Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊያልተዳረሰ ፈውስ

ያልተዳረሰ ፈውስ

ቀን:

መገናኛ አካባቢ በአንድ ፋርማሲ ውስጥ ነው፡፡ ከውጭ የገባው ሰው ‹‹ሚክስታርድ አገኘህ እንዴ?›› ሲል ፋርማሲስቱን ጠየቀ፡፡ ‹‹ሚክስታርድም ኢንሱላታርድም እስካሁን አላገኘንም፤›› በማለት መድኃኒቱ ቀናት መጥፋቱንና መቸገራቸውን ገለፀ ማርማሲስቱ፡፡

ሚክስታርድና ኢንሱላታርድ በክትባት መልክ ለስኳር ህመምተኞች የሚሰጡ መድኃኒቶች ናቸው፡፡ ሁለቱም አገር ውስጥ አይመረቱም፡፡ የኢትዮጵያ የፋርማሲውቲካል ማኑፋክቸሪንግ ስትራቴጂ እንደሚያሳየው ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ መድኃኒቶች 75 በመቶ የሚሆኑት ከውጭ አገር ሲገቡ 25 በመቶ የሚሆነው ማለትም እንደ ህመም ማስታገሻ፣ አንቲባዮቲክ፣ የፓራሳይት መድኃኒቶች፣ የጉንፋን ሽሮፖችና የመሳሰሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታል፡፡

አልፎ አልፎ ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶች እጥረት እንደሚያጋጥም ይነገራል፡፡ ‹‹ሚክስታርድና ኢንሱላታርድ ሰሞኑን ከገበያ ጠፍተዋል፤›› ያሉት ፋርማሲስቱ ብዙ ጊዜ አገር ውስጥ የማይመረቱ መድኃኒቶች እጥረት እንደሚያጋጥም ይናገራሉ፡፡ ብዙ ህመምተኞችም የታዘዘላቸውን መድኃኒት ሲያጡ ‹‹ከውጭ የሚገቡ ተቀራራቢ መድኃኒቶችን እንደሚሰጧቸው ይገልፃሉ፡፡ ቢሆንም ግን አንዳንዴ በመድኃኒቶች በቀላሉ አለመተካት ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡

በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረቱ መድኃኒቶች አሞክሲሊን፣ ፕሮኬን ፔንሲሊንና ቤዛንቲን ፔንሲሊን ከወር በላይ ገበያ ላይ አለመገኘታቸውን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ፕሮኬን ፔንስሊንና ቤዛንቲን ፔንሲሊንን የሚተካ ከውጭ የሚመጣ መድኃኒት አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ህመምተኞች እየተንገላቱ ይገኛሉ፤ ትልቁ ችግር ይህ ነው፤›› በማለት አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ይናገራሉ፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች የመፈወስ አቅምም ከሌሎቹ ዝቅ ያለ ነው የሚሉት ፋርማሲስቱ ‹‹ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶች አገር ውስጥ ከሚመረቱት ዋጋቸው ከሦስት እስከ አምስት እጥፍ ከፍ ይላል፤›› ይላሉ፡፡ ብዙዎቹ ተጠቃሚዎች በተለይም ልዩ ትዕዛዝ ሲኖር የውጩን እንደሚመርጡ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች ከጣሊያን፣ ከጀርመን፣ ከግሪክና ከመሳሰሉት አገሮች የሚገቡ መድኃኒቶችን ይጠቀማሉ፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ዛሬ ላይ የህሙማንን ሕይወት ለማዳን ሰዎች በአገር ውስጥ የማይመረቱ መድኃኒቶችን አልያም ወደ አገር ውስጥ የማይገቡ መድኃኒቶችን በተለያየ መንገድ ለማስገባት ይሞክራሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን አቅም ሊኖር ይገባል፡፡ አልያም ከአገር ውጭ የሚኖር የቅርብ ዘመድ ማግኘት ግድ ይላል፡፡ በዚህ መልኩ መድኃኒቱን እስኪያገኙ ጥቂት የማይባሉ ቀናትን በስቃይ ለማሳለፍ ይገደዳሉ፡፡ ሕይወታቸውን የሚያጡም አሉ፡፡

መንግሥት ከ2010 እስከ 2015 የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አዘጋጅቶ ሲተገብር ቆይቷል፡፡ በዚህ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ በኢንዱስትሪ መስፋፋት ስር የመድኃኒት አምራች ዘርፉም ተካትቷል፡፡

ኤክስፖርት ሚደረጉ መድኃኒቶችን በዓመት 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማድረስ፣ በዘርፉ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ጥቅም ላይ ማዋልና የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ድርሻ ወደ 50 በመቶ ከፍ ማድረግ በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙ ግቦች ነበሩ፡፡ ይህንን ከማሳካት አኳያም መንግሥት የውጭ ድርጅቶች በአገር ውስጥ የሚያመርቱበት መንገድ አመቻችቶ የውጭ አገር ድርጅቶች ዘርፉን ተቀላቅለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በበቂ መጠን ማምረት ባለመቻሉ የመድኃኒት ጉዳይ አሁንም ጥያቄ ውስጥ እንዳለ ይገኛል፡፡

ዛሬም መድኃኒት ፍለጋ ከአንዱ ፋርማሲ ወደሌላው የሚሯሯጡና አጥተው ተስፋ የሚቆርጡ ሰዎች ጥቂት አይባሉም፡፡ አቶ አስመላሽ ገብሬ የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ሜዲካል ሰፕላይ ሴክተር አሶሴሽን ጸሐፊ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት በሚያደርገው እገዛ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡

‹‹በፊት ከውጭ ከሚመጣው ጋር እኩል እንሠራ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከውጭ የሚመጣው 5 በመቶ ግብር ይከፈልበታል፡፡ እኛ ደግሞ ከ0 እስከ 35 በመቶ ታሪፍ እንከፍል ነበር፤›› የሚሉት አቶ አስመላሽ፣ ጉዳዩን ለመንግሥት በማስረዳት ሁኔታው ተጠንቶ መንግሥት 0 ታሪፍ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡ ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶች መብዛትም ሌላው ችግር ሲሆን ‹‹ለምሳሌ ከህንድ ጋር መወዳደር አንችልም፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ሁለት ድርጅቶች ኤክስፖርት እያደረጉ ይገኛሉ ነገር ግን የገበያ ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ ዋጋ ሰብረው መድኃኒት በገፍ በማቅረብ ገበያውን የሚቆጣጠሩ ከሩቅ ምሥራቅ ኩባንያዎች አሉ፡፡ መድኃኒቶችን ለማምረት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች በከፍተኛ ወጪ ከውጭ ይገባሉ፡፡ ይህን እዚሁ ለማምረት ካልተቻለ ብዙ መሥራት እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

አገር ውስጥ ያለውን ገበያ ማድረስ ባይቻልም ሁለቱ አምራች ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ ጀምረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በ2014 ከ2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማስገባት አልተቻለም፡፡ ይህም በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማስገኘት ከታሰበው 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እጅግ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የአገር ውስጥ የመድኃኒት ፍላጎት ከማድረስ አኳያ 200 የሚሆኑ መድኃኒቶችና የመድኃኒት ማምረቻ ግብዓቶች ወደ አገር የሚያስገቡ ተቋማት ይገኛሉ፡፡

አስፈላጊ ተብለው ከተመዘገቡት 380 መድኃኒቶች የአገር ውስጥ አምራቾች 90 ያህሉን ብቻ ያቀርባሉ፡፡ ይህም በአገር ውስጥ በየመድኃኒት መሸጫ መደብሩ የመድኃኒት እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡

የፋብሪካዎቹ አቅም ውስን ነው፡፡ በአገር ውስጥ ምርት መወሰን የማይታሰብ ነው የሚሉት አቶ አብነት ድንበሩ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች አስመጪዎችና አከፋፋዮች የጋራ መድረክ ኮሚቴ ሰብሳቢና የካሮጋ ፋርማሲዩቲካል አስመጪና አከፋፋይ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ካሉት መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች ማምረት የጀመሩት ከ11 አይበልጡም፡፡ የምርት መጠናቸውም በብዛትና በዓይነት አነስተኛ ነው፡፡ በአገሪቱ ያለው ፍላጐት ከ20 በመቶ በላይ ማቅረብ አይችሉም፡፡ ስለዚህም ያለውን የገበያ ክፍተት መድኃኒቶችን ከውጭ በማስገባት ይሸፈናል፡፡

ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚሆኑ አንቲ ኢንፌክሽን፣ የህመም ማስታገሻና የካንሰር መድኃኒትን የመሰሉ መድኃኒቶች ያስመጣሉ፡፡ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍም አገሪቱ በመድኃኒት ራሷን እንድትችል እንደሚያደርግ የታመነበት ብሔራዊ የፋርማሲውቲካል ማኑፋክቸሪንግ (National Strategy and plan of action for pharmaceutical manufacturing development in Ethiopia) ረቂቅ ስትራቴጂ ተቀርጾ ባለፈው ማክሰኞ በካፒታል ሆቴል በባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጐበታል፡፡

ጆርጅ ሮሺኞ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለረጅም ዓመታት ያለገሉ ሲሆን፣ ከ2015 እስከ 2025 የሚቆየው የአሥር ዓመቱ ስትራቴጂ ሲዘጋጅ አማካሪ ነበሩ፡፡ ጥራት ያለው መድኃኒት ማቅረብ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ፣ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ የሚያሟሉ አምራቾች እንዲፈጠሩ ማገዝ ከስትራቴጂው ዓላማ መካከል ናቸው፡፡ እንደ ጆርጅ ገለጻ፣ ስትራቴጂውን በሥራ ላይ ማዋል ከተቻለ አገሪቱ በአፍሪካ ግንባር ቀደም መድኃኒት አምራች ልትሆን እንደሚችል ያምናሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ብዙዎቹ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ አላሟሉም፡፡ ‹‹ምዘናው ከተደረገላቸው ስምንት ፋብሪካዎች የጥራት ደረጃውን አሟልተው ያለፉት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ፋብሪካዎች የጥራት ሰርቲፊኬት ሊያገኙ ጥቂት ቀርቷቸዋል፤›› በማለት የጥራት ደረጃ ላይ ስለሚታዩ ሁኔታዎች ጠቁመዋል፡፡

ስትራቴጂው አስመጪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ የሚያስችሉ ዕድሎች አስቀምጧል ያሉት አቶ አብነት ስትራቴጂው በሥራ ላይ ከዋለ አገሪቱ በመድኃኒት ራሷን እንደምትችል ያምናሉ፡፡

ዶ/ር መብራቱ ካሳሁን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ እንዳሉት፣ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከዘርፉ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማስገኘት የታሰበ ቢሆንም ከአምስትና ከስድስት ሚሊዮን ከፍ ማለት አልተቻለም፡፡ ፋብሪካዎች መቶ በመቶ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ የማድረግ ዕቅድም ተካትቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ፋብሪካዎቹ ከ60 በመቶ በላይ አቅማቸውን መጠቀም አልቻሉም፡፡ ሌሎችም በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተያዙ ግቦች አፈጻጸም ከታቀደው በታች ሆኗል፡፡ የአቅም ውስንነት፣ ማምረት የሚችሉ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ሴክተሩ አለመግባት፣ በዘርፉ የተጠበቀውን ያህል ውጤት ለማስገኘት ካልተቻለባቸው ምክንያቶች መካከል ናቸው፡፡ ‹‹ምቹ አድርጐ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሄድንበት ሥራ በቂ አልነበረም፡፡ የመሬት አቅርቦት፣ ማበረታቻ ድጋፎች ማነስና የአገልግሎት አሰጣጣችን ማነስም ግቡን እንዳይመታ አድርጓል፤›› በማለት በመንግሥት በኩል የነበረውን ክፍተት ገልጸዋል፡፡

የፋብሪካዎቹ ከአቅም በታች የሆነ ምርትም ሌላው ችግር ነው፡፡ ከ60 በመቶ በላይ አቅማቸውን መጠቀም አልቻሉም፡፡ 40 በመቶ ክፍተት አለ፡፡ ‹‹ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ አላደረግንም፤›› የሚሉት ዶ/ር መብራቱ ፋብሪካዎቹ ጋርም የራሳቸው የሆነ ችግር መኖሩን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ሥራ ያልጀመሩ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፈጥነው ወደ ሥራው መግባት አለባቸው፡፡ ከመሬት ጋር በተያያዘና በራሳቸው ድክመት ወደ ሥራው ያልገቡ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ ይህም የተጠበቀውን ያህል እንዳናመርት እንቅፋት ሆኗል፤›› ይላሉ፡፡

ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ መድኃኒት ፋብሪካዎችን ለማብቃት የግድ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ መሥፈርቱን ለማሟላት ከአመራረት ቴክኒክ፣ ዶክመንቴሽን፣ ከሰው ኃይል ከአካባቢ ጀምሮ ብዙ መሠራት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያም በከፍተኛ በጀት የተጀመረ የኢትዮ ጀርመን የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ነበር፡፡ በዚህ ፕሮጀክት አማካሪዎች ተቀጥረው ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባወጣው መሥፈርት መሠረት የማማከሩ ሥራቸውን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ‹‹በጣም ውድ የሆነ ድጋፍ ነው፡፡ በወቅቱ ከተፈተሹ ስምንት ፋብሪካዎችም ሁለቱ መሥፈርቱን አሟልተው ሰርቲፊኬት ወስደዋል፡፡ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ፋብሪካዎችም ሰርቲፊኬት ለማግኘት ጫፍ ላይ ደርሰዋል፤›› የሚሉት ሚኒስትር ዲኤታው በ2018 አራት ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ሰርቲፊኬት እንዲያገኙ የማስቻል ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ለማሳካትም በቂ ፋይናንስና የኩባንያዎች ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡ በዕቅዱ መሠረት መሥራት ከተቻለ ወደ ኤክስፖርት ገበያ መግባት ቀላል ነው፡፡ ‹‹ሰርቲፊኬት ያላቸው ፋብሪካዎች በዙ ማለት አቅም ያላቸው ተወዳዳሪ ኩባንያዎች አፈራን ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህም አገሪቱ በመድኃኒት ምርት ራሷን እንድትችልና የዜጐችን እንግልት የሚቀንስ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡   

90 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚኖርባት በሚነገርላት አገር ውስጥ የመድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች ቁጥር ውስን መሆን አቅርቦቱን ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ 22 የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ሲኖሩ፣ አራት ዋና ዋና በውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ድርጅቶች ከአቅም በታች ያመርታሉ፡፡ ለአገር ውስጥ አቅርቦትም ከ20 በመቶ በላይ ሊያቀርቡ አልቻሉም፡፡ በ2014 የአገር ውስጥ አምራቹ ገበያው ከሚፈልገው 500 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት መድኃኒት ማቅረብ የተቻለው 44.225 ሚሊዮን የሚሆነውን ብቻ ነው፡፡

በዓመት ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ገበያ ሲኖር፣ በየዓመቱ በ25 በመቶ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በ2012 ፍሮስት ኤንድ ሱሊቫን የሚባል የጥናት ተቋም የአገሪቱ ገበያ በ2018 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ ጠቁሟል፡፡ የዕድገት መጠኑም በዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ያስገድዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...