ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ኃይሌ ገሪማ ‹‹የጡት ልጅ›› የተሰኘውን ፊልማቸውን ለመሥራት ከጥቂት ቀናት በፊት በኢንተርኔት የገንዘብ ማሰብሳሰብ ጀምረዋል፡፡
የፊልሙ ታሪካዊ ዳራ በ1960ዎቹ ከጣልያን ወረራ ሃያ ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ፊልሙ በማደጎ በአገር ውስጥ ለአንድ ሀብታም ዳኛ ቤተሰብ የተሰጠች ዓይናለም የተሰኘች የ13 ዓመት ልጃገረድ ሕይወት ላይ ያተኩራል፡፡ ታዳጊዋ በማደጎ በወሰዳት ቤተሰብ መልካም አስተዳደግና ጥሩ ኑሮ እንደሚጠብቃት ቃል ተገብቶላት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሳዳጊዎቿ ቤት የጉልበት ሠራተኛ እንድትሆንና ስቃይ እንዲደርስባት ሆነ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆና ግን ከአንድ ፖሊስ በፍቅር ወደቀች፡፡ ፍቅረኛዋ ከነበረችበት አስከፊ ሁኔታ እንድታመልጥ ቢያደርጋትም ከዓመታት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ አገኛት፡፡
የፊልም ባለሙያው ኃይሌ ገሪማ እንዳሉት ልብ ወለድ ድራማ የሆነው ፊልሙ የሰብአዊ መብት በተለይም የማፍቀር መብት አንድምታ አለው፡፡ የፊልሙ ስክሪፕት ተጽፎ የተጠናቀቀው ከሰባት ዓመታት በፊት ሲሆን ለማሰባሰብ የታሰበው 500,000 ዶላር ነው፡፡
የዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸላሚ የሆኑት ፕሮፌሰር ኃይሌ ከሠሯቸው ፊልሞች መካከል ጤዛ፣ ዓድዋ፣ ሳንኮፋ እና ቡሽ ማማ ይገኙበታል፡፡