Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቢገጥም ባይገጥም እኛን ምን አገባን?

እነሆ ከሜክሲኮ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። ይህ ዙር ዛሬም ሒሳቡን ያወራርዳል። ትናንት የበረደው ዛሬ እየወበቀው፣ ያጣ እያገኘ፣ የጥላቻና የትዝታ ምጥማጥ ልቡን የጎተተው ዛሬ በፍቅር ክንድ ተደግፎ እየተነሳ፣ አፋፉ ላይ ቁልቁል ሲያንዣብብ እናያለን። መኖር የማያሳየን የለም። እግር ይራመድ እንጂ የሒደት ሸንተረር ከህልውናችን አፈር ላይ አሻራውን ያኖራል። እንዲያ ከታመመን እንዲህ ልንፈወስ፣ ወዲህ ስናሽካካ ወዲያ ማዶ ተንሰቅስቀን ልናለቅስ፣ በተቃራኒ ስሜቶችና ሁነቶች የተገነባች ዓለም ላይ የሞት ሞት እንኖራለን። ያም መንገድ ይኼም መንገድ ነውና!

ታክሲያችን እየሞላች ነው። የአንገታቸው ቆዳ መሟሸሽና አስተጣጠፍ ያስተክዛል። እርጅና ብርታት ነፍጓቸው ሳያበቃ ጡንቻቸው ምርኩዛቸውን አጥብቆ አልይዘው እያለ ከእጃቸው ያፈተልካል። አዛውንቷ በሁለት ወጣቶች ተደግፈው ታክሲዋ ላይ ወጡ። ሦስት ሰው ይቀራታል። ጋቢና ሁለት መልከ መልካም ሴቶች፣ ከሾፌሩ ጀርባ አዛውንቷ፣ ቀጥሎ እኔ አንድ ጎልማሳ፣ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አዛውንቷን ደግፈው ያሳፈሩት ወጣቶች ተቀምጠዋል። መጨረሻ ወንበር አንዲት ወይዘሮና የማኅበራዊ ድኅረ ገጽ ማማ ላይ ቀልቧ የተረሳት ወጣት አለን። ወያላው በአንድ እጁ ትኩስ ሻይ ይዞ ፉት እያለ በግራው በዘይት የወዛ ፓስቲ እየገመጠ ከንፈሩን አሞጥሙጦ ብቻ ግቡ ይላል። የማሞጥሞጥ ዘመን ነው ተብሏል እንዴ? አሞጥሟጩ በዛ እኮ!

“አይ ጉድ እህል ክብሩን ጣለ። ለነገሩ ዘንድሮ ምን ክብሩን ያልጣለ ነገር አለ?” ይላሉ አዛውንቷ። ጎልማሳው ብዙ እንዲያወሩ ፈልጎ ፈገግታ ያሳያቸዋል። “እየው እስኪ። አሁን እንዲህ መንገድ ላይ የጎረሱት አንጀት ጠብ ይላል? ምናለበት ዘወር ብሎ ቢበላ?” ብለው፣ “ሁሉም ነገር መንገድ ለመንገድ የሆነበት ጊዜ። እንዲያው እንዲህ ያለ ዘመን?” ብለው ከራሳቸው ጋር የተጣሉ ሲመስሉ፣ “ተመስገን ነው መብላት መቻሉም። በኋላ እኮ ዕዳው ለእኛ ነው፤” አላቸው ወያላውን እያስተዋለ ጎልማሳው። “አሁንስ መቼ ይቀርልናል? የሥልጣን እንደሆነ ትንሽና ትልቅ የለውም። ቆይ ታየዋለህ በደረጃው አፉን ሲከፍትብንና ሲያንኳስሰን፤” ብለው ትንሽ አሰብ አድርገው ቀጠሉ። “መንገድ ላይ መብላት ሲለመድና እንደ ሥልጣኔ ሲታይ፣ ልመናም እንደ ሥራ ፈጠራ መታየት ጀመረ ብዬ ነው እንጂ እኔማ ምን አግብቶኝ ልጄ? የእዩኝ ዕወቁልኝ ባይነት ግብዝነት ዓይን ያወጣው ሰው በአደባባይ እንጥሉ እስኪታይ አፉን ከፍቶ መጉረስ ሲጀምር ነው። እንግዲህ ከዚያ ጊዜ አንስቷ አየህ እንጥል የማሳየት ውድድር ደሃ ሲያባዛ፣ ሀብታሙን ጥቂት ሲያደርገው እያየን ነው። በረሃብ ጊዜ ስንዴ ሲረዳ ያልተሽቀዳደመ ኩሩ ሕዝብ ከነልጅ ልጆቹ እየተግተለተለ የልመና ባህል መወራረስ የጀመረው መንገድ ለመንገድ መመገብ ከመጣ ወዲህ አይደለም ልትለኝ ነው? እኛ መቼ ወደን ሆነ ብርጭቆውን ትተን እርጎ በጣሳ መጠጣታችን? ይኼን ፍራቻ ነበር። ብቻ እንዲያው . . .” አዛውንቷ ለራሳቸው ማጉረምረም ያዙ። ቀላልና ምንም የማይመስለንን የጎዳና ላይ አመጋገብ ሥርዓት እንዴት አድርገው ከመልካም እሴቶች መጠውለግ ጋር ሊያጣምዱት እንደፈለጉ ተሸራርፎ ሲገባን ‘አይ የድሮ ሰው’ አልን። አይ የድሮ ሰው!

