Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና ሪል ስቴት ኩባንያ በአራት ቢሊዮን ብር ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፀሐይ ሪል ስቴት ቀጥሎ ሁለተኛው የቻይና ኩባንያ በአራት ቢሊዮን ብር በአዲስ አበባ ከተማ የሪል ስቴት ፕሮጀክት ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኖረ፡፡ ሲኖ ማርክ የተባለው ይህ የቻይና ኩባንያ አገር በቀል ኩባንያ ከሆነው ሳባ ኢንጂነሪንግ ጋር ግንባታ ለማካሄድ ስምምነት የፈጸመው፣ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ለመገንባት ነው፡፡

ግንባታው የሚካሄደው ሳባ ኢንጂነሪንግ ከፕራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በገዛው አዲስ ብሎክ ሼር ኩባንያ ይዞታ በሆነው፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎተራ አካባቢ በሚገኝ 60 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡

የሳባ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሳምሶን በኩረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ሥፍራ ላይ ከፍታቸው 20 ፎቅ የሆኑ 21 ሕንፃዎች ይገነባሉ፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታ አራት ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ በኢንቨስትመንቱ ላይ ሁለቱም ኩባንያዎች እኩል ድርሻ እንደሚኖራቸው ኢንጂነር ሳምሶን ተናግረዋል፡፡

ሕንፃዎቹ በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፉ ሲሆን፣ በተቀረው ቦታ ላይ የተለያዩ የስፖርት ማዕከላት፣ የገበያ ማዕከላት፣ የሕፃናት መጫወቻዎችና አረንጓዴ ሥፍራዎች ይካተታሉ፡፡

ይህ ግንባታ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚጠናቀቅ መሆኑን፣ ሽያጩም ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሚካሄድ ኢንጂነር ሳምሶን ተናግረዋል፡፡

የሕንፃዎቹን ግንባታ ለማስጀመር ባለፈው እሑድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት የሲኖ ማርክ ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ያን ሲን ሊ እንደተናገሩት፣ የሕንፃዎቹ ግንባታ በፈረንሳይ የሕንፃ አሠራር ዘይቤ ይከናወናል፡፡

የቻይና ኩባንያዎችን ጨምሮ የህንድ፣ የቱርክና የአውሮፓ ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከተማ በሪል ስቴት ልማት ለመሳተፍ ፍላጎት ከማሳየት አልፈው ፕሮፖዛል በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ነገር ግን መንግሥት የውጭ ኩባንያዎች በራሳቸው መንገድ፣ በሪል ስቴት ልማት እንዲሳተፉ ለማድረግ የጀመረውን የፖሊሲ ጥናት ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ጉዳዩ በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡

የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ሲጂሲ ኦቨርሲስ መንግሥት ለውጭ ኩባንያዎች መሬት ስለመስጠትም ሆነ ስለመከልከል አቅጣጫ ከመያዙ በፊት፣ በየካ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ አካባቢ ባገኘው መሬት የሪል ስቴት ልማት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ሲጂሲ ኦቨርሲስ ከሌላ የቻይና ኩባንያ ጋር በመሆን ያቋቋመው ፀሐይ ሪል ስቴት በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ2.5 ቢሊዮን ብር በጀት፣ ከፍታቸው 12 ፎቅ የሆኑ የመኖሪያ ሕንፃዎችን እየነባ ይገኛል፡፡

አዲሱ የቻይና ኩባንያ ሲኖ ማርክ ከሳባ ኢንጂነሪንግ ጋር ግንባታ የሚያካሂድበት መሬት ባለቤት አዲስ ብሎክ ሼር ኩባንያ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችን የሚያመርት ሲሆን፣ ሳባ ኢንጂነሪንግ ከፕራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ገዝቶታል፡፡

ሳባ ኢንጂነሪንግ ከኢትዮጵያ ባሻገር በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በመክፈት በውኃ ሥራዎችና በተለያዩ የግንባታና የማማከር ሥራዎች የተሰማራ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡ ሲኖ ማርክ ደግሞ ከአሥር ዓመታት በላይ በሪል ስቴት ልማት ውስጥ እንደቆየ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች