ሰላም! ሰላም! ሰሞኑን እኛ ሠፈር የአገራችን የ13 ወራት ፀጋ ጥያቄ ተነስቶበት መከራውን ሲያይ ነበር። የአገሬ ሰው በሰው ሠራሽ ችግር ከመንገዋለል በራሱ በፀጋው መንገዋለል ለምን እንደሚቀናው አይገባኝም። የምር! እና እኔም የመንደሬን ፖለቲካ በአንክሮ ስከታተል ሰነበትኩ። በሠፈራችን የተካሄደው ንትርክ (ውይይት ያላልኩት ሳንጨርስ ቡጢ ጨብጠን ስለወጣን ነው) መነሾ አብዛኛው የመንደራችን ነዋሪ በጉንፋን ‘ቫይረስ’ በመረፍረፉ ነው። አንዳንድ ዕድሜ ጠገብ ሰዎች በጉንፋን ዙሪያ ያላቸውን ተሞክሮ ሲያካፍሉ ከተናገሩት፣ “… እንደምታውቁት እኛ ከአክሱም ሐውልትና ከላሊበላ ውቅር ቤተ አምልኮ ዕድሜያችን የሚያንሰው ትንሽ ነው። በዘመናችን ያላየነው፣ ያልጨበጥነው የተትረፈረፈ ገንዘብና ቪላ ብቻ ነው እንጂ በጤና አንታማም ነበር። ዕድሜ ለእነ ጤና አዳም፣ ለእነ ነጭ ሽኝኩርት፣ ለማርና ለጥቁር አዝሙድ ደግሞም ለድንግልና ጉንፋን የሚሉት ጅል ‘ቫይረስ’ አናውቅም። (ድንግልና? ድንግልናን ምን አመጣው? ሰው ይንሾካሾካል) አዳምጡ! ታዳያ እንደምታዩት ዕድሜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ሆነና 13 ወራት ሙሉ ድህነትን ለማባረር ደፋ ቀና እንደማለት፣ ጉንፋን ለማባረር ባልበላ አንጀታችን ዝንጅብል እናኝካለን…” አሉ የዕድሜ ጠገቦች ማኅበር ዋና።
አስከትለው፣ “… እንደ ዛሬው የኑሮ ጫና ቅጥ እያጣ ዋጋውን ሳይቀንሰው በፊት ሞታችን በራሱ እኮ ውድ ነበር። በጤና ዕጦት ማለት በነቀርሳ፣ በስኳርና በልብ ችግር የተሞተ ሞት የለም ለማለት እችላለሁ። ቂጥኝና ጨቡዴን በሌላ ርዕስ እመለስበታለሁ (አንዳንዱ ይስቃል)፡፡ ይልቁንም ለነፃነታችን፣ ለክብራችን፣ ለእምነታችን፣ ለአልገዛም ባይነታችን ነው ውድ አወዳደቅ የወደቅነው። አይደለም እንዴ? (ተሰብሳቢዎች ‘እውነት ነው’ ብለው አንገታቸውን ላይ ታች ያወዛውዛሉ)… ዛሬ ግን ክቡሩን ማዕድ እያዳቀሉ እሱን በመከራ ፊታችን ሲያቀርቡልን መቼም ረሃብ ነውና እያላመጥን ይኼው በሽታም ሙስናም የመከላከል አቅማችን ደከመ። በዓመት 13 ጊዜ አጎንብሰን አሪቲ ስንታጠን ፎቆች ተጀምረው አልቀው ዓይኖቻችን ተቁለጨለጩ፤” ብለው ዓይናቸውን አቁለጨለጩ። እንቁልልጩን ያመጣው እብደት ስብሰባ መሀልም ሠራ መሰል?
