Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የታሪፍ ድርድር ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የኃይል ሽያጭ ታሪፍ ላይ ድርድር ተጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከታንዛኒያ አቻው ጋር ሰሞኑን በዝርዝር የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ውይይት ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ መኩሪያ ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል ሁለቱ አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ግብይት ለማካሄድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

‹‹አሁን በኃይል ሽያጭ ታሪፍ ላይ ለመወሰን ውይይት እየተካሄደ ነው፤›› በማለት አቶ መኩሪያ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የምትሸጠው ከኢትዮጵያ እስከ ኬንያ ድረስ እየተዘረጋ ባለው የኃይል መስመር ነው፡፡ ከኬንያ እስከ ታንዛኒያ ደግሞ 400 ኪሎ ቮልት መሸከም የሚችል የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በመገንባት ላይ ነው፡፡

አቶ መኩሪያ እንደገለጹት፣ የታንዛኒያ መንግሥት በኬንያ በኩል በተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኤሌክትሪክ ሲቀበል ለመስመሩ ኪራይ ይከፍላል፡፡ አቶ መኩሪያ ጨምረው እንደገለጹት፣ ወደ ኬንያ የሚዘረጋው መስመር እየተጠናቀቀ በመሆኑና ወደ ታንዛኒያም የሚዘረጋው መስመር እየተገባደደ በመሆኑ፣ ኬንያና ታንዛኒያ በተመሳሳይ ወቅት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

‹‹በተመሳሳይ ወቅት ኤሌክትሪክ ማስተላለፍ ባይቻል እንኳ፣ ግፋ ቢል ሊኖር የሚችለው ልዩነት ከአንድ ዓመት አይበልጥም፤›› በማለት አቶ መኩሪያ ፕሮጀክቱ እየተፋጠነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኬንያ መንግሥት ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ባካሄደው ድርድር 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድንበር አካባቢ ለሚገኙ የኬንያ ከተሞች መንግሥት 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

በሦስቱ አገሮች መካከል እየተዘረጋ የሚገኘው የኃይል መስመር በሚጠናቀቅበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ለሁለቱ አገሮች 800 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ይጠበቅባታል፡፡ ለሁለቱ አገሮች የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ከጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ተነስቶ በወላይታ በኩል እየተዘረጋ ባለው የኃይል መስመር ነው፡፡

ለአፍሪካና ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የቀረፀችው ኢትዮጵያ፣ በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በርካታ ስኬቶችን አልማለች፡፡

በአሁኑ ወቅት 2,368 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ላይ የደረሰችው ኢትዮጵያ፣ አሁን ግንባታው 42 በመቶ ከተጠናቀቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት፣ በዚህ የበጀት ዓመት የተሻለ የዝናብ መጠን ከተገኘ ሥራ ከሚጀምረው ጊቤ ሦስት 1,870 ሜጋ ዋት፣ አሁን 72.3 በመቶ ከተጠናቀቀው ካሉቶ ጂኦተርማል 70 ሜጋ ዋት፣ 59.6 በመቶ ከተጠናቀቀው ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ፕሮጀክት 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አገሪቱ ከውኃ 50 ሺሕ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከጂኦተርማል 10 ሺሕ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እንዳላት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች