Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ነጥብ ማስቆጠርስ በሐሳብ ብልጫ ነው!

ሰላም! ሰላም! ሰሞኑን ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ማጉረምረም አብዝታለች። ‹‹ኧረ ምን ብናደርግ ይሻል ይሆን?›› የሚለው ካፏ አይጠፋም። ስወጣ ስገባ ‹‹ማንን ነው?›› እላለሁ። ‹‹ጊዜውን አታይም! እሱም ለነገር አዋጣ የተባለ መሰለበት እኮ!›› ትለኛለች። እኔ ደሞ ‹‹ጊዜው›› ባለችኝ ቁጥር ‘የእኛን ነው ወይስ መጪውን ነው?’ እያልኩ ድንግርግር ይለኛል። ምን ላድርግ በቀኝ እያሳየ በግራ የሚጫወተው መንገዱን ሲሞላው። የእኛ ሰው የምታውቁት ነው። ለምሳሌ አንዱ ባለፈው ሰሞን (ገና ታዳጊ ወጣት እኮ ነው ብታዩት) ‘ቪትዝ’ እያጋዛሁት ‹‹ይኸውልህ ባንተ ዕድሜ ባለንብረት የሚኮንበት ጊዜ ላይ ደረስን። ተመስገን በል፤›› ብለው ‹‹እም!›› አለኝና እያሾፈ፣ ‹‹አንቺ ባትወለጅ እናትሽ ባይኖሩ፣ ማን ያበላን ነበር ዶሮ ከእነ ፀጉሩ’ ብለህ መልዕክቴን አድርስልኝ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ይኼንን ትችሉታላችሁ?

መቼም ዘመኑ የብልጦችና የምስጦች ሆኖ እየበሉ ማልቀስን ሙጥኝ ብሎ እሳት የሚያራግበው አላስቀምጠን ብሏል። ‹‹ግን ምን አለበት ቅር የሚለን ጉዳይ ላይ ሁልጊዜ ነገር ከመሸንቆር እንደ ንቁ ተሳታፊ ብናግዝ? በሐሳብ ለመታገል ባንደክም?›› ስል  ሳያስጨርሰኝ፣ ‹‹ኤድያ!›› ብሎ የሚያቋርጠኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ‹‹አንበርብር! የቅስቀሳ ጊዜ እኮ ገና ነው! ሰዓቱ ሲደርስ ትደርስበታለህ፤›› ብሎ ቅስሜን ይሰብረዋል። በተማረ የማዝነው ታዲያ ይኼን ጊዜ ነው። በልዩነቶች ውስጥ አገር የምትባለዋን ትልቋን ጉዳያችንን መርሳት ፊደል በቆጠረ ሰው ሲብስ አያሳዝናችሁም? የምር! የአሥር ሳንቲም ቆሎ (ቆሎ በአሥር ሳንቲም ቢገኝ በኑሮ ውድነት መንግሥትን መቼ እናማርር ነበር እንዳትሉኝ) ኮርሽሞ፣ አንድ ጣሳ ውኃውን (ውኃ ካልሄደች) ላፍ አርጎ የሚያድር ምስኪን ከተመስገን ሌላ ምን ቅኔ ያውቅና! የሳይንሱን ዳዊት ደግመን በዕውቀት ጢም ብለናል ባዮች ግን ‘ጠማማውን እንጨት እየቆረጣችሁ ይኼም ማገር ሆኖ ቤት ትሠራላችሁ?’ እያሉ በየማኅበራዊ ድረ ገጹ ያነታርኩናል። ሰው በስንቱ ያፍራል እናንተ!

የእኔ ነገር ሁሌ ከእናንተ ጋር ጨዋታዬን ስጀምር በብሶት ነው። ለነገሩ እንኳን ክፉና ደግ ለይተው እንዲሁም ከእናት ሆድ ስንወጣ በለቅሶ ድብልቅልቁን አይደል የምናወጣው? ብሶት በአስተዳደር ከመማረር በፊት ይኼውላችሁ እዚያ ይጀምራል። በቀደም ታዲያ አንድ አራስ ልጠይቅ ከማንጠግቦሽ ጋር ፊትና ኋላ ሆነን እንጓዛለን። እሷ ፊት እኔ ኋላ። ‹‹ኧረ ሰው ምን ይለናል? መሀል ከተማ እየኖርን እንደ ጨለማው ዘመን እየነዳሁሽ ስጓዝ? ተይ ቀስ በይ እኩል እንራመድ፤›› ስላት አትሰማም። ይኼ ‘ሌዲስ ፈርስት’ ያላፈላው ጉድ የለም። እኔማ አንዳንዴ ሳስበው ቴክኒኩን ቀይሮ ቀስ እያለ ወደ ኋላ እየጎተተን ሳይሆን አይቀርም። እናንተስ አትታዘቡም እንዴ?

የዴሞክራሲ እሴቶች ብለን ስንፎክር መብትን ደመቅ፣ መከባበርን ደብዘዝ አርገን መጻፍ ካላቆምን እንጃልን! እናላችሁ የትጥቅ ታጋዮች መስለን ማንጠግቦሽና እኔ ሱክ ሱክ ስንል ባዶ እጃችንን መሆናችን ታወቀኝ። ‹‹ማንጠግቦሽ! ከእዚህ ሱቅ አበባ ነገር እንግዛ እንጂ ባዶ እጃችንን ሰው ቤት?›› ብላት ‹‹አበባ ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ይጥቀም እንጂ ለአራስ ምን ይጠቅማል? ካልክ ስንት ነገር አለ፤›› አለች ኮስተር ብላ። ‘ስንት ነገር’ንና ኮስተር አባባሏን አልወደድኩትም። ‹‹በይ ተይው እኔ ባዶ እጅ ከመንጦልጦል ይሻላል አልኩ እንጂ ለ‘ቤቢ ሻወር’ ገንዘብ የለኝም። ለራሴ በወጪ ሻወር ተራቁቻለሁ፤›› ብዬ ፍርጥም አልኩ። እኔስ ማን ነኝ ታዲያ?! ቆይ ግን የአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽ ዕቅድ ውስጥ እንደተካተተ ሁሉ በትንቅንቅ እየፈለፈለ አራስ ደግፈን፣ ዕቁብ ጥለን፣ ለዕድር አዋጥተንና ለወገብ አጉባጩ ኑሯችን ያለንን አራግፈን ምን ሊቀረን ነው? ግራ ገባን እኮ ሰዎች!

የጨዋታ ነዳጁ ጨዋታም አይደል? አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ አሻሽጣለሁ። ገዥና ሻጭ ‘ለደላላ አንተ ካልከፈልክ አንተ’ እየተባባሉ አጉል ንትርክ ውስጥ ገብተውብኛል። አጓጉል ነገሩ ከመበራከቱ የተነሳማ አሁን አሁን እኔ ነኝ ያለ ‹ሆረር› ፊልምም አላስደነገጠኝ ብሎ ሆሊውድ ዝግ ስብሰባ ላይ ነው አሉ (ይህቺ ስብሰባ ብላ ብላ ሎሳንጀለስ ገባች?)፡፡ እና አንድ ሰው ‹‹ወንድም!›› እያለ ይጎነትለኛል። ለራሴ ብው ብያለሁ። ‹‹ምን ላድርግህ?›› ብዬ ስዞር ልመና ነው። ‹‹እባክህ ውጭ አገር ልሄድ ስለሆነ ሙላልኝ!›› አይለኝም? ከተወለድኩ እንደዚያ ስቄ እንደማላውቅ ውልና ማስረጃ ሄጄ መፈረም እችላለሁ። ሳቄ በጣም ስላስፈራኝ (ኋላ ደግሞ ኑሯቸው አልጋ ባልጋ ከመሆኑ የተነሳ በሳቅ የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር ጨምሯል’ ተብዬ ልማታዊ ዜና ልሁን?) እየተናነቀኝ ራሴን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠርኩ። ‹እንኳን ይኼን ይኼን አዲስ አበባን በድለላ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረን የለም እንዴ?› የሚለኝ ደላላ ወዳጅ ነበረኝ።

 እንዲህ ያሉ ‘ላይቭ ኮሜዲያን’ ባይበራከቱልን ኖሮ በመቆዘም ብቻ አንዘልቀውም’ እያልኩ ‹‹ላንተ መኮብለያ እኔ መሙላት ብችል አልቀድምህም ነበር?›› ብዬ አባረርኩት። እንዲያው እኮ! ወዲያው ‘እኔ አልከፍልም አንተ ክፈል’ ሲባባሉ ጊዜዬን የፈጁት ደንበኞቼ በምን እንደማለዝብ ‘አይዲያ’ ብልጭ አለልኝ። ኩላሊት እኮ ነበረን የዛሬን አያድርገውና በሽፍት እየተኛን በሽፍት የምንማርበት ዘመን ላይ ተፈጥረን እንጂ። እና የጓደኛውን ለማኝ የ‹ቅፈላ› አቤቱታ ስነግራቸው እነሱም በሳቅ አውካኩ። ወዲያው አንደኛው ‘ኮሚሽኔን’ መዥረጥ አድርጎ ከፈለኝና ‹‹ይኼ ሰውዬ ሰሞኑን ዓይኑን ታስሮ በቀጭን ከፎቅ ፎቅ ከተሻገረው ሰውዬ በምን ያንሳል?›› አለኝ። ዋናዬን ካገኘሁ በኋላ ውኃ በማይቋጥር ፍልፍስና ስለማልመሰጥ ‹‹እስኪ ጠይቅልኝ?›› አልኩና ላጥ! ደፋርና ጭስ!

ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት እጄ ላይ ነበርና ደግሞ ስበር ወደዚያ “ሄድኩ። ለደሃ ታስቦ የሠራ ቤት የካፒታሊስቶች ካርታ ጨዋታ አንዱ አካል መሆኑን መቼም ዛሬ እንደ አዲስ አናወራውም። ባሻዬ አንዳንዴ ልጃቸው ተምሮና የራሱ ሥራ እያለው፣ ራሱን ችሎ በቤት ችግር ብቻ ከቤታቸው መውጣት አለመቻሉ ውል ሲላቸው ‘ዘራፍ’ ይላሉ። ‹‹አንበርብር? ‘ማርክሲዝምና ሶሻሊዝምና ለጊዜው ጠረጴዛ ሥር አስቀምጠናቸዋል። ጊዜው ሲደርስ እናወጣቸዋለን’ የተባለው እውነት ሆኖ የምናይ ይመስልሃል?›› ይሉኛል። ‹‹እንዴት ባሻዬ?›› ስላቸው፣ ‹‹ትርፍ ይዞታና ትርፍ ቤት እየነጠቀ በቤት ችግር አሳር ለሚያዩ ልጆቻችን እንዲያከፋፍልልን ነዋ፤›› ብለው ሳይጨርሱ፣ ‹‹ኧረ ባሻዬ ዝም ይበሉ ሰው እንዳይሰማዎት!›› ብዬ ዝም አሰኛቸዋለሁ። ደግሞ የትናንቱ አልበቃ ብሎ ሌላ መዓት ይጎትቱብኝ? እሳቸውን እንደ ሕፃን ልጅ እሹሩሩ ስል ታዲያ በጎን ራሴን እጠይቃለሁ ‘እውነት እንዲያ ተብሏል?’ እያልኩ።

ጎበዝ! ዘመኑ የመረጃ አይደል? እስኪ በ‘ዩቲውብ’ ጎዳና ስታልፉ ‘ሰርች’ አድርጋችሁ ንገሩኝ። ዳሩ የዘመኑ ኢንተርኔት ተጠቃሚ የሰው ሚስትና የሰው ባል ፕሮፋይል ሲበረብር ለጠቃሚ ሰነድ መሰብሰቢያ ጊዜ አይተርፈውም አሉ። ‘አሉ ባትቀርልን ኖሮ የኅትመት ውጤት በተራቆተበት በዚህ ጊዜ ምን ይውጠን ነበር?’ ያለኝ አንድ ጋዜጣ ማንበብ የሚወድ ወዳጄ ነው። ቤቱን የምትሸምተው ወጣት ሁሉን ነገር ከጨራረሰች በኋላ፣ ‹‹ገንዘብ ይኑር እንጂ ቤትስ የባል ያህል አልጠፋም፤›› አለችኝ። ‹‹ይገርማል! ወንዶችም አንቺ እንደምትይው የሚሉት ሚስት ጠፋ ነው፤›› ስላት፣ ‹‹ተወው እባክህ! ሁላችንም የአገርና የጎጆ ነገር በፀበሉ ማለት ተጠናውቶን ነው ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን የሆነው፤›› ብላኝ የምትቆርጠውን ቆረጠችልኝ። የመርዙን መድኃኒት አውቆ ሸሽጎ ‘እህህን’ ፋሽን ማድረግ ተይዟል ልበል? ምን ትላላችሁ?      

በሉ እንሰነባበት። እንደተለመደው ስሮጥ ውዬ ሳላስበው መሽቶ ሰዓቱ ገፍቷል። በስንት ትርምስ አንዲት ታክሲ ያዝኩና ወደ ሠፈሬ ማዝገም ጀመርኩ። አውላላ ሜዳ ላይ ታክሲዋ ቆመች። ምነው ቢባል ‘ጎማ ተንፍሶ’ ተባለ። ተሳፋሪው ተንጫጫ፡፡ ‹‹አሁን እዚህ ለጅብ ልታስበሉን ነው ጎማ ተነፈሰ የምትሉን?›› ይላል አንዱ። ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ምን ችግር አለው ጎማ ነው ይቀየራል። ዋናው መንገድ ትራንስፖርት አለመስማቱ ነው። ይኼኔ ቢሰማ ‘የትራንስፖርት ችግር መቼ ይቀረፋል?’ ስንለው ‘ሁለት ወር ሦስት ወር ታገሱ!’ ማለት በለመደበት አፉ ‘ጎማው እስኪቀየር በእግራችሁ ወክ አድርጉ’ ተብለን ነበር። ያኔ ምን ይውጠን ነበር?›› ይላል። ወያላው፣ ‹‹እባካችሁ ተባበሩን፣ ወረድ ወረድ በሉና ቶሎ ቀያይረን እንጓዝ፤›› ሲል አንዲት ነገረኛ ያዘችው። ‹‹ጭራሽ ልወርድ? እንዲያው አደራህን እዚህ ላይ መውረድ ቀላል ሲሆን ያየኸው?›› ብላ ጮኸችበት።

ጎማ መቀየሩ አሥር ደቂቃ አይፈጅም ነበር። በአጉል ጭቅጭቅ ከወዲያ ወዲህ ሰው በነገር ሲተጋተግ ከ30 ደቂቃ በላይ ቆምን። ኋላም ሾፌሩና ወያላው ሲታገሉ ገሚሱ እነሱ አውቀው እንዳስተነፈሱት ሁሉ ‘የት አባታቸው’ ሲል፣ ገሚሱ ባግዝ ሽሙጡ ይገለኛል ብሎ ፈርቶ ጥጉን እንደያዘ የተነፈሰው ጎማ ተቀይሮ ሄድን። በነጋታው የማታ አገባቤን ለባሻዬ ልጅ ሳጫውተው፣ ‹‹መኪናው ቢጓዝ ለጋራ ጥቅም! ጎማውም ቢቀየር ለሁሉ ጥቅም! መንገድ ቢሠራ ለጋራ ጥቅም! አገር ብትለወጥ ለትውልድ ብተርፍ ነው! ምነው ይኼን ያህል?›› ብሎ እሱ ደግሞ መልሶ እኔኑ ይጠይቀኛል። ‘የማይረባ ሙግት ምን ያደርግልሻል፣ ተጠጋልኝ እያልሽ ምን ያራግጥሻል?’ አለ ከሚስቱ ጋር በኑሮ ያልተስማማ አባወራ። ‹‹ኧረ ለመሆኑ የሚወራውና የሚሠራው አራምባና ቆቦ ሆኖ እስከ መቼ? መለወጥ ናፍቀን ዋጋ መክፈል ጠልተን ይሆናል?›› ስለው ምሁሩን የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት መሆኑን ካመንን ዋናው ጉዳይ ለሐሳብ ብልጫ መጨነቅ ነው፤›› አለኝ፡፡ እውነት ነው፡፡ ነጥብ ማስቆጠርስ በሐሳብ ብልጫ ነው፡፡ መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት