Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የፌስቡክ የፖለቲካ ጭቅጭቅና ቅጥ ያጣ ስድድብ ሲሰለቸኝ በጨዋታ እያዋዙ ቁም ነገር የሚያመጡ ሰዎች ይናፍቁኛል፡፡ አንድ ጊዜ በዘርና በሃይማኖት የሚጨቃጨቁ ሰዎች በጣም ስላሰለቹኝ ከፌስቡክ ዓለም ራሴን አግልዬ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ምርጥ ቀልዶች የሚነበቡበትን አንድ የውጭ ዌብ ሳይት መከታተል ስጀምር፣ ትኩሳቴ ሲቀንስና የሚጫጫነኝ ነገር ጥሎኝ ሲጠፋ ይታወቀኝ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይኼ የፖለቲካችን ጉዳይ ወፈፍ እያደረገኝ የፌስቡክ ገጼን እያጨነቆርኩ በአለፍ ገደም ባየውም፣ ምሬቱ ያንገሸግሽ ነበር፡፡

አንድ ጊዜ አንዱ ወፈፌ ‹‹በጂሌ እናርዳቸዋለን…›› የሚል ዓይነት አስተያየት ሰንዝሮ የሐበሻ ልጆችን ከዳር እስከ ዳር ቀፎው እንደተነካበት ንብ ሲያነሳሳ፣ የነበረው ደም ፍላትና በብልግና የታጀበው ፉከራ አይረሳኝም፡፡ በአንድ ወቅት የዳያስፖራው (በተለይ የአክራሪው) ጌጥ ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ‹‹ባለ ጂሌ›› ውግዝ ከመአርዮስ ሲባል እንኳን ፌስቡክ መጠቀም፣ ፌስቡክ የፈጠረውን ሰውዬ የተራገሙ ጓደኞቼን አልረሳቸውም፡፡ ብቻ ማኅበራዊ ሚዲያው በወጉ ባለመያዙ ምክንያት እየደረሰ ያለው ቀውስ ግን አስፈሪ ነው፡፡ ቁም ነገርንና ቀልድን ማዋዛት የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡

በቀደም ዕለት አንዱ የፌስቡክ ታዋቂ ተሳታፊ አንድ ደስ የሚል ቀልድ ጣል አደረገ፡፡ ሚስት ለባሏ፣ ‹‹ይኼ በራችን ላይ ያለው የኔ ቢጤ በጣም ያስጠላኛል፤›› ትለዋለች፡፡ ባል ደግሞ፣ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ሚስት፣ ‹‹ትናንት የሚበላ ምግብ ስሰጠው እሱ ደግሞ ዛሬ የምግብ አሠራር ማስተማሪያ ዘዴ የሚል መጽሐፍ ሰጠኝ፤›› ትለዋለች፡፡ ይህቺን ቀልድ ያካፈለን ፌስቡከኛ፣ ‹‹ለእኛ የማይታየንን ጉድለታችንን፣ ስህተታችንና ደካማ ጎናችን የሚነግረንን ሰው እንውደድ የእኔ ምርጦች!›› በማለት ቁም ነገሩን በዋዛ አቀረበው፡፡ በበኩሌ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ የመሰላቸውን ሰነዘሩ፡፡ ‹‹ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር›› እንዲሉ ፈረንሣዮች የተለያዩ አስተያየቶች ተነበቡ፡፡

- Advertisement -

ይህ በአካል የማላውቀው የፌስቡክ ተሳታፊ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያነሳቸው ሐሳቦች ይገርሙኛል፡፡ እሱ የቆመለትን የፖለቲካ ዓላማ ባልደግፍም፣ የመሰለውን በመወርወሩና መነጋሪያ ሐሳቦችን በማቅረቡ ሁሌም በልቤ ክፉ አይንካህ እላለሁ፡፡ ሳስበው በጣም ቅን ሰው ይመስለኛል፡፡ ያዝልቅለት፡፡ ለእኛ የማይታየንን ጉድለት ከሚነግሩን ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እንድንመረምር ስለጋበዘንም ደግሜ አመሠግነዋለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ያጋጠሙኝን ጉዳዮችም እንዳነሳቸው አድርጎኛል፡፡

በ1996 ዓ.ም. አምባሳደር ቴአትር በራፍ አጠገብ ከአንድ የድሮ ወዳጄ ጋር እገናኛለሁ፡፡ ለዓመታት ተያይተን ስለማንተዋወቅ ሐራምቤ ሆቴል ቢራ እየጠጣን ላዋራው ስለፈከግኩ ይዤው ሄድኩ፡፡ መቀመጫችንን ይዘን ቢራ ካዘዝን በኋላ ጨዋታ ጀመርን፡፡ ቢራዎች እየተጠጡ ጨዋታው እየደራ ሲሄድ፣ ወዳጄ የኢሕአዴግ አባል ወይም ቅልጥ ያለ ደጋፊ መሆኑን አወቅኩ፡፡ በበኩሌ ማንም የማንም ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ ቢሆን ግድ የለኝም፡፡ ማንም ከየትኛው ብሔር ወይም ዘር ቢመጣ ለእኔ  ሰው ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡ፣ ከእንስሳ የማይሻሉ የሰው ዘር ከሚያንቋሽሹና ሰብዓዊነትን ከሚያራክሱ ሰው ተብዬዎች በጣም የተሻልኩ ነኝ፡፡ አንዳንድ ወዳጆቼ ‹‹ኢንተርናሲዮናልን የዘመርክ ኮሙዩኒስት›› ይሉኛል፡፡ የወዳጄ ኢሕአዴግነት አልደነቀኝም፡፡ የደነቀኝ ግን በጣም ታታሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪ ፕሮቴስታንት የነበረ ሰው እንዴት ፖለቲካ ውስጥ ገባ የሚለው ነው፡፡ ለጊዜው ቢደንቀኝም በኋላ ግን ተውኩት፡፡ ሰው ሆኖ የማይለወጥ ማን አለ?

ወዳጄ የኢሕአዴግን ቅዱስነትና ለዚህች አገር የተላከ ‹መሲህ› መሆኑን ሲያብራራልኝ የበፊቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪነት በጣም የረዳው ይመስል ነበር፡፡ እኔ ግን ኢሕአዴግ በጣም ጠግቦ ሕዝብን በመርሳት አገሪቱን እያደኸያትና የተከፋፈለ ኅብረተሰብ እየፈጠረ መሆኑን ተከራከርኩ፡፡ የጊዜ ጉዳይ መሆኑን እንጂ ኢሕአዴግ አገር ለማልማት እየተዘጋጀ መሆኑን፣ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ታሪክ እንደሚታይ ነገረኝ፡፡ በጣም አሳቀኝ፡፡ የሚቀጥለው ምርጫማ በነፃነት ከተካሄደ ኢሕአዴግ ያልቅለታል አልኩት፡፡ የሕዝቡ ምሬት ጫፍ ላይ መድረሱን አስረዳሁት፡፡ አልተግባባንም፡፡ እሱ ግን እንዲህ አለ፡፡ ‹‹ወንድሜ እስቲ ውሳኔውን ለሕዝቡ እንተውና ከውጤቱ በኋላ እንነጋገር…›› ብሎኝ ተለያየን፡፡ ልክ ነበር፡፡ በምርጫ 97 የሆነውን ስለምናውቅ እዚህ መዘርዘሩ አይጠቅምም፡፡ አንድ ነገር ግን መረሳት የሌለበት የውሳኔ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በድምፁ ጉድለቶችንና ችግሮችን ሲያስተጋባ መኖሩ ግን አይረሳም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ሕዝቡን ማን ሰማው? ደካማ ጎናችን ሲነገረን የሚያሳብደን ስንት ነን? ኢሕአዴግን ጨምሮ ማለት ነው፡፡

ሌላው በቅርቡ የገጠመኝ ነው፡፡ ፒያሳ መሀል መኪናዬን አቁሜ በእግሬ ስንቀሳቀስ ለምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየተራ እየቀሰቀሱ ይጓዛሉ፡፡ የኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ ፓርቲና የኢዴፓ ቀስቃሾችን ነበር ያየሁት፡፡ አንዱ ጥግ ላይ ሆኜ ሁለት ሰዎች ሲያወሩ እሰማለሁ፡፡ አንደኛው፣ ‹‹እኔ እኮ ምርጫ የሚባለው ነገር በሃያ ዓመት አንዴ ቢደረግ ነው የሚሻለው ነው የምለው…›› ሲል፣ ሌላው፣ ‹‹ምን ነካህ? ሃያ ዓመት የምትለው ማን ደስ እንዲለው ነው? ቢከፋም ቢለማም በየአምስት ዓመቱ እየመረጡ በመለማመድ አምባገነንነትን በሒደት ከአገራችን ማስወጣት አይሻልም? …›› ይለዋል፡፡ በዚህ መሀል አንዱ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል፣ ‹‹የእዚህ አገር ፖለቲካ ፓርቲዎች ከስህተታቸው አይማሩም፡፡ ገዥው ፓርቲ አገሪቱን ሰንጎ ይዞ ምረጡኝ ይላል፡፡ ተቃዋሚዎቹ አቅማቸውን ሳያውቁ እየገቡ ድራሻቸው ይጠፋል፡፡ ሁሉም ዕውነቱ ሲነገራቸው አይገባቸውም፡፡ ሁሉም እንደገና ተጠፍጥፈው ካልተሠሩ ዴሞክራሲ ብሎ ነገር የለም፤›› ብሎ መንገዱን ሲቀጥል እኔም ወደ መኪናዬ ተመለስኩ፡፡ ወፈፍ ያደረገው ሰውዬ ሰሚ ቢያገኝ ጥሩ አልነበር?

እናም ወዳጆቼ ድክመታችንና ጉድለታችን ሲነገረን በአክብሮት መቀበል ብንለምድስ? በጥላቻና በመረሩ ቃላት ለሕዝቡ ባይተዋር የሆኑ ረቂቅ ነገሮችን ይዘን ከመተጋተግ ይልቅ በቀልድ እያዋዛን ስንነጋገር መልዕክቶቻችን ለጊዜው ባይሰሙም፣ በሒደት ግን መልካም ዘር ይዘራሉ፡፡ አልሰማ ብሎ ያስቸገረን፣ በቀልድና በቁም ነገር እያዋዛን ብንመክረው ከረር ካለው አቀራረባችን በተሻለ ይሰማናል፡፡ ሥልጣኑ ላይ ጉብ ያለውን ኃይል ‹‹ቆይ ነገ›› እያልን ራሳችንን ለበቀል ስናመቻችበት ሰንሰለቱን የበለጠ ያጠብቀዋል፡፡ ከወዳጅነት ይልቅ ጠላትነትን ስናበረታታ እንኳንስ ሰው ገራም እንስሳም ቢሆን ዘሎ ጉብ ይልብናል፡፡ ከላይ መነሻችን በነበረው ቀልድ መሠረት የኔ ቢጤው ሴትዮዋ የሰጠችውን ምግብ ከበላ በኋላ፣ በነጋታው የምግብ አሠራር  ማስተማሪያ ዘዴ መጽሐፍ ይዞ የመጣው የበላው ስላልጣፈጠው፣ ወይም የበለጠ ብትሠራ በሚል ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችንም ለኃይል የቀረበ ጽንፈኝነት ውስጥ ገብተው ከሚፋጠጡ ይልቅ ዘዴኛ ቢሆኑ አይመረጥም ትላላችሁ? እኔ የገባኝ እንዲህ ነው፡፡ እናንተም ጨምሩበት፡፡

(ዘውዱ መካሻ፣ ከአዲሱ ገበያ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...