Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአልባሳትና በቆዳ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉ 11,000 ሴቶችን ለማሠልጠን ስምምነት ተፈረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአምስት አማካሪ ድርጅቶች ጥምረት የተዋቀረው ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ 11 ሺሕ ሥራ አጥና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶችን በአልባሳትና በቆዳ ክህሎት ለማሠልጠንና ለማስቀጠር፤ በፋሽንና ስፌት መስክ ከተሠማሩ ሁለት አገር በቀል የግል ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት ፈጸመ፡፡

የመጀመሪያው ስምምነት ከሰኔ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በሦስት ዓመታት ቆይታ 7,800 ሴቶችን በቅድመ ቅጥር ክህሎት ለማሠልጠን ሐሙስ ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከዎሲ ዓለም አቀፍ የፋሽን ዲዛይን ሥልጠና ተቋም ጋር ውል እንደፈጸመ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነስ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ሁለተኛው ስምምነት ሒደቱ ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቁ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ስሙን ከመግለጽ ከተቆጠበው ከአንድ ሌላ የፋሽንና የስፌት ሥልጠና ተቋም ጋር ሲሆን፣ 3,200 ሠልጣኞችን በመጪው አንድ ዓመት ውስጥ አሠልጥኖ ለማስቀጠር ተዋውሏል፡፡

ሥልጠናው በድምሩ 5.4 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚኖረው ሲሆን፣ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡  

ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥነት እያደገ ያለውን የአልባሳትና የቆዳ ምርት ዘርፍ ሊሸፍን የሚችል፤ ዘርፉ የሚያሻውን ክህሎትና ዕውቀት የጨበጠ በቂ የሰው ኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ እጥረት እንዳለ በመታመኑና በተለይ በአምራች ድርጅቶች እንደ ዋነኛ ተግዳሮት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡

እንደ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ መረጃ በሥልጠናው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ በአልባሳትና በቆዳ ምርት ኢንዱስትሪ ውስጥ ሊሰማሩ የሚችሉ ብሎም ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት መደበኛ የሥራ ቅጥር ያልነበራቸው በድህነት የሚኖሩ ሴቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሠልጣኞቹ መሠረታዊ የክህሎት ሥልጠና በመቅሰም ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥርና በኢንቨስትመንት ወጪያቸው በፍጥነት እያደጉ ወዳሉት የአልባሳትና የቆዳ አምራች ድርጅቶች በመደበኛነት እንዲቀጠሩ ያስችላቸዋል፡፡

ሠልጣኞቹ የሚመለመሉት አሠልጣኞቹ ድርጅቶችና ቀጣሪ እንደሚሆኑ የሚታሰቡት የዘርፉ አምራች ድርጅቶች በጋራ ተወያይተው በሚያስቀምጡት መስፈርት ይሆናል፡፡ የሥልጠናው ሒደቱን ለማቀላጠፍም የዘርፉን አምራች ድርጅቶችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ የሚቋቋም የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ለመመሥረት በሒደት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የእነዚህ ዕቅዶች ውጤታማነት ከተገመገመ በኋላ እንደ ተሞክሮው ግኝት ሥልጠናዎቹን በከፍተኛ መጠን ለማስፋፋት መታቀዱም ተገልጿል፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ተቋም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ውስጥ በጨርቃ ጨርቅ አምራችና ላኪዎች አማካኝነት 170 ሺሕ አዲስ የቅጥር ዕድሎች እንደሚፈጠሩ፤ በተመሳሳይም የቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ተቋም 158,600 አዲስ ቅጥር እንደሚፈጠር ተተንብየዋል፡፡ በዚህ ትንበያ መነሻነት የየንዑስ ዘርፎቹ የሠለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት በቀጣይ ዓመታት ይበልጥ እንዳይሰፋ ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡

የሥልጠናውን ዕቅድ የቀረፀውና አፈጻጸሙን የሚመራው ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የተሰኘው የአምስት አማካሪ ድርጅቶች ስብስብ ሲሆን፣ የእንግሊዝ መንግሥት አካል የሆነው የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ዲኤፍአይዲ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉን ለመደገፍ ባበረከተው የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ ነው፡፡

ዲኤፍአይዲ (Private Enterprise Programme Ethiopia – PEPE) ወይም ‹‹የግልድርጅት ፕሮግራም በኢትዮጵያ›› የተሰኘ ከ2005/6 እስከ 2013/4 ድረስ ለሰባት ዓመታት የሚዘልቅ የ70 ሚሊዮን ፓውንድ (2.2 ቢሊዮን ብር) የልገሳ ገንዘብ የመደበለት በኢትዮጵያ የሀብት ፈጠራንና የግሉን ዘርፍ ለማጎልበት የወጠነው ግዙፍ ፕሮግራም ነው፡፡ አብዛኛው የፔፔ የልገሳ ገንዘብ ደግሞ በኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ አስፈጻሚነት፣ ለሴቶችና ለድሆች ይበልጥ የሥራ ዕድል እንደሚያስገኙ በሚታመኑ አራት ዘርፎች እየዋለ ነው፡፡ እነዚህም ጥጥ-ጨርቃ ጨርቅ፣ የቁም እንስሳት-ቆዳ፣ አትክልት-ፍራፍሬና የፋይናንስ ተደራሽነት ናቸው፡፡

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ከላይ በተጠቀሱት ዘርፎች ውስጥ ያሉ ዘርፍ ተኮር ማነቆዎችን በመለየትና ሁነኛ መፍትሔዎችን በመቅረፅ እንዲሁም ከባለድርሻዎች በተለይም በዘርፉ ከተሰማሩ የግል ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት፣ የግል ክህሎት እንዲጨምር በዚህም ይበልጥ የበዙ ሥራ አጦችንና ሴቶችን እንዲቀጥሩ የማሳለጥ ተግባር ያከናውናል፡፡ በተለይም የግሉ ዘርፍ ሀብቱን ለማፍሰስ ደፍሮ በማይሳተፍባቸው ወይም በማያዋጣውና ከላይ እንደተጠቀሰው ያሉ ችግር ፈቺ ውጥኖችን ቀምሮ በወጪ መጋራት መርህ ከፊል ወጪውን በመሸፈንና የቴክኒክ እገዛ በማበርከት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጥረት እንደሚያበረታታ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነር የሚባለው ስብስብ የሚያካትተው ‹‹የግል  ድርጅት ፕሮግራም በኢትዮጵያ›› ጥላ ሥር ከሚታቀፉ በርካታ የልማት ዕቅዶች መካከል አብዛኛውን ዕቅዶች እንዲያስፈጽሙና እንዲያስተዳድሩ በዲኤፍአይዲ የተቀጠሩ አምስቱ የልማት አማካሪዎች ዲኤአይ አውሮፓ (ዋነኛውና መሪ አማካሪ)፣ ፈርስት ኮንሰልት፣ ኢንክሉድ፣ ኢታድና ቢካድ የተባሉት አማካሪዎች ስለመሆናቸው ከኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች