Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኑሮ ውድነት አንገብጋቢ ሆኗል!

በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአንፃራዊ ሁኔታ ጋብ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት እንደገና እያገረሸበት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ምግብ ነክና ምግብ ያልሆኑ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በየዕለቱ ዋጋቸው አልቀመስ እያለ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት እየተፈታተነ ነው፡፡

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሰሞኑን ያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ በራሱ የሚናገረው አለው፡፡ ይኸውም የግንቦት 2007 ዓ.ም. የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 9.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ለጭማሪው በምክንያትነት የተጠቀሰው በግንቦት 2007 ዓ.ም. የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ 141.3 በመቶ ሲሆን፣ በግንቦት 2006 ዓ.ም. ግን 129.1 በመቶ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የግንቦት 2007 ዓ.ም. የምግብ ዋጋ ግሽበት ከግንቦት 2006 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በ10.1 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የዋጋ ግሽበት ሥሌት መሠረት በግንቦት 2007 ዓ.ም. የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 7.5 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡ ይህም በምግብ ዋጋ 6.9 በመቶ፣ ምግብ ነክ ባልሆኑ ደግሞ 8.2 በመቶ የዋጋ ግሽበት ታይቷል፡፡

አሁንም ከኤጀንሲው መረጃ ሳንወጣ በግንቦት 2007 ዓ.ም. ሁሉም የምግብ ክፍሎች ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በተለይ ሥጋ፣ ወተት፣ አይብ፣ እንቁላል፣ ዘይትና ቅባቶች፣ ስኳር፣ አትክልት፣ ጥራጥሬ (በተለይ ምስር) ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም (ያልተፈጨ በርበሬ) የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ናቸው፡፡ በኤጀንሲው መረጃ መሠረት በበቆሎ፣ በማሽላና በስንዴ ዋጋ ላይ መጠነኛ ቅናሽ በመታየቱ የዳቦና የእህል ዋጋ ግሽበት በ0.9 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ ብሏል፡፡ ለዚህም የዋጋ ግሽበት ምክንያቶች በጫት፣ በልብስና በመጫሚያ፣ በኮንስትራክሽን ዕቃዎች (በተለይ ሲሚንቶ)፣ በማገዶ እንጨት፣ በቤት ዕቃዎችና በቤት ማስጌጫዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡ በትራንስፖርት ኢንዴክሱ ላይ ግን ቅናሽ መታየቱን የኤጀንሲው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ከኤጀንሲው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መግለጫ በመውጣት ገበያውን ለመቃኘት ሲሞከር የዋጋ ግሽበቱ ያመጣው የኑሮ ውድነት አንገብጋቢ ሆኗል፡፡ ገቢና ወጪ በማይመጣጠኑበት አገር ውስጥ ጫናውን ሕዝቡ ሊሸከመው አይችልም፡፡ በእርግጥ መንግሥት በጣም መሠረታዊ የሚባሉ የምግብ ምርቶች (ዘይት፣ ዱቄት…) ዋጋ እየደጎመ ቢሆንም፣ ከሁሉም በላይ ግን ሥርዓት አልባ የሆነው የግብይት ሥርዓት አንድ ሊባል ይገባዋል፡፡ መንግሥት ገበያው ውስጥ ገብቶ ዋጋ ይወስን፣ ወይም በዚህና በዚህ ይሸጥ እንዲባል ሳይሆን ይህ ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ተቆጣጣሪ ያስፈልገዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱን እያባባሱ ካሉት ተጠቃሽ ችግሮች መካከል አንዱ ገበያው በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር መዋሉ ነው፡፡ ዋጋ በአድማ እየተወሰነና የምርቶች ሥርጭት ሥልታዊ በሆነ መንገድ እየተስተጓጎለ ስለ ነፃ ገበያ መነጋገር ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ከአምራች ወይም ከአስመጪ እስከ ችርቻሮ ንግድ ድረስ ያለው መጠኑ የበዛ ሰንሰለት በፍላጎትና በአቅርቦት ሕግ መተዳደር ያለበትን ጤናማ ግብይት ጤና እያሳጣው ነው፡፡ ጥቂቶች ገበያውን እንደፈለጉ በሚያሾሩበት አገር ውስጥ የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን እየገረፈው ነው፡፡

በሌላ በኩል ሕዝቡን ከአልጠግብ ባዮች ይታደጋሉ የተባሉ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራትና በመንግሥት የተቋቋሙ የማከፋፈያ ድርጅቶች ጥቅም ግልጽ እየሆነ አይደለም፡፡ እነዚህ ዋጋን በማረጋጋት የምርቶችንና የሸቀጦችን ሥርጭት ፍትሐዊ ያደርጋሉ የተባሉ ተቋማት ሕዝቡን ከሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሊከላከሉ አልቻሉም፡፡ ብዙዎቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ እየሳቱ በአልጠግብ ባዮች መጠለፋቸው እየተነገረ ነው፡፡ ሕዝቡን አስመራሪ ከሆነው የኑሮ ውድነት ሊታደጉት ካልቻሉ የእነሱ ህልውና ምን ይጠቅማል? ወይ በአግባቡ ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ፣ ካልሆነም ዘግቶ መገላገል ይበጃል፡፡

የግብይት ሥርዓቱ የተመሰቃቀለና ለሕዝቡ ህልውና አደገኛ እየሆነ ነው፡፡ ምንም ዓይነት አሳማኝ የሆኑ ምክንያቶች ሳይኖሩ በጣም መሠረታዊ የሆኑ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋቸው ሲጨምር ይታያል፡፡ ምስር፣ በርበሬ፣ ሥጋ፣ ድንች፣ ዘይት፣ ወተት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንቁላል፣ ወዘተ ድንገት ዋጋቸው ሲጨምር ለጭማሪው አጥጋቢ ምክንያት አይሰማም፡፡ የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት መከታተልና መቆጣጠር የሚገባቸው መንግሥታዊ አካላት ምንም ሲሉ አይደመጡም፡፡ ሕዝቡን ከሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነት ማን ይታደገው?

ዜጎች በመኖሪያ ቤቶች ችግር ምክንያት በኪራይ ይኖራሉ፡፡ አከራዮች እንደፈለጉ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ አንድ ሰው በወር ከሚያገኘው ደመወዝ ከግማሽ በላይ ለቤት ኪራይ እየከፈለ የቀረውን ማብቃቃት አቅቶት በችግር ሲጠበስ ተስፋው ማን ነው? መንግሥት ገበያው ውስጥ ገብቶ ዋጋ መወሰን የሌለበት ቢሆንም፣ ከአጠቃላይ ሁኔታዎች ጋር የተገናዘበ ፖሊሲ ማውጣት ይከብዳል ወይ? ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት የተጠናወታቸው ሰዎች በዘፈቀደ ትርፍ ሲያጋብሱ፣ እንዴት በመቶኛ የሚሠላ የትርፍ ህዳግ ማውጣት ያቅታል? አሁን በመታየት ላይ ያለው አሳሳቢ የኑሮ ውድነት የመንግሥትን ትኩረት ያሻል፡፡

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ መካከለኛ ገቢ ያለው አገር ለመፍጠር እየተሠራ ነው ሲባል፣ አሁን ያለውን አገር የሚገነባ ዜጋ ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ የዛሬው በወጉ ሳይኖር የነገውን የተመቻቸ አገር ሊፈጥር አይችልምና፡፡ ስለዚህ መንግሥት ዙሪያ ገባ ችግሮችን ፈትሾ መፍትሔ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ አገሪቱ የባለሙያዎች ደሃ አይደለችምና ለመፍትሔ ፍለጋ የሚያግዙ ባለሙያዎች ዕድሉ ተሰጥቷቸው ይሳተፉ፡፡ አሁን ባለው የተመሰቃቀለና ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ምክንያት ዜጎች ተገቢ ያልሆነ መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡

በተለይ በጣም መሠረታዊ የሚባሉ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችና አገልግሎቶች የዋጋ ግሽበት በሕዝቡ ውስጥ ምሬት እየፈጠረ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ጋብ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት እያንሰራራ ነው፡፡ መፍትሔው ደግሞ ሙሉ ኃይልን በዚህ ላይ በማዋል የዋጋ ግሽበቱን ቢቻል መቀነስ፣ ካልሆነ ደግሞ ባለበት ማስቆም የግድ ይላል፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ በመካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚባሉ ዜጎች ጭምር ኑሮውን መቋቋም አቅቷቸዋል፡፡ ለኑሮ ውድነት መፍትሔ ይፈለግ፡፡ በጣም አንገብጋቢ ሆኗል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...