Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር

ቀን:

ከምርጫው ማግሥት ጀምሮ ሕዝብ የሚፈልገው አለ

በያሲን ባህሩ

ጤና ይስጥልን ክቡርነትዎ! እንዴት ከረሙ? ዘንድሮ በተለይ ያለፉት ወራት እርስዎና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሥራ በዝቶባችሁ የቆያችሁ ይመስለኛል፡፡ ምርጫ 2007 ሲቀርብ አገር እንደሚመራ አካል የምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ አስታፊና ሰላማዊ መሆን ያስጨንቃል፡፡ እንደ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ በየትም ብሎ በየት አብላጫ ድምፅ ማግኘትና ሥልጣን መጨበጥን የሚጠላ የለም፡፡ ከሁሉ በላይ ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታና ለታሪክ እውነተኛ ሆኖ መገኘት የህሊና ፈተና ነው፡፡

ለዚህም ነው በየቦታው የመሠረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ፣ ያለቀ ፕሮጀክት ሲመርቁ (የባቡር ሐዲድ ሲነጠፍ ፕሮጀክት ተጠቃለለ እየተባለ ሒደቱን ጭምር መናገር ቅር ቢያሰኝም) ታይተዋል፡፡ በፓርቲም ሆነ በመንግሥት መድረክ የተለያዩ ስብሰባዎችንና ጉባዔዎችን ሲመሩም ነበር፡፡ ይሁንና ሕዝቡ ምን አለ? ምን ይፈልጋል? ኢሕአዴግና መንግሥት ከሠራ ነው ውጤታማ ክንውን በላይ የጎደለን ምንድው? ብለው ጠበቅ ያለ ጥያቄ ስለማንሳትዎ አልሰማሁም፡፡ ምናልባት በምርጫው ማግሥት ካቢኔዎን ሰብስበው ወይም በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ መክረውበት ሊሆን ይችላል፡፡

በእኔ በኩል እንደ አገር ተቆርቋሪ ዜጋ ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ ብዙዎቹን መልካም ጅምሮቹን በማድነቅ ለፓርቲው ድምፁን እንደሰጠ ሰው ሕዝብ ሊደመጥበት የሚገባው ጊዜ አሁን ይመስለኛል፡፡ ሥራዬ ንግድ በመሆኑ በባህሪው ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ባለጉዳዮች ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡ በመዝናኛዎችና በተለያዩ የከተማው አደባባዮች የመገናኘቴን ያህልም በሕዝቡ ውስጥ የሚነገሩና የሚብላሉ ጉዳዮችን በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ ለዚህም ነው በቀጥታ በእርስዎ አድራሻ ደብዳቤ ጽፌ አገር ወዳዶች ሁሉ እንዲመለከቱትና እንዲያጤኑት የፈለግኩት፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

በቅድሚያ በአምስተኛው ምርጫ በማሸነፋችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት ነበረብኝ፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ምርጫው ተጭበርብሯል? ዘንድሮም የኮሮጆ ስርቆት ተፈጽሟል? ከአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎቻችን ተዛቢዎቻችን ተባረዋል፣ በአንዳንድ አካባቢ ድብደባና እንግልት ነበረ፣ በሕዝቡ ላይ ተፅዕኖ ተፈጥሮበት ነበር…የሚሉ ክሶችንና ወቀሳዎችን ለጊዜው እንተወውና ኢሕአዴግ እንዴት አብላጫ ድምፅ አገኘ መባል አለበት፡፡

በእኔ ዕይታ በዘንድሮው ምርጫ ኢሕአዴግ ያሸነፈባቸው ምክንያቶችን በሦስት ጎራዎች ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ አንደኛው ኢሕአዴግ መንግሥት ሆኖ አገሪቱን በመራባቸው 24 ዓመታት ውስጥ ከተከናወነው ልማት፣ ሰላምም ሆነ ዴሞክራሲ (ከነችግሩ) ተጠቃሚ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ የሚገቡት የአንድ ወጣት ዕድሜ ያህል መንግሥት በሆነው የኢሕአዴግ ዘመን ውስጥ የልጅነት፣ የወጣትነትም ሆነ የጉልምስና ጊዜያቸውን አሳልፈዋል፡፡ ሥርዓቱን ካለፉት አገዛዞች ጋር በማነፃፀር ከጎደሉት ይልቅ የሠራቸውን በጎ ተግባሮች ዋጋ በመስጠት ድምፃቸውን እንደሚሰጡት መገመት ይቻላል፡፡

ሁለተኛው ለኢሕአዴግ ድምፁን የሰጠው ወገን መነሻው ፍርኃትና ሥጋት ነው፡፡ ‹‹ይቺን በብዝኃነት የምትታወቅ፣ የበርካታ ፍላጎቶች ቅርጫት የሆነች አገር እንዴት ያልተጠናከሩና ለጋ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ይመሯታል?›› የሚሉ በርካታ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ ከዚህ ፍርኃት በመነሳት ‹‹ከማላውቀው መልዓክ የማውቀው ሰይጣን››ን እየተረተ ሲቆዝም የነበረው ቁጥሩ ትንሽ አይመስለኝም፡፡

እዚህ ላይ አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን ቁም ነገር ቃል በቃል መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ወጣቱ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን የሚሸከም ባህሪ እንዳሌለው አረጋግጫለሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢሕአዴግን እንዳይደግፍ ያደረጉት ክስተቶች እየበዙ እንደመጡ ይናገራል፡፡ ‹‹በነፃ እንደራጅ፣ በሕጋዊ መንገድ መብታችን ይከበር ያሉ ሰዎች ይታሠራሉ፡፡ ሕግ ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነትና ዋነኛ ተግባር ቢሆንም፣ ሐሳብን የመግለጽና የመዘዋወር መብትም ተፅዕኖ ውስጥ እየወደቁ ነው….›› በማለት ማሳያዎቹን ሲዘረዝር ከርሟል፡፡ ከሁሉ በላይ በታችኛው የመንግሥት እርከን ላይ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነትና እየተለመደ የመጣ ሙስና ያስቆጨዋል፡፡ በዚህም ኢሕአዴግን መምረጥ የለብኝም ብሎ ከተዘጋጀ ሳምንታት አልፈዋል፡፡

የምርጫው ዕለት እሱና ፈጣሪ ብቻ ሆነው በቆሙበት የድምፅ መስጫ ሳጥን ውስጥ በአዕምሮው የመጣው ነገር ግን ሌላ ሆነ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግን ባልመርጠውም፣ የማልተማመንበትን የፖለቲካ ፓርቲ መርጬ በአገሬ ላይ ሌላ ዱብ ዕዳ ከሚመጣ ካርዱን ላበላሸው›› የሚል፡፡ በመሆኑም በሁለት ፓርቲዎች ድምፅ መስጫ መሀል ኤክስ ምልክት በማስፈር ድምፁ ውድቅ እንዲሆን ማድረጉን ተናግሯል፡፡

የዚህ ዓይነት ድምፅ ሰጪዎች በርከት እንደሚሉ መጠርጠር ይገባል፡፡ ተቃዋሚዎች ተጣምረውና ተጠናክረው፣ ለዓመታት አማራጫቸውን እያሳዩ፣ ሕግና ሥርዓት ተከትለው ከሠሩ ኢሕአዴግን በነፃ ድምፅ አሰጣጥ ሊጥሉት የሚችሉት ከላይ የተጠቀሱ መራጮችን ድምፅ ስለሚያገኙ ነው፡፡ እርግጥ በዘንድሮው ምርጫ በዜጎች አዕምሮ ሥጋት እንዲፈጠር በተከታታይ ሲሰጡ የነበሩ የሥነልቦና መግለጫዎች ተፅዕኖ አላደረጉም ማለት ይከብዳል፡፡

ሦስተኛው የኢሕአዴግ መራጭ መጪውን ጊዜ ተስፋ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ፓርቲውን ቢደግፍም የረካም ያልረካም፣ በፊት ኢሕአዴግን ቢቃወምም አንዳንድ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል በሚል ተስፋም የመረጠ አለ፡፡ እኔ ከእዚህኛው ተርታ ከመሆኔም በላይ ብዙ ጓደኞቼ ሐሳቤን እንደተጋሩት ተረድቻለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

‹‹ዜጎች ኢሕአዴግ ወደፊት ሊሠራላቸው የሚፈልጉት ምንድነው?›› ብሎ መነሳትና ከላይ እስከ ታች በእውነት ላይ የተመሠረተ መረጃ መያዝ ነው ቀዳሚው የእናንተ ሥራ መሆን ያለበት፡፡ መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ኮንዶሙኒየም…ይሠራልን ለሚሉ ሰዎች አቅም በፈቀደ መጠን በተጀመረው መንገድ ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ ግን ዜጎች የሐሳብና የህሊና ነፃነት ይሻሉ፡፡ ሙስናና ማጭበርበር እንዲወገድ፣ የመኖር ዋስትናም በሚገባ እንዲከበር ይመኛሉ፡፡ በየትኛውም መለኪያ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ መለያየት እንዳይኖር በተሳሳተ ታሪክ ጥላቻ እንዳይነግሥ የሚፈልጉ እጅግ በጣም በርካታ ናቸው፡፡

በአገራቸው ሠርተው ለመብላት፣ በፍትሐዊነትና በግልጽ አሠራር ለሥራ መደራጀት፣ በእኩልነት ተጠቃሚ መሆን ያቃታቸው እንዲሁ የመንግሥትን የለውጥ ዕርምጃ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በተጀመረው የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና መከባበር ላይ ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በትውልዱ ውስጥ አለመቀረፁ የሚያሠጋቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ከሁሉ በላይ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሁም ተሳትፎ መቼ ይሰፍናል የሚለው ጥያቄ በየጓዳው የሚመነዥክ ተግዳሮት ነው፡፡

ክቡርነትዎ እርስዎ እንደ ኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትዎ እነዚህ ችግሮችም ሆኑ ጥያቄዎች የሉም፡፡ ቅዥቶች ናቸው ሊሉ ይችላሉ፡፡ መብትዎ ነው፡፡ ግን ይኼን መነሻ ይዞ ሕዝቡ ሐሳቡን የሚገልጽበትና በነፃነት የሚደመጥበት መድረክ በየደረጃው መፍጠር ብልህነት ነው፡፡ እነዚህ የምክክርና የውይይት ፎረሞች ደግሞ እስከ ዛሬ እንደሚደረገው ‹‹በድርጅት አሠራር›› የሥርዓቱ ደጋፊዎችና የፎረምና የሊግ አባላት ብቻ የሚገኙባቸው ሊሆኑ አይገባም፡፡ አርሶ አደሩ፣ ሠራተኛው፣ ባለሀብቱ፣ ምሁራን፣ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችና ተማሪዎች በነፃነት መናገርና መደመጥ ይሮርባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ከሁሉ በላይ የሚካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ‹‹ለፖለቲካ ፍጆታና ለፕሮፓጋንዳ›› መሆን የለበትም፡፡ አወያይ የፓርቲ ካድሬዎችም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ከየትኛውም ጥምዘዛ የሐሰት ሪፖርት ወጥተው ‹‹ሕዝቡ ምን እያለ ነው?›› ለሚለው ጥያቄ ሚዛናዊ መልስ ለመንግሥት ማድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

መንግሥት እኮ ግትር መሆን የለበትም፡፡ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ፣ የሕዝብ ፍላጎትና ተጨባጩ ሀቅ አቋሙ እንዲፈትሽ፣ አካሄዱ እንዲያጤን ያስገድዱታል፡፡ ስለዚህ ማሻሻያ ለማድረግም ሆነ በነበረው ለመቀጠል ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ ስለሆነ ሊደመጥ ይገባዋል፡፡ ያልተባለውን እያቀነባበሩ፣ መሬት ላይ የሌለውን እውነት ለውሳኔ ሰጪው ማቀበል ዴሞክራሲያዊው ጉዞ ያደናቅፈዋል፡፡ በመሠረቱ ከእርስዎ ጀምሮ መረጃው የሚደርሰው የመጨረሻው ስትራቴጂካዊ የሥራ መሪም ‹‹ምን? እንዴት? የት? መቼ…›› የሚሉ የማያልቁ ጥያቄዎችን እየመዘዘ ሁሉንም የአገሪቱን ጉዳዮች መመርመር አለበት፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

አስመሳይነትና አድርባይነትን የሚታለልና የሚያጋልጥ መሪ በራሱ በአስመሳዩ ጭምር የሚደነቅና የሚከበር ብቻ ሳይሆን፣ ሞቶም የሚዘነጋ እንዳልሆነ ከናፖሊዮን ታሪክ አንዱን ላስታውስዎት፡፡ ናፖሊዮን በውጭ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ዕውቀት የሚረዳው ታሌራ የሚባል ፈረንሣዊ ፖለቲከኛ የቅርብ ሰው ነበረው፡፡ ይሁንና ታሌራ ክህደት የሚሠራ፣ ለራሱ ጥቅም ሲል የተዛባ መረጃ እየሰጠ የሚያሳስት መሆኑን ናፖሊዮን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡

አንድ ቀን ናፖሊዮን ወደ ጦርነት ሲሄድ የሠፈረበት ቦታ ታሌራን አስጠራና ስለመንግሥቱ ጉዳዮች በድንኳኑ ውስጥ ሲያነጋግረው አመሸ፡፡ ናፖሊዮን አልጋው ላይ ተኝቶ ስለነበረ እያነጋገረው ያለልማዱ እንቅልፍ ይዞት ሄደ፡፡ ታሌራም ሳይነሳ ከናፖሊዮን አጠገብ እንደተቀመጠ ሌሊቱ ነጋ፡፡ ናፖሊዮን ጧት ሲነሳ ታሌራን እዚያ ተቀምጦ ሲያገኘው ምክንያቱን ጠየቀው፡፡ ‹‹ግርማዊነትዎ ሳያሰናብቱኝ ስለተኙ ከጌታዬ ሳላስፈቅድ መሄዱ የለብኝም በማለት ቁጭ ብዬ አደርኩ፤›› ብሎ መለሰ፡፡ ቢሆንም መተኛቴን ስታውቅ ብትሄድ ይሻል ነበር ብሎ ናፖሊዮን መልሶለታል፡፡

ታሌራ ግን፣ ‹‹ለንጉሠ ነገሥቴ ያለኝ ታማኝነት እስከዚህ ድረስ ነው፤›› እያለ በመፎከር ይኼንኑ ነገር ለጓደኞቹ ሲያጫውት፣ ነገሩ በቅዥት እሱ የማያውቀውን ሚስጥር አውጥቼ ሲናገር ሊሰማ ስላሰበ ነው እንጂ እውነትስ እኔን አክብሮ አይደለም ብሎ ናፖሊዮን መለሰ፡፡ ታሌራ ይኼን በሰማ ጊዜ በታማኝትና ጌታውን በማፍቀር የሠራው ሥራ እንዲህ በመጥፎ በመተርጎሙ አዘነ፡፡ ናፖሊዮን ከሞተ ብዙ ጊዜ በኋላ ግን ንጉሡ እውነተኛ ምኞቹን እንዳወቀበት መስክሮ ናፖሊዮን ብልህና አስተዋይ ሰው እንደነበረ አድንቆ ተናግሯል ይባላል፡፡

ከዚህ የሩቅ ዘመንና የሌላ ዓለም ታሪክ የምንማረው ሁሉን በመጠርጠር ሥጋት እንበጥበጥ ሳይሆን አስመሳይነትን እንፈትሽ፣ የሕዝቡን ስሜት እንወቅ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ካባ ተጀቡነው፣ በሕዝብ የሥልጣን ኮርቻ ላይ በመፈናጠጥ ሕዝብ የሚያውቀው ፀሐይ የሞቀው ጥፋት የሚሠሩ የሉም? ሥልጣንን ተገን በማድረግ ዋነኛ ኮንትሮባንዲስቶች፣ የቅሸባ ተውኔት መሪዎች፣ መሬት አጣሪና ቸብቻቢዎች የሉም ይባል ይሆን? መመለስ ያለበት ነጥብ ነው፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የግምገማ መድረክ ላይ ጠንከር አድርገው የጀመሩ የካቢኔ አባላት ጭምር ‹‹ለአንተስ ይኼን ማን ፈቀደልህ?›› የሚል የአፀፋ ጅራፍ ሲወርድባቸው እንደነበር ተሰምቷል፡፡ በክፍለ ከተማ ሕገወጥ ግንባታ ያላግባብ ፈቀድክ፣ ዕጣ ለወጣላቸው የቤት ዕድለኞች አለዋውጠህ ሰጠህ፣ ወዘተ የተባለ ተገምጋሚ እስከ ላይኛው እርከን ድረስ አቃቂ ቃሊቲ ያጠርከው ቦታ የማን ነው? የሚል ድፍረትን ተላብሷል፡፡ ይኼ አካሄድ ከዋለ ካደረ ደግሞ መርህ ይበተናል፣ ሥርዓትና ሕግ ይፈርሳል፣ አገርና ሕዝብን ለጉዳት ይዳረጋል፡፡

ክቡርነትዎ!

እርስዎን ጨምሮ የአንዳንድ ነባር የፖለቲካው መሪዎችን ስም በመጥቀስ በየመሥሪያ ቤቱ የተወሸቁ ጥቅመኞች በግልጽ መለየት አለባቸው፡፡ ሕዝቡ ኢሕአዴግን ሲመርጠው ከላይ በጠቃቀስኳቸውና ሌሎች ባልተነሱ ምክንያቶች ቢሆንም፣ በቀጣይ ‹‹ይታረምልን›› የሚለው ጉዳይ ብዙ ነው፡፡

በመንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ (በሕዝብ ሀብት የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ) ግልጽነትና ተጠያቂነት ለምን ተጠናክሮ አልስፋፋ አለ? ሌላው ቀርቶ ሰዎች ሲሾሙና ሲሻሩ ምንም እንኳን የኢሕአዴግ ጉዳይ ቢሆንም በመርህ ላይ የተመሠረቱ መሥፈርትና የሚያግባባ መመዘኛ አይታይም፡፡ ከብቃት፣ ከችሎታና ከተቀባይነት በላይ ለሿሚው ግለሰብ ያለ ቅርበት፣ የሃይማኖት፣ የብሔርና የዝምድና መሳሳብ በዝቶ ነው የሚታየው፡፡ አሁንም እርሱ ከዚህ ማኅበረሰብ ስለሆነ ለዚህ አይመጥንም የሚሉ ጭፍሮችም እየታዩ ነው፡፡ ታዲያ ይኼ አካሄድ ሕዝብን ያስደሰተ ይመስልዎታልን?

ዘንድሮ በአየሁዋቸው ውስን የምርጫ ክርክሮች ተቃዋሚዎች የሚያነሷቸው አንዳንድ ሐሳቦች ወዲያው የሕዝብ ቀልብ የሚስቡት ለምን ይመስልዎታል? መቼም ተፎካካሪዎች ከኢሕአዴግ ካድሬዎች በላይ የበሰሉ ተሟጋቾች አቅርበው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ አማራጭ ፖሊሲና ማኒፌስቶ ሠርተው በማቅረባቸውም አይደለም፡፡ ይልቁንም ዋነኛው ማጠንጠኛ ሕዝብ የሚባለው ግዙፍ ተቋም ውስጥ በአንድም በሌላም የሚብሰከሰኩና የሚብላሉ ጉዳዮችን (መንግሥት ችግር ማርገብ ይለዋል) እየመዘዙ በማውጣታቸው ነው፡፡

ይኼን ሁሉ ልማት የሠራ፣ ሰላምንም ቢሆን ለማንም በሚያኮራ መንገድ ያስከበረ መንግሥት፣ አገራዊ ስሜት የለውም ተብሎ ሲተች ሚዲያዎች መፈተሽ አለባቸው፡፡ ይኼን ያለው ተቃዋሚው ብቻ ነው? ሕዝቡ፣ ከሕዝቡ ውስጥስ የትኛው ብሎ መመርመር ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ የኢሕአዴግን ግልጽ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምን እንደሆነ አውቀናል፡፡ ቢሆንም በስደት ያሉ ዜጎችን ጉዳት በቁጭት በማዳመጥ፣ በአገሪቱ ድንበርም ሆነ በሌሎች ጥቅሞች ላይ አጀንዳ በመፍጠር፣ ዜጎች አገራዊ ስሜት እንዳያዳብሩ በማነፅ፣ ሉላዊነት (Globalization) በበረታበት ዓለም ብሔር ተኮር መፈላለግን በመቀነስ፣ በዜጎች ላይ የእኔነት ስሜትና አገራዊ ተቆርቋሪነትን በማዳበር ተጨማሪ ሥራና የአቅጣጫ ለውጥ አያስፈልግምን?

ኢሕአዴግ በዚች አገር ውስጥ ብዝኃነት እንዳለ በመገንዘብ ለልዩነትና ለብዝኃነት የሰጠው ትኩረት ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በግሌ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እስካለ ድረስ ልዩነት መንፀባረቁና የኩራት ምንጭ መሆኑ ጉዳት እንዳልሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ይኼን የሃይማኖት፣ የዘር፣ የቋንቋ፣ የቀለም፣ የፆታ…ስብጥር የተገነዘበው መንግሥት ግን በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ሁሉም አንድ ዓይነት አመለካከት ያራምድ ብሎ ሲነሳ እብደት ይመስለኛል፡፡ እርስ በርሱ ተጋጭቶ የሚወድቅ ድርጊትም ነው፡፡

ክቡርነትዎ!

አሁን አንድ ለአምስት የተባለውን የ‹‹ልማት›› አደረጃጀት መንቀፍ ተቃዋሚነት ሊመልስዎ ይቻላል፡፡ እርግጥ ለኢሕአዴግ የምርጫ ሥራም ሆነ ልማቱን በሕዝቡ ተሳትፎ ለማራመድም እንዳገዘ ይገመታል፡፡ ግን ከፈቃደኝነት ውጪ በሆነ መንገድ፣ በዚያ ትስስር አለመደራጀት በሚያስፈርጅበትና በሚያስገልልበት ሁኔታ እንደ ትልቅ ድል ሊነገር ይገባል? ዴሞክራሲን የህልውና ጉዳይ ብሎ የአመለካከት ብዝኃነትን የሚሸከም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እገነባለሁ የሚልን አገር የት የሚያደርስ ነው?

ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያና ኤርትራ መላውን የአገሪቱ ሕዝብ አንድ ለአምስት ሳይሆን አንድ ለአንድ ቢያስተሳስሩት ብዙም አይገርምም፡፡ በአገሪቷ አማራጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ የለም፣ ወይም ቢኖርም አንድ ስለሆነ ጠዋት ማታ እሱኑ እየበጠበጡ ከመጋት ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ለእኛ ታዲያ እንዴት የእነሱ ፈለግ ያስኬደናል? አንድ ለአምስት የግል መብትን እንደሚዘነጥል፣ በሕዝብ ሀብት በሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ መግባት እንደሌለበት፣ በመኖሪያ አካባቢም አማራጭ ሐሳብን እንደሚገድብ ራሱ ኢሕአዴግስ ለምን አያጠናውም ማለት እሻለሁ፡፡

በመሠረቱ ይኼ ነገር በዕምነትና ከልብ ባልሆነ አስመሳይነት ውስጥ የሚገነባ ትውልድን እንዳያበዛ እሰጋለሁ፡፡ ለእርሻ ሥራ፣ ለጥናት፣ ለጤና፣ ለልማት ወይም ለመንገድ ሥራ በጋራና በማኅበር መንቀሳቅስ እንደሚጠቅም፣ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ግን የምርጫ ድምፅ መስጠት በየትኛውም ዓለም መቼም ቢሆን አልተሰማም፡፡ ስለዚህ ይኼ አካሄድ በጥብቅ ሊፈተሽና የሕዝቡ ፍላጎት ሊጠየቅበት ይገባል፡፡ ይህንን ያነሳሁት በየቦታው በርካታ እሮሮ ስለተሰማ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በየጊዜው በሚያከናውናቸው ተግባራት ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማዳበር፣ ፍትሐዊና ርትዕ አስተዳዳርን በማስፈን እንዲመረጥ መሥራት አለበት፡፡ ለእዚህም ካሳካው ይልቅ ያላሳካውንና ወደኋላ የቀሩበትን በመፈተሽ ደጋፊዎቹን ማብዛት ነው ያለበት፡፡ ይኼን በማድረግ ሕዝቡ በነፃነት በሚሰጠው ድምፅ ሃምሳም መቶም ዓመት አገር ቢመራ ሊከለከል አይችልም፡፡ ግን በተፅዕኖ ምርጫ፣ ገለልተኝነቱ የሚያጠራጥር አስፈጻሚ በመያዝ፣ ተቀናቃኝን በጉልህ በማዳከምና የፍርኃት ሥነ ልቦና በመርጨት፣ ወዘተ ከሆነ የራሱ አደጋ አለው፡፡ ዋናውን የዴሞክራሲ ጉዞም ያጨናግፈዋል፡፡

ክቡርነትዎ!

እዚህም ላይ አንድ የሌላ አገር አብነት ማንሳት እወዳለሁ፡፡ የሩሲያው አምባገነን መሪ ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን ከሞት ጋር ግብግብ ተያይዞ በሚቃትትበት ጊዜ፣ አልጋ ላይ ሆኖ ከሞቱ ልይቅ ይበልጥ ሲያስጨንቀው የነበረ ሐሳብ ነበር፡፡ ይኼውም የእርሱን ቦታ ማን እንደሚይዝና የሚመራው ፓርቲም እንዴት ሆኖ ያለተቀናቃኝ ለዘለዓለም ሥልጣን ላይ በመቆየት ኮሙዩኒዝምን ዕውን ማድረግ ይችላል የሚለው ነበር፡፡ ሌኒን ከሞተ በኋላ የእሱን ራዕይ እንፈጽማለን በሚሉና የራሳቸውን መንገድ ይከተላሉ በሚባሉት በስታሊንና በትሮትስኪ ተከታዮች መካከል ከፍተኛ ሽኩቻ ተካሂዶ በመጨረሻ አሸናፊው ስታሊን ወደ ሥልጣን ወጣ፡፡ የሩሲያ ታሪክም በደም እየጨቀየ በመጨረሻም በውርደት ታሪክ ተንኮታኮተ፡፡

ከዚህ መነሻ የእኛው ኢሕአዴግ ‹‹እኔ ከሌለሁ እንበታተናለን›› የሚል መፈክር በማንሳት የአማራጭ በሮችን እንዳይዘጋ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ይልቁንም በቅንና በአገራዊ ስሜት በተቃኘ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሕግና ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ ፍርዱን ለሕዝብና ለታሪክ መተው ነው የሚሻለው፡፡ ለውጥ በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ፣ በሆደ ሰፊነት ዜጎች ዕምነታቸውን እንዲያራምዱ፣ የመደራጀትንና ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብታቸው እንዳይሸራረፍ መደረግ አለበት፡፡ መሸማቀቅ፣ መሸሽና መገለል ተወግዶ ሁሉም በንቃትና በዕምነት እንዲሳተፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሌላ ጊዜ በምጽፍልዎ ማስታወሻ እስከምመለስ ድረስ በምርጫው ማግሥት በሕዝቡ ይፈልገዋል በማለት ስሜቱን ለመነካካት ሞክሪያለሁ፡፡ በዚህ መነሻ እውነታውን መፈለግ፣ ማጥራትና ዜጎችን ማዳመጥ የእርስዎና የመንግሥትዎ ድርሻ ነው፡፡ መልካም የአዳማጭነት ዘመን ይሁንልዎ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...