ብዙም ሳይቆይ ተሰብሳቢዎች በሦስት ምድብ ተከፋፈሉ። ስብሰባውን የሚመሩት ባሻዬ ሦስት ተናቋሪዎችን ለመገላገል ከመቀመጫቸው ተነስተው ወደ ተሰብሳቢዎቹ ቀረብ ብለው ለማረጋጋት ሲጥሩ ሦስት ጊዜ አስነጠሳቸው። ወዲያውም “ጉሮሮዬን ከረከረኝ፤” ማለት ጀመሩ። አንድ የጉንፋን ‘ቫይረስ’ ያልተጋባባቸው ባሻዬ ቡዝዝ ማለታቸውን አይቼ ጠጋ አልኩና “ባሻዬ ቤት ላድርስዎና እኔም ወደ ሥራዬ ልሂድ። ይህን ጭቅጭቅ እንኳን እርስዎ የዓለም የምግብ ተራድኦ ድርጅትም አያረግበው፤” አልኳቸው። ምንክንያቱም ከሦስቱ አንደኛው ቡድን፣ “አመጋገባችን ላይ ፍራፍሬ ስለማናበዛ ነው ጉንፋን የተከታተለብን። መፍትሔውም የሠፈራችን አትክልት ቤት ከዛሬ ጀምሮ የሙዝና የብርቱካን ዋጋ በግማሽ እንዲቀንስ ለመንግሥት አቤት ማለት ይገባናል፤” ይላል። ሁለተኛው ደግሞ “የደላው ሙቅ ያኝካል!” ሲል ጀምሮ፣ “ፍራፍሬው ቀርቶብን በቀን ሦስቴ ጥራጥሬ አግኝተናል ወይ?” ባዩ የተከማቸበት ቡድን ነው።
ሦስተኛው ደግሞ፣ “ጥራጥሬም ተገኘ ፍራፍሬም ታከለ አበቃቀሉ ሳይንሳዊና ቤተ ሙከራዊ መሆኑን በቶሎ እስካላስቆምን ድረስ ለዴሞክራሲ፣ ድህነትን ታሪክ በማድረግ ሒደት ለመሳተፍ፣ ለነፃነትና ለፍትሕ የሚበቃ ዕድሜ አይኖረንም። በነቀርሳና በጉንፋን ሟቹ የኢኮኖሚ ዕድገቱን መብለጡ አይቀርም። ይህ ደግሞ ሳይታለም የሚፈታ ነው፤” ብሎ ለራሱ ዕልልታውን ያቀልጠዋል። ጭብጨባውን ያጦፈዋል። ባሻዬ ዙሪያ ገባውን በጥልቅ ማስተዋል ቃኝተው ነገሩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ሲረዱ፣ “በውይይት ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከዚህ ባህል አትወጡም፤” ሲሉ ትዕንቢት መሰል እርግማን አወረዱ። ይዣቸው ወጥቼ ወደ ቤታቸው ስሸኛቸው ደግሞ፣ “አንበርብር” አሉኝ “አቤት?” አልኳቸው። “ዝም ብዬ ሳስበው በሽታ የመከላከል አቅማችን ብቻ አይደለም የከዳን። ተነጋግሮና ተደማምጦ የመግባባት አቅማችን ጭምር እያደር አንሶብኛል፤” አሉኝ። ምን ያላነሰን አቅም አለ ባሻዬ? ምን ያላነሰን አቅም አለ?
ባሻዬን ወደ ቤታቸው አስገቤቼ እየተጣደፍኩ ወደ ቀጠርኩት ደንበኛ ተጓዝኩ። ደግሞ ከቀጠሮዬ ሰዓት ትንሽ ማርፈዴን ሳይ ላይቋጭ ነገር፣ ‘የአገራችን የ13 ወራት ፀጋ ጉንፋንን ጨመረ ወይ?’ ብሎ ጀምሮ ሰዓቴን ባቃጠለው ስብሰባ እጅግ አዘንኩ። በስንቱ እንደምንበታተንና እንደምንቃጠል እኮ ዘንድሮ። ታዲያ እኔ ግን ከአመጋገቤ ጋር ተያይዞ የጤንነቴ ጉዳይ ያሳስበኝ ጀምሯል። ደግሞ እኮ ስትፈሩ የማያማችሁ ጭምር ማመም ይጀምራል። ወዲያው ለማንጠግቦሽ ደውዬ፣ “የተከበሩ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ፍራፍሬና አትክልት ተመጋቢዎች ጎራ ዞሬያለሁ፤” ስላት፣ “በል ሰው እንዳይሰማህ። ሰው ምነው በልቼ በሞትኩ እያለ አንተ ጭራሽ ማማረጥ ጀመርክልኝ? ወይ ጥጋብ!” አለችኝ። እኔ እኮ ስለጤና ማሰብና ራስን መንከባከብ ከጥጋብና ከሙስና ጋር አጉል መቆራኘቱ ነው ሊገባኝ ያልቻለው። ቀጠለችና ጤናችን በአመጋገብ ሳይሆን ሰው አፍ ባለመግባት እንደሚጠበቅ ልታስረዳኝ ብዙ ጣረች። እንግዲህ እንደ ማንጠግቦሽ መዝገበ ቃላት ከሆነ ከሥጋ ተመጋቢዎችና ከአትክልት አዘውታሪያን ቀጥሎ ሦስተኛው ለጤና ተስማሚ አመጋገብ በሰው አፍ አለመታኘክ መሆኑ ነው። ጉድ እኮ ነው እናንተ!
ደንበኛዬን የቀጠርኩት ለስድስት ወራት የሚከራይ ዘመናዊ ቪላ ላሳየው ነው። ሳገኘው ፂማም፣ አሰላሳይና ሽቅርቅር ቢጤ ነው። የተቀባው ሽቶ በየአካባቢያች በወል የምንታደለውን የደረቅ ቆሻሻና የፍሳሽ ቱቦ ጠረን ሰንጥቆ ብዙ ‘ማይልስ’ ይቀዝፋል። እንግዲህ በቅርቡ እሱን የመሰሉ ልማታዊ ባለፀጎች የሚበራከቱ ከሆነ ከአካባቢ ፅዳት ጉድለት ሳይሆን ጉንፋን የሚይዘን ከሽቶ ይሆናል ማለት ነው። ከሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሀል አንዱ ዜጎችን በሽቶ ጉንፋን ማስያዝ ቢሆን ሊገርመን አይገባም ማለቴ ነው። ለማንኛውም ሽታና ሽቶውን ስናልፈው፣ ቤቱ እንደሚሆነው ወስኖ ደንበኛዬ የስድስት ወራት ኪራይ እዛው ሆጭ አለ። በካሽ። ለእኔ ደግሞ ‘ኮሚሽኔን’ በቼክ ሊሰጠኝ እጁን ኪሱ ሲሰድ ‘ቼኩ’ መጥፋት። ትንሽ ከተወናበደ በኋላ ሲያስታውስ ከቤቱ ረስቶት ወጥቶ ነው። “በል ምሳ ሰዓትም ስለደረሰ አብረን ወደ ቤት ሄደን ምሳ በልተን ቡና ጠጥተን ጽፌልህ ከሰዓት ባንክ ትሄዳለህ፤” ሲለኝ እሺ አልኩ። እንደ አላዲንና ፋኖሱ ታሪክ፣ ‘ጂኒ ተሸክሞኝ የምሄድ እስኪመስለኝ በደንበኛዬ እጅግ ዘመናዊ አውቶሞቢል ጋቢና ተቀምጬ ስጓዝ ወፍ ነካችኝ ብሎ እንደሚቋረጠው የአገሬ ኤሌክትሪክ ኃይል አንጎሌ ውስጥም የኃይል መቆራረጥ ተከሰተ። አደራ ደግሞ ሲያንጦለጡላችሁ ሚሊዮን በሚሸመቱ አውቶሞቢሎች ላይ ተንጠልጥላችሁ እኔን የገጠመኝ የኃይል መቆራረጥ ካጋጠማችሁ፣ ለጂቡቲ በምንሸጠው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳታሳብቡ። አደራ በሰማይ አደራ . . . (በምድር ልል ነበር የምድር አደራና የአገር አደራ በራስ ጥቅም እየተለወጠ ስለተቸገርን ትቼዋለሁ) ፡፡
“Anyway” እንዳለው ፈረንጅ፣ እኛም ‘ኤኒ-ዌይ’ ብለን እንደገለበጥነው (public service ሲሉ አይተን ‘ፐፕሊክ ሰርቪስ’ እንዳልነው ማለት ነው፡፡ እናንተ ደግሞ የምሳሌ ቀብድ ካልተሰጣችሁ አንዳንዴ የማወራው አይገባችሁም) ደንበኛዬ ቤት ምሳዬን ግጥም አድርጌ በላሁ። እሱ ግን ምሳው ‘ቫይበር’ ላይ የቀረበ ይመስል ቤቱ ከገባ ጀምሮ ቀና ብሎ አላየኝም። ታዲያ ግጥም አድርጌ በላሁ ስላችሁ ረሃቤ ላይ በእህል አፋሸኩ ላለማለት በመጠንቀቅ ነው። ምን ታውቁት የለ ጨው የለው ቅባት የለው የሀብታም ቤት ምግብ። ግን ‘ኧረ እህል ጡር አለው’ ተብለን ስላደግን (እንዳሁኑ ትውልድ ምግብ ደፍተን፣ የተደፋ አፍሰን በልተን፣ የእንጀራ ፀጋ ቀሎብን፣ የሆድ ነገር ገዝፎብን ስላላደግን) ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን ካልሆነ ጨውና ቅባት የለውም ብለን እህል አናንጓጥጥም። ‘ሲሪየስ!’ ቡና ተፈልቶ አቦል እስኪቀዳ ያን አስገራሚ ቤት ስቃኝ፣ ‘ይኼን የመሰለ ቤት እያለው ለምን ይሆን ደንበኛዬ ሌላ ቤት መከራየት ያስፈለገው?’ ስል ከረፈደ ጠየቅኩ። ወዲያው ደንበኛዬ ስልክ ሊያናግር ወደ ውጭ ወጣ። ምን ገንዘብ ቢሞላ ‘ኔትወርክ’ እና ሆድ አይሞሉም እሺ? . . . አዎ!
‘ቫይበሩን’ እስኪጨርስ አላስችል ብሎኝ ቡናውን እንድትቀዳው ቡና ወደምታፈላው የቤት ሠራተኛ ስዞር፣ እንባዋ ኩልል እያለ አፍንጫዋን ትጨምቃለች። ጉንፋን ነው ብዬ እንዳላልፋት እንዲያ ካለ የእንቧ ፏፏቴ ጀርባ የማይጠፋውን ማጣት አመጣሽ ችግር ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። ምን እንደሆነች ጠየቅኳት። የወንድሟን በጠና መታመም አጫወተችኝ። ሕመሙ የአጥንት ካንሰር መሆኑን አብራራችልኝ። ግራ እንደገባት ያስታውቃል። አኳኋኗ ቅስሜን ሰብሮታል። ሐዘኗ ተላልፎብኛል። አላስችለኝ ስላለ ደንበኛዬ ሳያየኝ “ማስታመሚያ ይሁንሽ” ብዬ ጥቂት ብር ሰጠኋት። ከባሻዬ ልጅ ጋር ሄጄም ወንድሟ እንደምጠይቀው ለራሴ ቃል ገብቼ ስልክ ቁጥሯን ተቀበልኩ። ደንበኛዬ ስልኩን አናግሮ ጨርሶ ሲመለስ፣ “በአንዴው ከእንባ ወደ ሳቅ?” ሲል ጠየቃት። እየተፍለቀለቀች ‘ጋሼ’ ብላ ጠርታኝ “የወንድሜን ነገር አጫውቻቸው ስጦታ ገንዘብ ሰጡኝ፤” አለችው። ለእኔም ለእሷም አፈርኩ። ግን እሱ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “ስንት ሰጠሃት?” አይለኝ መሳችሁ? እንዲህ ይባላል ግን? በዚህ አጀብ ስል መለስ ብሎ፣ “በይ የሰጠሽን ብር እንደ ደመወዝ ቁጠሪው፤” ብሎት አረፈው። “ባለፀጋ መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ…” አለ ያ ናዝራዊ!
በሉ እንሰነባበት። በስንተኛው ቀን ቀትር ላይ ከባሻዬ ልጅ ጋር የባጥ የቆጡን እያነሳን ስንጫወት ድንገት ያች ልጅ ትዝ አለችኝ። ለባሻዬ ልጅ የባለፀጋውን ጥያቄና መልሶች አጫውቼው ስለነበር፣ “ለምን አሁን ሄደን ወንድሟን አናየውም?” አለኝ። ሁሌ ግሮሰሪ ከመጎለት አንዳንዴም የታመመ መጠየቅ ለምድራችን መንግሥት እንደማያዋጣ እያወቅን የሰማዩን ተማምነን ዘለቅን። ደወልንላት። “ሠፈሬ ቦሌ ነው፤” ስትለን “የያዝነውን ስለማንለቅ እንጂ ቦሌ እኮ በቃ ደንበኛ የጭቁን መንደር ሆናለች፤” አለኝ የባሻዬ ልጅ ፈገግ ብሎ። አፀፋውን አልመለስኩም። በተፈጥሮዬ በደሃና በዘር የሚቀለድ ቀልድ ስለማልወድ ይሆናል። ማስመሰል ቢመስልብኝም ‘ሼር’ ላድርጋችሁ ብዬ ነው። ሰው ስንት የማይረባ ነገር ‘ሼር’ ያደርግ የለ እንዴ?
የነገረችን ሥፍራ ብዙ ጉራንጉር ማቆራረጥ ግድ ይላል። ወጥታ ተቀበለችን። እየመራች ከደረቅ ቆሻሻ መጣያ ገንዳ አጠገብ በጭቃ እንደነገሩ የተመረገች ሦስት በአራት ቤት አስገባችን። ወንድሟ አልጋ ላይ ተኝቷል። ግርጌው ጡት ያልጣለች ሕፃን ተኝታለች። “ልጄ ናት፤” አለች ሳንጠይቃት። “ቁጭ በሉ፤” ተባልን። ተቀመጥን። ወንድሟ እየተፍለቀለቀ ስለ በሽታው ይነግረን ጀምሯል። ስለጠየቅነው ያለ መጠን ተደስቷል። መዳን እንደማይችል፣ የአጥንት ካንሰር እንደሆነና ገና የ18 ዓመት ልጅ መሆኑን ተስፋ በሚነበብባቸው፣ ነጋቸውንና ያለመጠን የሚናፍቁ ዓይኖቹን አንዴ ወደ እኔ አንዴ ወደ ባሻዬ ልጅ እያንከባለለ ይነግረናል። እህቱ ታቋርጠናለች። “ጋሼ አንበርብር በሰጠኸኝ ገንዘብ ያዘጋጀሁት ምሳ ነው። ሙያዬን ቅመሱ እስኪ፤” አለችን። ችሮታና ሌሎችን ማሰብ ለምን በሌላቸው እንደሚብስ ሳስብ፣ የሰጠኋትን የገንዘብ መጠን ጠይቆኝ ሲያበቃ ‘ደመወዝሽ ነው’ ያላት ባለፀጋ ውልብ አለብኝ። እንባዬ ግጥም ሲል አይቶ የባሻዬ ልጅ ቆነጠጠኝ። ያቀረበችውን አብራን ቀማምሳ ያች ምስኪን ደሃ፣ ሕፃኗ አልቅሳ ታስነሳታለች። ግን እስከ መቼ እንታገል እያልን የተኮላሹ ህልሞች መቃብር ሲወርዱ ዓይተን እንዳላየን የምናልፈው? አንተዛዘን እያልን ያልተኖሩ ልጅነቶች የምንጽፈው? እስከ መቼ ንፉግነት ባለው ይብሳል? እስከ መቼስ ያለን ማካፈል የደሃ ብቻ ጌጥ ይሆናል? እስከ መቼ የባከኑ ዕድሜዎች ሲቆጠሩ ይኖራሉ? እኛስ ቆጠራችንን የምናቆመው መቼ ይሆን? ቸር ሰንብቱ እስኪ! መልካም ሰንበት!