የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዓርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካወጀ በኋላ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት የሚወስዳቸው አሥራ ስምንት ዕርምጃዎች ይፋ ተደርገዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ቅዳሜ የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ለስድስት ወራት ለሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በአሥራ ስምንት ጉዳዮች ላይ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ በአስቸኳይ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ከተከለከሉ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሠራጨት፣ እነዚህን መልዕክቶች የያዙ መልዕክቶችን ማስተላለፍ፣ በቡድን መደራጀትና በአደባባይ ሠልፍ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል የሰዓት ዕላፊ፣ በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ፣ ማንኛውንም ሰው መፈተሽ፣ ሰዎችን ከተወሰነ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ፣ የጦር መሣሪያና ሌሎች ስለታማ ነገሮችን ግለሰቦች ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ፣ በብሔር ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ማቋቋም፣ መሠረታዊ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን መቆጣጠር፣ መደበኛ ሥራን የሚያስተጓጉሉ እንከኖች እንዳይከሰቱና ሌሎች ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተገልጿል፡፡
በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ሊታወጅ የቻለበትን ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹም በመደበኛው የሕግ አግባብ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ሰላም ማረጋገጥ፣ በየአካባቢው የሚጠፋውን የሰው ሕይወት፣ የሚወድመውን የግልና የመንግሥት ንብረት ማስቆም ስላልተቻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ሁከቶችና ብጥብጦች እየተከሰቱ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጉዳት መድረሱን፣ ዜጎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ መደረጋቸውን፣ የመንግሥትና የሕዝብ ተሽከርካሪዎች በኃይል እንዲቆሙ እየተደረጉ መውደማቸውን፣ የኢንቨስትመንት ተቋማት ከጥቅም ውጪ እየተደረጉና አመድ እየሆኑ ሠራተኞቻቸው እየተበተኑ መሆኑን ሚኒስትሩ በመግለጫው ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ዜጎችም በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ከመታገዱም በላይ፣ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ የተቸገሩበት ጊዜ ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባ የበርካታ ዲፕሎማቶች መናኸሪያ እንደሆነች የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በዚህም ሳቢያ የአገር ገጽታ ክፉኛ እየተጎዳ ነው ብለዋል፡፡
በመደበኛው ሕግ ማስከበር እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ሲደረግ እንደነበር ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ይህን ማድረግ ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ መገደዱን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ አምስት ክፍሎችና አሥራ ስምንት ክልከላዎችን የያዘ እንደሆነ ገልጸው፣ ዝርዝር መመርያው ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው በመላ አገሪቱ እንደሆነና በሚቀጥሉት አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ብለዋል፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአሥራ ሰባት ቀናት አድርጎት በነበረው ስብሰባ፣ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ካልተመለሰ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃል የሚል ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተመራ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአገር መከላከያ ሚኒስትር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የደኅንነት ኃላፊዎች፣ የክልሎች የፀጥታ ምክር ቤቶች አባላትና ሌሎችንም ያካተተ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ለሚሠሩ ስህተቶችና የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ የሚከታተል የአስቸኳይ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቡድን እንደሚቋቋም ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ መርማሪ ቡድኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቋቋም ገልጸዋል፡፡
የምርመራና የክስ ሒደቶችን የሚከታተሉ በፌዴራል ፖሊስና በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚደራጁ ክፍሎች እንደሚኖሩ፣ በፌዴራል ደረጃ ይህን ሥራ የሚሠሩ ችሎቶች እንደሚደራጁ አስረድተዋል፡፡
የአገሪቱ መከላከያ ኃይል አገሪቱን ሊቆጣጠር ይችላል ስለሚባል በዚህ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ምንድነው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሲራጅ በሰጡት ምላሽ፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ ምንም ዓይነት ዕቅድ የለም ብለዋል፡፡
አገሪቱ ያለችበት ወቅት አስቸጋሪ በመሆኑ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት የሚሉ ወገኖች ስላሉ በዚህ ላይ ምን የታሰበ ነገር አለ የሚል ጥያቄም ተነስቶላቸው በሰጡት ምላሽ፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ስለሆነ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም እሳቤ የለውም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