- Advertisement -

የድምፅ አልባ ዜጎች ፍላጎት እንዲደመጥ ማረጋገጫ ይሰጥ!

ምርጫ 2007 ተጠናቋል፡፡ የሚቀር ነገር ቢኖር አጠቃላይ ውጤቱን መግለጽ ነው፡፡ ከወዲሁ ግን ኢሕአዴግና አጋሮቹ የፓርላማውን 442 መቀመጫዎች ማሸነፋቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ተደርጓል፡፡ ጊዜያዊ ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርቲያቸውን የመረጡትን ብቻ ሳይሆን፣ ያልመረጡትን ጭምር እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ መልካም ሐሳብ ነው፡፡

ምርጫ የዴሞክራሲ አንደኛ ምሰሶ ሲሆን፣ በምርጫ አማካይነት በሰላምና በነፃነት ተወዳድሮ ማሸነፍና መሸነፍ ያለ ነው፡፡ ዋናው ትልቁ ነገር ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ነፃ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት እንዴት ይቀጥላል የሚለው መሆን አለበት፡፡ በምርጫ ለተሸነፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸውን የሰጡ ወገኖች ድምፅ እንዴት መሰማት አለበት የሚለውም ተጠቃሽ ነው፡፡ አሁን በምርጫው በተገኘው ውጤት መሠረት አሸናፊውም ሆነ ተሸናፊው ስለሕዝብ ድምፅ መከበር የየራሳቸውን አቋም ሲያንፀባርቁ፣ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ‘የሕዝብ ድምፅ ይሰማ’ መባልም አለበት፡፡ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እናንሳ፡፡

ዴሞክራሲ በባህሪው ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከረና እየጎለበተ የሚሄድ የመንግሥት መመሥረቻ ብቸኛው መንገድ እንዲሆን፣ ለፖለቲካው ምኅዳር ጠቃሚ የሆኑ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ ባህል ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በእኛ አገር ለዓመታት እንደታየው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት መርዛማ መሆን የለበትም፡፡ የፓርቲን ጥቅም ከአገር ጥቅም በላይ በማስቀደም ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንዳይፈጠር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጠ ዴሞክራሲን ማጎልበት አለባቸው፡፡ ኢዴሞክራሲያዊነትንና ሕገወጥነትን ባስወገዱ መጠን በእርስ በርስ ግንኙነታቸውም ሆነ የፖለቲካ ምኅዳሩን የተሻለ ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ነፃና ሰላማዊ ከባቢ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ሕዝብም በነፃነት የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖረው ይረዳሉ፡፡ ሕዝብ ነፃነት ሲሰማው ተሳትፎው ይጨምራል፡፡ ለፍላጎቶቹ አቅም በፈቀደ መጠን እርካታ ስለሚያገኝ መንገዱ ሁሉ ቀና ይሆንለታል፡፡

በምርጫ አብላጫውን ወይም ሙሉ በሙሉ አሸንፎ ፓርላማ የተቆጣጠረ ፓርቲ ድምፅ ከሰጡት ባልተናነሰ ለተቃዋሚ ድምፆችም ማሰብ አለበት፡፡ መንግሥት የመሠረተው ገዥ ፓርቲ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ሲነድፍ ለእነዚህ ድምፅ አልባ ወገኖች መጨነቅ አለበት፡፡ ዴሞክራሲ አሳታፊ ነው ሲባል የአባላትንና የደጋፊዎችን ብቻ ሳይሆን፣ የተለየ አመለካከት ያላቸው ወገኖችን ሐሳብ ማካተት ጭምር ነው፡፡ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ወደ ፓርላማው ሲመሩ፣ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎች የሕዝብ አስተያየቶችን ሲሰበስቡ፣ በተቻለ መጠን የተለየ አቋም የሚያንፀባርቁ ወገኖችን ድምፅ መስማት አለባቸው፡፡ የፓርላማ አባላት ታማኝነታቸው ከምንም ነገር በላይ ለወከላቸው ሕዝብና ለህሊናቸው መሆን አለበት ሲባል፣ እነዚህን ድምፅ አልባ ዜጎች ያስቡዋቸው ለማለት ነው፡፡

ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ ‘ሕዝቡ በሰጠን ድምፅ ነው የተመረጥነው’ ሲሉ፣ በተቃራኒ አቅጣጫ የቆሙ ዜጎች ለአገር ጠቃሚ ሐሳብ እንደሚያበረክቱ በማሰብ እነዚህን ወገኖች ማዳመጥ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል አገር የሚመራው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ መወያየትና መደራደር አለበት፡፡ አሁን ባለው ጊዜያዊ ውጤት መሠረት የፓርላማውን 81 በመቶ መቀመጫዎች ተቆጣጠረ ማለት፣ የ81 በመቶ መራጮችን ድምፅ አገኘ ማለት አይደለም፡፡ በአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት መሠረት በተሻለ ቁጥር የመራጮችን ድምፅ አገኘ ሲባል፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ለማሸነፍ አያስችላቸው እንጂ የማይናቅ ቁጥር ያለው የሕዝብ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ያ የሕዝብ ድምፅ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መሰማት አለበት፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር በጋራ መምከርና መግባባት ላይ መድረስ አሁን ያለውን የደፈረሰ ግንኙነት ያጠራዋል፡፡ ለዓመታት የዘለቀውን የተበላሸ የፖለቲካ ምኅዳር ያስተካክለዋል፡፡ የሕዝቡን ተሳትፎ ያሳድጋል፡፡ ይኼ በጥብቅ ይታሰብበት፡፡

ዜጎች በአገራቸው የደኅንነት ሥጋት እንዳይገባቸውና የየዕለት ውሎአቸው ሰላማዊ እንዲሆን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ጥቃት ይደርስብናል ወይም ተፅዕኖ ይደረግብናል ብለው እንዳይሰጉ፣ የሕግ የበላይነት መኖር መተኪያ የለውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍርድ ቤቶች በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች ያለምንም ተፅዕኖ ሥራቸውን በአግባቡ ሲወጡና የሕግ የበላይነትን ሲያስከብሩ ዜጎች በሰላም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውም ይጨምራል፡፡ ሕገወጦች የሕግ የበላይነትን እንዳይጋፉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይጣሱ ልዩ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር እንዲረጋገጥ ሲደረግ፣ የተለየ ሐሳብ ወይም አማራጭ ያላቸው ዜጎች ድምፅ ይደመጣል፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ የሲቪል ማኅበራት አለመኖር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ሲቪል ማኅበራት ዜጎች በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸው እንዲከበሩና እነዚህን መብቶች እንዲንከባከቡ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ሲቪል ማኅበራቱ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ መብቶቻቸውን እንዲረዱ ከማብቃታቸውም በላይ፣ ነውጥና ሁከት እንዲወገዱ ሁነኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ አንድ ዜጋ መብቱን ባወቀ መጠን ኃላፊነት እንዲሰማውና በአገር ግንባታ የራሱን ድርሻ እንዲጫወት ይረዳሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት (ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ…) ሲጠናከሩና በብቃት ሲመሩ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ተግባራቸውን በአግባቡ እየተናበቡ እንዲያከናውኑ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ሲቪል ማኅበራትና የዴሞክራሲ ተቋማት ባበቡና በተጠናከሩ መጠን የሕዝቡ በራስ የመተማመን መንፈስ ይጨምራል፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ለአገርም የሚጠቅመው ይኼው ነው፡፡

