ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) በአብዛኛው ጥቅም ላይ ሲውሉ የሚሰማው በጦርነት ቀጣና ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ድሮን ጥቅም ላይ የምታውለው ደግሞ አሜሪካ ናት፡፡ አሜሪካ ድሮን የጦርነት ቀጣናን ለማሰስ፣ ለመቆጣጠርም ሆነ ተፈላጊ ዒላማን ለመምታት ስታውል፣ ከዚህ ባለፈ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአሜሪካ ውስጥ ብቻ ለሚቀረፁ ፊልሞች ጥቅም ላይ ማዋል ጀምራለች፡፡
እ.ኤ.አ. በ2014 በሩሲያ ሶቺ ለተከናወነው የክረምት ኦሊምፒክ ቀረፃም ድሮን ጥቅም ላይ ውሎ ነበር፡፡ በአሜሪካ በኒብራስካ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ማስ ኮሙዩኒኬሽንስ ኮሌጅ ‹‹ድሮን ጆርናሊዝም ላቦራቶሪ›› ተቋቁሟል፡፡ የድሮን ጆርናሊዝም ሲነሳ አጠያያቂ የሆኑ የሥነ ምግባር ጉዳዮች ተያይዘው የሚወሱ ቢሆንም፣ አስቸጋሪና አዳጋች እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች በሚደርሱበት ጊዜ በቀላሉ ለመዘገብ ይቻል ዘንድም እ.ኤ.አ. በ2011 ‹‹ፕሮፌሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ድሮን ጆርናሊስትስ›› ተቋቁሟል፡፡
በህንድ የሕግን ተፈጻሚነት ለማጠናከር ብዙዎቹ የፖሊስ ዲፓርትመንቶች በድሮን ቅኝት ያደርጋሉ፡፡ በቻይና ደግሞ ድሮን ለየት ያለ ተግባር ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በአሜሪካ ድሮን ለጦርነት ሲውል በቻይና ደግሞ የፈተና ኩረጃን በመቆጣጠር አዲስ ጥቅም ይዞ ተከስቷል፡፡
የፈተና ኩረጃ በተለይም የብሔራዊ መልቀቂያ ወይም ዩኒቨርሲቲ መግባትና አለመግባትን የሚወስነው ፈተና ላይ የሚስተዋለው የተንሰራፋ ኩረጃ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገሮች ራስ ምታት ነው፡፡ በመሆኑም አገሮች የፈተና ኮድን መቀያየርን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ሆኖም ይህ ኩረጃን ሊያስቀር አልቻለም፡፡ ከቻይና ሰሞኑን የወጣው ዜና ግን ለየት ያለ ነው፡፡ በአገሪቱ ሥር የሰደደውን የፈተና ኩረጃ ለማስቆም በዘንድሮው ፈተና ‹‹ድሮን›› ዘብ አቁማለች፡፡
በቻይና በየዓመቱ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወይም የኮሌጅ መግቢያ ፈተና ይወስዳሉ፡፡ ለማንኛውም ተማሪ ይህን ፈተና ተፈትኖ ከማለፍ ውጪ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ኮሌጅ ሊቀላቀልበት የሚችል ሌላ አማራጭ የለም፡፡ በመሆኑም የኮሌጅ መግቢያ ፈተናው ለተማሪዎችም ሆነ ለወላጆች አስጨናቂ ነው፡፡
በቻይና ‹‹ጋኦካኦ›› የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የአንድን ተማሪ በተለይም ከደሃ ቤተሰብ የመጣውን ለወደፊት የመማርንም ሆነ ሥራ የማግኘት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ነው፡፡ ጥሩ ሥራ ለማግኘትም የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ ፈተናው ደግሞ በዓለም በዚህ ደረጃ ከሚሰጡ ፈተናዎች ከባዱና ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበትም እንደሆነ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡
በቻይና ኩረጃ እንዳይኖር ለማድረግ ተማሪዎች በሚፈተኑበት ክፍል ተቆጣጣሪ ካሜራዎች የሚገጠሙ ሲሆን፣ ማንኛውም ተማሪ የሞባይል ስልኮችንም ሆነ ዲጂታል የእጅ ሰዓቶችን ይዞ እንዳይገባ ከመግቢያው ጀምሮ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ በታገዘ ፍተሻ ያልፋል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው የፈተና ወረቀቶቹ በየአዳራሹ ከመበተናቸው በፊት ቀድመው እንዳይወጡም መቆጣጠሪያ በተገጠመላቸው መኪኖች ተጭነው ይሄዳሉ፡፡ ባለፈው እሑድና ሰኞ በተሰጠው ፈተና ደግሞ ኩረጃን ለመከላከል ከተገጠሙ ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ ድሮን ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
