በኢትዮጵያ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ዘንድ በርካታ ሀገረሰባዊ እምነቶችና ልማዶች አሉ፡፡ ከነዚህም አንዱ ወደፊት የሚከሰት ወይም ሊገጥም የሚችልን ሁኔታ ባጠቃላይ የአንድን ሰው የወደፊት ዕድል (ዕጣ ፈንታ) ቀድሞ ለመገመት ወይም ለማወቅ የሚደረገው ትንበያ ነው፡፡ ይህን ሀገረሰባዊ እምነት ከሚያከናውኑት መካከል በበርታ ብሔረሰብ ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይጠቀሳሉ፡፡ ትንበያውን የሚያደርጉት በብሔረሰቡ ዘንድ ነሪ ወይም መይሳ ተብለው ይታወቃሉ፡፡
በፎክሎሪስቷ እታገኘሁ አስረስ መሪነት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙት ብሔረሰቦች ባህላዊ ቅርሶች ላይ ጥናት ያደረገው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቡድን እንዳተተው፣ ትንበያ ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ አንድ ሰው ጉዞ ሲያደርግ ምን ሊገጥመው እንደሚችል ለመገመት ነው፡፡ ትንበያ በበርታዎች ዘንድ ወደ ሌላ አካባቢ ጉዞ ከመደረጉ በፊት በየትኛው ቀን ጉዞ ቢጀመር (ከቤት ቢወጣ) ጥሩ ዕድል እንደሚያጋጥም ለማወቅ ያግዛል፡፡ ባለሙያው (ተንባዩ) የጉዞ አቅጣጫውና ዓላማው ከተነገረው በኋላ በየትኛው ቀን ጉዞ ቢጀመር ያሰበው እንደሚሳካና ጥሩ ዕድል እንደሚገጥመው፣ በየትኞቹ ቀናት ደግሞ ክፉ ነገር እንደሚገጥመውና ያሰበውን እንደማያገኝ ወይም እንደማይሳካ ይነግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ የጠፋ ከብት ወይም ዕቃን ለማግኘት በየት አቅጣጫ (በኩል) ቢኬድ ሊገኝ እንደሚችል አዋቂዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንድ ግለሰብ በየትኛው የሥራ መስክ ቢሰማራ በቂ ሀብት ወይም ንብረት ማግኘት እንደሚችል የሥራውን ዘርፍ በመጥቀስ ጭምር ለምሳሌ በወርቅ ማዕድን ቁፋሮና ማውጣት ቢሰማራ የተትረፈረፈ ገንዘብ ሊያገኝ እንደሚችል አስቀድሞ ይገመታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለአቅመ አዳም የደረሰ ጉብል ለትዳር ያጫት ሴት ከወደፊት ሕይወቱ ስኬት ጋር በተያያዘ ይቺን ሴት የምታገባ ከሆነ ጥሩ ዕድል አይገጥምህም ወይም የመጨረሻ ደሀ ስለምትሆን እሷን ትተህ አዋቂዎቹ የሚጠቁሙትን አብሯት ልጅም ሆነ ሀብት ሊያፈራ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን እንዲያገባ ይደረጋል፡፡ ከበሽታ ጋር በያያዘ ደግሞ ወደፊት ጊዜውን በመጥቀስ በኃይለኛ በሽታ ስለምትያዝ አስቀድሞ ለትንበያ አዋቂዎቹ (ነሪ) አስፈላጊ የሆነውን ክፍያ በመፈጸም በሽታውን ከወዲሁ መከላከል የሚያስችል አቅም ለመፍጠር በሹዌ የሚባል ዛፍ ቅጠል በማመጣት በሽተኛው ላይ ልቀቅ እያለ እንዲያራግፉበት ይደረጋል፡፡
አዋቂው ትንበያ ከሚያደርግበት ሰዓት ሰባት የቀንድ አውጣ ግልፋፊ ወይም ዛጎል (ሀውዲ) መሬት ላይ እየወረወረ በጥሞና ወይም የእጅ መዳፉን ይመለከታል፡፡
ጠቀሜታው ትንበያ የወደፊት ዕድልን ለማወቅ፣ በየትኛው ጊዜ ቢደረግ ስኬት እንደሚገኝ፣ ከብት ከቤት ሲጠፋ ይኑር አይኑር ለማወቅና ከየት ሊገኝ እንደሚችል ለመጠቆም እንደ አንድ ሥነ ልቦናዊ መፍትሔ የሚጠቀሙበት ባህል ነው፡፡
በቁሳዊ መገለጫውም አዋቂው ትንበያ ሲያካሂድ ሰባት የቀንድ አውጣ ግልፋፊ ወይም ዛጎል ይይዛል፡፡ አንዳንድ መድኃኒቶችን ለምሳሌ ያህል ኦዮን የሚባል ተከል ሥር ቆፍሮ በማውጣትና በእጁ በመያዝ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን ለሚተነብይለት ሰው ይሰጣል፡፡ መድኃኒቱም በአፍ የሚወሰድ ሳይሆን ተቀጥቅጦ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የሚረጭ ነው፡፡
የቀንድ አወጣጡ ግልፋፊ ወይም ዛጎል መሬት ላይ በመበተንና የእጅ መዳፍ በማየት ስለ አንድ ግለሰብ የወደፊት ዕድልም ይተነብያል፡፡
ስለ አጥኚዎቹ መግለጫ ቅርሱ ከዘመናዊ ትምህርትና የሕክምና ዕውቀት ጋር መስፋፋት ጋር በተያያዘ ስለትንበያው እውነትነት የመጠራጠር አዝማሚያ በሰፊው እየተስተዋለ በመሄዱ የቅርሱ ትግበራ እየተዳከመ ይገኛል፡፡ ለቅርሱ ቀጣይነት በአዋቂዎች በኩል ለመረጡት አንድ ልጀቻው ዕውቀቱን ከማስተላለፍ ባለፈ ምንም ጥረት እየተደረገ አይገኝም፡፡