- እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ይቅርታ ተደረገላቸው
በወልቃይት ምክንያት በተፈጠረ ውዝግብና ግጭት የሽብር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በሒደት ላይ የነበሩት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱና ንግሥት ይርጋ ክሳቸው ተቋረጠ፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ፣ ኮሎኔል ደምሰው አንተነህና ሌሎች ፍርደኞች በይቅርታ እንዲፈቱ፣ የፌዴራል ይቅርታ ቦርድ ወስኖ ለአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ተላለፈ፡፡
ኮሎኔል ደመቀ በጎንደር ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ በፀጥታ ኃይሎች ሲከበቡ፣ የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ የሰው ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡ እሳቸውም ለፀጥታ ኃይሎች እጃቸውን መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡ ፈጽመውታል የተባለውን የሽብር ወንጀል የማየት ሥልጣን ያለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢሆንም፣ ከሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ በመሰማቱ የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት ተነጋግረው፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በውክልና እንዲያይ የሚያስችል ሥልጣን ስላለው ሲመረምር ከርሟል፡፡
ዓርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ኮሌኔሉ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ለየካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት በገባው ቃል መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የኮሎኔል ደመቀንና ከእሳቸው ጋር የተከሰሱ ሌሎች ግለሰቦችን ክስ እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡
በተመሳሳይ ክስ የጎንደር ወጣቶችን በማነሳሳት የግንቦት ሰባትን ዓላማ ለማስፈጸም ስትንቀሳቀስ ነበር ተብላ፣ ጉዳይዋ ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤት ተልኮ ክሷን እየተከታተለች የነበረችው ንግሥት ይርጋም ክስ ተቋርጧል፡፡ ንግሥት የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ፣ የመከላከያ ምስክሮቿን አብሯት ከተከሰሰው ቴዎድሮስ ተላይ ጋር ከመጋቢት 11 እስከ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ለማሰማት ቀጠሮ እንደተሰጣት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል በሽብር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በ2002 ዓ.ም. የዕድሜ ልክ እስራት ተርዶባቸው በእስር ላይ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ፣ ኮሎኔል ደምሰው አንተነህና ሌሎችም ፍርደኞች በይቅርታ ቦርድ ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲፈቱ ለአገሪቱ ርዕሰ ብሔር መተላለፉ ታውቋል፡፡
ዓርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ክሳቸው የተቋረጠላቸውና ይቅርታ የተደረገላቸው 101 ሰዎች ከእስር እንዲፈቱ መንግሥት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የግንቦት ሰባት 56፣ የኦነግ ደግሞ 41 አባላት መሆናቸው ታውቋል፡፡