ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው አፍሪካ ሰርከስ አርትስ ፌስቲቫል ከየካቲት 23 እስከ የካቲት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ይካሄዳል፡፡ አዘጋጁ ፍካት ሰርከስ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት፣ በፌስቲቫሉ ከአሥራ አንድ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ የሰርከስ ክለቦች ይገኛሉ፡፡
የመጀመርያው የአፍሪካ ሰርከስ አርትስ ፌስቲቫል በ2008 ዓ.ም. ሲዘጋጅ፣ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ የሰርከስ ክለቦች መገኘታቸው ይታወሳል፡፡ ለሦስት ቀናት የተካሄደው ፌስቲቫል የተለያዩ የሰርከስ ትርዒቶች የቀረቡበት ነበር፡፡ አዘጋጆቹ እንደገለጹት፣ በፌስቲቫሉ ከ12,000 በላይ ተመልካቾች የተገኙ ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የባህል፣ የቅርስ፣ የሲኒማ፣ የፎቶግራፍና የሥነ ጥበብ ማስተዋወቅ ፈንድ ሥር የሚገኝ ነው፡፡
የዘንድሮው ፌስቲቫል ለሦስት ቀናት በመኮንኖች ክለብ ይካሄዳል፡፡ የሰርከስ ትርዒቶቹ በሁለት መድረኮች (በድንኳን ውስጥና ከድንኳን ውጪ) ይቀርባሉ፡፡ በፌስቲቫሉ በሰርከስ ዘርፍ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው የሰርከስ ድንኳንም ይመረቃል፡፡ የሰርከስ ድንኳን ምርቃት በኢትዮጵያና በመላው አህጉሪቱ የሰርከስ ዘርፍ ያለውን ጠቀሜታ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡
በፌስቲቫሉ ከሚቀርቡ ትርዒቶች በተጨማሪ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ የልምድ ልውውጥ ኮንፈረንሶች ይካሄዳሉ፡፡ በዋና ዋና የንግድና የባህል ማዕከሎች ሰርከስ ይቀርባል፡፡ ልጆች ሰርከስ የሚለማመዱበት ቦታ መዘጋጀቱንም አዘጋጆቹ አሳውቀዋል፡፡ በፌስቲቫሉ አዘጋጁ ፍካት ሰርከስን ጨምሮ ኮሎኮሎ ሰርክ አርቤን (ከሞሮኮ)፣ ዚፕ ዛፕ (ከደቡብ አፍሪካ)፣ ሳራካሲ ትረስት (ከኬንያ)፣ ማርዮኔታስ ጂጋንቴስ (ከሞዛምቢክ) ቲና ፋን (ከጊኒ) እና ሌሎችም የሰርከስ ክለቦች ትርዒት ያሳያሉ፡፡