Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕዝቡን ወደፈለጉት አቅጣጫ ለመውሰድ መብቱም ሆነ አቅሙ የላቸውም››

አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት

አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት ሲሆኑ፣ ቀደም ብለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የኮሙዩኒኬሽንስ ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ሕወሓት ኢሕአዴግን በመወከል በትግራይ ክልል በአላማጣ የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በአምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተወዳድረዋል፡፡ እስካሁን ይፋ ከተደረጉ 442 መቀመጫዎች ኢሕአዴግና አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ አሸናፊ መሆናቸው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ተደርጓል፡፡ ሚኪያስ ሰብስቤ ፓርላማውን ለመጀመርያ ጊዜ የሚቀላቀሉትን አቶ ጌታቸውን በምርጫው ውጤት፣ በፖለቲካ ምኅዳሩ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በፓርላማ ወኪል የሌላቸው ዜጎች ድምፃቸውን በሚያሰሙባቸው መንገዶች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጊዜያዊ ውጤቶች እንዳሳዩት ከሆነ በአምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ኢሕአዴግና አጋሮቹ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የክልል ምክር ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይኼ ያልተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ውጤት ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፡- እያንዳንዱ ፓርቲ ወደ ምርጫው ሲገባና ዕጩ ሲያቀርብ አሸንፋለሁ ብሎ በማሰብ ነው፡፡ ሁሉም ዕጩዎች አሸናፊ ሆነው መውጣታቸው ብዙ ጊዜ አይሳካም ማለት ነገሩ ዕውን ሲሆን ተቀባይነት አይኖረውም ማለት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ በምርጫው 501 ዕጩዎችን ሲያቀርብ በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ለማሸነፍ ታግሏል፡፡ እስካሁን በ442 ክልሎች አሸንፏል፡፡ የምርጫው ውጤት ሲገለጽ በ501 ክልሎች ካሸነፈ ይኼ ማለት ሁሉንም ወንበሮች ለማግኘት የሚያስችል ድጋፍ አንቀሳቅሷል ማለት ነው፡፡ የሒደቱ ዴሞክራሲያዊነት የሚለካው ባሸነፍከው መቀመጫ ቁጥር አይደለም፡፡ ሒደቱ ነፃና ፍትሐዊ ነበር ወይ ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ዞሮ ዞሮ ውሳኔው የሚሰጠው በመራጩ ሕዝብ ነው፡፡ ለኢሕአዴግ ቁልፉ ጉዳይ መቶ በመቶ ማሸነፉ ሳይሆን ለመራጩ ሕዝብ ፖሊሲዎችን በተመለከተ ማሳመኑ ነው፡፡ ሕዝቡ አገሪቱን ለመለወጥ ያለው ብቸኛ አማራጭ ኢሕአዴግ መሆኑን በዚህ ምርጫ በግልጽ አሳይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ግን በአገሪቱ የሰፈነውን የፖለቲካ ከባቢና የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ገለልተኝነት ይወቅሳሉ፡፡ በተለይ 1ለ5 የተሰኘው ማኅበራዊ አደረጃጀት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፡- እነዚህ ወቀሳዎች አዲስ አይደሉም፡፡ ለእነዚህ ወቀሳዎች መልስ ከመስጠቴ በፊት ዴሞክራሲ ለኢሕአዴግ ምን ማለት እንደሆነ በቅድሚያ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ዜጎች በተቻለ መጠን ሙሉ የፖለቲካ ነፃነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ ሥራቸው በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ መቃወም በመሆኑ፣ ኢሕአዴግን በተመለከተ አዎንታዊ ነገር ይናገራሉ ብዬ አልጠብቅም፡፡ ነገር ግን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች ዜጎች ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን ስንል ይህንን አደረጃጀት እንደግፋለን ማለት ነው፡፡ የዜጋው የተናጠል ተሳትፎ ብቻውን ትርጉም አይሰጥም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡን የተለያዩ ፍላጎቶች መሠረት አድርገው የተደራጁት ለዚህ ነው፡፡ መንግሥት ልማትን ለማረጋገጥ የሕዝቡ ሙሉ ተሳትፎ ያስፈልጋል የሚለው ያለ ዜጎች ተሳትፎ ልማትን ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡

ይህን በተደራጀ መንገድ ለማረጋገጥ የሚደረገው አወቃቀር ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በአሜሪካ ለምሳሌ ፓርቲዎች በየቤቱ እየሄዱ በር በማንኳኳት መራጭ ይሆናል ላሉት ዜጋ ስለፓርቲያቸው በመግለጽ የምረጡኝ ዘመቻ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ዜጎችን በተለያዩ አደረጃጀቶች በማቀፍ መንቀሳቀስ ልትመርጥ ትችላለህ፡፡ ይኼ አደረጃጀት 5፣ 7 ወይም 9 አባላት ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ ይህ አደረጃጀት የተሰጠውን የቤት ሥራ ወይም ልማታዊ እንቅስቃሴ በተገቢ መንገድ መፈጸሙ ነው፡፡ የ1ለ5 አደረጃጀት የተዋቀረው ለምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዓላማው ለልማት ሥራዎች ሕዝቡን ለማንቀሳቀስ ነው፡፡ በአጋጣሚ አደረጃጀቱ ዜጎችን በፖለቲካ ጉዳይ በማንቀሳቀስ አንድን ፓርቲ ተጠቃሚ ካደረገ፣ መታወቅ ያለበት ይኼ የተቋቋመበት ዓላማ እንዳለ ሆኖ ነው፡፡ ይኼ አደረጃጀት የተለያየ ቅርፅ ሊኖረው ይችላል፡፡ ኢሕአዴግ በሚያስተዳድራቸው ክልሎች ውስጥ ወይ አርብቶ አደሮች አልያም ገበሬዎች ይኖራሉ፡፡ ለሁለቱም አንድ ዓይነት አደረጃጀት አንጠቀምም፡፡

      ስለ አደረጃጀቱ ይህን ካልኩ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋቱን ወይም ለዜጎች ሙሉ ነፃነት መፍቀዱን የሚወስነው ገዢው ፓርቲ አይደለም፡፡ ይኼ ዜጎች የመብት ጥያቄያቸውን ምን ያህል በቁም ነገር ይወስዱታል በሚለው የሚወሰን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ማኅበረሰብ በዓለም ላይ በጣም ፖለቲካዊ የሆነ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ የገበሬውን ሕይወት የተመለከቱ ማንኛውም ዓይነት ውሳኔዎች ያለ ገበሬው ተሳትፎ አልተወሰዱም፡፡ ሁሉም ውሳኔ በዜጎች ተሳትፎ በሚወስኑበት አገር ሕዝቡ የኢሕአዴግን ፖሊሲዎች ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ራሱን ስላቆራኘ ኢሕአዴግን መረጠ ማለት አግባብነት የለውም፡፡ ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕዝቡን ወደፈለጉት አቅጣጫ ለመውሰድ መብቱም ሆነ አቅሙ የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ልዩነት እንዳይኖር አድርጓል ተብሎ ይተቻል፡፡

አቶ ጌታቸው፡- ክሶች ሁሌም ይኖራሉ፡፡ ኢሕአዴግ ያልተከሰሰበት ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ ፖሊሲ ለምን ቀረፀና ፕሮጀክቶችን ይፋ ለምን አደረገ ተብሎ ተተችቷል፡፡ እነዚህ ነገሮች ለአገር ያላቸው ጠቀሜታ ግልጽ ቢሆንም፣ የመራጮቹን ይሁንታ ለማግኘት ነው የተፈጸሙት ተብሎ ነው የተተቸው፡፡ እነዚህ ክሶችና ትችቶች ነጥብ የላቸውም፡፡ ገዢ ፓርቲ ፕሮጀክቶችን እንዲፈጽም ይጠበቃል፡፡ በዚህ ሒደት ዜጎች በፓርቲው ላይ ያላቸው አመለካከት ቢቀየር ምንም የሚገርም ነገር አይሆንም፡፡ ዋናው ጉዳይ የሕዝቡ ምርጫ ነው፡፡ የመንግሥትና የፓርቲው ልዩነት ሰፍቷል ስለሚባለው ጉዳይ ሁኔታው የሚያሳየው ከእይታው አንፃር ነው፡፡ ሰፊ የድጋፍ መሠረት አለን ሲሉ የነበሩና በምርጫው በቂ ዕጩዎችንና ታዛቢዎችን ማሰማራት ያልቻሉ ተቃዋሚዎች፣ ገዢው ፓርቲ በሥልጣን ላይ ብዙ ስለቆየ የተሻለ ተጠቃሚ ነው ማለታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡

እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ሕዝቡ ሄደው ሐሳባቸውንና አቋማቸውን ሸጠው በርካታ አባላትን እንዳይመለምሉ ተከልክለዋል ወይ የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች አባላትን ለመመልመል ጥረት ሲያደርጉም አይታዩም፡፡ ከምርጫ ዓመት በፊት ሥራቸውን ሲሠሩም አትሰማም፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ መስመር መቀላቀልን የሚጠቅሱት በተግባር ስለተቀላቀለ አይደለም፡፡ ይልቁንም የመንግሥትን ሀብት ለራሳቸው መጠቀም ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት ያሉት በመሆኑ የመንግሥትን መዋቅር መጠቀም አያስፈልገውም፡፡ ገዢው ፓርቲ ፖሊሲ ቢያፈልቅም የሚፈጸመው በመንግሥት መዋቅር ነው፡፡ በመንግሥት መዋቅር ዜጎችን በማስገደድ ምርጫ አያሸንፍም፡፡ ኢሕአዴግ የሚያሸንፈው በሠራው ሥራና ለመሥራት በሚገባው ቃል ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንሠራለን የሚሉት ነገር መራጩን አሳምኖ የሚያሸንፍ ድምፅ አላስገኘላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግና የመሰብሰብ መብት ላይ ገደብ ሲደረግ ይታያል፡፡

አቶ ጌታቸው፡- የመሰብሰብና ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብቶች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያላቸው ናቸው፡፡ ገደብ የተደረገው በመብቶቹ ላይ ሳይሆን በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታዎች ላይ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የትም ቢሆን ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ክልከላው የተፈጸመው ገዢው ፓርቲ ለተቃውሞ ምንም ክፍት ቦታ ስለማይሰጥ ነው የሚል ስሜት የማይሰጥ ክስ ያቀርባሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም በመስቀል አደባባይ ሰፊ የኮንስትራክሽን ሥራ የምናከናውነው እነሱ እዚያ አካባቢ ሊያደርጉ ያሰቡት ሰላማዊ ሠልፍ እንዳይደረግ ለማደናቀፍ ነው እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ባለፉት 20 ዓመታት የተለመደ ነገር መሆኑን ነው፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የግድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሆን የለብህም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አልፎ አልፎ የሚከለከሉት ባልተጠበቀና ተቀባይነት በሌለው ቦታ ላይ ካላደረግን ስለሚሉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ተመዝግበው ሕጋዊ የምስክር ወረቀት ያላቸው ከ70 በላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ ሁሉም ማለት ይቻላል ደካማና የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ ላሉበት ደረጃ ገዢው ፓርቲ ተጠያቂነት የለበትም?

አቶ ጌታቸው፡- ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ላይ መግለጽ ስህተት ነው፡፡ እኔን ጨምሮ የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት ሁሉንም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ የሚፈርጅ የሚመስል ቋንቋ አስበን ባይሆንም እንጠቀማለን፡፡ ይኼ ግን የፓርቲው አቋም አይደለም፡፡ በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለዚህ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለምን እንደተከፋፈሉ አላውቅም፡፡ ገዢው ፓርቲ በዚህ የሚወቀስበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ የእኛ አገር የምርጫ ሥርዓት አንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት (First-Post-The-Post) በመሆኑ የተሻለ ድምፅ ያገኘው ያሽንፋል፡፡ ስለዚህ ለማሸነፍ የተሻለ አደረጃጀትና ተሳትፎ ያስፈልግሃል፡፡ ይህን ሳይገነዘቡ መከፋፈል ከመረጡ መንግሥት በዚህ ለምን ይወቀሳል? አንዳንዴ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲል መንግሥት ምርጫውን እንዲያጭበረብር የሚጠበቅ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎቹ የቤት ሥራቸውን መሥራትና መራጩን የሚያሳምን ፖሊሲ ቢቀርጹ ነው የሚሻለው፡፡ ስለዚህ ለውጤቱ ተቃዋሚዎቹ መውቀስ ያለባቸው ራሳቸውን ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ሐሳባቸው ጥሩ ቢሆንም የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላትና አማራጭ ሆነው ለመቅረብ ብዙ ይቀራቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ዴሞክራሲ እንደ ልማት ሁሉ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ብዙዎች በዚህ አባባል አይስማሙም፡፡ የኢኮኖሚ ስኬት መለኪያዎች ግልጽ ሲሆኑ፣ የመንግሥት የዴሞክራሲ መለኪያዎች ምንድን ናቸው?

አቶ ጌታቸው፡- የዴሞክራሲ መለኪያዎቻችን ከሞላ ጎደል የልማት መለኪያዎቻችንም ናቸው፡፡ በዚህ አገር ያለዴሞክራሲ ልማት የሚመጣ የሚመስላቸው ካሉ ይህችን አገር አያውቋትም፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱን ሳናስተካክልና ከብሔር፣ ከሃይማኖት፣ ከቋንቋ፣ ከሕዝብ ስብጥር ጋር የተያያዙ የብዝኃነት ጥያቄዎችን ስንመልስ የትም ልንደርስ አንችልም፡፡ የሕዝቡን ተሳትፎ የምናረጋግጥበት የፖለቲካ ምኅዳር ስንፈጥር የምናመጣው የልማት ፖሊሲ ምን ያህል መልካም ቢሆን ሊሳካ አይችልም፡፡ አፈጻጸሙ ብቻ ሳይሆን ቀረፃው፣ ቁጥጥርና ክትትሉ ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ሊሳካ አይችልም፡፡ እዚህም እዚያም ችግሮች ቢገጥሙትም የዴሞክራሲ ባህል ግን ገንብተናል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በኢኮኖሚ ዘርፉ ያስመዘገብነው ስኬት የመጣው በፖሊሲ አወጣጥ፣ አፈጻጸምና ቁጥጥር ላይ የሕዝብ ተሳትፎን በማረጋገጣችን ነው፡፡ ይኼ ዴሞክራሲ ካልሆነ ሌላ ምንም ነገር ዴሞክራሲ ሊሆን አይችልም፡፡ አልፎ አልፎ ከባህል ጋር የተያያዙ ኋላቀር አመለካከቶች ያጋጥሙናል፡፡ ቁርጠኝነትን በተመለከተ ግን ከልማት ባልተናነሰ ለዴሞክራሲም ቁርጠኛ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የዴሞክራሲ ዕድገት ወደኋላ ሲሄድ ኢኮኖሚ ግን ባለሁለት አኃዝ ዕድገት እያሳየ ነው የሚለውን ትችት እንዴት ያዩታል? ዴሞክራሲን በተመለከተ ያለው አረዳድ ችግር ያለበት ለምንድነው?

አቶ ጌታቸው፡- የምዕራባውያን ሚዲያን በየቀኑ የማየት ሱስ ካለብህ ሕዝባዊ ተሳትፎን ዴሞክራሲ ከማለት ይልቅ፣ ሰርከስ ብለህ ለመጥራት የሚያስችሉ ቋንቋዎችን የማዳበር ዕድልህ ይሰፋል፡፡ የምዕራባውያን የሚዲያ ተንታኞች 33 ሚሊዮን ሕዝብ ወጥቶ በሰላማዊና በተረጋጋ ሁኔታ መምረጡን ሰርከስ ብለውታል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ረብሻ፣ ደም መቃባትና ምርጫ ተጭበረበረ የሚል ሁከት ስለሌለ፡፡ ዋሽንግተን ወይም ለንደን ያለ ግለሰብ ዴሞክራሲ ብሎ የሚያስበው ነገር እዚህ አገር ያሉ ሕዝቦች ከሚያስቡት ሊለይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ላለመስማማት ልንስማማ እንችላለን፡፡ እዚህ አገር ዴሞክራሲ ማለት አንድ መቀመጫውን ለንደን ያደረገና ለዚህ አገር እንግዳ የሆኑ ሐሳቦችን የሚያራምድ ድርጅትን ማስደሰት አይደለም፡፡ እንኳን ዴሞክራሲ ወደኋላ ሊመለስ ዛሬ በተቃራኒ ሕዝቡ ከምንጊዜውም በላይ የዴሞክራሲያዊ ሒደቱ ባለቤት ሆኗል፡፡ ነገር ግን በምዕራባውያን ዘንድ ዴሞክራሲ ተብሎ የሚገለጸው ነገር በጣም ቀንሷል፡፡ ይኼ ደግሞ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን መልካም ዜና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዘንድሮው የምርጫ ውጤት በአዲስ አበባ ወደ 35 በመቶ የሚሆኑት መራጮች ኢሕአዴግን አልመረጡም፡፡ በመሆኑም በፓርላማ ተወካይ አይኖራቸውም፡፡ አንዳንዶች ለዚህ የምርጫ ሥርዓቱን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ጌታቸው፡- የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት በጣም ደሞክራሲያዊና አሳታፊ ከሆኑ የምርጫ ሥርዓቶች አንዱ ነው፡፡ እንግሊዝ ትጠቀምበታለች፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዝሃነት ላላቸው አገሮች ተመራጭ ነው፡፡ ለአናሳ ማኅበረሰቦች ውክልና ያረጋግጣል፡፡ ሕጉን ከመቀየር ይልቅ ተቃዋሚዎች ቢጠናከሩ መልካም ነው፡፡ መንግሥት የምርጫ ሕጉ ለውጥ የሚያስፈልገው ከሆነ ብሎ አጥንቷል፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል ብለን አናስብም፡፡ ጥናቱ ከሦስት ዓመት በፊት የተደረገ ሲሆን፣ አሁንም በድጋሚ ልናየው እንችላለን፡፡ መንግሥት ያልመረጡትን ዜጎች ድምፅ ለመስማትና እነሱን የሚጎዳ ውሳኔ ላለመወሰን እንደሚጥር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከውጤቱ በኋላ ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በፓርላማ ወንበር ባይኖራቸውም አገር የሚለውጥ ሐሳብ እስካመጡ ድረስ ገዢው ፓርቲ አብሯቸው ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት መንገዶችን በመጠቀም ነው መንግሥት ድምፃቸውን የሚሰማው?

አቶ ጌታቸው፡- በነገራችን ላይ ኢሕአዴግን የመረጠ አንድ ዜጋ በኢሕአዴግ የፖሊሲ አፈጻጸም መቶ በመቶ ይስማማል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶች ኢሕአዴግን የመረጡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያራምዱትን የጥላቻ ፖለቲካ ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የትኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ድምፃቸውን ይሰማል፡፡ ባህሉ በመሆኑ ኢሕአዴግ ከሕዝቡ ጋር ይመካከራል፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ሕዝቡን ያወያያል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2002 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አንዱ መንገድ ቢሆንም፣ በዘንድሮው ምርጫ ትልቅ ድምፅ ያመጡት ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰማያዊና መድረክ ግን አባል አይደሉም፡፡

አቶ ጌታቸው፡- ምክር ቤቱ ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ ጥሩ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ እነዚህ ትልልቅ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱን አክብረው እስከሠሩ ድረስ በሥራ ላይ ያለው ወይም የሌላ ትልቅ ምክር ቤት አባል የማይሆኑበት ምክንያት አይታየኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የተመዘገቡና ሕጋዊ የምስክር ወረቀት ያላቸው መሆኑ ሕገ መንግሥቱን ስለማክበራቸው ማሳያ አይሆንም?

አቶ ጌታቸው፡- ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው መንገድ ውጪ ለመሥራት መሞከር ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ላይ ድርድር አይኖርም፡፡ ይኼ የሕግ የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ ሕገወጥና ሕገወጥ መንገድን ቀላቅሎ መሥራት አይቻልም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...