረዚዳንት ባራክ ኦባማ የተናገሩት ልብን የሚነካ ነውና እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡

“በዓለም የሚከናወነውን አስመልክተን ስንናገር እምነት ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ ተደጋግፈው ለመነሳት፣ ረሃብተኞችን ለመታደግና ድሆችን ለመንከባከብ፣ የተጨነቁትን ለማፅናናትና ፀብን አብርዶ ሰላም ለማስፈን ጥረት የሚያደርጉ መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡  ይህም ሆኖ እምነት ተጠምዝዞና ተዛብቶ ሕዝብን የሚከፋፍል ሽብልቅ እንዲያውም ከዚያ የከፋ የጦር መሣሪያ እየሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምናየው የጽንፈኛነትና የሁከት ድርጊት ለአንድ ቡድን ወይም ሃይማኖት ተነጥሎ የሚተው ሳይሆን፣ በኛም ውስጥ ሃይማኖታችንን የሚያዛባና የሚያፋልስ አዝማሚያ አለ፡፡ በዛሬው ዓለም ጥላቻን የሚያራምዱ ኃይሎች ትዊተር ከፍተው የራሳቸውን በዘረኝነት፣ በጠባብነት፣ በትምክህተኛነትና በእብሪተኛነት የተሞላ አስተሳሰባቸውን እያሰራጩ ነው፡፡ እናም በመጀመሪያ በቅንነት እንጀምር፡፡ በእኔ አመለካከት ዕምነት የሚጀመረው በመጠነኛ ጥርጣሬ ነው፡፡ በዚህ ጥርጣሬ ውስጥ ስንሆን ትክክለኞቹ እኛ ራሳችን ብቻ ስለሆንን ፈጣሪ ለእኛ እንጂ ሌሎችን የሚያነጋግር አይመስለንም፡፡ ፈጣሪ እኛን የሚንከባከበን እንጅ ሌሎችን የሚንከባከብ አይመስለንም፡፡ እውነትን የያዝን እኛ ብቻ የሆንን ይመስለናል፤” ነበር ያሉት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles