Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጣት በሚቆጠሩ ላኪዎች ላይ የተንጠለጠለው የወጪ ንግድ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በሚፈለገው ደረጃ ለመራመድ ያልቻለ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሆኗል፡፡ የተከታታይ ዓመታት አህዛዊ መረጃዎች በግልጽ እንደሚያሳዩትም የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዘርፍ ከአዙሪት ያለመውጣቱን ነው፡፡

በተለይ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች አገኛለሁ ብላ ያቀደችውና በተግባር በተገኘው መካከል ሰፊ ልዩነት ታይቷል፡፡ ከ50 በላይ ከሚሆኑ የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ አንዳቸውም ያስገኛሉ ተብሎ የተያዘላቸውን የውጭ ምንዛሪ ሊያመጡ አልቻሉም፡፡

ዋና ዋና ከሚባሉት እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ሥጋና የሥጋ ውጤቶች፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ወርቅና የመሳሰሉት የአገሪቱ የውጭ ንግድ ምርቶች እያስገኙ ያሉት የውጭ ምንዛሪ ገቢ በቀደሙት ዓመታት አስገኝተው ከነበረው ያነሠ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዓመታዊው የወጪ ንግድ ገቢ 65 በመቶውን የሚያስገኙት ቡና፣ የቅባት እህሎችና ወርቅ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ምርቶች ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አንፃር የሚፈለገውን ግብ አልመቱም፡፡ የቡና ገቢ በየዓመቱ 31 በመቶ እያደገ ይሄዳል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም፣ በየዓመቱ ከዕቅዱ 25 በመቶ ቅናሽ እየታየበት ነው ተብሏል፡፡ ወርቅም በተመሳሳይ ቅናሽ የታየበት ዘርፍ ሆኗል፡፡

የ2007 የዘጠኝ ወር አፈጻጸም እንደሚያሳየውም የወርቅ ወጪ ንግድ ገቢ በ19 በመቶ ወርዷል፡፡ ዕድገት እየታየበት የነበረው የቅባት እህሎች የወጪ ንግድ ገቢ ሳይቀር ከቀደመው ዓመት ዘጠኝ ወር አኳያ በ20 በመቶ ቀንሷል፡፡ የአበባ ምርትም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተቀመጠው ማሳካት የቻለው 47 በመቶ ብቻ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአገሪቱን የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀው የምሳ ላይ የውይይት ፕሮግራም፣ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አወት ተክኤ ዘርፉ የተጠበቀውን ያህል እንዳልተጓዘ አሳይተዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቴ ደግሞ በየትኛውም አገር የወጪ ንግድ ብዙ ፈተናዎች ያሉበትና አስቸጋሪ ቢሆንም በኢትዮጵያ ከሌላውም የበለጠ ፈታኝና ተግዳሮት የበዛበት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ እንደሚፈለገው ሊሆን አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ ብዙ የሚባልበት ግን ትንሽ የሚገኝበት ይህ ዘርፍ ለምን ውጤቱ አነሰ ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ምክንያቶች ይደረደራሉ፡፡

በጥቂት ላኪዎች ላይ የተንጠለጠለው ዘርፍ

የአገሪቱ የወጪ ንግድ እንደተፈለገው ሊራመድ ካልቻለባቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል አንዱ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ቁጥር አናሳ መሆን ነው፡፡

አቶ አወት በዕለቱ የሰጡት በአኃዝ የተደገፈ ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ ያሏት ላኪዎች ቁጥር 1,825 አካባቢ ነው፡፡ ይህ የላኪዎች ቁጥር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጻጸር እንኳ አነስተኛ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ያነሰ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኬንያ እንኳን ከ4,410 በላይ ላኪዎች እንዳላት ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ላኪዎች ቁጥር በዚህን ያህል ደረጃ አነስተኛ መሆኑ በወጪ ንግድ ዕድገቱ ላይ የራሱ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ የላኪዎች ቁጥር ማነሱ ብቻ ሳይሆን ዓመታዊ የመላክ አቅማቸው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የሚፈልገውን ግብ ለመምታት አላስቻለም፡፡

የተከታታይ ዓመታት መረጃዎችን በመጥቀስ በኢትዮጵያ ላኪዎች ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አወት፣ ከ1,825 ላኪዎች ውስጥም በዓመት ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስገኙ የወጪ ንግድ ምርቶችን የሚልኩት ከጠቅላላ ላኪዎች ውስጥ አምስት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡

ይህም የወጪ ንግዱ በጥቂት ላኪዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ሁለት ሺሕ የማይሞሉ ላኪዎችን ይዞ ብዙ መጠበቅ አዳጋች ነው በማለት በውይይት መድረኩ ላይ አስተያየት የሰጡ ተሳታፊዎች፣ ለላኪዎች ቁጥር ማነስ ምክንያቱ ታውቆ መፍትሔ መበጀት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የአቶ አወት ጥናታዊ ጽሑፍም በየዓመቱ ወደ ወጪ ንግድ ሥራ ከሚገቡ ላኪዎች ይልቅ የሚወጡት እየበለጡ መምጣት ችግር እንዳለ ጠቋሚ ነው ይላል፡፡ መፍትሔው ምን ይሁን የሚለው ላይ ጥርት ያለ ምላሽ ባይሰጥበትም ችግሩን አውቆ መፍትሔ መፈለጉ ግን ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አቶ አወትም ሆኑ አቶ ኤልያስ ይስማማሉ፡፡ የላኪዎችን ቁጥር በማሳደጉ ረገድ የመንግሥት ድርሻ ከፍ ያለ ነው ያሉት አቶ አልያስ፣ እነዚህ ላኪዎች ከገበያ እንዳይወጡ፤ አዳዲሶችም እንዲገቡ መንግሥት ሊደግፋቸው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የሌሎች አገሮች መንግሥታት ላኪዎቻቸውን እንደሚደጉሙ ያስታወሱት አቶ ኤልያስ፣ በኢትዮጵያ ላኪዎች በሥራቸው ላይ እንዲቆዩ የሚያደርግ አሠራር መዳበር አለበት፡፡ ድጋፉ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው የከሰረን ላኪ በፋይናንስ ጭምር በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባውም ጠቅሰዋል፡፡

የወጪ ንግዱና ውስን መደረሻዎቹ

በጥቂት ላኪዎች ትከሻ  ላይ የተጫነው ተንጠልጥለው የወጪ ንግዱ ዘርፍ ሌላው ችግር ለበርካታ ዓመታት ከአገሪቱ ምርት የሚገዙ አገሮች ጥቂት ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአቶ አወት ገለጻ የኢትዮጵያ ምርቶች የሚላክባቸው አገሮች ውስን መሆን በወጪ ንግዱ ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ የበለጠ የወጪ ንግድ ገቢ ለማግኘት ምርቱ የሚላክባቸውን አገሮች ማስፋት የግድ ባይልም በዚህ ረገድ ትልቅ ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም ወደ እስያ ከሚላከው የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው ከቻይና የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡ ወደ አውሮፓ አገሮች ተልኮ ከተገኘው የወጪ ንግድ ምርት ውስጥ ስዊዘርላንድ 38 በመቶውን ስትይዝን ኔዘርላንድ 27 በመቶ፣ ጀርመን 16 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ ከአውሮፓ አገሮች ከሚገኘው ገቢ የወጪ ንግድ ገቢ ከ84 በመቶ በላይ የሚሆነው ከአራት አገሮች የሚገኝ ነው፡፡

ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያለው የወጪ ንግድ አኃዛዊ መረጃም ተመሳሳይ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አወት፣ ኢትዮጵያ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ከላከቻቸው የተለያዩ ምርቶች ከተገኘው ውስጥ 50 በመቶው ከሶማሊያ የተገኘ ነው፡፡

ስዊዘርላንድ ወርቅ፣ ኔዘርላንድ አበባ ከኢትዮጵያ በመግዛት የሚታወቁ በመሆኑ፣ ከአውሮፓ አገሮች ብልጫ ያለውን ድርሻ መያዛቸውም ተመልክቷል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ የወጪ ንግድ የአገሪቱ ላኪዎች የንግድ መዳረሻ አገሮች ለማስፋት ያለመቻላቸውንና ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ያሳየ ነው ተብሏል፡፡  ቻይና ስዊዘርላንድና ሆላንድ የሚቀበሉትን ምርት ሳይታሰብ አንቀበልም ቢሉ ሊፈጠር የሚችለው አደጋ ቀላል አለመሆኑም በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡

እንደ አበባ ያሉ ምርቶች አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እየተመለከቱ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ቢጠቁሙም፣ ዋና ዋና የሚባሉት የወጪ ንግድ ምርቶች መዳረሻ ግን በጣት በሚቆጠሩ አገሮች ላይ መመሥረቱ ዘላቂ ጥቅምን ይጐዳል ተብሏል፡፡

ቡናና እየወረደ የመጣው ገቢ

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ታሪክ ቡና አሁንም ድረስ ቀዳሚ ነው፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ተደርጐ የሚወሰደው ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ምርት መጠን ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ጥቅም እየተገኘበት ግን አይደለም፡፡

በየዓመቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና መጠንም ዕድገት የማይታይበት ብቻ ሳይሆን በተከታታይ ዓመታት ገቢው እየቀነሰ የመጣ ነው፡፡ አቶ አወት እንደገለጹት፣ ለውጭ ገበያ ይቀርባል የተባለው ቡና በአራት በመቶ ቀንሷል፡፡ ገቢውም በዚያው ልክ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. ባሉት ተከታታይ ዓመታት ከቡና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 833 ሚሊዮን ዶላር፣ 747 ሚሊዮን ዶላርና 714 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

የቡና ምርት እየጨመረ ባለበት ወቅት ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት መጠን እያሽቆለቆለ መምጣት ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ያነሰ ቡና ለውጭ ገበያ ያቀርቡ የነበሩ አገሮች ከኢትዮጵያ ቀድመው ሄደዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመረችው ቬትናም ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ቡና በእጅጉ አሳድጋለች፡፡ ቡናን ጨምሮ ከሌሎች የወጪ ንግዷ እያገኘች ያለው ገቢ ከ120 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ እንደምሳሌ ቀርቧል፡፡

ፈቀቅ ያላለው ጥራት

በየትኛውም አገር የወጪ ንግድ ተፈታኝ ሥራ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ደግሞ በበለጠ ተግዳሮት የሚበዛበትና አስቸጋሪ የሚሆንበት በርካታ ምክንያቶች አሉ ተብሏል፡፡

እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ፣ ለአገሪቱ የወጪ ንግድ ያለማደግ አንዱ ምክንያት የሚላኩት ምርቶች በግብርና ምርት ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ መሆናቸው ነው፡፡ ችግሩ ግን ይህ ብቻ አይደለም ያሉት አቶ ኤልያስ ‹‹እስካሁን ወደ ውጭ የሚላኩት የአገሪቱ የግብርና ምርቶች ያደጉ አገሮች የሚጠይቁትን የጥራት ደረጃ የሚያሟሉ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ምርቶች እየተሸጡ ያሉት በተፈጥሮ ይዘታቸው ተመራጭ በመሆናቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቡና ጣፋጭና ተፈለጊ በመሆኑ፣ ሰሊጥም ከአገሪቱ ኢኮሎጂ አንፃር ጥሩ ጣዕም ያለው ምርት በመሆኑ እንጂ የውጭ ምንዛሪ እየተገኘባቸው ያለው በጥራት ደረጃቸው ተመዝኖ አይደለም በማለት የጥራት ችግር ሌላው የወጪ ንግድ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለውን ቡና ገዝተው እሴት ጨምረው የበለጠ ዋጋ እንዲያወጣ አድርገው የሚልኩት ሌሎች አገሮች ናቸው፡፡ እሴት ጨምሮ በመላክ ሊያስገኝ የሚችለው ጥቅም ከፍተኛ ቢሆንም፣ ምንም እሴት የማይጨምርባቸው ምርቶችን መላክ ላይ ማዘንበሉ ዘርፉን እንደጎዳ አመላክተዋል፡፡

አቶ አወትም የአቶ ኤልያስን ሐሳብ የሚያጠናክር ምሳሌ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና ሁለት ሦስተኛው ያልታጠበ ነው፡፡ ይሁንና እሴቱን ጨምረውበት መልሰው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አገሮች ግን ከ200 በመቶ በላይ ገቢ እያገኙበት ነው በማለት ጥራትና እሴት ጨምሮ ያለመላክ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ጠቅሰዋል፡፡ በቀላሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እሴት ጨምሮ የመላክ ልምዱ እንዲዳብር የላኪዎችና የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ መሆን እንዳለበትም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የወጪ ንግዱ የወጪ ንረት

የወጪ ንግድ ያሉበት ችግሮች በርካታ ቢሆኑም አቶ አወት ግንባር ቀደም ብለው ካስቀመጧቸው ዋና ዋና ችግሮች ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለመላክ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ ሆኖ መገኘት ነው፡፡

ላኪዎች ምርቶቻቸውን ለመላክ የሚያወጡት ወጪ ተወዳዳሪ አላደረጋቸውም፡፡ አንድ ላኪ ምርቱን ለመላክ 44 ቀኖች ይፈጁበታል፡፡ ይህ ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያ 26 ቀን፣ ሩዋንዳ 26፣ ኡጋንዳ 28 ቀን ይፈጅባቸዋል፡፡

በተለይ ሩዋንዳ ወደብ አልባ አገር እንደመሆኗ ወደብ ያለመኖር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ሩዋንዳ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ምርት ለመላክ ከአራት ዓመት በፊት 44 ቀን ይፈጅባት ነበር፡፡  አሁን ግን ወደ 26 ቀን አውርደዋለች፡፡ ይህንን ያደረጉት የጉምሩክና ተያያዥ ሥራዎችን 24 ሰዓት በመሥራት የተንዛዙ፣ አሠራሮችንና ሰነዶችን በመቀነስ የአንድ መስኮት አገልግሎት በመስጠት አሠራሩን ቀልጣፋ አድርገዋል፡፡ ይህንን በማድረጋቸውም አንድ ላኪ ይፈጅበት የነበረውን ጊዜ ቀንሰዋል፡፡ በኢትዮጵያም ይህንን ማድረግ ይገባል ይላሉ አቶ አወት፡፡ ወጪው በጨመረ ቁጥር ተወዳዳሪነትን የሚገድብ በመሆኑ የተንዛዛ አሠራሮችን መቅረፍ ግድ ይላል ብለው፣ አንድ ላኪ አሁን ባለው አሠራር ጉዳዩን ለማስፈጸም የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን መጎብኘትና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን ማሟላቱ የላኪዎችን ወጪ እያናረ ተወዳዳሪነታቸውን እየቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዓለም ባንክ 800 ላኪዎችን በማናገር ያሰፈረው መረጃም ይህንኑ የሚያሳይ ነው ያሉት አቶ አወት፣ አሠራሮችን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ ያሻል በማለት መክረዋል፡፡ በወጪ ንግድ ዘርፍ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ያሏቸውን ነጥቦችም አስቀምጠዋል፡፡  

አቶ ኤልያስ በበኩላቸው ላኪዎች አሉባቸው የተባለውን ችግር ለመቅረፍ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተለይተው ሊቀርቡ ይገባል ብለዋል፡፡ አቶ አወት ከሌሎች ችግሮች በተለየ ባስቀመጡት የላኪዎች ወጪ መብዛትና የተንዛዛ የጉምሩክ አሠራር ላይ አስተያየት የሰጡት የንግድ ምክር ቤቱ የግልግል ደዳኝነት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል ናቸው፡፡ አቶ ዮሐንስ ቀልጣፋ አሠራር እንዲኖር ለማድረግ መጀመሪያ የተረጋጋ ሥርዓት እንዲኖር ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ በተለይ አዳዲስ ሠራተኞችን በማስገባት ብቻ መረጋጋት ሊመጣ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ሕግጋቶችንና ፖሊሲዎችን ማውጣትም መፍትሔ አያመጣም ይላሉ፡፡

‹‹የተረጋጋ አካሄድ ከሌለና ሁልጊዜ አዳዲስ አሠራር የሚፈጠር ከሆነ የተቀላጠፈ አሠራር ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህንን መሥራት አለበት፡፡ አዲስ አሠራሮች፣ ፖሊሲዎች፣ ምኞቶች እየተፈጠሩ የሚሄዱ ከሆነ፣ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ ቢያንስ ያለውን ሕግ ሥርዓት አስይዞ በማስኬድና በማስፈጸም የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች