Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቀድሞ የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በሙስና ተጠርጥረው ተከሰሱ

የቀድሞ የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በሙስና ተጠርጥረው ተከሰሱ

ቀን:

–  ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተጠቅሷል

የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘካርያስ አሰፋና የኢንስቲትዩቱ የፋሲሊቲና ሰርቪስ አስተዳደር ኃላፊና የጨረታ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ጉይቴ ወልደ ማርያም፣ ሳሊም መሐመድ ባሙኒፍ ከሚባል አጠቃላይ አስመጪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር ሙስና ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘካርያስ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም፣ ለኢንስቲትዩቱ አገልግሎት የሚውሉ የአዳራሽ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ፑልፒት/አንትሮንስና መድረክ ከእነአክሰሰሪዎቹ ግዢ ሲፈጸም፣ የፌዴራል የግዥ አፈጻጸም መመርያን በመተላለፍ 3,590,179 ብር ክፍያ አላግባብ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡ ግዢው የተፈጸመው ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ባሉት የተለያዩ ጊዜያት መሆኑንም ክሱ ይጠቁማል፡፡

ለኢንስቲትዩቱ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን ለመግዛት በተለያዩ ጊዜያት የወጡትን ጨረታዎች ማሸነፉ የተጠቆመው ሳሊም መሐመድ ባሙኒፍ አጠቃላይ አስመጪ ቢሆንም፣ ሐምሌ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. የወጣውን የፌዴራል መንግሥት የግዥ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 28ን የጣሰ መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ መመርያው እንደሚያብራራው በማንኛውም ሁኔታ ጨረታውን ላሸነፈ ድርጅት ከጠቅላላ ዋጋው 30 በመቶ በላይ ቅድሚያ ክፍያ አይፈጸምም፡፡ ነገር ግን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ለአሸናፊው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ከጠቅላላ ዋጋው 60 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ በቅድመ ክፍያ እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

የግዥ መመርያ ቁጥር 28 አንቀጽ 2 እንደሚያስረዳው፣ ቅድመ ክፍያ የሚፈጸመው አሸናፊው ድርጅት በቅድሚያ ክፍያ ከሚወስደው ገንዘብ መጠን ጋር እኩል የሆነ ዋስትና ሲያቀርብ ብቻ መሆኑን ቢደነግግም፣ ዋና ዳይሬክተሩ ግን ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ያለምንም ዋስትናና ከመመርያ ውጪ 60 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ያለዋስትና እንዲከፈል መፍቀዳቸውን፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥት የግዥ ሥርዓትን ለመወሰንና ተቆጣጣሪ ኤጀንሲውን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 430/1997 አንቀጽ 43 እና የግዥ መመርያ ቁጥር 28 አንቀጽ 11.14 ላይ የተደነገገውን፣ ተከሳሾቹ መተላለፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ድንጋጌዎቹ እንደሚያስረዱት፣ የጨረታው አሸናፊ ቢያንስ የውሉን ዋጋ አሥር በመቶ ለውል ማስከበሪያነት ለመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ማስያዝ እንዳለበት ቢገልጽም፣ ድንጋጌውን በመተው ግዴታዎቹ በውሉ እንዳይካተቱ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ አሸናፊው ድርጅትም በድንጋጌው መሠረት ገቢ ማድረግ ያለበትን ገንዘብ እንዳላስያዘ ክሱ አክሏል፡፡

የጨረታው አሸናፊ ዕቃዎቹን በውሉ መሠረት ገቢ ማድረግ ሲገባው ሳያደርግ ቢቀር፣ በግዥ መመርያው መሠረት ዕቃውን ካላቀረበበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ ዜሮ ነጥብ አንድ በመቶ በጠቅላላ ሒሳቡ (በተከፈለው መጠን) ተባዝቶ ቅጣት እንደሚከፍል መደንገጉን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ ይህንን ባለመፈጸማቸው መንግሥት 1,058,953.4 ብር በድምሩ ማጣቱን ጠቁሟል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስና አቶ ተስፋዬ በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ ጠቅላላ አስመጪው አቶ ሳሊም መሐመድ (በሌሉበት) በልዩ ወንጀል ተካፋይነት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

አቶ ሳሊም በሌሉበት የተከሰሱ ሲሆን፣ አቶ ዘካርያስ የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ ዋስትና እንደሚከለክል ተነግሯቸው ክሳቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ታዟል፡፡ አቶ ተስፋዬ የተከሰሱበት የወንጀል ሕግ ዋስትና እንደማይከለክል ተገልጾ በ7000 ብር ዋስትና ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የአቶ ሳሊምን መቅረብ ለመጠባበቅ ለሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...