የፓልም የምግብ ዘይት ንግድ ለአራት የግል፣ ለአራት ኢንዶመንቶችና ለአንድ የመንግሥት ኩባንያ ብቻ መሰጠቱ ያስቆጣቸው 15 ኩባንያዎች አቤቱታቸውን ለንግድ ሚኒስቴር አቀረቡ፡፡ ቅሬታ አቅራቢ ኩባንያዎቹ የዘይት ንግድ ለተወሰኑ ኩባንያዎች ብቻ እንዲሰጥ በተወሰነበት ወቅት፣ በተናጠል ያቀረቡት አቤቱታ ምላሽ ባለማግኘቱ ጥያቄያቸውን የጋራ በደብዳቤ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎቹ ቀደም ሲል በዘይት ንግድ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጌት አስ ኢንተርናሽናል፣ ካንትሪ ትሬዲንግ፣ ትራኮን ትሬዲንግና ነፃ ትሬዲንግ ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች በጻፉት ደብዳቤ፣ አገሪቱ የምታራምደው የነፃ ገበያ ሥርዓት እንደመሆኑ፣ የፓልም ዘይት ንግድ ለሁሉም ኩባንያዎች ክፍት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ የንግድ ሥራው ለተወሰኑ ነጋዴዎች ብቻ መሰጠቱ የንግድ ሥርዓቱን ከማዛባቱ በተጨማሪ፣ የንግድ ውድድርን የሚያቀጭጭ ስለሆነ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ አያደርግም የሚል አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
ንግድ ሚኒስቴር በቅርቡ ወዲህ መዛባት የታየበትን የፓልም ዘይት ንግድ ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል በማለት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመምከር ሥራውን በጥቅሉ ለዘጠኝ ኩባንያዎች መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ሥራው የተሰጣቸው የግል ኩባንያዎች በላይነህ ክንዴ አስመጭና ላኪ፣ ሆራይዘን ኢትዮጵያ፣ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና አልሳም ትሬዲንግ ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ይህ ሥራ የተሰጣቸው የዘይት ፋብሪካ በመገንባት ላይ ናቸው ተብሎ ነው፡፡ አልሳም ከሲንጋፖር ኩባንያ ዊልማር ጋር በሰባት ቢሊዮን ብር የዘይት ፋብሪካን ጨምሮ 14 ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪም ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ቡሬ አካባቢ ግዙፍ የዘይት ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ሆራይዘን ኢትዮጵያም እንዲሁ የዘይት ፋብሪካ ፕሮጀክት ያለው ሲሆን፣ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ደግሞ ከፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ አማሬሳ የምግብ ዘይት አክሲዮን ማኅበርን የገዛ በመሆኑ ሥራው ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች የዘይት ፋብሪካ በመገንባት ሒደት ላይ ቢሆኑም፣ ከውጭ ዘይት አስመጥቶ ከማከፋፈል ጋር የሚያገናኘው ነገር ባለመኖሩ አሥራ አምስቱ ኩባንያዎች ሥራው ሊሰጣቸው እንደማይገባ እየሞገቱ ናቸው፡፡
ከግል ኩባንያዎች በተጨማሪ የኢንዶመንት ኩባንያዎች የሆኑት ጉና ትሬዲንግ፣ ቢፍቱ አዱኛ ቢዝነስ፣ አምባሰል ንግድ ሥራዎችና ወንዶ ንግድና ኢንቨስትመንት ይህ ሥራ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ መንግሥት የሸቀጥ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በቅርቡ ያቋቋመው አለ በጅምላ ይገኝበታል፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ቅሬታ አቅራቢ ነጋዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት የግል ኩባንያዎችን ከዘይት ንግድ አስወጥቶ ራሱ መሥራት ሲጀምር ያን ያህል ቅሬታ አልተሰማም፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለተወሰኑ ኩባንያዎች ብቻ መሰጠቱ በብዙ አቅጣጫዎች ጎጂ ነው ብለዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በግንቦት ወር በጻፈው ደብዳቤ እነዚህ ድርጅቶች ከቀረጥና ከታክስ ነፃ እንዲሆኑና የመድን ሽፋናቸውም 50 በመቶ ብቻ እንዲሆን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ በተመሳሳይ ወቅት በጻፈው ደብዳቤ ኩባንያዎቹ የዘይት ግዥ ጥያቄ ሲያቀርቡ ባንኮች እንዲያስተናግዷቸው አዟል፡፡
ከ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ፓልም ዘይት በዓመት ወደ አገር ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ሰፊ ሥራ ለተወሰኑ ኩባንያዎች ብቻ እንዲሰጥ መደረግ አልነበረበትም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ ነጋዴዎች፣ የንግድ ሚኒስቴርን ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