Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርበሃና ላላንጎ ገዳዮች ቅጣት አዝኛለሁ

በሃና ላላንጎ ገዳዮች ቅጣት አዝኛለሁ

ቀን:

ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸገር ኤፍኤም 102.1 ሬዲዮ ጣቢያ ከቀትር በኋላ በተላለፈው የእንዳልክና ማኅደር ፕሮግራም፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለአቅመ አዳም ባልደረሰች የ16 ዓመት ታዳጊ ሕፃን ሃና ላላንጎ ደፋሪዎች ላይ የእስር ብይን መስጠቱን ሰማሁ፡፡ ታዲያስ አዲስ በተባለው ፕሮግራም ደግሞ ሰይፉ ፋንታሁን  የፍርድ ቤቱን ውሎ ዜና ዘግቦ፣ በፍርድ አሰጣጡ ሒደት ላይ ወላጅ አባቷን ምን ተሰማዎት? ሲል የሃናን አባት ቃለ ምልልስ አስደመጠ፡፡

 ወላጅ አባቷም የፍርድ ብያኔው እጅግ በጣም እንዳሳዘናቸውና ከእንግዲህ ከአምላክ እንጂ ከማንም እውነተኛ ፍርድ አገኛለሁ ብዬ አልጠብቅም ሲሉ በእንባ ሲቃ ነበር የገለጹት፡፡ እንዴትና በምን ምክንያት ብሎ ሲጠይቃቸውም፣ ‹‹እነዚህ የሰው አውሬዎች (አውሬ እንኳ ይራራል) እጅግ ዘግናኝ፣ እርኩስና ሰይጣናዊና ግፍ በእንቦቅቅላ ልጄ ላይ ፈጽመውና እንድትሞት ፈርደውባት እነሱ ግን በሕይወት ኖረውና ቁጭ ብለው በወህኒ ቤት እንዲቀለቡ፣ ነገ ተቀልበው ሲወጡ በእኔ ልጅ ላይ የፈጸሙትን ዓይነት ሰቅጣጭ ሰቆቃና ከልብ የማይጠፋ ሐዘን በሌላው ወገኔ ላይ እንዲያደርሱ ከፈቀዱ (ከወሰኑ) ዳኞች ምንም ዓይነት ፍትሕና ይግባኝ አልጠብቅም፡፡ አልጠይቅም፡፡ ፍርዱን የምጠብቀው ከአንድ አምላክ ብቻ ነው፤›› ነበር ያሉት፡፡

እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባው ታላቅ ቁም ነገር፣ ወላጅ አባት ከፍርድ አሰጣጡ ኢፍትሐዊ ውሳኔ ባሻገር ፍትሕ አገኛለሁ ብለው በየጊዜው እየተመላለሱ የፍርድ ቤት ደጃፍ መጥናታቸው፣ በቤተሰባቸው ላይ የደረሰው ስቃይና ሰቆቃ፣ አሟሟቷ ስቃይ የተሞላበትና ከኅሊና የማይጠፋ በመሆኑ (ከአሟሟትም እኮ ጣዕም ያለው አሟሟት አለው) በቤተሰቡ ላይ የደረሰው የሞራል ውድቀትና ተስፋ መቁረጥ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ በመጨረሻው ሰዓት እንኳ ተኩላዎቹ የጭካኔና የስቃይ መርግ ሁሉ በታዳጊዋ አካልና አዕምሮ ላይ አድርሰው ከተበጣጠሰ ቆሻሻ ፌስታል ባነሰ ሁኔታ፣ ክቡር የሆነውን ሰው ያውም ታዳጊ ሕፃን ጎዳና ላይ ሲጥሉ፣ ምናልባት በጣም ምናልባት መዳን እንኳ ብትችል በቂ የሕክምና ዕርዳታ ባለማግኘቷ መሞቷ እንደ አንድ ወላጅ አባት ሲታሰብ፣ የሃና አሟሟት ለቤተሰቧ ድርብ ሞት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

እኔም የሴት ልጆች ወላጅ አባት በመሆኔ፣ የቤተሰባቸው ስቃይ ስቃዬ፣ ሕመማቸው ሕመሜ ከመሆኑ ባሻገር እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ አንዴ በዚህ ሌላ ጊዜ በዚያ ሠፈር መንደርና ክልል የምንሰማው ዘግናኝ ሰቆቃ ወዴት እየሄድን ነው? ያስብላል፡፡ እውነት የዜጎቹን ሰላምና ደኅንነት የሚጠብቅ መንግሥት አለን? እስከ መቼስ ነው ሴት ሕፃናት ልጆቻችን በሰላም ወጥተው መግባታቸው የሚያሳስበን? ብዬ ለመጠየቅ እገደዳለሁ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አውሬዎቹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የተቀጡና ከእነዚሁ አንዱ በአስገድዶ መድፈር ተከሶ የተቀጣ መሆኑ እየታወቀ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ በተኩላነቱ እንዲቀጥል መፍቀዱ የሕግን አስተማሪነት በምንም መልኩ ገላጭ አንይሆንም፡፡ የሕግ አስተማሪነት እዚህ ጋ እንዲገለጽ ከተፈለገ እንደ አንድ ወላጅ የገዳዮቹ ቅጣት አንሷል ባይ ነኝ፡፡

ለመሆኑ እነዚያን አንድ ሰሞን ያዙን ልቀቁን እያሉ በትላልቅ ሆቴሎች ሞቅ ባለ አበል ተቀምጠው መግለጫ በመግለጫ የሚያንደቀድቁት የሴት ሕፃናት መብት ተሟጋቾችና የግል ጋዜጠኞች ያ ሁሉ የአንድ ሰሞን ቡራ ከረዩ፣ የሚዲያ ጩኸትና ጡሩንባ ዛሬ በተሰጠው የፍርድ ውሳኔ ላይ ምን እያሉ ይሆን? ወይስ ወደፊት በሚፈጠረው አዲስ ክስተት ላይ ያው የተለመደውን ስብሰባ፣ መግለጫና መለከት ያሰሙና ይነፉ ይሆን? በሃና ላላንጎ ላይ የደረሰው ዘግናኝ ስቃይና ሞት በአገሪቱ ትልልቅ ባለሥልጣናት ሕፃናት ልጆች ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ዕውን ፍትሕ ምን መልክ ይኖራት ነበር?

(አማቾ ማሆጋኖ፣ ከናዝሬት)

*********

መንግሥት ለአገሪቱ የስደት መንስዔዎች ምላሽ ይስጥ

ዜጋ መከበር አለበት፡፡ በአገሩ መሥራት አለበት፡፡ ለዚህ የሚረዳ የተመቻቸ ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ሁሉ በአገር ውስጥ ተሟልቶለት ስደት ይሻለኛል የሚል ካለ፣ የግለሰቡ ምርጫ ይሆናል። አሁን ላይ ግን የሰውዬው ምርጫ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከዩኒቨርሲቲና ከኮሌጅ ተመርቆ ሥራ የለም፤ ሥራ እንኳ ቢፈጥር ገንዘብ የሚያገኝበት መንገድ በጣም አሰልቺ በመሆኑ፣ ወደ ስደት የሚያስኬድ ነው።

 ስለዚህ መንግሥት ይህንን ማስተካከል አለበት፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ትላልቅ ፋብሪካ በመገንባት የተወሰነ የተማረ የሰው ኃይል እንኳ ተቀጥሮ የሚሠራበትን መንገድ ጣልቃ ገብቶ ለመሥራት፣ እንደ ለስኳርና ለዘይቱ እንደሚያደርገው ሁሉ ለዜጋውም መጨነቅ አለበት። መንግሥት በአንድ ወገን በየትምህርት ተቋሙ እያስገባ ያስተምራል፡፡ በሌላ  ወገን ግን ከትምህርት በኋላ ሥራ መያዝ ያስፈልጋቸዋል? ብሎ ተገቢውን ክትትል አያደርግም።

ስለዚህ መንግሥትና ሕዝብ ወደ ስደት የሚሄዱ ሰዎች ላይ ሲያወጡ የነበረው ወጪ ሁሉ ኪሳራ ነበር ማለት ነው። እኔ በጣም አዝኛለሁ፡፡ በተለይ ዳንኤል ሐዱሽ የሚባለው ጓደኛዬ በጨካኞቹ የአይኤስአይኤስ አሸባሪዎች ሲታረድ ካየሁ በኋላ ደም አልቅሻለሁ። ምክንያቱም ጓደኛዬ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ሥራ ማጣቱን ይነግረኝ ስለነበረ ነው። መማሩ የቱ ላይ ነው ጥቅሙ? ለክብሩም ይታሰብበት። ይህን ማለት መንግሥትን መቃወም ማለት አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ደጋፊ ነኝ፡፡ ነገር ግን በጣም ክፍተት መኖሩን ለማስገንዘብ ስል ነው ይህንን የምገልጸው። አሁንም መንግሥት አፋጣኝ መልስ መስጠት የሚሻው ጉዳይ ስለሆነም ነው።

(አብርሽ ገብረሊባኖስ፣ ከአዲስ አበባ)

**********

ኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲዋን ታሻሽል

      ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ ቢሆንም ማንኛውም ሰው ለአፍ መፍቻ ቋንቋው የተለየ ባህላዊ ትስስርና ፍቅር ይኖረዋል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ስለሆነ መካድ አይቻልም፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው የአገራችን የቋንቋ ፖሊሲም ሁሉም ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንዲያገኙ፣ ክልሎችም የየራሳቸው የሥራ ቋንቋ እንዲኖራቸውና በፌዴራል ደረጃ አማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ይደነግጋል፡፡ ይህ ፖሊሲያችን ምን ምን ችግሮች አሉት? ለምንስ ይተቻል? የሌሎች አገሮች የቋንቋ ፖሊሲስ ምን ይመስላል? የእኛስ እንዴት ሊሻሻል ይችላል? የሚሉ ጉዳዮችን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ በመሠረቱ የትኛውም ቋንቋ ከመግባቢያነቱ አልፎ ከማኅበረሰቡ ጋር ባህላዊ ቁርኝት እስካለው ድረስ፣ አንዱ ከሌላኛው የሚበልጥበት ወይም የሚያንስበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን አንዱ ቋንቋ ከሌላው ተለይቶ ለመንግሥታዊና ለማኅበራዊ ግልጋሎቶች እንዲውል ከሚያስችሉ መሥፈርቶች ውስጥ የቋንቋው ተናገሪዎች ብዛት፣ ለጽሑፍ የሚያገለግል ፊደል ስለመኖሩ፣ ቋንቋው ለማኅበራዊ ግልጋሎቶች ማለትም ለመማሪያ፣ ለሃይማኖታዊ ክንዋኔዎችና ለፍርድ ቤቶች አገልግሎትና ለሌሎች መንግሥታዊ ሥራዎች መዋሉና አለመዋሉ አንዱን ቋንቋ ከሌላው ተመራጭ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከ81 የማያንሱ አገር በቀል ቋንቋዎች አሏት፡፡ ይህ ትልቅ ስጦታና እሴት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአንፃሩ እንግሊዝኛ፣ ዓረብኛ፣ ቻይንኛ፣ ፈረንሳይኛና ሌሎች የውጭ ቋንቋዎችም የከተሜውን ማኅበረሰብ በፍጥነት እየወረሩና ቀልባቸውን እያማለሉ ይገኛሉ፡፡

የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲ ዳሰሳ

      የአንድ ቋንቋ ተናገሪ ሕዝቦች አንድን አገር ከመሠረቱ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋቸው የብሔሩ ወይም የሕዝቡ ቋንቋ ይሆንና ከተለያዩ አገሮች ጋር የሚግባቡበት አንድ ወይም ከዚያም በላይ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ጨምረው ይጠቀማሉ፡፡ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሕዝቦች አንድን የጋራ አገር በጋራ ከመሠረቱ ደግሞ ሁለት ዓይነት የቋንቋ ፖሊሲን ሊከተሉ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ሥልጣንን የተቆጣጠረውና መንግሥት መመሥረት የቻለ አካል የፈለገውን ቋንቋ ለሥራ እንዲውልና ሌሎች ቋንቋዎች በሒደት እንዲጠፉ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ አውሮፓውያን አፍሪካን በወረሩ ጊዜ ሁሉም ወራሪዎች የየራሳቸውን ቋንቋ በወረሩት ሕዝቦች ላይ በግድ ጭነውባቸዋል፡፡ ሌሎች አገር በቀል አምባገነን መንግሥታትም ተመሳሳይ ድርጊት በአገር በቀል ቋንቋዎች ላይ ፈጽመዋል፡፡ የሁሉንም ቋንቋዎች እኩልነት በመቀበል በግልጽ መሥፈርት አንድ ወይም ሁለት ወይም ብዙ ቋንቋዎች ለብሔራዊ ጥቅም እንዲውሉ ማድረግና ሌሎች ለብሔራዊ ግልጋሎት ያልተመረጡ ቋንቋዎች ደግሞ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በሕግ ሊደነግጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ናይጄሪያ አራት ብሔራዊ የሥራ ቋንቋዎች አላት፡፡ ጂቡቲ አራት ብሔራዊ ቋንቋዎች አላት፡፡ ኬንያ ሁለት ብሔራዊና ብዙ ክልላዊ ቋንቋዎች አላት፡፡ ኤርትራ ሦስት ብሔራዊ የሥራ ቋንቋዎች አላት፡፡ ትናንት የተፈጠረች ደቡብ ሱዳን እንኳ ሁለት ብሔራዊ ቋንቋዎችን አጽድቃለች፡፡ የኔልሴን ማንዴላዋ ደቡብ አፍሪካ 11 ቋንቋዎችን ለብሔራዊ ግልጋሎት እንዲውሉ አድርጋለች፡፡

      በኢትዮጵያ ከ130 ዓመታት በፊት ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ መንግሥት ሥር ከመሰብሰባቸው በፊት የየራሳቸውን ቋንቋ ይጠቀሙ እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከአጤ ምኒልክ በኋላ ግን ነገሮች ሁሉ ተቀየሩ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴና ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም አማርኛን የሥራና ብሔራዊ ቋንቋ አደረጉ፡፡ ከደርግ መንግሥት በኋላ ሥልጣን የተቆናጠጠው ኢሕአዴግ፣ በቋንቋ ፖሊሲ በኩል ችግሮች እንዳሉብን አምኖ ቢቀበልም፣ አግባብነት ያለው ዘላቂ የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጧል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ጊዜያዊ የማስታገሻ መርፌ ሰጥቶን ነው የለቀቀን፡፡ የተሟላና ዘላቂ የቋንቋ ፖሊሲ አላስቀመጠልንም፡፡ ክልሎች የሚመቻቸውን የሥራና የትምህርት ቋንቋ መርጠው ተግባራዊ እንዲያደርጉ መደረጉ አንድ በጎ ጅምር ቢሆንም፣ በፌዴራልና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ግን ያው የቀድሞው የአንድ ቋንቋ አዋጅ ተግባራዊ ማድረጉንና ማስፈጸሙን ቀጥሎበታል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ከዓለም ብቸኛዋ የአንድ ቋንቋ ፖሊሲ አራማጅና በተቃራኒው የብዙ ቋንቋዎች ባለቤት አገር ያደርጋታል፡፡ ለነገሩ የመረጡልንን አንዱን የአማርኛ ቋንቋስ ሁላችንም በሥርዓቱ እንድንማር መች አደረጉና?

      በክልሎች ደረጃ በተለይም በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በሶማሌ፣ በአፋርና በሌሎች ክልሎች የሚሰጠው ትምህርት የክልሉን ቋንቋ ብቻ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ፣ በእነዚህ ክልሎች እየተቀረፁ ያሉ ወጣቶች የአንዱ ክልል ወጣቶች ከሌላው ክልል ጋር እርስ በርስ የሚግባቡበት ቋንቋ እየጠፋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛም በብዙ ምክንያቶች በእነዚህ ክልሎች በቂ ትኩረት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ለሌሎች ቋንቋዎች ዕውቅና ሰጥቶ ወደ ራሱ ማሳደግ ባለመፈለጉ፣ ክልልች በአማርኛ ቋንቋ ላይ የበቀል ዕርምጃ እየወሰዱ ያሉ ይመስላል፡፡ እንግሊዝኛውም ቢሆን አሁን ባለው የትምህርት አሰጣጥ ፖሊሲያችን የምንቀጥል ከሆነ፣ በዚህ ቋንቋም መግባባት የሚችል ትውልድ እየተፈጠረ ነው ማለት ይከብደል፡፡ እንግዲህ በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልጆቻችን የሚግባቡበት ቋንቋ እየጠፋ መሆኑ ትልቁ ችግራችን ነው፡፡ የማይግባባ ትውልድስ መጨረሻው ምን ይሆን? የማይግባባ ትውልድ እንዴትስ አንድ የጋራ አገር መገንባት ይችላል? በማኅበረሰብ ደረጃስ ማን ነው የአንዱን ቋንቋ እንደ ጠቃሚ እሴትና ሀብት ቆጥሮ ለመማር ጥረት እያደረገ ያለው?

የቋንቋ ፖሊሲያችን ምን ቢሆን ይሻላል?

      ኢትዮጵያ የቋንቋዎች ሀብታም አገር በመሆኗ ለሁሉም ቋንቋዎች እኩል ዕውቅና የሚሰጥ ሕግና ፖሊሲ ያስፈልጋታል፡፡ ለፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የሚያገለግል ቋንቋ ወይም ቋንቋዎች ምናልባትም ከጊዜ በኋላ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚግባቡበት ቋንቋዎችና ከሌሎች አገሮች ጋር የምንግባባበት ዓለም አቀፍዊ ቋንቋም ያስፈልገናል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የቋንቋ መሥፈርቶችና ሌሎች ተጨማሪ ሁኔታዎችን በማጤንና ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የአገራችን የቋንቋ ፖሊሲ በአንደኛ አማራጭ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞና እንግሊዝኛ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሆነው እንዲያገለግሉ ቢደረግና ክልሎች ደግሞ ከሦስቱ የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች ሁለቱንና የየራሳቸውን ክልላዊ የሥራ ቋንቋ በመጨመር ተግባራዊ የሚያደርጉበት ፖሊሲ ቢወጣ፣ በቋንቋ በኩል ያሉትን ችግሮቻችንን በዘላቂነት የሚፈታ ይሆናል፡፡ ምክንያት አማርኛ 29.33 በመቶ የአፍ መፍቻ ተናጋሪዎችና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችም ተናጋሪዎች ስላሉት አንዱ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ቢሆን የሚያግባባ ነገር ነው፡፡ አፋን ኦሮሞ ደግሞ 33.8 በመቶ የአፍ መፍቻ ተናጋሪዎችና ከሌሎች የተወሰኑ ብሔር ብሔረሰቦች ማለትም በኮንሶ፣ ሺናሻ፣ ሶማሌ፣ ሲዳማና ከአገር ውጭም በቦረና በኩል የሚኖሩ የኬንያ ዜጎች ቋንቋውን የሚናገሩ ሕዝቦች ስላሉ፣ አንዱ የፌዴራል ቋንቋ መሆን ይኖርበታል፤ ተገቢም ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ ቋንቋዎችም እንግሊዝኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ቢደረግ የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርገንና የሚያግባባን በመሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ ክልሎችም ከሌሎች አገር በቀል ቋንቋዎች በተጨማሪ በቋንቋ ፖሊሲያቸው ውስጥ እንግሊዝኛን እንደ አንድ የሥራ ቋንቋ ተግባራዊ ቢያደርጉ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡ ሌሎች ቋንቋዎች ከ10 በመቶ በታች ተናጋሪዎች ብቻ ስላሏቸው በፌዴራል ደረጃ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በሕግ ቢደነገግና ሁሉም ብሔረሰብ የየራሱን ቋንቋ በሚኖርበት ክልል፣ ዞን ወይም ወረዳ የሥራ ቋንቋው አድርጎ የማሳደግና የመጠቀም መብቶቹ የበለጠ ተጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም ነው፡፡

      በሁለተኛ አማራጭ እንግሊዝኛ ብቻ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ማድረግና ክልሎች ደግሞ በእንግሊዝኛው ላይ የየራሳቸውን ቋንቋ በመጨመር ለሥራና ለትምህርት የሚገለገሉበት ሕግ ቢደነገግ፣ በአንድ በኩል አንዱ የሌላውን ሊያጠፋ ይችላል የሚል ሥጋቶችና ውጥረቶች ይረግባሉ፡፡ በሌላ በኩል በፌዴራል ደረጃም ሆነ በየትኛውም ቦታ እንግሊዝኛ ሊያግባባን ይችላል፡፡ እንግሊዝኛ መለማመዱ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ እንድንሆን ስለሚያደርገን እንደ አማራጭ መወሰዱ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአገር ውስጥም ቢሆን ለሁሉም የብሔር ብሔረሰቦች እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ እንግዲህ ሁሉም ዜጋ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ይህ ተግባር በዋናነት የመንግሥት ሥራ ቢሆንም እኛም እንደ ማኅበረሰብ፣ እንደ ዜጋ አንድነታችንን ሊጠግኑ የሚችሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማመንጫት መቻል አለብን፡፡ ሌሎች ቋንቋዎችን ትቶ አማርኛን ብቻ የአገሪቱ ቋንቋ ለማድረግ የተደረገው ሙከራ ከፍተኛ ኪሳራ ከማስከተሉ ውጭ ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለም አይተናል፡፡ ለዘመናት በመካከላችን ቅራኔና አለመተማመን እንዲፈጠርም ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁን ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ኢፍትሐዊ የሆነውን የቋንቋ ፖሊሲያችን እናስቀጥላለን እያልን ተበታትነን የዓለም መሳቂያ እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡

(ገዳ ገነሞ፣ ከፊንፊኔ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...