ከአዛውንቷ አጠገብ ሲራመድ ጠደፍ ጠደፍ የሚል ኮልታፋ ከመቀመጡ፣ መጨረሻ ወንበር ሁለት ኮረዶች ከመሰየማቸው፣ ወያላው እጁ ላይ የተቅለጠለጠውን ዘይት በፊቱና በፀጉሩ እየጠረገ “ሳበው” ብሎ በሩን ዘጋ። ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረች። ሲጓዝ ብቻ ሳይሆን ሲናገርም የሚጣደፈው ከአዛውንቷ አጠገብ የተሰየመው ኮልታፋ ተሳፋሪ፣ “እኛ ለሆዳችን አናምነውም አንተ ፊትህን ትቀባዋለህ፤” ሲል ወያላውን ያናግረዋል። “ግድ ነዋ በዚህ ኑሮ ላይ የኮስሞቲክስ ወጪ ተጨምሮ ይቻላል ታዲያ? እንኳን እኛ ወንዶቹ ሴቶቻችንም አልቻሉት፡፡ በስንት የስፖንሰር እገዛ እንኳ አልሞከሩትም። ልክ አይደለሁ?” ጋቢና ወደ ተቀመጡት ቆነጃጅት አስግጎ ይጠይቃል። ትከሻቸውን ሰብቀው በንቀት ሲያልፉት ወያላው ከፍቶት “ሒሳብ ወጣ ወጣ፤” ብሎ ፊቱን ዘፈዘፈው። ችኩሉ አሁንም በቸኮለ አነጋገር፣ “ኧረ አረጋጋው ባርሴሎናን ይመስል ጨዋታው ከመጀመሩ ጎል ካላገባሁ ትላለህ እንዴ?” ሲለው ወያላው ሳቀ። ይኼን ጊዜ ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ “ጊዜው የፍጥነት ነዋ። ጎሉ ፈጣን፣ ዕድገቱ ፈጣን፣ ውድቀቱ ፈጣን፣ ጋብቻው ፈጣን፣ ፍቺው ፈጣን፣ ሁሉ ነገር ፈጣን። ኧረ ተጨማሪ 30 ደቂቃ ናፈቀን። አልናፈቀህም ሁለተኛ ዕድል?” አለ ወደ እኔ ዞሮ። “ ‘ምን ታረጊዋለሽ?’ የሚለውን ዘፈን መስማት ነው፤” አለ ኮልታፋው ፊቱን አዙሮ። “ቆይ ግን እኛ ዘፈን ብቻ እየተገባበዝን እስከ መቼ?” አለ ጎልማሳው የሞቀ ፈገግታ እየለገሰ። “እስክንታደለው መታገል ነው። ሌላ ምን ይደረጋል? ቢቻለን ደግሞ እስከ መቼ የሚል ጥያቄ ማቆም አለብን። የጊዜና የዴሞክራሲ ጥያቄ ለጊዜው ይዘለለን በሚለው የምንጣላ አይመስለኝም፤” አለ ኮልታፋው። ይኼኔ “መጡ?!” ብለው አዛውንቷ አፋቸውን በመዳፋቸው ሲያስጠልሉ ሁላችንም ፈገግ አለን።

“ምነው እማማ?” ጠየቃቸው ጎልማሳው። “አይ ‘ዴሞክራሲን’ የሰማኋት መስሎኝ ነው፤” አሉት። “ፖለቲካ ይፈራሉ?” ተራውን ኮልታፋው ሲጠይቅ፣ “ብፈራ እመርጥ ኖሯል? እኔ ፖለቲካና ሰይጣን አልፈራም። ቅዱስ ሚካኤልን እንጂ። እንዲያው የሰማዩንም የምድሩንም መጠየቅ አቁመን የት ልንደርስ እንደምችል ግራ ገብቶኝ ነው፤” ብለው ዝም ሲሉ ወይ ምድራዊ ገነት ካልፈጠርን አልያም ለሰማዩ መንግሥት ካልተጋደልን፣ ለጊዜና ለዴሞክራሲ መሀል ሰፋሪ ሆነን መኖር እንደማንችል አንዳንዶቻችን ገባን። አንዳንዶቻችን ብቻ እየገባን ተቸገርን እንጂ!

እየተጓዝን ነው። ደህና ተሟሙቆ የነበረው ጨዋታ ወዲያው ቀዝቅዞ ሁሉም በሞባይል ስልኩ ‘ኢንተርኔት’ ይጎረጉር ጀመር። ጋቢና ከተቀመጡት ቆነጃጅት አንዷ፣ “አንቺ ይህቺ ልጅ ግን አታፍርም? በእኔ ሹራብ ነው አሥር ጊዜ ፎቶ እየተነሳች ‘ፖስት’ የምታደርገው? እኔማ እጽፍላታለሁ፤” ብላ ለ‘ኮሜንት’ ስትንደረደር ሁሉም ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ወደ ጋቢና ያይ ጀመር። “ኧረ ነውር ነው። ምን ነክቶሻል? ‘እጀ ጠባብህን ቢወስድብህ መጎናፀፊያህን አትከልክለው’ እያለ አንቺ ለአንድ ጨርቅ አብረሻት ትገመቻለሽ። ተይው ይመርባት። ማነው ደግሞ በዛሬ ጊዜ በራሱ ወርቅ የደመቀው? ዘመኑ እኮ የመነካካትና የመቀማማት ነው፤” ጓደኛዋ ልታረጋጋት ስትጥር “ታዲያ ዝም ማለት ነው ጥሩ? ተበድረው የማይመልሱ ሰዎችና መንግሥታትማ ልካቸውን ማወቅ አለባቸው፤” አለችና ‘ኮሜንት’ መጻፍ ጀመረች። ጎልማሳው ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ “የሰው ወርቅ ስትል ትሰማለህ? እውነቷን እኮ ነው። በሰው ላብ የሚሸለመው፣ በሰው ፕሮፖዛል ጨረታ የሚያሸንፈው፣ በመተትና በድግምት የሰው ዕድል እያስገለበጠ ለልጅ ልጆቹ የደም ዕዳ የሚያወርሰውን እያየን እንዳላየን ስናልፈው መኖራችን አያበሳጭም? ደግነቱ እንዳሁኑ ጊዜ አስተያየት መስጫ ሳጥን ሰው በኪሱ ይዞ አይዞር። እንኳን ግለሰብ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴውም ብትል። ዕድሜ ለ‘ፌስቡክ’ ግን ቢያንስ አየህ ማንም የሚሰማን ባይኖር፣ ማንም ኮሜንታችን መስጦት ‘ላይክ’ ባያደርገው ተናግሮ እንደ መተንፈስ ያለ ፈውስ የለም፤” ይለኛል። ተናግሮ ነው ተሳድቦ መተንፈስ? ለማለት የፈለገው አልገባኝም። ‘ኮሜንቱ’ ሁሉ በስድብ ጀምሮ በስድብ የሚያልቅ ነዋ!

  ጉዟችን ቀጥሏል። ሻሽ የጠመጠመች አንዲት የገጠር ደርባባ ታክሲያችንን አስቁማ ገባች። ስልክ እያወራች ነው። ስለወዳጅ ዘመዶቿ ጤንነት ጥቂት ስትጠያይቅ ቆየች። ወዲያው አንድ የቅርቧ ሰው መሞቱን ተረዳች መሰል ጩኸቷን አቀለጠችው። ገሚሱ ማባበል ጀመረ። ሌላው “ተዋት! ማልቀስ እኮ ሰብዓዊ መብቷ ነው፤” ይላል። እዬዬው አልበቃን ብሎ የመብት ክርክሩ ጦፈ። “ኧረ እንዲያውም ከቻለች የእኛን ጨምራ ታልቅስ። ሐዘን የበዛበት ኑሮአችን እንባና ደመወዛችንን ጨረሰው፤” ሲል አንዱ፣ “የማንን እንባ ማን ያምጣል? የማንን ፍርድ ማን ይቀበላል? የዘራነውንማ እንጨድ እንጂ ተውን፤” ይላል ሌላው። ሾፌሩ ጭቅጭቁን ከምንጩ አደርቃለሁ ብሎ፣ “ሃሎ ከአንድ እስከ ሦስት እስክቆጥር ማልቀስ ካልተውሽ ታሪፉን እጥፍ የሚያስከፍል ማዕቀብ ይጣልብሻል፤” ሲላት፣ “ለምን ደግሞ በገዛ እንባዬ?” ብላ አንባረቀችበት። ሾፌሩ ‘እውነት ይህቺ ልጅ ከአገሬ ናት ከሞስኮ?’ ሳይል ቀረ? ይኼኔ ጎልማሳው፣ “አይ የሰው ልጅ ለእንጀራው ሲባክን የወዳጅ ዘመዱን ሞት መንገድ ለመንገድ ይረዳ ጀመር?” ሲለኝ ከጀርባችን የተቀመጡት ወጣቶች ሰምተውት፣ “ኧረ እንዲያውም ዕድሜ ለአገራችን ኔትወርክ። አቋራጭ መንገድ እንደ መውደዳችና እንደ መጠቀማችን ብዛት ኔትወርካችን እየተቆራረጠ ባያግዘን ኖሮ፣ ከረሳናቸው የየዋህነትና የመተሳሰብ ቀናት ሕልፈት አንፃር መርዶ ተቀምጠን መቼ የሚሊኒየማችንን ግብ ለማሳካት ደፋ ቀና እንል ነበር?” ተባባሉ። መተሳሰብና መደጋገገፍን የቀበሩ ቀናት የሚያጣድፉት የሚሊኒየሙ ራዕያችን ግን ፍፃሜው እንዴት ይሆን?

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ጫጫታው ቀንሷል። ወያላው መልስ እየመለሰ ደርሶ እንባዋ ኩልል እያለ ለሚያስቸግራት ተረጂ የሶፍት መዋጮ ያመላልሳል። መጨረሻ ወንበር ድምጿ ሳይሰማ የተቀመጠችው ወይዘሮ፣ “ይኼኔ የሰውን ሕይወት፣ የአገርን የድህነት ታሪክ የሚቀይር መዋጮ አስፈልጎ ቢሆን ኖሮ የአሁኑን ያህል ባልሆንን ነበር፤” አለች። “ምን ነካሽ? ሐበሻ የምር ለውጥ ቢወድ ከኋላው ተነስተው ጃፓንና ቻይና ጥለውት ይሄዱ ነበር?” አለ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ። “ምን ይደረግ? ሲበልጡን አንወድ። ከቀደሙን አንማር። ደርሶ ሰው ቁልቁል ስናይ ነው መንፈሳችን የሚረካው። ይኼ ቁልቁል ለመተያየት ስንከፋፋ፣ ስንዳማና ስንነፋፈግ ኖረን ኖረን ይኼው ዛሬ መሬት መሬት እናያለን። መሬት የግል እንደሆነ ሁሉ፤” አለ ኮልታፋው። “እንዲያው በምን ቀን ብንፈጠር ይሆን?” ስትል ወይዘሮዋ አዛውንቷ ቀበል አድርገው፣ “በሰኔና በሰኞ” አሉ። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ሲከፍተው ጎልማሳው “ቀን እንደ መግደል በሰኞ አማካይተን በሰኔ ስንሞት እያየህ ነው? ቀንን ግደል! ቀን አይግደልህ!” ብሎኝ ቀድሞኝ ወረደ። ‘ወይ ሰኔና ሰኞ?’ እያልኩ ተከተልኩት። ለመሆኑ ከሰኔና ከሰኞ ምን አለን? ሰኔና ሰኞ ገጠሙ አልገጠሙ ምን አጨናነቀን? ቋቱ ላይሞላ መከራ! ቢገጥም ባይገጥም እኛን ምን አገባን? መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት