Thursday, February 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገሪቱ መድኃኒት አምራቾች የሚታሰበውን የምርት መጠን ማስመዝገብ አልቻሉም

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመድኃኒት ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው 20 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንዳልተቻለ ተገለጸ፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መጨረሻ ዓመት ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ 20 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ የታቀደ ቢሆንም ከሁለት ሚሊዮን ዶላር የበለጠ ገቢ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በአገር ውስጥ ካሉት 22 መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች መካከል፣ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ የጀመሩት ጥቂቶች ሲሆኑ ‹‹ባለው ምርት የአገር ውስጥ ገበያንም መሸፈን አልተቻለም፡፡ ካፕሱሎችና የእንስሳት የክትባት መድኃቶች እንዲሁም ሌሎች ወደ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ይላካሉ፡፡ የእንስሳት ክትባት በመላኩ ረገድ ደህና ነን፤›› ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስ ናቸው፡፡

እንደ ዶ/ር መብራህቱ ገለጻ፣ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች አቅማቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ በማገዝ እስከ 50 በመቶ የአገር ውስጥ ገበያን እንዲሸፍኑ ማድረግ ብሎም ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ታቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፋብሪካዎቹ ከ60 በመቶ በላይ አቅማቸውን መጠቀም አልቻሉም፡፡ በመሆኑም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አፈጻጸም ከታቀደው በታች ሊሆን ችሏል፡፡

የአቅም ውስንነት፣ ማምረት የሚችሉ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ አለመግባት፣ በዘርፉ የተጠበቀውን ያህል ውጤት ለማግኘት ካልተቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የልዩ ልዩ ማበረታቻ ድጋፎች ማነስ፣ የመሬት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ዕቅዱ ግቡን እንዳይመታ አድርጓል ተብሏል፡፡ ‹‹ምቹ አድርጐ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሄድንበት መንገድ በቂ አልነበረም፤›› ሲሉ በመንግሥት በኩል የነበረውን ክፍተት ዶ/ር መብራህቱ ገልጸዋል፡፡

በማምረት ላይ የሚገኙት ፋብሪካዎች ከአቅም በታች ለማምረታቸው የፋብሪካዎቹ የአሠራር ችግርም ድርሻ እንዳለውና ከመንግሥት በኩልም ‹‹ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ አላደረግንም፤›› ሲሉ የመንግሥትም ኃላፊነት መጓደሉን ይናገራሉ፡፡

አቶ አስመላሽ ገብሬ የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ሜዲካል ሰፕላይ ሴክተር አሶሴሽን ጸሐፊና የአስሚ ኢንዱስትሪ ጄኔራል ማናጀር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት መንግሥት ለዘርፉ የተለያዩ እገዛ እያደረገ ቢገኝም፣ ለምርት የሚያስፈልጉትን ጥሬ ዕቃዎች አገር ውስጥ ማምረት እስካልተቻ ድረስ ብዙ መሥራት እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡  

‹‹ጥሬ ዕቃ ከውጭ ይመጣል፡፡ ነገር ግን አሁን ጥሬ ዕቃ ማቅረብ የምንችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሜዲስናል ሹገር፣ ስታርችና ለካፕሱል ማምረቻ የሚሆን ቦንማሮ አለን፡፡ ይህንን ሥራ ላይ ለማዋል ቴክኖሎጂው ያስፈልጋል፤›› የሚሉት ዶ/ር መብራህቱ፣ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ወደ ማምረቱ እንዲገቡ ማድረግ የሚል ሐሳብ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ 20 የማድረስ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ግን ተሳክቷል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሥራ ያልጀመሩ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ ‹‹እነዚህ ፈጥነው ወደ ሥራ መግባት አለባቸው፡፡ ከመሬት ጋር በተያያዘና በራሳቸው ድክመት ወደ ሥራ ያልገቡ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ ይህም የተጠበቀውን ያህል እንዳናመርት እንቅፋት ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመድኃኒት ፋብሪካዎችን ቁጥር ስምንት ለማድረስ መታቀዱን የገለጹት ዶ/ር መብራህቱ፣ ከአመራረት ቴክኒክ፣ ከሰነድ አያያዝ፣ ከሰው ኃይል፣ ከአካባቢ ጀምሮ ብዙ መሠራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ አኳያ ባለፉት ጊዜያት በከፍተኛ በጀት በተጀመረው በኢትዮ ጀርመን የአቅም ግንባታ ፕሮግራም መሠረት የተወሰኑትን ፋብሪካዎች ማብቃት ተችሏል ተብሏል፡፡ እንደ ዶ/ር መብራህቱ የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መሥፈርት ለማሟላት ፋብሪካዎቹን የማማከር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ከተፈተሹ ስምንት ፋብሪካዎችም ሁለቱ ብቻ መሥፈርቱን አሟልተው ሰርቲፊኬት ወስደዋል፡፡ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ፋብሪካዎችም ሰርቲፊኬት ለማግኘት ጫፍ ደርሰዋል፡፡

በዘርፉ የታየውን ከዕቅድ በታች የሆነ አፈጻጸም እንደሚያሻሽል የታመነበት ብሔራዊ የመድኃኒት አምራቾች ረቂቅ ስትራቴጂ ተቀርጾ፣ ባለፈው ማክሰኞ በካፒታል ሆቴል በባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ጆርጆ ሮሺኞ፣ በመድኃኒት ዘርፍ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ባለሙያ ናቸው፡፡ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የሚቆየው ስትራቴጂ ሲዘጋጅም አማካሪ ነበሩ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ጥራት ያለው መድኃኒት ማቅረብ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ፣ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን የሚያሟሉ አምራቾች እንዲፈጠሩ ማገዝ ከስትራቴጂው ዓላማዎች መካከል ናቸው፡፡ ይህንንም ለማድረግ መንግሥት በዘርፉ ስለሚታዩ ተግዳሮቶች በየጊዜው ጥናት በማድረግ ለአምራች ድርጅቶች ድጋፍና እገዛ ሊያደርግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ አብነት ድንበሩ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች አስመጪዎችና አከፋፋዮች የጋራ መድረክ ኮሚቴ ሰብሳቢና የካሮጋ ፋርማሲዩቲካል አስመጪና አከፋፋይ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስትራቴጂው አስመጪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ የሚያስችሉ ዕድሎችን አስቀምጧል ያሉት አቶ አብነት፣ ስትራቴጂው በሥራ ላይ ከዋለ አገሪቱ በመድኃኒት ምርት ራሷን እንደምትችል ያምናሉ፡፡

የአገሪቱ የመድኃኒት ገበያ ከ400 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ በየዓመቱም የ25 በመቶ ዕድገት የሚያሳይ ሲሆን፣ በ2012 ፍሮስት ኤንድ ሱሊቫን የተባለ አጥኚ አካል የአገሪቱ የመድኃኒት ገበያ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡ አስፈላጊ ተብለው ከተዘመገቡ 380 የመድኃኒት ምርቶች መካከል የአገር ውስጥ አምራቾች ከ90 ዓይነት በላይ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ዓምና ከ44 ሚሊዮን ብር የበለጠ የገበያ ሽፋን መስጠትም አልቻሉም፡፡ 

ይህንን ገበያ ለማርካት 22ቱ ፋብሪካዎች የሚቻላቸው አይመስልም፡፡ በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት 200 አስመጪና አከፋፋዮች ምርቶችን እያስመጡ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች