Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊትውልዱን ለአደጋ ያጋለጡት የአዲስ አበባ ሺሻ ቤቶች

ትውልዱን ለአደጋ ያጋለጡት የአዲስ አበባ ሺሻ ቤቶች

ቀን:

የሺሻ ዕቃ እንደአሁኑ ሳይዘምን እንደ ዋንጫ በጌጠኛ ቁሶች ሳይጌጥ በፊት በኮኮናት ቅርፊትና ረዘም ባለ ቀሰም እንደ ነገሩ ተደርጎ ነበር የሚሠራው፡፡ በሰሜን ምዕራባዊ የህንድ ግዛቶች በተለይም በፓኪስታን፣ በራጃስታንና በጉጅራት ድንበሮች አካባቢ የሰፈሩ ህንዳውያን ያዘወትሩት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኮኮናቱ ቅርፊት ውስጥ ኦፒየምና ሀሺሽ ጨምረው ረዘም ባለው ቀሰም ወደ ውስጥ ይስቡታል፡፡ ሺሻ ለድሮ የህንድ የቤት እመቤቶች መዝናኛ ሲያልፍ ደግሞ የኑሮ ደረጃ ማሳያም ነበር፡፡

ከህንድ እንደተጀመረ የሚነገርለት ሺሻ በያኔዋ ፋርስ፣ በፓኪስታን፣ በአፍጋኒስታን አድርጎ ወደ ሌሎች አጎራባች አገሮች ተዛመተ፡፡ ቀጥሎም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እስያና የዓረብ አገሮች ብሎም ወደ ሰሜን አፍሪካ ግዛቶች ተዋወቀ፡፡ ከአንዱ አገር አንዱ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ በአሁኑ ወቅት በመላው አገር ከሲጋራ ባልተናነሰ መጠን ጥቅም ላይ አየዋለ ይገኛል፡፡ የሲጋራን ያህል በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የለም የሚል እምነት ስላለም እንደ ጊዜ ማሳለፊያነት ጥቅም ላይ ቢውል ችግር የለውም የሚሉ የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲበዛ በማድረጉ ረገድ ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

ዘመናዊው ሺሻ ከመስፋፋቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ሺሻን ተክቶ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ጋያ ነው፡፡ ጋያ በቅልና በቀሰም የሚሠራ የትምባሆ ማጨሻ ነው፡፡ ‹‹ድሮ መርካቶ ገበያ ውስጥ እናቶች እየከፈሉ ያጨሱ ነበር፤›› ያሉት አንድ የከተማዋ ነዋሪ የሺሻ ንግድ የጀመረው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች ናርጊሌ፣ አርጊሌ፣ ጎዛ እና ሀብሊበብሊ የሚሉ ስያሜዎች ተሰጥተውታል፡፡ በውስጡ የሚጨመሩ አነቃቂ ተክሎች ዓይነትና ቃናዎች እንዲሁም በጊዜ ሒደት በዝተዋል፡፡ በኦቾሎኒ፣ በቸኮላት፣ በሚንትና በተለያዩ ጣዕሞች የሚዘጋጀው ሞአሰል ከተለያዩ ነገሮች ጋር ይቀመማል፡፡ ሞአሰል ትምባሆ፣ ማር፣ ሞላሰስና ሌሎች መአዛ ከሚሰጡ ግብዓቶች ይዘጋጃል፡፡

- Advertisement -

ዋንጫ መሳይ ቄንጠኛ ዕቃዎቹና ሳቢ መአዛቸው ይሁን በሌላ የሺሻ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ይህም የሁሉም የዓለም አገሮች ችግር ሲሆን፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ መነገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮችም በስፋት እየተዘወተረ ይገኛል፡፡ በዚሁ መጠን ከሺሻው ጋር አብሮ የሚቀርበው ጫትም አስከፊነቱን እንዲጨምር አድርጓል፡፡ መጠኑ የተለያየ ቢሆንም በዚህ ድርጊት ታዳጊዎችና አዋቂዎች በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

አዋቂዎችን ከሥራ፣ ተማሪዎችን ደግሞ ከትምህርት ገበታቸው እንዲዘናጉ እያደረገ እንደሚገኝ የተነገረው በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሕገወጥ ሺሻና ጫት የማስቃም ጉዳይን አስመልክቶ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ነገርም በየመንደሩ ያሉ የሺሻና የጫት ቤቶች መበራከት ነው፡፡ ገንዘብ እያስከፈሉ ሺሻና ጫት የሚያስጠቅሙ ሕገወጥ ንግድ ቤቶች ሺሻና ጫት በቀላሉ እንዲገኝ ከማድረግ ባለፈ ሌላም ትውልዱን አደጋ ላይ እየጣሉ የሚገኙ ድርጊቶች የሚከናወኑባቸው ቦታዎች መሆናቸውን በውይይቱ ተነስቷል፡፡

‹‹ትውልድ እየተፈታተነ ያለው የጫትና የሽሻ አደጋ›› በሚል በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ጫትና ሺሻ ቤቶች በየመንደሩ በስፋት እየተከፈቱ ነው፡፡ መሰል ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች ለተለያዩ የንግድ ዘርፎች የሚያወጧቸውን የንግድ ፈቃድ በሕገወጥ መንገድ ለሺሻ ማስጨሻና ማስቃሚያ ቤትነት እያዋሉ እንደሚገኙ ጽሑፉ ያብራራል፡፡ አንዳንድ መኖሪያ ቤቶች በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ በመኖሪያ ቤትነት የተመዘገቡ ነገር ግን እንዲህ ላሉ ተግባራት የሚውሉ ቤቶች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡

‹‹ከሕንፃ ስር ለፓርኪንግ ተብለው የሚተዉ ቦታዎች ሳይቀሩ መቃሚያና ሺሻ ቤቶች ይሆናሉ፡፡ ለዚሁ ተግባር ብለው ሙሉ ሕንፃ የሚከራዩ፣ ሰፊ ቅጥር ያላቸው የመኖሪያ ቪላዎችን የሚከራዩና ወደ ሺሻ ቤትነት የሚቀይሩ ሕገወጥ ነጋዴዎች ብዙ ናቸው፡፡ ማሳጅ ቤቶችና የእንግዳ ማረፊያዎችም ለዚሁ ተግባር እየዋሉ ነው፤›› ያሉት የቦሌ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በርሄ ናቸው፡፡ መኪኖችን ሳይቀሩ ለመቃሚያነት የሚውሉበት ሁኔታም ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ ነው፡፡

አንዳንድ ሺሻ ቤቶች ከባድ ጥበቃ የሚደረግላቸውና ከመግቢያቸው ጀምሮ ዙሪያቸው በወጠምሻ ቦዲ ጋርዶች የሚጠበቅ ሲሆን፣ እነሱን አልፎ ወደ ውስጥ ለመግባት አስቸጋሪ እንደሆነ አቶ ዮሐንስ ይናገራሉ፡፡ ይህም ሕግ ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት ከማደናቀፉ በላይ ደንብ አስከባሪ አካላትን አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባር የተሰማሩ ነጋዴዎች እጅ ከፍንጅ በሚያዙበት ወቅት ሕጋዊ ፈቃድ ኖሮኝ ግብር እየከፈልኩ ነው ምሠራው ብለው ለማወናበድ የሚሞክሩ እንደሚያጋጥሙ፣ ይህም አልሳካ ሲላቸው ለማስፈራራት የሚጥሩ መኖራቸውን፣ ከዚህ ሲያልፍም ገንዘብ ከፍለው የሚያስደበድቡ መኖራቸውን በአንዱ የደንብ አስከባሪ ላይ የደረሰውን የመደብደብ አደጋ በምሳሌነት በማንሳት አቶ ዮሐንስ የችግሩን ጥልቀት አስረድተዋል፡፡

በሥራቸው ‹‹ዳያስፖራ ነኝ አገር ላለማ ነው የመጣሁት፤›› የሚሉ ግዴለሾች፣ ከቅጣት ለማምለጥ እጅ ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ ያጋጥሟቸዋል፡፡ ‹‹ሺሻ የማያስጠቅሙ ጭፈራ ቤቶች ደንበኛ እስከማጣት ይደርሳሉ፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ ሕጋዊ ነጋዴዎች ጭምር በግድ ወደዚህ ተግባር ተስበው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩ እንግዶች መካከል አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ በበኩሉ በዚሁ ጉዳይ ሚሊዮኖችን አውጥቶ ከቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ወረድ ብሎ በሚገኘው ጋሞ ታወር የከፈተውን ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ለመዝጋት መገደዱን ተናግሯል፡፡ ሲኒማ ቤቱ ከተከፈተ ዓመት ያለፈው ቢሆንም የተጠበቀውን ያህል ደንበኞች ማፍራት ግን አልቻለም፡፡ የቤቱን ደንበኛ ማጣት የተመለከቱ አንዳንዶች ‹‹ይህንን የመሰለ ቤት ከፍተህ ሺሻ ቁጭ ቁጭ አድርግ እንጂ አታውቅም እንዴ አሉኝ፡፡ ከዚያም እንዲህ አድርጌ ከማተርፍ ብዬ በዚሁ ምክንያት ቤቱን ዘጋሁ፤›› በማለት አርቲስቱ ያጋጠመውን ለመድረኩ አካፍሏል፡፡

እንደ ፋሽን በከፍተኛ መጠን እየተንሰራፋ የሚገኘው የሺሻና የጫት ማስቃም ቢዝነስ በሌላ ንግድ የተሰማሩን ሳይቀር እንደቅመም ጣል እንዲያደርጉበት እያስገደደ ይገኛል፡፡ የማኅበረሰቡን ጥቅም ያስቀደሙ እንደ ሠራዊት ያሉ ዜጎች ንግድ ቤታቸውን በኪሳራ ሲዘጉ፣ በተቃራኒው ትርፋቸውን ያስቀደሙ ደግሞ ሺሻን ከመጠጥ፣ ከጫት፣ ከማሳጅና ከሌሎች ነገሮች ጎን እያቀረቡ ነው፡፡ አንዳንድ ባርና ሬስቶራንቶችም ለዚህ ተግባር የሚውል ጥግ ለይተው እንደሚተዉ ታዝበናል፡፡

ትውልድን የማጥፋት ኃይል ያላቸው እነዚህ አነቃቂ ተክሎችን መሸጥና መጠቀም ግን በአገሪቱ ሕግ የተከለከሉ አይደለም፡፡ እንዲያውም በገፍ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡና የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ሆነው እያገለገሉ ያሉ ናቸው፡፡ ሞአሰሉ የሚሠራበት ትምባሆ፣ ከሺሻው ጎን የሚቀርበው ጫት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ካቀኑ ተክሎች መካከል ናቸው፡፡ ታድያ እነዚህን አነቃቂና ለሱስ የሚዳርጉ ዕፆችን በጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያዝ ሕግ ለማውጣት አስቸጋሪ ሆኖ እስካሁን ቆይቷል፡፡ ከአጫሾች የሚወጣው ካንሰር አማጭ ጭስ የማያጨሱን እንዳይጎዳ ሲባል ሲጋራ ሕዝብ በተሰበሰበበት እንዳይጨስ፣ አነቃቂውን ጫትም በመኪናው ውስጥ በተለይም አሽከርካሪዎች በጉዞ ላይ እንዳይቅሙ ከመከልከል ባለፈ የተለየ ክልከላ አለመደረጉ የሚታወቅ ነው፡፡

‹‹ጫት የመሸጥ ፈቃድ ይሰጣል፤ ነገር ግን ማስቃምም ሆነ ሺሻ ማስጨስ አይቻልም፤›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ የጫትና የሺሻ ቤት ማስጠቀሚያ ፈቃድ እንደማይሰጥ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ነጋዴዎች ለሌላ ንግድ ያወጡትን ፈቃድ ለሺሻና ማስቃሚያ ቤት ይጠቀማሉ፡፡

‹‹20,000 ብር የሚከራይ ቤት ለሺሻ ንግድ ሲሆን በ40,000 ብር ነው የሚከራየው፡፡ ምክንያቱም በሥራው የሚገኘው ገንዘብ ከፍተኛ ስለሆነ መክፈል አያቅታቸውም፤›› ሲሉ አከራዮች የሚከፈላቸው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ተከራዮችን እንደሚስብ ገልፀዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ተግባራት በብዛት የሚከናወኑትም ከመንገድ ገባ ብለው በሚገኙ መንደሮች ሲሆን፣ ሙዚቃና ሌሎች ነገሮች ስለሚኖሩ በዙሪያቸው የሚኖሩ ዜጎችን በድምፅ ብክለት እንዲቸገሩ እንደሚያደርጉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

እንዲህ ባሉ ሺሻ ቤቶች ተላላኪ ሆነው የሚሠሩ ደላሎች በብዛት የሚገኙ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች እየመለመሉ ለወሲብ እንደሚያቀርቡ አቶ ዮሐንስ ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት አረጋግጠዋል፡፡ እነዚህ ሕገወጥ ንግድ ቤቶች ለግብረ ሰዶም መስፋፋትም ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉም፣ ወንደኛ አዳሪነት እንዲስፋፋ አንዱ ምክንያት እንደሆኑም በቁጭት ተናግረዋል፡፡ የጫትና የሺሻ ቅኝ ተገዥ ትውልድ እንዳይፈጠር ጠንክረን መሥራት አለብን ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ ችግሩ በብዛት የሚታየው ቦሌ መድኃኔዓለም ዙሪያና በሃያሁለት አካባቢ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡  

በወረዳው በሚገኙ እነዚህ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት ብቻ በዚህ ሥራ የተሰማሩ 175 ሕገወጥ ቤቶች ተዘግተዋል፣ በ1282 የሺሻ ዕቃዎችም ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ስለተደረሰባቸው እንጂ በድብቅ የሚሠሩ ሌሎች ብዙ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡ ዕርምጃ እንዳይወሰድባቸው በየመኖሪያ ቤቱ በድብቅ ከሚሠሩ ሕገወጦች በተጨማሪ የሥራ ሰዓታቸውን ከቀን ወደ ሌሊት ያዞሩ ብዙ እንዳሉ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ በከተማዋ ከእኩለሌሊት ጀምሮ ቅልጥ ያለ ንግድ የሚያካሂዱ ሺሻ ቤቶችን ለማዘጋት ‹‹በመንግሥት ሥራ ሰዓት እየወጣን እየገባን የምንወጣው ሥራ አይደለም፡፡ የተሻለ ልፋት ይጠይቃል›› ብለዋል ኃላፊው፡፡

እንዲህ ያለው ሕገወጥ ድርጊት በሚበዛበት አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ዒላማቸው አድርገው የሚከፈቱ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች፣ ጫት ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ፑልና ከረንቡላ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች ትውልድን እያጠፉ መሆናቸውን የተናገሩት የቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩ በትምህርት ሰዓት ተማሪዎች ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ገብተው እንደሚስተናገዱ የገለፁት በቁጭት ነበር፡፡

‹‹ሌላው ቢቀር ከነዩኒፎርማቸው እንዳይገቡ ቢከለክሉ ምናለበት፡፡ በሌላ በኩል ተማሪዎችን ለማዘናጋት ደይ ፓርቲና ኮንሰርት የሚያዘጋጁ አካላትም ወደ ቅጥሩ በድብቅ ፍላየሮች ለተማሪው እንዲደርስ ያደርጋሉ፡፡ ልጆቹን ወደ መስመር ለማስገባት በጣም ተቸግረናል፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ ተማሪዎችን ዒላማ አድርገው የሚከፈቱ ሕገወጥ ንግድ ቤቶች ላይ ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ጉዳዩ ሁላችንንም ዕረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ሞታችንን ቆመን በዓይናችን እያየን ነው፤›› ያሉት በዕለቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኮሚሽነር አቶ ማቴዎስ አስፋው መፍትሔ ይሆናል ያሉትን አካፍለዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ፀድቆ በሕትመት ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ 10ኛ ማስተር ፕላን እንዲህ ላሉ ማኅበራዊ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ነገሮችን አካቷል፡፡ በየመንደሩ የሚገኙ ጭፈራ ቤቶች፣ ማሳጅ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች፣ መቃሚያ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች በዋና መንገድ ዙሪያ እንዲሆኑ የሚል መመሪያ አካቷል፡፡

በዋናነትም ትምህርት ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች 500 ሜትር ራዲየስ መራቅ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ነው፡፡ ‹‹የመኖሪያ ዞን፣ የኢንዱስትሪ ዞን እየተባለ እንደሚከለለው ለጭፈራ ቤቶችና ለመሳሰሉት የተለየ ቦታ መከለል አለበት፤›› በማለት በሒደት የተለየ አካባቢ እንደሚበጅላቸው አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማስተር ፕላኑ የድምፅ ብክለትን ለመከላከል ሲባል ጭፈራ ቤቶች በሕንፃዎች ምድር ቤት ድምፅ በማያስወጣ መልኩ መሠራት አለባቸው የሚል መመሪያም ያካተተ ነው፡፡

 አንድ የሺሻ አጫሽ በአንድ የሺሻ ማጨስ ሥርዓት ወቅት ወደ ሳንባው የሚያስገባው አንድ የሲጋራ አጫሽ ከ100 እስከ 200 ሲጋራዎች አጭሶ ከሚያስገባውን የጭስ መጠን ጋር ይመጣጠናል:: አንድ ሲጋራ በአማካይ ከ500 እስከ 600 ሚሊ ወደ ውስጥ የሚተነፈስ ጭስ አለው:: አንድ የሺሻ ማጨስ ሥርዓት 90ሺ ሚሊ ወደ ውስጥ የሚተነፈስ ጭስ እንዳለው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በርካታ ሰዎች በተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት ሺሻ ማጨስ ሲጋራ ከማጨስ ይልቅ ጤናማ ነው ብለው ያምናሉ:: ነገር ግን ይህ ትክክል አለመሆኑን “walking against tobacco companies harm” በሚል መርህ የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ ያስረዳል፡፡ የሺሻ ጭስ ከሲጋራ ጭስ የሚለየው በውኃ መቀዝቀዙ ብቻ መሆኑን፣ ይህ መቀዝቀዝ የሺሻን ጭስ ከሲጋራ ጭስ ይልቅ ለጉሮሮና ለሳንባ ጉዳት አልባ እንዲመሰል ማድረጉን፣ ነገር ግን ጉዳት አልባ ቢመስልም የሺሻ ጭስ ከሲጋራ ጭስ ጋር እኩል ጎጂ መሆኑን ጽሑፉ ያስረዳል:: እንዳውም የጭሱ ቅዝቃዜ ያለ ችግር ወደ ውስጠኛው የሳንባ ክፍል እንዲገባ ስለሚያደርገው የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ያትታል::

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...