‹‹ግሪክ ዕዳዋን ባለመክፈልዋ ምክንያት ከአውሮፓ ኅብረት አባልነት ከመባረር ለመዳን ጠንካራ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርባታል፡፡››
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቡድን ሰባት የበለፀጉ አገሮች ስብሰባ ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ ኦባማ እንደሚሉት የግሪክ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ግሪካውያን ጠንከር ያለ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ የግድ ይላቸዋል፡፡ ‹‹ለግሪክ አሁን የሚያስፈልገው ከዚህ ቀውስ ውስጥ ለመውጣት አስቸኳይ መፍትሔ የሚያፈላልግ መንገድ ብቻ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ መድረስ ለዘለቄታው ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኦባማ እንደሚሉት፣ ግሪክ አሁን ማድረግ ያለባት አበዳሪዎቿን የሚያስደስት ሥራ መሥራት ሳይሆን፣ ለዘለቄታው ብልፅግና ሊያመጣ የሚያስችል መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ብቻ ነው፡፡ ከ300 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ዕዳ ያለባት ግሪክ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ስላለች፣ አበዳሪዎቿም እንዲለሳለሱ ኦባማ ጥሪ አድርገዋል፡፡ አበዳሪ አገሮች ግን ግሪክ መፍጠን አለባት እያሉ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ግሪክ ከአውሮፓ አባልነት ትሸኛለች የሚለው ብዙዎችን እያግባባ ነው፡፡