- የሌሴቶ ቡድን ነገ አዲስ አበባ ገብቶ በዕለቱ ወደ ባሕር ዳር ያመራል
- የስታዲየሙ መግቢያ ከፍተኛው 700 ብር ዝቅተኛው 50 ብር ሆኗል
ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 ከአልጄሪያ ሌሴቶና ሲሼልስ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) እሑድ (ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም.) በባሕር ዳር ሁለገብ ስታዲየም የመጀመርያውን ማጣሪያ ከሌሴቶ አቻው ጋር ያደርጋል፡፡ ዋሊያዎቹ ከሰኔ 1 ቀን ጀምሮ በባሕር ዳር ግራንድ ሪዞርት ሆቴል ከትመው ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛል፡፡ የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት አዲስ አበባ ገብቶ ማምሻውን ወደ ባሕር ዳር ያመራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ የዋሊያዎቹ የዋና አሠልጣኝነትን መንበር በተረከቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ እሑድ ግንቦት 30 ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በወዳጅነት ጨዋታ ተገናኝተው 1 ለ0 የተሸነፉበት አጋጣሚ የቡድናቸውን እንቅስቃሴ በመልካም ጎኑ እንደተመለከቱት ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ መግለጫውን ተከትሎም በዋሊያዎቹ ስብስብ ዙሪያ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየቶች ተሰምተዋል፣ እየተሰሙም ይገኛል፡፡ በተለይ ደግሞ በውድድር ዓመቱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ለክለቦቻቸው ውጤታማነት ጉልሕ ድርሻ ከነበራቸው ልጆች ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ አለባቸው ተስፋዬ፣ የደደቢቶቹ ሳምሶንና ታደለ መንገሻ የመሳሰሉት በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ምርጫ ሳይካተቱ መቅረታቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
ዋሊያዎቹ ከዛምቢያ አቻቸው ጋር በነበራቸው የወዳጅነት ጨዋታ ግን ቀደም ሲል ሲደመጡ የነበሩ አስተያየቶችና ትችቶች የቀዘቀዙበት፣ በዋናነት ልምድ የሌላቸው የተባሉ ወጣቶች በስታዲየም የታደመውን ተመልካች ሊያሳምን የሚችል እንቅስቃሴ ማሳየት መቻላቸው በአገሪቱ መታየት ያልቻሉ ግን ደግሞ ቢታዩ ትልቅ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ተጨዋቾች እንዳሉ ማረጋገጫ ሆኖ መታየቱን ጭምር የተናገሩ አሉ፡፡
ይህን አስተያየት ከሰጡት ውስጥ አቶ እንግዳወርቅ ዘውዴ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ አቶ እንግዳወርቅ፣ አሁን ባለው የዋሊያዎቹ ስብስብ የተካተቱ ወጣት ተጨዋቾች ጥንካሬና ተስፋ ሰጭነት ነገ ለመቀጠሉ ምንም ማረጋገጫ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ የአስተያየት ሰጪው ሥጋት ‹‹ባሬቶ የሰውነትን ዮሐንስ ደግሞ የባሬቶን የቡድን ዝግጅት እያፈረሱ ከምንም መጀመር፣ ቀደም ሲል የነበረውን ጠንካራ ጎን እንዲቀጥል ድክመቱን ደግሞ በማረም ብሔራዊ ቡድኑ መሠረቱን ሳይለቅ የሚዘጋጅበት ሥርዓት ሊኖረው ሲገባ ያ ሲሆን አይስተዋልም፤›› ብለው የአሠልጣኝ ዮሐንስ የዝግጅት ሁኔታም ከእነዚህና መሰል የአሠራር ድክመቶች ትምህርት ተወስዶ በፌዴሬሽኑ ተገቢ እገዛና ክትትል እንዲደረግለት ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እሑድ በባሕር ዳር ስታዲየም ለሚደረገው የኢትዮጵያና የሴሌቶ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የስታዲየም መግቢያ ዋጋ በደረጃ በመከፋፈል ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት ክብር ትሪቢዮን 700 ብር፣ ከዛ ቀጥሎ ላለው ቦታ ደግሞ በየደረጃው 300 ብር፣ 150 ብር፣ 100 ብርና የመጨረሻው 50 ብር መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የመከላከያና የዋሊያዎቹ ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው ባጋጠመው ጉዳት ከሌሴቶ ጨዋታ ውጪ መሆኑ ተሰማ፡፡ በሱ ምትክ የዳሽን ቢራው ግብ ጠባቂ ቴዎድሮስ ጌታሁን ለሙከራ መጠራቱ የተሰማ ሲሆን፣ ለእሑዱ ጨዋታ ግን የሙገር ሲሚንቶ ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ የመሠለፍ ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ተጠብቋል፡፡