የዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ሦስተኛው ውድድር ላይ አዲስ ክስተት ሆኖ ብቅ ያለው የ17 ዓመቱ ወጣት ኢትዮጵያዊ ዮሚፍ ቀልጀቻ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበር በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ ባለፈው ሐሙስ (ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም.) በሮም ስታዲየም በተከናወነው የ5000 ሜትር ሩጫ ዮሚፍ በዚህ ዓመት ከ13 ደቂቃ በታች የፈጸመ የመጀመርያው አትሌት ለመሆን ችሏል፡፡
ከአገሩ ልጆችና ከኬንያውያን ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደረገው ዮሚፍ ሩጫውን ያጠናቀቀው በ12 ደቂቃ 58.39 ሰከንድ ነው፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ተያይዘው በተመሳሳይ 12፡58.69 ጊዜ የገቡት ኬንያዊው ፖል ታኑይና ኢትዮጵያዊው ሐጎስ ገብረ ሕይወት ናቸው፡፡ የመጨረሻውን ሁለት ዙር ከስምንት ያላነሱ ተወዳዳሪዎች ሲፎካከሩ ሦስት ሯጮች ከ13 ደቂቃ በታች ለማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ ኢማና መርጊያ በ12፡59.78 አምስተኛ ሌላው ኬንያዊ ቶማስ ሎንጎሲዋ በ12፡59.78 አምስተኛ ሆኗል፡፡ ቀደም ብሎ በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያ ድሉን ያገኘችው በዓለም የ800 ሜትር ሻምፒዮኑ መሐመድ አማን ሲሆን የገባበት ጊዜ 1፡43.56 የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡ የቅርብ ተቀናቃኙ ቦትስዋናዊ ኒጄል አሞሰን አስከትሎ ገብቷል፡፡