Friday, January 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለቀላል ባቡሩ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያሰራጩ ጣቢያዎች ሥራ ጀመሩ

ለቀላል ባቡሩ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያሰራጩ ጣቢያዎች ሥራ ጀመሩ

ቀን:

ለአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር ከብሔራዊ ኃይል ማሰራጫ በመሳብ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያዳርሱ አራት ሰብስቴሽኖች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡

በአያት አደባባይ አቅራቢያ ሲገነባ ቆይቶ የተጠናቀቀውን ኃይል ማሰራጫ ሰብሰቴሽን፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኪኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ  ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ሥራ አስጀምረዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ ግንባታቸው ያለቀው አራት ሰብስቴሽኖች በጠቅላላው 160 ሜጋ ዋት ኃይል ለከተማው ባቡር የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ለባቡሩ መስመር ግንባታ ከተመደበው 470 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ በ85 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነቡት እነዚህ የኃይል ማሰራጫዎች በአያት፣ በምንሊክ አደባባይ፣ በጦር ኃይሎችና በቃሊቲ አካባቢ ተገንብተው ዝግጁ ሆነዋል፡፡

የሰብስቴሽኖቹን ግንባታ ያከናወነው የቻይናው ናሽናል ግሪድ ኩባንያ በእህት ኩባንያው ቻይና ኤሌክትሪካል ኤንድ ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ በኩል አከናውኗል፡፡ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት፣ ለባቡሩ ኃይል የሚያቀርቡት ማከፋፈያዎች በቀጥታ ከዋናው ማሰራጫ እንዲቀበሉ በማድረግ ምንም ዓይነት የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥማቸው የራሳቸው መስመር ተዘርግቶላቸዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለባቡሩ የሚያቀርቡት ማከፋፈያዎች ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ቢዘጋጁም፣ በቀጥታ ወደ ባቡሩ ለማድረስ የሚስችሉ ዝርጋታዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ ኢንጂነር አዜብ በበኩላቸው ከማከፋፈያዎቹ ኃይል ተቀብለው ለባቡሩ የሚያደርሱ ኬብሎች ቀበራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል፡፡

ምንም እንኳ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ግንባታቸው ተጠናቋል ቢባልም፣ የተወሰነ መዘግየት እንዳጋጠመና ይህም ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ መሆኑን ዶ/ር ደብረ ጽዮንና ኢንጂነር አዜብ ይፋ ተናግረዋል፡፡ የኃይል ማከፋፈያዎቹ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ደምሰው ዘለቀ በበኩላቸው፣ ለኃይል ማከፋፈያ ግንባታ ማካሄጃ የሚያስፈልጉትን ቦታዎች ማግኘት የተቻለው፣ በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ውስጥ እንደነበርና ምንም እንከን ሳያጋጥም ሥራው ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የከተማው ቀላል ባቡር አገልግሎት ለመጀመር ፍተሻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ የገለጹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ እየተካሄዱ የሚገኙት ሙከራዎችና ፍተሻዎች መጠናቀቅ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ ባቡሩ በየትኛውም ጊዜ ሊጀምር ዝግጁ ቢሆንም፣ የሚካሄዱበት ሙከራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ ለሚገኘው መስመርም ስቴትግሪድ የተሰኘው የቻይና ኩባንያን ጨምሮ አራት ተቋራጮች ኮንትራቱን ወስደው እየገነቡት እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ በመጪው ዓመት የአዲስ-ጂቡቲ መስመር ተጠናቆ እንደሚመረቅ ይፋ አድርገዋል፡፡

ኢንጂነር አዜብ በበኩላቸው፣ በመጪው ዓመት ጥር ወር ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው የባቡር ኃይል ማሰራጫ ግንባታ የጂቡቲ መንግሥት የሚያካሂደውን ግንባታ እኩል መጀመርና ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅበት ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በአዲስ አበባና በጂቡቲ መካከል የሚዘረጋው የባቡር መስመር በየቀኑ 1,500 የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚያደርጉትን ምልልስ በመቀነስ፣ ሁለት ቀናት ይፈጅ የነበረውን ጉዞም ወደ አሥር ሰዓት ዝቅ በማድረግ፣ የገቢና የወጪ ንግዱን እንደሚያቀላጥፍ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ 752 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዲስ አበባ -ጂቡቲ መስመር ከቻይና መንግሥት በተገኘ ፋይናንስ በቻይና ኩባንያዎች በመገንባት ላይ ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...