Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልእየሞተ ያኖረ ግእዝ

እየሞተ ያኖረ ግእዝ

ቀን:

በመልካሙ ተክሌ

እየሞተ ይመስላል እንጂ ሞቶ አልተቀበረም፡፡ አሁን ሲነድ አልታየም እንጂ የተዳፈነ እሳት ነው፡፡ የግእዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ሁነኛ ስፍራ ነበረው ተብሎ የሚያበቃ ብቻም አይደለም፡፡ ከትናንታችን ጋር የተያያዘው ግእዝ ከዛሬአችን እና ከነገአችን ጋርም ይተሳሰራል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ ግእዝ ከትናንት ጋር ብቻ እንደሚያያዝ እና ገና ድሮ ሞቶ እንደተቀበረ ያወጁ ወገኖችም አሉ፡፡ ለእነዚህኞቹ ቋንቋው ለመጨረሻ ጊዜ የሞት ጣር ይዞት የታየው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ሞተ ቢሉም ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ቢያንስ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንደምትጠቀምበት ሲያዩ የሚሰጡት ምላሽ በአፍ መፍቻነት ካልዋለ ሞተ ነው የሚባለው አዘለም አቀፈም ያው ተሸከመ ነው ይላሉ፡፡ እንደሚታወቀው በአፍ መፍቻነት ሳይውሉ በርካታ ቋንቋዎች በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሞቱ ግን ማለት አይደለም፡፡

- Advertisement -

በሌላ በኩል ደግሞ ግእዝ  በመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ተወሰነ እንጂ ገና አልሞተም እንደውም የመነሻ የትንሣኤው ጊዜ አሁን ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ከነዚሁ መካከል ማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ‹‹የግእዝ ቋንቋ ፋይዳ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት አንፃር›› የሚል እና ‹‹የግእዝ ቋንቋ መስተፃምራዊ ሐረግ መዋቅሮች›› በሚል አንድ ጥናታዊ መድረክ አዘጋጅቶ ሁለቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

ከጥናታዊ ጽሑፎቹ የመጀመርያውን ያቀረቡት እና በቋንቋው የግእዝ ተናጋሪ ቤተሰብ እስከ መመሥረት የደረሱት መምህር ደሴ ቀለብ ናቸው፡፡ በጉባኤው ላይ እንደተነገረው መምህር ደሴ በታሪክ የመጀመርያ ዲግሪአቸውን በፊሎሎጂ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን አሁን የዶክትሬት ዲግአቸውን በመማር ላይ ናቸው፡፡ እንደውም በዕለቱ አስተያየት ከሰጡ ተወያዮች ለመጀመርያ ጊዜ ያያቸው አንዱ “ጢማቸው የተንዠረገገ ሽማግሌ” ይመስሉት እንደነበር ገልጧል፡፡ የመምህሩ ወጣትነት በግእዝ ዙርያ ካሁን በኋላም ብዙ እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡

የግእዝ ቋንቋ ቤተሰብ እስከመመሥረት የደረሱት መምህር ማኅበረ ቅዱሳን በሚያሳትመው ሐመር መጽሔት ላይ ግእዝ በማስተማርና መጻሕፍት  በመጻፍም ይታወቃሉ፡፡ እንደርሳቸው ሁሉ የግእዝ ቋንቋ በማስተማርና የቋንቋውን ሥርአተ ሰዋስው አስመልክቶ ‹‹መርኆ ሰዋስው ዘልሳነ ግእዝ›› የሚል መጽሐፍ በማዘጋጀታቸው የሚታወቁት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጁ ሊቅ መምህር ዘርአ ዳዊት አድሐናም ሆኑ ግእዝ ቋንቋን በኮሌጅ ደረጃ እያስተማረ በዲፕሎማ የሚያስመርቀው ኮሌጃቸው በጉባኤው አንድም ጊዜ አለመጠቀሳቸው ከፍተኛ አግራሞት አሳድሯል፡፡ በዚሁ መጽሐፋቸው መግቢያ መምህር ዘርአ ዳዊት ስለግእዝ አስፈላጊነት ሲናገሩ “በኢትዮጵያ ግእዝን ሳያውቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ታሪክን፣ ባህልን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ቀደምት የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርአትና የአምልኮ ወዘተ መጻሕፍትን ማወቅ እጅግ ያዳግታል፤” ካሉ በኋላ ሲያጠቃልሉ ቋንቋውን የአገሪቱ የባህል፣ የሃይማኖት የታሪክና ሕግ መሠረትነት አስረግጠዋል፡፡

በዚህ የግእዝ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሳይንስ፣ ሕግ፣ ሕክምና፣ ባሕረ ሐሳብ ጥናት አውታርነት  የሚስማሙት መምህር ደሴ ቀለብ፣ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የእንግሊዝ ወታደሮች ከዘረፏቸው ውስጥ አብዛኛው ቅርሶች የግእዝ መጻሕፍት መሆናቸውንና ወደ ሌሎች ውጭ አገሮች ከተጋዙት የኢትዮጵያ መጻሕፍት አብዛኛው የግእዝ መሆናቸውንም በቁጭት ይገልፃሉ፡፡ ከጥናቶቻቸው በአንዱ የገጠማቸውን የግል ገጠመኝ በማስታወስም ‹‹የኛኑ የግእዝ መጻሕፍት ለኛው መልሰው በውጭ ምንዛሪ ያከራያሉ፡፡ በአሜሪካ ያለ የኛውን የግእዝ መጽሐፍ ማይክሮ ፊልም ፈልጌ ብጠይቅ በጣም ብዙ ዶላር ተጠይቄአለሁ፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸው ብቻ አይደሉም ይህን የተጠየቁት፡፡ ሌሎች ብዙ ኢትዮጵያውያንም ከደጃቸው ሞፈር ተቆርጦባቸዋል፡፡

እንደ መምህር ደሴ አባባል ግእዝ የገቢ ምንጭ የሆነው በውጭ አገሮች ላሉ ባለሙያዎች ብቻም አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ አስጎብኚ ድርጅቶችና ግለሰብ አስጎብኚዎችም አሁን ላይ በግእዝ እንጀራ እየበሉ ነው የሚሉት መምህር ደሴ፣ ቋንቋው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ መገልገያ ነው ተብሎ መቆጠሩን አይቀበሉትም፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም የተጠቀሱት አስጎብኚዎችና ተመራማሪዎች እንኳ ቢወሰዱ ከተለያዩ ሃይማኖቶች እንጂ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ፡፡

ግእዝ እንደዚህ የገቢ ምንጭ የሆነው የአገሪቱን የተለያዩ የኪነጥበብ፣ ሥነጥበብ፣ ሥነፈለክና ባሕረሐሳብ ፣ሥነ መለኮት፣ ፍልስፍና፣ ሕክምና ወዘተ ያካተቱ ጥልቅ የምርምር ሥራዎችን በመያዝ በሺሕ ለሚቆጠሩ ዘመናት በመያዙ ነው፡፡ በጥንታዊ ብራና የታጨቁ እነዚህን የግእዝ መጻሕፍትና ሌሎች መዛግብት ለማየት ጎብኚዎች ባሕር አቋርጠው ቢመጡ ያላቸውን ጠቀሜታ በመረዳት እንጂ የተፈጥሮ መስህቦችን እንደመጎብኘት ያህል ያዝናናናል ብለውም አይደለም፡፡ የብራና መጻሕፍት ስርቆሽ የበረከተበትን ምክንያት ስናጤን ከዚህ ጀርባ የውጭ አገሮች ኢትዮጵያ በግእዝ ምን ያህል ተራምዳ እንደነበርና ዋጋውን መረዳታቸውን እንረዳለን፡፡ የግእዝን የዕውቀት ምንጭነት በመጠቀም ለዘመናዊ የምርምር ሥራዎቻቸው መሠረትና ማገር ማድረጋቸውን ከኛው የወሰዱትን ዕውቀት ለኛው ለማስተማርና ለመሸጥ አለመመለሳቸውንም እንረዳለን፡፡ ለዚህም ነው መምህር ደሴ የኢትዮጵያውን የግእዝ ማይክሮ ፊልም  መጽሐፍ ገልበጥ ገልበጥ ለማድረግ በዶላር እንዲገዙ ግድ የተባሉት፡፡

ዘመኑ የመረጃ ነው፣ ዘመኑ የዕውቀት ነው በሚባልበት ባሁኑ ወቅት ለብዙ ነገሮች ምንጭ የሆነውን ግእዝን ልናሳድገው፣ ልንንከባከበው ሲገባ ሞቷል አልሞተም እንባባላለን፡፡ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሆኑ ሴት ተማሪዎች ታክሲ ውስጥ በትምህርት ቤቱ እንደ ትምህርት ዓይነት ግእዝ ስለመሰጠቱ እያወሩ ሲሄዱ ከጎኔ ተቀምጦ የነበረ ሰው  “የሞተ ቋንቋ እያስተማሩ ጊዜያችሁን ያባክናሉ” ሲላቸው የሰማ ሌላ  ከፊት የነበረ ተሳፋሪ “ግእዝን በመማር አለመሞትህን  አረጋግጥ” ብሎት እንደወረደ አስታውሳለሁ፡፡

እሱ የሞተ ቋንቋ ይበለው እንጂ እንኳን አልሞተም፡፡ ካልሞተ ደግሞ እንዲያገግም ማድረግ ይቻላል፡፡ ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ በዲፕሎማ መስጠቱና በሌሎች ጥቂት ትምህርት ቤቶች መሰጠቱ በአብነት ትምህርት ቤቶች ብቻ ተወስኖ እያጣጣረ ነው የተባለለትን ቋንቋ አለመሞቱን ያረጋግጣል፡፡ አሁን አሁን የቀድሞውን ያህል ጠንክሮ ባይታይም የነ መምህር ደሴ የግእዝ ተናጋሪ ቤተሰብ  ዓይነት እንቅስቃሴዎችም  የግእዝን ትንሣኤ አይቀሬነት ያመላክታሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ግእዝን በዲፕሎማ ከነባለቤታቸው ተምረው ቋንቋውን የቤተሰባቸው መግባቢያ ቋንቋ ያደረጉት ኢንጂነር ዮሐንስ ሙከራ አንድ እርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ቤተሰብ በግእዝ መነጋገር ከጀመረ ነገ ሁለት፣ ሦስት፣ መቶ፣ ሺሕ ወዘተ የማይነጋገርበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡

አማርኛ በርካታ ቃላት የወሰደው ከግእዝ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ስለዚህ ስለአማርኛ ለማጥናት የግእዝን ጓዳ መዳሰስ የግድ ይላል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጥናትም የግእዝ መኖር አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም  የየራሳቸው ችግሮች ይኑሩባቸውም ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክ ድርሳናት የተጻፉት በግእዝ ነው፡፡ ስለዚህም ነው የኢትዮጵያን ታሪክ አጠናለሁ የሚል ግእዝን ማወቅ ግዴታው ነው የሚባለው፡፡ እንደ ኢዮብ ሉዶልፍን የመሰሉ የውጭ አገር ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ ሳይመጡ ግእዝን በማጥናት የአገሪቱን ታሪክ ያጠኑት፡፡ መቼም ኢትዮጵያ ሆኖ ግእዝን ማጥናት ውጭ አገር ሆኖ ይህንኑ ቋንቋ ከማጥናት ይቀላል፡፡ የግእዝ መጻሕፍትም ሆኑ ሌሎች መዛግብት የመጀመርያ ደረጃ የታሪክ ምንጮች ናቸው፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የመሳሰሉ  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያስጠኑት በእንግሊዝኛ ነው፡፡ አንድን ታሪክ የገዛ አገሩ ቋንቋ እያለ በውጭ ቋንቋ ማጥናት የታሪክ ምንጩን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ የሚደርገው ይመስላል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የትምህርት ተቋማት የኢትዮጵያ ታሪክ ብለው ግእዝን ከተማሩ በኋላ በጻፉ የውጭ አገሮች ምሁራን የተደረሱቱ ናቸው ማጣቀሻ ሆነው  የቀረቡት፡፡ ይህ የአገሩን ሰርዶ በውጭ በሬ ከመሆኑም ባሻገር በቅኝ ገዢዎች ከመገዛት ያላነሰ አንገት ያስደፋል፡፡

ከዚህ የበለጠ የሚነጋግረው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሆነው ግእዝ የተወሰኑ ብሔረሰቦች እና የአንድ ሃይማኖት ብቻ ንብረት አድርገው የሚቆጥሩ መኖራቸው ነው፡፡ እነሱ ግእዝ አይወክለንም ከሱ ይልቅ ሌላ የውጭ ሀገር ቋንቋ ማወቅ ነው የሚበጀን ይላሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ምንም ኢትዮጵያዊ ደም ሳይኖራቸው እንደነ ሉዶልፍ ያሉቱ ግእዝን አጥንተው የራሳችንን ታሪክ በነሱ እርሳስ ጽፈው በነሱው ላጲስ ያጠፉልናል፡፡ ቢሆንም ግን እነሱ ዘንድ ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌን ባለእዳ ያልሆነው  ተቀብሎት እዚህ ገና ግእዝን  በዲፕሎማ ማስተማር በጀመረ ኮሌጅ ስንንገዳገድ እነሱ በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው የግእዝ መጻሕፍት ከማጨቃቸውም በላይ በዶክትሬት ዲግሪ ቋንቋውን ያስተምራሉ፡፡

እነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገር በቀሉን ዕውቀት ወደ ሁለተኛ ታሪክ ምንጭ በማውረድ በእንግሊዝኛ ሲያስተምሩ በሩሲያ፣ በኮርያ፣ በጀርመን፣ በኩባ፣ በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግን በምሕንድስና፣ በሒሳብ፣  በኅብረተሰብና በሌሎችም የጥናት መስኮች ከፍተኛ ትምህርት ሲያስተምሩ ቀደም ብለው ቢያንስ ለስድስት ወራት ወይንም ለአንድ ዓመት የየአገሮቻቸውን ቋንቋ በማስተማር ቋንቋዎቻቸውን ለማስፋፋት ይጥራሉ፡፡

እኛስ ቋንቋዎቻችንን  በተለይ ግእዝን እንዴት ነው የምናስፋፋው የሚል ጥያቄ እዚህጋ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ቋንቋው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ብሔረሰቦች ብቻም አይደለም፡፡ ግእዝ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ንብረት ነው፡፡ ግእዝ የእገሌ ብሔረሰብ ያልተባለ የሁላችንም የጋራ ቋንቋ በመሆኑና በሁሉም ረገድ የበለጸገ ቋንቋ መሆኑ እየሞተ ያኖረንን ግእዝን ለብሔራዊ ቋንቋነት መታጨትም ይችላል፡፡ ግን ከዚያ በፊት ህልውናው ተረጋግጦ መስፋፋት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላትም ሆኑ በየዓመቱ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መካሔድ የጀመረው የግእዝ አገር አቀፍ ጉባኤ ሚና ትልቅ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...