– ሰባት ሰዎች በጭስ ታፍነው ጉዳት ደርሶባቸዋል
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሸራ ተራ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ፣ ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አካባቢ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ግምቱ ያልታወቀ ንብረት ወደመ፡፡
አደጋውን ለመቆጣጠር በአካባቢው ያለው የፕላስቲክ ጫማ፣ ዘይት፣ ሳሙና፣ ብርድ ልብስና ለመቀጣጠል አደገኛ የሆኑ ዕቃዎች ክምችት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ አካባቢው በጭስ በመታፈኑ እሳት አደጋ ተቆጣጣሪዎች ወደ ውስጥ ደፍረው ለመግባት እንዳዳገታቸውና ለረዥም ሰዓታት እሳቱን መቆጣጠር ሳይቻል መቆየቱንም አክለዋል፡፡
የእሳት ቃጠሎው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አካባቢ መጀመሩን በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ነጋዴዎች በመተባበር ከየጊቢው ውኃ በመቀባበልና በየጣራው ላይ ወጥተው ውኃ በመርጨት የተቻላቸውን ካደረጉ በኋላ፣ የእሳት አደጋ መከላከል ሠራተኞች እንደደረሱላቸውም ተናግረዋል፡፡
የእሳቱ መነሻ በውል ባይታወቅም ከመሀል አካባቢ እንደተነሳና ቤቶቹም እርስ በርስ የተያያዙ በመሆናቸው፣ ለመኪና መግቢያ አስቸጋሪ እንደነበር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡ እሳቱ እየጨመረ በመሄዱ ከሰባቱም ክፍለ ከተማ የእሳት መከላከያ ማሽነሪዎች ቢመጡም፣ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት አለመጥፋቱም ታውቋል፡፡ አራት የውኃ ቦቴዎች ውኃ በማቅረብ ሲተባበሩ እንደነበር፣ አንድ የኤርፖርቶች የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪ ተጨምሮ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡ የተዳፈነ እሳት፣ የፕላስቲክ ዕቃዎችና ጨርቃ ጨርቆች ለማጥፋት ሲያስቸግሩ ተስተውሏል፡፡ ሠራተኞቹ እሳቱን እያጠፉ ባለበት ጊዜ ከሥር ከሥር የሱቆቹ ባለቤቶችም ከተቃጠለው ዕቃ ክምር የተለያዩ ዕቃዎችን ለማውጣት ሲረባረቡ ታይተዋል፡፡
አብዛኞቹ በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች ዕቃቸውን በማውጣትና እሳቱ ያልደረሰበት ቦታ በመከመር የማዳን ሥራ ሲሠሩ ተስተውለዋል፡፡ ነጋዴዎቹ አይሱዙ በመከራየት ዕቃቸውን በመጫን ወደተለያዩ ቦታዎች ሲወስዱና ቤታቸውም የተቃጠለባቸው ነዋሪዎች እያለቀሱ በከፍተኛ ሐዘን ሲዋከቡ ታይተዋል፡፡ ንብረታቸውንም አድነው በየቦታው የከመሩት ነጋዴዎች ሲመሽባቸው በላስቲክ እየሸፈኑ ወደ ቤታቸው ለመሄድ ተገደዋል፡፡
በወቅቱ ከአሥር በላይ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች በማሰማራት ከ150,000 ሊትር በላይ ውኃ፣ 300 ሊትር ፎም እንደተጠቀሙ የገለጹት አቶ ሰለሞን መኰንን፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የእሳት አደጋው ተነስቷል ተብሎ የተደወለው ከቀኑ 8፡57 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ከተደወለላቸው በኋላ ግን፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀድሞ በመድረስ ዕርዳታ እንደጀመረ፣ ሌሎቹም ስድስቱ ክፍላተ ከተሞች በየተራ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ከአራት ሰዓት በኋላ ለመቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡ እስከ ዓርብ ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ስለደረሰው ጉዳት መጠን ማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