ሚዲያው የሙያ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ ሲሠራ ነፃነቱንና ገለልተኝነቱን ከማረጋገጡም በላይ፣ ለድምፅ አልባ ዜጎች ድምፅ ይሆናቸዋል፡፡ በተለይ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚዲያዎች ከገዥው ፓርቲ ባልተናነሰ፣ ለአማራጭ ሐሳቦች በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው፡፡ ድምፃቸው የማይሰማ ዜጎች ወይም ቡድኖች ለአገር ጠቃሚ ሐሳብ ስላላቸው መስተናገድ ይኖርባቸዋል፡፡ እስካሁን ያለው ባይተዋር የማድረግ አባዜ መገታት አለበት፡፡ ድምፃችን መሰማት አለበት የሚሉ ወገኖች እንዲስተናገዱ ድጋፍ ማድረግ ለዴሞክራሲው ዕድገት ያግዛል እንጂ ችግር አይፈጥርም፡፡ ይኼም በብርቱ ይታሰብበት፡፡

ገዥው ፓርቲ መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን ድምፅ አግኝቶ ፓርላማውን በአባላቱና በአጋሮቹ ሲሞላው፣ የሌላውን ወገን ድምፅ ያገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማግለል የለበትም፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለመሥራት ቃል ሲገባ፣ ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ያልተደረገውን ግማሽ መንገድ ድረስ የመሄድ አዝማሚያ ማሳየት አለበት፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የደጋፊዎቻቸው ድምፅ እንዲሰማና ግንኙነት እንዲጀመር ከአሁኑ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ከምርጫው በኋላ በኩርፊያም ሆነ በሌላ ምክንያት የተቀዛቀዙ ካሉም ድጋፋቸውን ለሰጣቸው መራጭ ሕዝብ ሲሉ ይንቀሳቀሱ፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን ደካማ ጎናቸውን በመፈተሽ በለውጥ መንፈስ ይነሳሱ፡፡ የግንኙነቱንም ዘይቤ በመቀየር ሥልጡን ያድርጉት፡፡ እስከዛሬ የነበረውን የተበላሸ ግንኙነት በዘመናዊ ገጽታ ይቀይሩት፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንደማይሠራ የሚሰብኩ ወገኖችን ሐሳብ በተሻለ ሥራ ያምክኑት፡፡

ገዥው ፓርቲም በአሁኑ ጊዜ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ያሉ ወገኖች ተስፋ ሳይቆርጡ በፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስብበት፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ እንዳበቃለትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ እንደተቀበረ በሰፊው ሲወራ፣ አገሪቱ እዚህ ደረጃ ላይ እንዳልደረሰች ማረጋገጫ ማቅረብ አለበት፡፡ ተቃዋሚዎችን ሕዝብ አልመረጣቸውም ተብሎ ጥጋችሁን ያዙ ማለት ሳይሆን፣ ለመረጣቸው ሕዝብ ክብር ሲባል ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸው መቀጠል እንዳለበት መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ድምፅ አልባ የሆኑ ወገኖች ፍላጎት እንዲደመጥ መንግሥት ማረጋገጫ መስጠት ይኖርበታል!

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

እየፀደቁ ያሉ አዋጆች ለሕዝብና ለአገር የሚኖራቸው ፋይዳ ይታሰብበት!

መንግሥት በስኬት አገር ለማስተዳደር ሕጎችን ሲያወጣም ሆነ ፖሊሲ ሲነድፍ፣ የሚቀርቡለትን ምክረ ሐሳቦች በአግባቡ ማስተናገድ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡ ቀደም ሲል በነበሩ ዓመታት የተለያዩ ሕጎች ተረቀው...

የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ያሉ ዕርምጃዎች ይታሰብባቸው!

መንግሥት የዋጋ ንረቱን ከ30 በመቶ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማድረጉን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካይነት በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ገበያው ውስጥ ያለው የምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋ የሚያሳየው...

አስፈሪውን የርዕደ መሬት አደጋ ለመከላከል አቅም ይገንባ!

የስምጥ ሸለቆ አካል በሆነው አዋሽ አካባቢ ለወራት የዘለቀው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉልበቱ እየጨመረ ከፍተኛ ሥጋት እየደቀነ ነው፡፡ በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ...

አገራዊ መልካም እሴቶች በፋይዳ ቢስ ድርጊቶች አይጎዱ!

በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሚኮሩባቸውና ለመጪው ትውልድ ጭምር ከሚያስተላልፏቸው መልካም እሴቶቻቸው መካከል በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖር፣ የብሔር ወይም የእምነት ገደብ ሳይኖር ተጋብቶ መዋለድ፣ ችግሮች...

ሰቀቀን!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ሰነበታችሁ ወገኖች በሙሉ፡፡ እኔ ወንድማችሁ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሳምንት አልፎ ሳምንት ሲተካ፣ ሁላችንም ሰላም ሆነን አገራችንን ባለን ዕውቀት፣ ልምድ፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና...

በተቃርኖ ፖለቲካ አገር እንዳትጎዳ ጥንቃቄ ይደረግ!

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፋት እየተሰሙ ያሉ ተቃርኖዎች አድማሳቸው ከመስፋቱ በፊት መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአገር ሁለንተናዊ ጉዳዮች ብሔራዊ የምክክር መድረክ ሊዘጋጅ ደፋ ቀና እየተባለ ባለበት ወቅት፣...

አዳዲስ ጽሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ቀኑን ሙሉ ከዋሉበት የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰው ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው]

የምን ስብሰባ ላይ ዋልኩ ነበር ያልከኝ? የሥራ አስፈጻሚ። የምን ሥራ አስፈጻሚ? የገዥው ሥራ አስፈጻሚ። ምን ገጥሟችሁ ነው የተሰበሰባችሁት? ለመረጠን ሕዝብ ቃል የገባናቸውን ተግባራት አፈጻጸም የምንገመግምበት የተለመደ ስብሰባ ነው። የገባችሁት ቃል...

ሕወሓትን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው መመርያ

በሁለት አንጃ ተከፍሎ የእርስ በርስ የቃላት ጦርነት ውስጥ የገባው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ልዩነቱን ትቶ ወደቀድሞው አንድነቱ በመመለስ የሚጠበቅበትን ጠቅላላ ጉባዔ የማድረግ አልያም...

ባንኮች እየፈጸሙት ያለው አቅርቦትንና ፍላጎትን ያላገናዘበ የውጭ ምንዛሪ ግዥ

የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ ዋጋ እንዲገበይ የወጣው ሕግ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከሰባት ወራት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ሕጉ ተግባራዊ በተደረገበት የመጀመርያው ቀን የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ...

አሳረኛው ኑሮ!

የዛሬው ጉዞ ከቦሌ ወደ ፒያሳ ይሆን ዘንድ ግድ ሆኗል፡፡ ለምን? በኑሮ  ምክንያት፡፡ የታክሲ መሠለፊያው ወሬ የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ ስለሚመጣው ተጨማሪ ታሪፍ ነው፡፡ ‹‹የእኛ ኑሮ...

የግለሰቦች ለመብታቸው ኃላፊነት አለመውሰድ ለአገር ያለው አደጋ

በያሬድ ኃይለመስቀል አንድ የማከብረው ኢኮኖሚስት አንድ መጽሐፍ እንዳነብ መራኝና ማንበብ ጀመርኩኝ። ይህንን መጽሐፍ ሳነበው ከዋናው ሐሳብ ወጣ ብሎ ስለ “የነፃ ተጓዦች ሀተታ” (The Free Rider...

‹‹የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ማጠናከር ያስፈልጋል›› አቶ ፍፁም አብርሃ፣ የአሚጎስ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር ከተመሠረተ አሥራ ሁለት ዓመታት ሆኖታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት 8,500 አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ አሚጎስ ስለተመሠረተበት ዓላማ፣ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት፣ የብድርና...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን