Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ ትኩረት ያገኘው የባህል መድኃኒት

አዲስ ትኩረት ያገኘው የባህል መድኃኒት

ቀን:

ባደጉና በታዳጊ አገሮች ከሚኖሩት 7.6 ቢሊዮን ሰዎች መካከል 80 ከመቶ ያህሉ የባህል መድኃኒቶች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል 70 በመቶ የሚሆኑ ተጠቃሚዎች የሚገኙት በታዳጊ አገሮች መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ከዓመታት በፊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

ባህላዊ መድኃኒቶችን ከሚያዘወትሩ አገሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ህንድና ጀርመን ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ 90 በመቶ የሚሆኑት የቻይና ሕዝቦች የባህል መድኃኒቶችን ያዘወትራሉ፡፡ 35 በመቶ የሚሆነውንም የመድኃኒት ፍላጎታቸውን የሚሸፍኑት ባህላዊ መድኃኒቶችን በመጠቀም ነው፡፡ የባህል መድኃኒቶችን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ በዓመት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር እንደምታንቀሳቅስ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በመላው ዓለም በአሁኑ ወቅት ካሉት ዘመናዊ መድኃኒቶች ውስጥ 75 ከመቶ የሚሆኑት ምንጫቸው ከተፈጥሮ ነው፡፡ በተለይ ለካንሰር ሕክምና የሚውሉ አብዛኞቹ ወይም 50 ከመቶ ያህሉ መድኃኒቶች የዕፀዋት ውጤቶች ወይም የዕፀዋት ትሩፋት ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የባህላዊ መድኃኒቶች አጠቃቀም ሁኔታ ሲቃኝ ደግሞ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የባህል መድኃኒቶች ተጠቃሚ ሲሆን፣ 90 በመቶ የሚሆኑት እንስሳትም ባህላዊ ሕክምና እንደሚደረግላቸው ዓለም አቀፉ ድርጅት ካወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባህልና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር  ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ አቶ አሸናፊ ታደለ እንደሚገልጹት፣ ኢንስቲትዩት የኅብረተሰቡን የባህል መድኃኒት አጠቃቀም ለማወቅ የሚያስችል የሁለት ዓመት ጥናት አዘጋጅቶ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡

‹‹በተወሰኑ ክልሎችና ዞኖች እየተዘዋወርን እስካሁን ድረስ ባካሄደው ጥናት መሠረት አብዛኛው ሰው የባህል መድኃኒቶችን በድብቅ እንደሚጠቀም ለማወቅ ችለናል፡፡ ማኅበረሰቡ ከዘመናዊ መድኃኒቶች ይልቅ በባህል መድኃኒቶች ላይ የበለጠ እምነትም አለው፡፡ የባህል መድኃኒት ከተፈጥሮ የተገኘ ነው በሚል ከጎንዮሽ ጉዳት ነፃ ነው፣ ወይም የጎንዮሽ ጉዳት የለውም ብሎም ያምናል፡፡ የጥናቱ ዋና ዓላማ ግን ዕፀዋቱና ዕውቀቱ ምን ይመስላል? ወይም ምን ዕፀዋት ለምን በሽታ የሚለውን መለየት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ለተለያዩ በሽታዎች ፍቱን ናቸው ተብለው በጥናት የተለዩ  35 የባህል መድኃኒቶች እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል 13ቱ ልዩ ልዩ የባህል መድኃኒቶች በላቦራቶሪና በእንስሳት ላይ ሙከራ እንደተደረገባቸው አስረድተዋል፡፡

የላቦራቶሪ ሙከራ ከተደረገባቸውና ለሰው ከሚውሉ የባህል መድኃኒቶች መካከል የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የሚውለውና በዘልማድ ‹‹ሽፈራው›› (ሞሪንጋ) እየተባለ የሚጠራው ዕፀዋት፣ ጦስኝና የጦስኝ ዘሮች፣ እንዲሁም ለቆዳ በሽታ ሕክምና ይውላሉ የተባሉት የጠጅ ሳርና ነጭ አዝሙድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በእንስሳት ላይ ሙከራ ከተደረገባቸው ውስጥም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጠቃሚ የሆነውን የእንስሳት ቆዳ ጥራት በመቀነስ የሚታወቀውን የእንስሳት ጥገኛ በሽታን ማጥፋት የሚያስችሉ የጠጅ ሳርና ባህር ዛፍ ዘሮች ይገኙበታል፡፡

በላቦራቶሪ ተሞክረው ያድናሉ? አያድኑም?  መርዛማ ናቸው?  አይደሉም? የዶዝ መጠናቸው ምን ያህል ነው? ወዘተ. በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የተፈተሹ ለሰው የሚውሉ የባህል መድኃኒቶች ለፈዋሽነታቸው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ወይም ፍንጭ ታይቶባቸዋል፡፡ ለእንስሳት ተብለው የተሞከሩ ዕፀዋት ግን ውጤታማነታቸው ወይም ፈዋሽነታቸው ተረጋግጧል፡፡

ለፈዋሽነታቸው ፍንጭ የታየባቸውና ውጤታማ ሆነው የተገኙ ዕፀዋት ሁሉ በባህል መድኃኒቶች ደረጃ በሚገባ ተቀምመው ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከተዘጋጁት የባህል መድኃኒቶች መካከል ለእንስሳት የሚውለው ወደ አዳሚ ቱሉ የፀረ ነፍሳት መድኃኒቶች ማምረቻና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ፤ ለሰው የውጭ ቆዳ የሚውሉና በፈሳሽና በቅባት መልኩ ተቀምሞ የተሰናዳው የባህል መድኃኒት ደግሞ በኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ (ኢፋርም) በሙከራ ደረጃ እንዲመረቱ ተደርጓል፡፡

ቀሪዎቹ ለሰው የሚውሉ ሌሎች የባህል መድኃኒቶች በሰው ላይ ሙከራ የማካሄድ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሙከራውን ለማከናወን ደግሞ ለሰው የሚውል ዘመናዊ መድኃኒቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እየተመረቱ የሚወጡ የባህል መድኃኒት ምዝገባና ዕውቅና ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለሰው የሚውሉ የባህል መድኃኒቶቹን የማምረት አቅም ያላቸው ዘመናዊ የመድኃኒት ፋብሪካዎች አሉን?  ለሚለው ጥያቄ አቶ አሸናፊ ሲመልሱ፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ጥሩ ጅማሮዎች እየታዩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለፋርማሲዩቲካል ማኑፋክቸሪንግ የሚውሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተቋቋሙ ናቸው፡፡ እነዚህም ፓርኮች አንደኛው ዓላማቸው የምርምር ውጤቶችን እየተቀበሉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማምረት ነው፡፡

እንደ አቶ አሸናፊ ማብራሪያ የባህል መድኃኒቶች ዘርፍ በርካታ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ከፈተናዎቹም መካከል ለሰው የሚለውን የባሀል መድኃኒት ለማምረት ከፍተኛ የበጀት እጥረት መኖር፣ የባህል መድኃኒት ተመራማሪና ጥራቱን የጠበቀ ላቦራቶሪ አለመኖር፤ ሰው ላይ ለመሞከር የሚያስችል መመርያና ደንብ አለመኖር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የባህል መድኃኒቶች ከተመረቱ በኋላ የመመዝገብና ዕውቅና የሚሰጥ አካልና ዘርፉን ሊያሳልጥ ወይም ሊያሳድግ የሚችል ፖሊሲ አለመኖር፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት (የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የደን፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር) ተቀናጅቶ አለመሥራት ከተግዳሮቶቹ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጤና ባለሙያዎች ባህላዊ መድኃኒቶችን እንደ ጎጂ ልማድ አድርገው ለማኅበረሰቡ ማስተማራቸው ለዘርፉ አለማደግ ሌላው ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ በዳይሬክተርነት ደረጃ ያለውን የባህል መድኃኒቶች  የሥራ ዘርፍ ወደ ምርምር ኢንስቲትዩት ማሳደግ በግድ አስፈላጊ መሆኑን ከአቶ አሸናፊ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የምርምር ተቋማት እየተስፋፉና ውስጣዊ አደረጃጀታቸውም እየተጠናከረ መምጣቱ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የባህል መድኃኒትን የሚያበረታታ የኢኖቬሽን ፖሊሲ ማዘጋጀቱ፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የባዮ ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) መዘጋጀትና አቅጣጫ መቀመጡ ዘርፉ ትኩረት ካደረገባቸው መልካም አጋጣሚዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...