Wednesday, September 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልበጥበባት ኮንፈረንስ የሙዚቃ ፖሊሲ እንዲረቀቅ ተጠየቀ

  በጥበባት ኮንፈረንስ የሙዚቃ ፖሊሲ እንዲረቀቅ ተጠየቀ

  ቀን:

  የግርማ ይፍራሸዋ ‹‹ሰመመን›› የዓመቱ ምርጥ ክላሲካልና ብሉዝ ሙዚቃ የሚል ቅጽል አትርፏል፡፡ ሥራዎቹን ባቀረበባቸው የአገር ውስጥና የውጪ አገር መድረኮች በርካቶችን አስደምሟል፡፡ ሙዚቃ በተማረበት ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መድረክ ላይ ‹‹ሰመመን››ን ሲያስደምጥም ታዳሚዎች በተመስጦ ተከታትለዋል፡፡ ከየመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፤ አክብሮታቸውን አሳይተዋል፡፡

  ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምስጋና ካቀረበላቸው ሦስት ሙዚቀኞች አንዱ ግርማ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ በክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍ ሰለሞን ሉሉና ቫለንቲና ሲምዮኖቫንም አወድሷል፡፡ በትምህርት ቤቱ የተዘጋጀውን ሦስተኛው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ምክንያት በማድረግ የተሰናዳው የክላሲካል ሙዚቃ ኮንሰርት ሦስቱን ሙዚቀኞች ያማከለ ነበር፡፡ ሥራዎቻቸው ተወስተዋል፤ ለአስተዋጿቸውም ተመስግነዋል፡፡

  ጥበባዊ ኮንፈረንሱ የተካሄደው ከግንቦት 25 እስከ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሆን፣ የክላሲካል ሙዚቃ ኮንሰርቱ ግንቦት 26 አመሻሽ ላይ ቀርቧል፡፡ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፣ መምህራንና ተጋባዥ ሙዚቀኞች ክላሲካል ሙዚቃ አቅርበዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ መምህር ዮናስ አያና ኮንዳክት የተደረገው የማሊ ሙዚቃ ‹‹ታምባላ ዋሊራ›› በሦስተኛ ዓመት ተማሪዎች ቀርቧል፡፡

  መረዋ ኳየር፣ በምዕራፍ ተክሌ የተቀናበሩና ኮንዳክት የተደረጉ አራት ዜማዎች አቅርበዋል፡፡ መሠረቱን በመንፈሳዊ ዜማ ያደረገው ‹‹ቅዱስ›› እና ከሲዳማ ሙዚቃ የተወረሰው ‹‹ሌምቦ›› ይጠቀሳሉ፡፡ የሹበርትን ቅንብር የትምህርት ቤቱ መምህራን አክሊሉ ዘውዴ፣ ዓለምነሽ አወልና ቫለንቲና ሲምዮኖቫ አቅርበዋል፡፡

  ‹‹አርትስ ፎር ሶሻል ቼንጅ›› (ጥበባት ለማኅበረሰባዊ ለውጥ) በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ሥር ካሉት የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት፣ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤትና ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የተውጣጡ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በትምህርት ቤቶቹ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በዘለለ ሥነ ጥበብ፣ ሙዚቃና ቴአትር ከማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ሕይወት ጋር በማጣመር ምልከታቸውን ያቀረቡ ባለሙያዎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

  በሙዚቃው ዘርፍ ከተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ስለሙዚቃ ፖሊሲ አስፈላጊነት የተደረገው ውይይት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ፣ እንግሊዛዊ ሙዚቀኛና መምህር ራሚ ሲያም መወያያ ነጥቦች ካቀረቡት ባለሙያዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

  ሙዚቀኛው ዳዊት አብዛኛው የኅብረተሰቡ ክፍል በሙዚቃ መደሰት እንጂ  ለባለሙያዎች ክብር አለው ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው በመጠቆም፣ በትምህርት ፖሊሲ ሙዚቃ ትኩረት እንዳልተቸረው ተናግረዋል፡፡ የሙዚቃ ዘርፍን ፈር ለማስያዝ ፖሊሲ እንደሚያሻ አክለዋል፡፡

  የሙዚቀኛውን ሐሳብ የተጋራው ራሚ የእንግሊዝን ተሞክሮ በመመርኮዝ ነው፡፡ በእንግሊዝ የሙዚቃው ዘርፍ የሚመራበት መርሕ ተግባር ላይ ከዋለ በኋላ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ መጨመሩንም ገልጿል፡፡ ሙዚቃ በተለይም ለባለሙያዎች የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍ እንዲል ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ፖሊሲ  እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ተናግሯል፡፡  

  ጥናት አቅራቢዎቹ ሙዚቃ ሙያተኞችን፣ ማኅበረሰቡን እንዲሁም አገሪቱን በአጠቃላይ በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ፖሊሲ እንደሚያሻው አመላክተዋል፡፡ የሙዚቃው ተግዳሮቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አብዛኞቹ ችግሮች በፖሊሲ መቀረፍ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

  ከታዳሚዎቹ መካከል ፖሊሲ ሲወጣ ሙያተኛውን ያማከለ ስለመሆኑ መታወቅ እንዳለበት የተናገሩ ነበሩ፡፡ ፖሊሲ ለውጥ አመላካች ሳይሆን ለሙያተኛው እንቅፋት እንዳይሆን የሚል ሥጋት ያቀረቡ አስተያየት ሰጪዎች ነበሩ፡፡ በቅርቡ የተረቀቀውን የፊልም ፖሊሲ በማጣቀስ ፖሊሲ በጥበባት ዘለቄታዊ ለውጥ ስለማምጣቱ ጠይቀዋል፡፡

  የፒኤችዲ ተማሪዎቹ አማረ ተሾመና በጎሰው የሸዋስ ‹‹በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ስሜት ቀስቃሽና አቃዛቃዥ የቋንቋ አገላለጾች›› የሚል ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በተለያዩ ዘመናት ሙዚቃ የማኅበረሰቡን ስሜት ለማነሳሳትና በተቃራኒው ለማቀዝቀዝ የዋሉ ሥነ ቃሎችን አቅርበዋል፡፡

  ከነዚህ መካከል ጀግንነትን ለማወደስ፣ መንግሥትን ለመቃወምና ለመደገፍ  አመጽን ለማበረታታትና ለመቃወም፣ በቀልን ለማነሳሳትና ለመንቀፍ የዋሉ ይጠቀሳሉ፡፡ በየዘመናቱ ኅብረተሰቡ ቅሬታውን፣ ደስታውን፣ ምኞቱንና ትውስታውን በመግለጽ ሙዚቃ ያለውን ሚና አስረድተዋል፡፡

  መሸፈትን የሚያበረታታው ‹‹ኧረ ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ፤ ላንተም ይሻልሀል ብቻ ከማደሩ›› እና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተማሪዎችን አመጽ ለማበረታታት የተገጠመው ‹‹ፖሊሱ ጉበኛ ዳኛው ፈሪ፤ ለፍትሕ ለዴሞክራሲ ተነሳ ተማሪ፤›› ይጠቀሳሉ፡፡  

  በሙዚቃ ትምህርት ላይ ትኩረት ያደረገው ‹‹የበገና ትምህርት ዕድገትና ያጋጠሙት ችግሮች›› በሲሳይ ደምሴ የቀረበ ጥናት ነው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ግዛው ኃይለማርያም ‹‹የዓለም የዜማ አውታር የማይናወጥ ጥበባዊ የሙዚቃ ማዕበል›› የተሰኘ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

  ከቴአትር ትምህርት ክፍል ጥናታዊ ጽሑፎች ያቀረቡት መምህራን ዘሪሁን ብርሃኑና ተስፋዬ እሸቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹የመድረክ ብርሃን በኢትዮጵያ ቴአትር›› የኢየሩሳሌም ካሳሁንና አቦነህ አሻግሬ ጥናት ነው፡፡ በቴአትር ቤቶች ስላለው የመድረክ መብራት አጠቃቀምና ችግሮቹ ያነሳል፡፡

  በየቴአትር ቤቶች ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች በማጣትና በመሣሪያ እጥረት ሳቢያ ስለተከሰቱ ችግሮች አንስተዋል፡፡ የመድረክ መብራት በፕሮፌሽናሎች ባለመሠራቱ በተዋንያን ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት የደረሰበትን አጋጣሚ ጠቅሰዋል፡፡ በቂ መሣሪያ አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡ የመድረክ መብራት ከቴአትር ዘርፍ ትኩረት እንዳልተሰጠውና የመሣሪያ ግብዓት ተሟልቶ በፕሮፌሽናሎች መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

  በሥነ ጥበብ ላይ ጥናታቸውን ካቀረቡት አንዱ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር አበባው አያሌው ‹‹ሪያሊቲ ኤንድ ኢማጅኔሽን ኢን ጎንደሪያን ፔይንቲንግ›› የሚል ጽሑፍ አቅርቧል፡፡ የጎንደር ዘመንን ሥነ ጥበብ ከአውሮፓውያኑ ጋር በንፅፅር ቀርቧል፡፡ የጊዜው ሥዕሎች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላችው መሆናቸውና እንዲሁም ከነባራዊ ሁኔታ መቀዳታቸው መወያያ ሆኗል፡፡

  መምህርት በረከትነሽ ግርማ በትምህርት ቤቱ በዲጂታል ፋብሪኬሽን ዘርፍ የሚሠራውን ሥራ የሚያሳይ ጥናት አቅርባለች፡፡ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን ጨምሮ ከተለያዩ ድርጀቶች ጋር የሚሠሯቸውን የዲዛይን ሥራዎች ገልጻለች፡፡ ከታዳሚዎች መካከል በተለያዩ ቁሶች ላይ የሚታዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዲዛይኖች እንዲጠበቁ ያሳሰቡ ነበሩ፡፡ ዲዛይኖቹን በተለያዩ ቁሳቁሶች በማስፈር ረገድ በባህላዊ መንገድ የሚሠሩት ባለሙያዎች ሥራዎች ታሳቢ እንዲደረጉ አስተያየት ተሰንዝረዋል፡፡

  19 ጥናታዊ ጽሑፎች በቀረቡበት ኮንፈረንስ ከሙዚቃ ኮንሰርት በተጨማሪ ድራማና የሥዕል ዐውደ ርዕይ ቀርቧል፡፡ በኮንፈረንሱ ከየትምህርት ቤቶቹ የተወጣጡ መምህራንና ተማሪዎች ታድመዋል፡፡ የተለያዩ የሙያ ማኅበራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋሞችም የመርሐ ግብሩ ተካፋይ ነበሩ፡፡ በመጀመርያው ቀን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተውጣጡ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በቤንዚንና ነጭ ናፍጣ ላይ ጭማሪ ተደረገ

  ከዛሬ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓም እኩለ ሌሊት ጀምሮ...

  ‹‹ለሰላምና ለዕርቅ መሸነፍ የለብንም›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

  የሰው ልጅ ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክህደትን...

  መፍትሔ አልባ ጉዞ የትም አያደርስም!

  ኢትዮጵያ ችግሮቿን የሚቀርፉ አገር በቀል መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡...

  ጦርነቱና ውስጣዊ ችግሮች

  መስከረም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው...