Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የስንብት ጥያቄ

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የስንብት ጥያቄ

ቀን:

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን የመሰናበት ጥያቄና የዜጎች ምላሽ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና ከመንግሥት ኃላፊነት በራሳቸው ፈቃድ ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ማስታወቃቸው፣ የሰሞኑ አንዱ የአገሪቱ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን የመሰናበት ጥያቄ አገሪቱ በገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በመሆኑ፣ በሕዝቡ ውስጥ የተደበላለቁ ስሜቶች ተንፀባርቀዋል፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያህል በኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሠሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ለሦስት ዓመታት ያህል መቆም ባልቻለው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በደረሰ ጉዳት በርካቶች በመሞታቸው፣ በመጎዳታቸውና ከቀዬአቸው በመፈናቀላቸው ሳቢያ ሥልጣን ለማስረከብ መገደዳቸው ታውቋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነትና ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ የገባችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነና ለዚህ ችግር የመፍትሔው አካል ለመሆን ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ላስቀመጥናቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ በገዛ ፍላጎቴና ፈቃዴ ከኢሕአዴግም ሆነ ከመንግሥት ኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርቤያለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ያቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄም በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተቀባይነት ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

በአገሪቱ ወጣቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ተገቢ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ መሠረት የመልቀቂያቸው የመጨረሻ ውሳኔ በሚመለከታቸው አካላት ይሰጣል ብለው እንደሚያምኑና መልቀቂያቸውም ተቀባይነት ይኖረዋል ብለው  ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ በሚቀጥለው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚተካቸውን ሊቀመንበር ይመርጣል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረግ በአገሪቱ ታሪክ የሚሠራበት፣ በዚህ መሠረትም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበትና እሳቸውም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብለው የሚጠሩበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተከሰተው አለመረጋጋትና የፖለቲካ ችግር ምክንያት የበርካታ ሰው ሕይወት መጥፋቱንና ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን፣ እንዲሁም የንብረቶችና የኢንቨስትመንቶች ውድመት መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍም በኢሕአዴግና በመንግሥት የተለያዩ ማሻሻዎች መጀመራቸውን፣ ማሻሻያዎችን ለማሳካትም ጥረት የሚያደርግበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን ለመልቀቅ ከተናገሩ በኋላ በአብዛኛው የተደበላለቁ አስተያየቶች ሲሰጡ ተደምጧል፡፡ አስተያየቶቹ በዋናነት በሁለት የተከፈሉ እንደሆነም ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

የመጀመርያው ቡድን በኢትዮጵያ ብዙም ያልተለመደና በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን መልቀቃቸው ሊያስመሰግናቸውና አገሪቱን ካለችበት አጣብቂኝ የሚያወጣ እንደሆነ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢሕአዴግ ሥርዓት ካልተቀየረ በስተቀር የአንድ ግለሰብ ከሥልጣን መውረድ፣ በአገሪቱ የሚያመጣው ለውጥ የለም ብለው የሚከራከሩ ናቸው፡፡

በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመጡት አቶ ኃይለ ማርያም የ53 ዓመት ጎልማሳ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት እንዳገለገሉና ከዚያ በኋላም ለትምህርት ወደ ፊንላንድና አሜሪካ ሄደው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንደሠሩ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊትም ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ቀደም ሲል የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላም አገሪቱ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለውጥ እንድታመጣ ጥረት እንዳደረጉ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ በተለይም በአገሪቱ ውስጥ ተጀምሮ የነበረው የባቡር መስመርና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንዲከናወን፣ የህዳሴ ግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅሙ ከፍ እንዲል፣ አገሪቱ በመንገድ ግንባታ እመርታ እንድታሳይ፣ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ እንድታስመዘግብና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወኑ ይነገራል፡፡

አገሪቱ በተለይም ከጎረቤትና ከሌሎች አገሮች ጋር የነበራት ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ያለሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልም ‹‹አስመራ ድረስ ሄጄ እደራደራለሁ፤›› ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተም አዲስ ፖሊሲ መከተል አለበት ብለው ያምኑ እንደነበርና ይህን ሐሳባቸውን ዕውን ሳያደርጉት ከሥልጣን ለመነሳት መወሰናቸውን ይገልጻሉ፡፡  ኢትዮጵያና ግብፅ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ካይሮ ድረስ ሄደው ሲነጋገሩ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህንና ሌሎች መልካም ሥራዎችን እንደሠሩ ቢታወቅም፣ በእሳቸው ዘመን በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ቀውስ እንደ ተከሰተና በዚህ ቀውስ ሳቢያም ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ለማቅረብ መገደዳቸውን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን አገሪቱ ቀውስ ውስጥ እንደገባች፣ እንዲያውም ከሥልጣን ለመነሳት ጥያቄ ማቅረብ የነበረባቸው ከዚህ በፊት እንደነበር የሚከራከሩም አሉ፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዳደ ደስታ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አቶ ዳደ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ብዙ ችግሮች ሲከሰቱ እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹የእሳቸው ጥፋት ይሁን አይሁን ባይታወቅም ባጋጠመ የሰላም መታጣት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ መደነቃቀፍ ፈጥሮ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ ቀውስ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ መንግሥት የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ውሳኔዎችን ቢያስተላልፍም፣ አሁንም ድረስ ቀውሱን ማስቆም እንዳልተቻለ ያስረዳሉ፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አሁንም በተለያዩ መጠለያ ካምፖች እንደሚገኝ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ተገልጿል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት ቢደረግም፣ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዳልተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በመጠለያ ካምፕ ያሉ ዜጎች በምግብና በውኃ እጥረት ከመቸገራቸውም በላይ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አላቆሙም፡፡

በአማራ ክልል በጎንደር፣ በወሎ፣ በጎጃምና በሸዋ በተለያዩ ጊዜያት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተከስተው የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ተቃውሞና ቀውሱ በእነዚህ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ቆሟል ማለት እንደማይቻል ተንታኞቹ ያስረዳሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ በወልዲያና አካባቢው በተከሰተው ግጭት ብቻ የአሥራ አምስት ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአራቱም አቅጣጫ በሚባል ደረጃ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና ግጭቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ በክልሉ ወጣቶች በተጠራው ተቃውሞ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረታቸው ወድሟል፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ በወጣቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ሲወስድ ቢታይም ተቃውሞውንና ቀውሱን ማስቆም አልቻለም፡፡

በተመሳሳይ በደቡብ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በጌዲዮ ዞን፣ የሰገን ሕዝቦች የኮንሶ ልዩ ወረዳና ባለፈው ሳምንት ደግሞ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ግጭቶች ተከስተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያም የዜጎች ሕይወት ሲጠፋ ንብረት ወድሟል፡፡

ሥር የሰደደውን የአገሪቱን ችግር ለመፍታት መንግሥት ከላይ ታች ሲል እያልኩ ነው ቢልም፣ ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሮችን በዘላቂነትና በአስተማማኝ ሁኔታ መፍታት አልቻለም፡፡

በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባልም መንግሥት የታሰሩ ዜጎችን ከእስር እንደሚፈታ በመግለጽ እስካሁን ድረስ በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከእስር ለቋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አሁንም በአገሪቱ ሰላም ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ይህ ችግር እየተከሰተ ባለበት ወቅት ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከሥልጣን ለመውረድ ጥያቄ ያቀረቡት፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብ በተመለከተ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቃል አቀባዩ እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ምኅዳር ያሰፋል፡፡

የእሳቸው ከሥልጣን መልቀቅ በአገሪቱ መረጋጋትን በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱን የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገርና አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ምኀዳር ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ቃል አቀባዩ አክለው ገልጸዋል፡፡   

አቶ ዳደ፣ ‹‹አንድ ዓይነት ጥፋት፣ አንድ ዓይነት ነገር እንዲቀጥል አንፈልግም፡፡ ስለዚህ በመቆየታቸው ችግሮችን የመፍታት ልምድ አልታየም፡፡ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ካልሆነ በስተቀር የእሳቸው መነሳት ተገቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ በበኩላቸው፣ የእሳቸው በግል ከሥልጣን መልቀቅ ብዙም የሚያስደስት ጉዳይ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህችን አገር ከቀውስ ለመታደግ የሥርዓት እንጂ የግለሰብ ለውጥ እንደማይጠቅም ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ እንደ ኦፌኮ ከግለሰብ ጋር ምንም ችግር የለብንም፡፡ በእርግጥ የግለሰብን ሚና ዝቅ አድርገን ለማየት አይደለም፡፡ ነገር ግን ችግራችን ከግለሰብ ሳይሆን ከሥርዓቱ ነው፡፡ የእሳቸው መልቀቅ ጉልቻ ከመለዋወጥ በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ዳደ የእሳቸው የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ እንዲያውም የዘገየ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሐሳብ አቶ ጥሩነህ ይስማማሉ፡፡ አቶ ጥሩነህ፣ ‹‹የእሳቸው ከሥልጣን መልቀቅ የዘገየ እንጂ ቶሎ የመጣ ወይም ደግሞ በአስፈላጊ ጊዜ መጣ ነው የሚባል አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

ታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን ለመልቀቅ ያቀረቡት ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነ ገልጸው፣ በዚህ ወቅት በራሳቸው ፈቃድ ለመልቀቅ ለአገሪቱ እንደ ጥሩ ጅምር ሊወሰድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አልጋቸው ላይ አይደለም የሚሞቱት፡፡ በእስር ወይም በመንግሥት ይገደላሉ፡፡ የአገሪቱ የቆየ ታሪክ ይህ ሆኖ ሳለ አሁን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ለመልቀቅ አበቃኝ ብለው በምክንያትነት የጠቀሱት ጉዳይ ውኃ የሚቋጥር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የእሳቸው ከሥልጣን መልቀቅ ግን በአገሪቱ ያለውን ቀውስ ይፈታል ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለው ሥርዓት በሥልጣን እስከቀጠለ ድረስ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዳደ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ የዘገየ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን የእሳቸው ከሥልጣን መውረድ በአገሪቱ መረጋጋት ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥራ ለመልቀቅ ጥያቄ በተመለከተ፣ ከአንድ ኃላፊነት የሚሰማው አመራር የሚጠበቅ ነው ማለታቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡ አገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረችበትን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት አገርን እየመራ ያለው ኢሕአዴግ ጥልቅ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ ሕዝብ እንዳይፈናቀልና ንብረት እንዳይወድም ጥረቶች ሲደረጉ እንደቆዩ አስረድተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ችግሮች አሁንም እንዳሉ ጠቁመው፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሲወስኑ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመሆን ያደረጉት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሚቀጥለው ካቢኔ ጉዳይም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚወሰን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያ አስገቡ ማለት ሥራ ቆመ ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፣ አጋጣሚው በአገሪቱ ታሪክ የመጀመርያ በመሆኑ ሰዎች ግር ሊላቸው እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያ ማስገባታቸውን በተመለከተ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ አቶ ሽፈራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሪ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ላለፉት 17 ዓመታትም የደኢሕዴን ሊቀመንበር ሆነው ማገልገላቸውን አስታውሰዋል፡፡

‹‹የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሕልፈትን ትከትሎ ጥበብ በተሞላበት አመራር ሕዝብን በማስተባበር የተጀመረው አገሪቱ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመመከትና ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተሞከሩ ጥረቶችን ታሳቢ በማድረግ አገሪቱን ለመምራት ሌላ ሰው መምጣት አለበት ብለው ስላሰቡ፣ ባሳለፍነው ረቡዕ ለደኢሕዴን የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በድርጅቱ ውስጥ ያላቸውን አስተዋጽኦ እስከ ሕይወት ፍፃሜ ድረስ ማበርከት እንደሚቀጥሉ በማረጋገጥ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ የደኢሕዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዝርዝር ከተወያየና ከመዘነ በኋላ ጥያቄውን ተቀብሎታል፤›› ብለዋል፡፡    

አቶ ጥሩነህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ የፈለጉበት ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንደሆነ አስታውሰው፣ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መሪዎች ራሳቸውን አሸንፈው እንደማያውቁና ራሳቸውን በማሸነፍ ረገድ በግላቸው ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዙ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አገሪቱ ያጋጠማትን ቀውስ ማስተካከልና መፍታት የሚቻለው በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያለውን የአገሪቱን ሕዝብ ያሳተፈ የፖለቲካ ሥርዓት መመሥረት ሲቻል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አሁን ያለውን መንግሥት (ፓርላማውን ጭምር በማፍረስ) አዲስ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት በማሻሻልና የሚመለከተውን አካል በማሳተፍ አገርን መታደግ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ዳደ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ መሪ መጥፎ ነበሩ ማለት አልችልም፡፡ ግን ራዕያቸው፣ ትልቅነታቸው፣ በሳልነታቸውና ጥበበኝነታቸውን ያሳዩበትን ጊዜ አናስታውስም፡፡ በዚህ ምዕራፍ መጠቃለሉ ለአገሪቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ቢያንስ የነበረው ነገር አለመቀጠሉ አንድ ምልክት ነው፤›› ይላሉ፡፡ በአገሪቱ የአመራር ቀውስ መከሰቱን ጠቁመው፣ አመራሮች ጣታቸውን ወደ ራሳቸው መቀሰር የሚገባቸው አሁን ሳይሆን ከዚህ በፊት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ 

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢኣድ) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልቀቂያ በተመለከተ ለመናገር አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ የእሳቸው መልቀቅም ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ፣ ‹‹መጀመርያም ሰውየው ሥልጣን ስላልነበራቸው ቢለቁ ለውጥ አይመጣም፡፡ ሥልጣኑን ሳይለቁ ብሔራዊ ዕርቅ ለማምጣት መታገል ይችሉ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታሪክ ተጠያቂነት የማይድኑ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የእሳቸው ከሥልጣን መልቀቅም የመፍትሔው አካል እንደማይሆንና የእሳቸው የመፍትሔው አካል እሆናለሁ ማለት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም እንደ መሪ የመፍትሔ አካል በመሆን ብሔራዊ ዕርቅ እንዲፈጠርና የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ተፅዕኖ መፍጠር ይችሉ ነበር ብለዋል፡፡ በመልቀቃቸው የመፍትሔ አካል ይሆናሉ ብለው ካመኑ ቢያንስ ካቢኔያቸውን መበተን ይገባቸው እንደነበር አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፣ ‹‹ይህን ጉዳይ የምመለከተው ካለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚች አገር ባለፉት ሁለት ዓመታት ቀውስ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፣ የዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ ምክንያቱ ኢሕአዴግ አገሪቱን ብቻዬን እመራለሁ ማለት፣ የሕዝቡ ዴሞክራሲዊ መብት አለመከበር፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አለመካሄድ፣ የሕግ የበላይነት አለመረጋገጥ፣ የሙስና መንሠራፋትና ሌሎች ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የሥርዓት ለውጥ እንዲደረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያ ሕዝቡ ከሚጠይቀው ጥያቄና ከሚጠብቀው ምላሽ የተለየ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህ መጥፎም ሆነ ጥሩ ክስተት ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የሆነ ሆኖ ግን አቶ ኃይለ ማርያም ተነስተው ሌላ ቢተካ ምንም ዓነት የፖለቲካ ለውጥ አይኖርም፡፡ እንዲያውም ወደ ባሰ ችግር የሚወስደን እንደሆነ ነው የሚታየኝ፤›› ሲሉ አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞ አመራር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፣ የአገሪቱ ችግር የተፈጠረው ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ሳይሆን ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ የተጠራቀሙ ችግሮች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ አቶ ኃይለ ማርያምም ሆነ አዲስ አመራር የሚባለው ችግሩን በመፍጠር ረገድ ዋናው ተጠያቂ አይመስለኝም፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ሥልጣን ከያዙ በኋላ ያለው ለውጥ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ኢሕአዴግ ውስጣዊ አንድነቱ እየተዳከመ በመምጣቱ፣ የሕዝብ ተቃውሞንና እንደዚህ ዓይነት ግጭትን የመቆጣጠር አቅሙ በመቀነሱ ወይም የአፈና አቅሙን አጣ እንጂ ችግሩ የመጣው አሁን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ስለዚህ የእሳቸው ከሥልጣን መልቀቅ ጉዳዩ ኢሕአዴግ ወደ አንድ የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግባት እንደ ብሶት መንገሪያ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚያ በተረፈ ግን ችግሩን በመፍታት ረገድ ሚናው ብዙ ነው ብዬ አላምንም፤›› ብለዋል፡፡ እስካሁን ባሉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን ይውረዱ የሚል ጥያቄ ሰምተው እንደማያውቁ ጠቁመው፣ የእሳቸው መልቀቅ ምሳሌያዊ የሆነ ሚና ሊኖራቸው ይችላል እንጂ ችግሩን ይፈታል ብለው እንደማያምኑ ጠቁመዋል፡፡  

በግል ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈቃዳቸው ከሥልጣን ለመልቀቅ መጠየቃቸው ለአገሪቱ አዲስ ነገር ነው ብለዋል፡፡ ለወደፊትም አስተማሪ ይሆናል ብለው እንደሚምኑ ገልጸዋል፡፡ ይህ የሆነው በሕዝብ ግፊት እንደሆነ ጠቁመው፣ ዋናው ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚችለው ነገር ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ማን ነው የሚሰየመው? በምን መሥፈርት? የሚለው ሊያሳስብ ይችላል እንጂ የአቶ ኃይለ ማርያም በዚህ ዓይነት ሥልጣን መልቀቅ ቀጣይ ትምህርት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዳዊት ይህ የሚያመለክተው የኢሕአዴግ ሞኖፖሊ እየፈረሰ እንደሆነ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹አሁን ካለው ሒደት በብርቱ መታሰብ ያለበት ከአመፅ ውጪ የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት በነፃነት በማራመድ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለውጥ እንዲመጣ በተደረገው እንቅስቃሴ በተለይ የኦሮሚያ ሕዝብና ወጣት ያስተማረው ነገር አለ፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከሰሞኑ ከእስር ከተፈቱ የፖለቲካ ሰዎች የሰማነውም ነገርም ቢሆን በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ብቻ የተለያዩ ፓርቲዎች እንደሚኖሩ ያሳየ ሲሆን፣ ይህ ለመድብለ ፓርቲ መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፤›› ብለዋል፡፡  

የአፍሪካ ፍልስፍና መምህሩ ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (/)፣ ‹‹አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ወይም የትኛውም መንግሥት ጤዛ ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ ፀሐይ ነው፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነ የትኛውም የመንግሥት ሥርዓት ይመጣል፣ ይሄዳል፡፡ ሕዝብ ግን ይኖራል፡፡ ለዚህ ነው ከፀሐይ ጋራ የተፎካከረ ጤዛ የለም የምንለው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ወይም የአገር መሪ በተለያየ ምክንያት ሥልጣኑን ሊለቅ ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ውስጥ የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሳለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ሥልጣናቸውን መልቀቅ ፈለጉ? ብሎ መጠየቅ ራስን ማሞኘት ነው፡፡ ጊዜ ያመጣውን ሐሳብ ማንኛውም የምድር ኃይል ማስቆም ፈጽሞ ስለማይቻለው፡፡ አገራችን ከገባችበት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመታደግ የግድ ይህ መሆን ነበረበት፡፡ ሆኗልም፡፡ አሁን የሚፈለገው የራስን ጥቅም ሳይሆን የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም መሪ ወደ ሥልጣን ማምጣት ነው፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ የምትፈልገው ሀቀኛና ብልህ የሆነ የአገር መሪ እንጂ ‹‹ጫላ›ወይም ‹‹ሐጎስ›› ወይም ‹‹ሱገቦ›› ወይም ‹‹ደምመላሽ›እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡ በተጨባጭ እየፈለገ ያለው የቀበሌ አስተሳሰብ ያላቸውን የአገር መሪዎችን ሳይሆን፣ የብሔር እኩልነትን (የቡድን መብት) እና የአገር አንድነትን (የግለሰብ መብት) ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሰከነ መንፈስ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መምራት የሚችል ጀግናና ቆራጥ መሪ ነው፡፡ አለቀ!››  ብለዋል፡፡

ከሁሉ በላይ ወደ ሥልጣን የሚመጣ ሰው በሕዝብ ስም የሚነግዱት ላይ ዕርምጃ የሚወስድ መሆን እንዳለበት ጠቁመው አገሪቱ የሌቦች፣ የሙሰኞችና የነፍሰ ገዳዮች ዋሻ እየሆነች መምጣቷን አስታውሰዋል፡፡

አገሪቱ ከሕዝቡ ጋር በመሆን እነዚህን ወንጀለኞች ወደ ፍርድ የሚያመጣቸው ሀቀኛ እንደምትሻ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ እያንዳንዱ ሰው እንደ ዜጋ ድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ አልበርት አንስታይን ሰላም በኃይል ሊጠበቅ አይችልም፡፡ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በመግባባት ብቻ ነው እንዳለን ሁሉ፣ ትልቁ ‹‹ሃይማኖት›መቻቻል መሆኑን አውቀን የአገራችንን ሰላም ማስጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ፈጣሪ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማንኛውም ክፉ ነገር እንዲጠብቅ አጥብቄ እመኛለሁ!›› ሲሉ ዶ/ር ዮሴፍ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...