ዳሂ ኦንላይን እንደዘገበው፣ ስድስት ተሽከርካሪ ተቆጣጣሪ ክንፎች የተገጠሙለት ድሮን በሉያንግ ከተማ የሚገኙ ሁለት የፈተና ማዕከላትን ከላይ ሆኖ በሬዲዮ የሚለቀቅለትን መረጃ በመከታተል የፈተናውን ሒደት ሲቆጣጠር ውሏል፡፡
የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ አንዳንድ ተማሪዎች ለመኮረጅ ሙከራ ሲያደርጉ ተይዘዋል፡፡ የኢነር ሞንጐሊያ ትምህርት ቤት ደግሞ 1,465 ተማሪዎችን ሕገወጥ ናቸው ሲል ከፈተና አግዷል፡፡
የ86 ዓመቱ ዋንግ ዣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙት ታዳጊ ወጣቶች ጋር ለፈተና የተቀመጡ አዛውንት ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም 14 ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወስደው የነበረ ቢሆንም ማለፍ አልቻሉም፡፡
በጤናው ዘርፍ የሙያ ትምህርት እንደተማሩ የሚናገሩት ዣ፣ የሁሌም ምኞታቸው የሆነውን ሜዲካል ዲግሪ አግኝተው ሙሉ የሕክምና ዶክተር የመሆን ህልም ለማሳካት ለ15ኛ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን ወስደዋል፡፡
‹‹አልጫወትም፣ የማተኩርበት ልምድ የለኝም፣ የምወደው ማንበብና መማር ነው፡፡ ፍላጎቴን ለማሟላት ማንም ላይረዳኝ ይችላል፡፡ ሆኖም አሁንም ፈተና መቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ ፍላጎቴን የማሳካበት መሰላል ነው ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉ ፈተናው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
በቻይና ለሁለት ቀናት በተካሄደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ወይም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና (ጋኦካኦ) 9.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ተፈትነዋል፡፡ በፈተናዎቹ ቀናት በመፈተኛ አካባቢ የሚገኙ የኮንስትራክሽን ሥራዎች እንዲቆሙ ተደርጓል፡፡ አሽከርካሪዎች ክላክስ እንዳያደርጉ፣ መንገደኞችም ተማሪዎችን እንዳይረብሹ የቁጥጥር ሥርዓቱ ተጠናክሮ ነበር፡፡
በአብዛኛው የእስያ ክፍል ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተናን አልፈው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ጫና እንዳለባቸው ይነገራል፡፡ ‹‹እለፍ! ማለፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መንገድህ ነው፣ ወደቅ! ወደ ኮሌጅ አትገባም፣ ዝቅተኛ ሥራ ትሠራለህ፤›› ዓይነት አካሄድ ስላለው ብዙ ተማሪዎች ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በፈተናው ክብደት ምክንያትም ራሳቸውን የሚያጠፉም አሉ፡፡
ከፈተናው መክበድና የቀጣይ ሕይወት ዕጣ ፈንታን ከመወሰን አንፃር ተማሪዎች በኩረጃ ይሳተፋሉ፡፡ ለኩረጃውም ከፍተኛ ቴክኖሎጂን ጨምሮ የተለያዩ ሥልቶችን ይጠቀማሉ፡፡ በጆሮሯቸው ውስጥ በቀላሉ ሊታዩ የማይችል ኢርፎን በመክተትና ውጭ ካለ ሰው ጋር በመነጋገር፣ በልብሶቻቸው ውስጥ መነጋገሪያዎችን በመግጠም፣ ኮምፒውተራይዝድ የሆኑ የእጅ ሰዓቶችን በማሰር ለፈተናው መልስ የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ የፈተና መልስ ከሚሸጡ ጋር በቴክኖሎጂ አማካይነት በመገናኘትና ፈተና የሚፈተኑ በመቅጠር ይጠቀማሉ፡፡ ፈተናውን ማለፍ ለቀጣይ ሕይወት ወሳኝ ነውና የመኮረጁን ድርጊት ወላጆችም ጭምር የሚያመቻቹት ነው፡፡
በቻይና የዚህ ዓይነቱ የኩረጃ ሥልት ከዚህ በኋላ ያበቃለት ይመስላል፡፡ በድሮን በመታገዝ የሚደረገው ቁጥጥር የትኛውንም ተማሪ የሚያነቃንቅ አይደለም፡፡ በየፈተና አዳራሾቹ በተገጠሙ የመገናኛ መሣሪያዎች አማካይነት ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ተማሪዎቹን ከኩረጃ አቅበው ሁለት ቀናትን አሳልፈዋል፡፡ ኩረጃን በድሮን ማለት እንዲህ ነው፡፡