– ከጁባ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ 20 ሚሊዮን ብር የመዘበሩ በቁጥጥር ሥር ዋሉ
በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከሁለት ዓመት በላይ ካስቆጠሩት፣ የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር የተያያዙ ሌሎች አምስት የንግድ ተቋማት ላይ ክስ ለመመሥረት በምርመራ ላይ መሆኑን፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ መላኩ ፈንታና በምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ገብረጊዮርጊስ እንዲሁም በሌሎች የባለሥልጣኑ ሠራተኞችና በንግድ ሥራ በተሰማሩ የግል ተቋማት ባለሀብቶች ከግብርና ከታክስ ጋር በተገናኘ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ረጅም የምርመራ ጊዜ ቢወስድም ክስ ከተመሠረተባቸውና ክርክር ከተጀመረ ከዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን በማየት ላይ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግ ምስክርን በመስማት ላይ ይገኛል፡፡
የእነ አቶ መላኩ ፈንታና ሌሎች የባለሥልጣኑ ሠራተኞችና ባለሀብቶች የክስ ሒደት ከላይ በተገለጸው ደረጃ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ የወንጀል ምርመራ ጋር የተያያዙ ናቸው ያላቸው አምስት ድርጅቶች በመንግሥት ላይ የ361.6 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዳደረሱ በማረጋገጥ፣ በተጨማሪ ምርመራ ላይ እንደሚገኝ ለምክር ቤቱ አሳውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌማን ባለፈው ሐሙስ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት፣ ‹‹በቀድሞ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣናት፣ አንዳንድ የባለሥልጣኑ ሠራተኞችና ከፍተኛ ነጋዴዎች ላይ ተጀምሮ ከነበረው ምርመራ ጋር በተያያዘ የአገር ውስጥ ግብርና የጉምሩክ ቀረጥ ባለመክፈል በተጠረጠሩ አምስት የግል ኩባንያዎች ላይ የኢንስፔክሽን ኦዲት በማስደረግ በተገኘው ማጣራት፣ 361.6 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ታክስ አለመከፈሉ በመረጋገጡ ምርመራው እየተከናወነ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት የተጠረጠሩትን ድርጅቶች ማንነት አልገለጹም፡፡ የድርጅቶቹን ማንነት ለማጣራት ሪፖርተር ያደረገው ሙከራም አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በእነ አቶ መላኩ ፈንታና በሌሎች ባለሀብቶች ላይ ክስ በመሠረተበት ወቅት፣ ምርመራ የተደረገባቸውና ክስ ያልተመሠረተባቸው 15 የግል ኩባንያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡
እነዚህም ኒያላ ሞተርስ፣ ፔትራም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሞኤንኮ፣ ጌትአስ ትሬዲንግ፣ አልሳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሜቴክ፣ አይካ አዲስ ትሬዲንግ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ ሆላንድ ካርስ፣ ቶታል ኢትዮጵያ፣ ሚድሮክ፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ ድሬ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ፣ ኢትዮ ሌዘር፣ ኢትዮ ቆዳ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮሚሽኑ በሌሎች በጠረጠራቸው የሙስና ወንጀሎች ላይም ምርመራ እያደረገ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
ቦሌ ክፍለ ከተማ በሐሰተኛ ማስረጃ መሬት እንዲያገኙ ተደርጓል በሚል በቀረበ ጥቆማ፣ 89 የመሬት ጉዳዮች ላይ ምርመራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በተለያዩ የግንባታ ሳይቶች ለሚከናወኑ ግንባታዎች የሚውሉ ጠጠር፣ ፕሪካስትና ብሎኬት ግዥ ጋር በተያያዘ አምስት ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ በተጠረጠሩ ሠራተኞችና አቅራቢዎች ላይ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደቡብ ሱዳን (ጁባ) ቅርንጫፍ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በመመሳጠር ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በመውሰድ ለግል ጥቅም በማዋላቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