Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የቡድን ሰባት ጉባኤተኞቹ

ትኩስ ፅሁፎች

ኃያላኑ መንግሥታት በተለይ ቡድን ሰባት ተብለው የሚታወቁት አገሮች መሪዎች ሰንበቱን (ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም.) ተንተርሰው በደቡባዊዋ ጀርመን ከአልፕስ ተራሮች ግርጌ በምትገኘው ክሩዑን ከተማ ተሰባስበው ነበር፡፡ እንደ ዶቸቬሌ ዘገባ፣ በባቫርያ ግዛት በሚገኘው ጥንታዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ ለጉባኤ የተቀመጡት የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የፈረንሣይ፣ የእንግሊዝ፣ የጃፓን፣ የካናዳ፣ የኢጣሊያ መሪዎች ናቸው፡፡ ሰባቱ መሪዎች ወንበር ዘርግተው በአየር ንብረት ለውጥ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ስላደረገችው ወረራ፣ የአይኤስ መስፋፋትና በኢቦላ በሽታና በመሳሰሉት ላይ መምከራቸው ተሰምቷል፡፡ በመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አጋፋሪነት የተሰባሰቡት መሪዎቹ በጥንታዊውና ታሪካዊው ቦታ ላይ ከመዝናናትም አልተቆጠቡም፡፡ ባህላዊ ምግብን ከመቋደስ ቢራውንም ከመጐንጨት አልሰነፉም፡፡ ሚስተር ኦባማ ክሩዑን ላይ እንደደረሱ በስፍራው ለተገኙት በባህላቸው መሠረት ጥቁርማ የቆዳ ሱሪ ለሚታጠቁት የባቬሪያ ሰዎች፣ ሰላምታቸውን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ቀልድም ጣል አድርገው ነበር፡፡ ‹‹የቆዳ ሱሪየን ረስቼ መምጣቴን ሳልነግራችሁ አላልፍም፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን አንድ የቆዳ ሱሪ እዚሁ ሳልሸምት አልመለስም፤›› ነበር ያሉት፡፡ ጉባኤያቸው ያለ ሳንካ እንዲጠናቀቅ ከመላይቱ ጀርመን የተወጣጡ 22,000 ፖሊሶች ቢገኙም አካባቢውን ግን ፀረ ካፒታሊስት አቋም ያላቸው ተቃዋሚዎች ማጥለቅለቃቸው ታውቋል፡፡ ፎቶግራፎቹ መራኂተ መንግሥት ሜርክል ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር በኤልማው ቤተ መንግሥት አፀድ ውስጥ ከሌሎቹ መሪዎች ነጠል ብለው ሲያወጉና ባራክ ኦባማ ክሩዑን መንደር ሲደርሱ በቢራ አቀባበል ላደረጉላቸው ‹‹ቺርስ›› ሲሉ ያሳያሉ፡፡      

******

ሠምና ወርቅ ያማርኛ ቅኔ

(ሀ)

ወላድ፡ኢትዮጵያ፡/፡ለልጆቿ፡ብላ፥

እጅግ፡ሳይጥሩባት፥/፡ሳይዘሯት፡አብቅላ፥

ስንዴውን፡ጠብቃ፥/፡እንክርዳዱን፡ነቅላ፥

ስትመግበን፡አየን፡/፡በፀሓይ፡አብስላ።

ምሳሌ፡ዘር፡ሀገራችን፥

ንጹሕ፡ዝናም፡መንግሥታችን።

        (ዮፍታሔ፡ንጉሤ።)

 (ለ)

ሰፌድና፡ወንፊት፡/፡እያለ፡በጃችን፥

ያልተነፋ፡ዱቄት፡/፡ምነው፡ማቡካታችን፧

        (አ.፡ኪዳነ፡ወልድ፡ክፍሌ።)

(ሐ)

ያ፡ማዶ፡ተራራ፡/፡ረዥም፡ነው፡በጣም፤

በከብት፡ነው፡እንጂ፡/፡በእግር፡አያስወጣም።

ያ፡ልጅ፡ተራራውን፡/፡ሊወጣ፡ያስባል፤

ዐዋቂ፡ሲያቅተው፡/፡ድኾ፡እንዴት፡ይዘልቃል።

       (ማኅተመ ወርቅ እሸቴ)

መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹ያማርኛ ሰዋስው›› (1948)    

 

 

 

ሼክ ናስረዲንና ስስታሙ ሰው

በአንድ ወቅት በጣም ስስታም ነገር ግን በጣም ሃብታም የሆነ የናስረዲን ጎረቤት ነበር፡፡ ናስረዲን ግን በጣም ድሃ ነበር፡፡ ናስረዲንም አላህ 1000 ፓውንድ እንዲሰጠው ይፀልይ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ስስታሙ ሰው የናስረዲንን ፀሎት ሲሰማ የመስጊዱ ጣሪያ ላይ ወጥቶ 999 ፓውንድ ሊወረውርለት አሰበ፡፡ ወደ መስጊዱም በመሄድ ናስረዲን አምላኩ ገንዘብ እንዲሰጠው ሲፀልይ ስስታሙ ሰው ገንዘቡን ማዝነብ ጀመረ፡፡ ናስረዲንም በጣም ተደስቶ ገንዘቡን ከሰበሰበ በኋላ መቁጠር ጀመረ፡፡ በመጨረሻም 1 ፓውንድ መጉደሉን ሲያውቅ ወደ ሰማይ አንጋጦ “አምላክ ሆይ፣ 1 ፓውንድ አጉድለህብኛልና ዕዳ አለብህ፡፡” አለ፡፡

በሚቀጥለው ቀን ጎረቤቱ ወደ ናስረዲን ቤት ሄዶ “አዳምጥ፣ ፀሎትህን ሁሉ ሰምቻለሁ በፀሎትህም የለመንከውን ገንዘብ 1000 ፓውንድ ካነሰ አልቀበልም ማለትህን ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ግን 999 ፓውንድ ስሰጥህ ተቀብለሃል” አለው፡፡ ናስረዲንም “ስለምን እያወራህ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ውጣ ከቤቴ” አለው፡፡

ስስታሙም ሰው ወደ ዳኛ ወሰደው፡፡ መንገድ ከመጀመራቸው በፊት ግን ስስታሙ ሰው በቅሎውን ጭኖ ኮቱን ለበሰ፡፡

ይህንን ባየ ጊዜ ናስረዲን “እኔ በጣም አርጅቻለሁ፣ በእግሬ መጓዝ አልችልም፡፡ በጣም ስለበረደኝም ወደ ዳኛ እንድሄድ ከፈለክ ኮትህን ለብሼ በቅሎህን መሳፈር አለብኝ፡፡” አለው፡፡

ስስታሙም ሰው 1000 ፓውንዱን ማጣት ስላልፈለገ በሃሳቡ ተስማማ፡፡

ከዚያም ጉዟቸውን ወደ ፍርድ ቤት ቀጠሉ፡፡ ናስረዲንም ዳኛውን በርቀት ባየው ጊዜ ኮት ለብሶ በቅሎዋን የተሳፈረው እሱ መሆኑን ዳኛው እንዲያይለት መጮህ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ቃዲው ድምፁን ሰምቶ ሲመለከት ሽማግሌውን ሰው ከበቅሎው ላይ አየው፡፡ ናስረዲን ከበቅሎዋ ላይ ወርዶ ካሰራት በኋላ ከሳሽና ተከሳሽ ከዳኛው ፊት ቀረቡ፡፡

ከሣሹ ስስታም ሰው “ጌታዬ ይህ ሽማግሌ አምላክን ‘1000 ፓውንድ ስጠኝ፡፡ ከዚያ ያነሰም ሆነ የበለጠ አልቀበልም’ ብሎ ሲፀልይ ሰምቼ ልፈትነው በማሰብ 999 ፓውንድ ብሰጠው ቃሉን አጥፎ ገንዘቡን ወስዷል፡፡” ብሎ ከሰሰው፡፡

ናስረዲንም በተራው “ጌታዬ ይህ ሰው እብድ ነው፡፡ ይህንን ማረጋገጥ እችላለሁ፡፡ በእርስዎ ፊት ይህንን የለበስኩትን ኮት የእኔ ነው ይላል፡፡” አለ፡፡

ስስታሙም ሰው አቋርጦት “በእርግጥ ኮቱ የኔ ነው!” ብሎ ጮኸ፡፡ ናስረዲንም በመቀጠል “በኮቱ ብቻ አይደለም የማረጋግጠው፡፡ በበቅሎ ስመጣ እርስዎ ጌታዬ አይተዋል፡፡ እሱ ግን በቅሎው የኔ ነው ይላል፡፡” አለ፡፡

ስስታሙም ሰው በድጋሚ “በእርግጥም የእኔ ነው::” ብሎ ጮኸ፡፡ ቃዲውም እውነትም ስስታሙ ሰው እብድ ነው ብሎ በማሰብ አባረረው፡፡ ወደ የቤታቸው ሲመለሱ ስስታሙ ሰው እጅግ በጣም አዝኖ ነበር፡፡

ናስረዲንም ጠርቶት “በሰውና በአምላክ መሃከል ለምን ለመግባት ትሞክራለህ? ሁለተኛ ይህ ድርጊት እንዳይለምድህ፡፡” ብሎ ገንዘቡን መለሰለት፡፡

  • በሃጂ አብዱሰታር መሃመድ በሽር የተተረከ የሐረሪ ተረት

********

ያማርኛ ስልት

 “ያማርኛ ስልት እንደ ሕዝቡ አራት ክፍል ነው። አንደኛው የቤተ ክህነት፣ ኹለተኛው የቤተ መንግሥት፤ ሦስተኛው የነጋዴ፤ አራተኛው የባላገር። የቤተ ክህነት ዐማርኛ በሰዋስው ተመሥርቶ ባገባብ የታነጠ፣ በትርጓሜ የተቀረጠ፤ በግእዝ አበባ የተጌጠ ነው። ከግእዝ በቀር ሌላ ባዕድ ቋንቋ አይገባበትም። የቤተ መንግሥት ዐማርኛ የግእዝ ትምርት ስላለበትና ሠራተኞቹ የካህናት ወገን ስለ ኾኑ እጅግ ስብቅል ነው፤ ቃላትን ኹሉ ‘እግዜር’ እንደ ማለት በማሳጠርና በማሳመር በማከናወን ይነገራል።

Anchor… የነጋዶችና የቀራጮች፣ የመዝገብ ጣፎች ዐማርኛ ግን እንደ ንፍሮና እንደ ልመና እኽል ቅይጥ ውጥንቅጥ ነው። ሥራቸውና መሣሪያቸው ከውጭ አገር ጋራ ስለ ኾነ በሸቀጡና በንግዱ ዕቃ መጠን በየጊዜው ሌላ ባዕድ ቋንቋ እየጨመረ፤ ሳይቸግረውም እየተበደረ ያነኑም እያዘናጎለ ብርዑን ‘ብዕር’ እያለ በድብልቅልቅነት ሲጣፍና ሲነገር ይኖራል። . . . የባላገሮች ዐማርኛ ሥረ ወጥ ነው። ጥፈትና ትምርት ስላጣ መታደስ፣ መለወጥ፣ መሰብቀል፣ መሻሻል የለውም። በዚያው በዱሮው በጥንተ ተፈጥሮው ይነገራል።”

  • ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መዝገበ ፊደል የግእዝና ያማርኛ ቋንቋ መክፈቻ››1926 ዓ.ም.

*********

ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን

ከጥንት ጀምሮ በቃል ሲነገር የሚኖረውን የአባቶቻችንን ተረት ብንመለከተው ብዙ የሚጠቅም ምክር እናገኝበታለን፡፡

በአርእስቱ እንደተነገረው ክፉ ሥራ መሥራት ጉዳቱ ለሠሪው ነው፡፡ ንብ ሌላውን አጠቃሁ ስትል በመርዟ ትነድፋለች፡፡ እሷም ይህን ክፋተ ከሠራች በኋላ አንድ ደቂቃ ሳትቆይ ትሞታለች፡፡ የእሳት ራትም እንዲሁ መብራቱን ለማጥፋት ስትሞክር ተቃጥላ ራሷ ትጠፋለች፡፡ ትንኝ ሰው ዓይን ለማወክ ትገባና ሕይወቷን አጥታ ተጎትታ ትወጣለች፡፡ እንክርዳድን የዘራ እንክርዳድን ያመርታል ክፉ የሠራም ሰው በክፋቱ ይጠፋል፡፡ በሰው የሚድነው በምነቱና በቅንነቱ ብቻ ነው፡፡

  • አያሌው ተሰማ ዘብሔረ ጎጃም ሰንደቅ ዓላማችን ጋዜጣ የካቲት 20 ቀን 1935 ዓ.ም.

 

 

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች