በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የምዕራብ አርሲ ዞን ማረሚያ ቤት ዓርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ፣ የአንድ ታራሚ ሕይወት ሲያልፍ በሦስት ታራሚዎች ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡
የማረሚያ ቤቱ በርካታ ማደሪያ ክፍሎች በእሳት መውደማቸው ተመልክቷል፡፡ የሻሸመኔ ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ናዶ አምቦ የቃጠሎውን መንስዔ በተመለከተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ታራሚዎች መንግሥት ስለሌለ ከማረሚያ ቤት ማምለጥ እንችላለን በማለት ያስነሱት ቃጠሎ ነው፡፡
‹‹ሆን ተብሎ በተነሳው ቃጠሎ የአንድ ታራሚ ሕይወት ሲያልፍ፣ በሦስት ታራሚዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል፤›› ያሉት አቶ ናዶ፣ ‹‹የማረሚያ ቤቱ በርካታ ክፍሎች በእሳት ጋይተዋል፤›› ብለዋል፡፡
ኃላፊው ጨምረው እንደገለጹት፣ ታራሚዎቹን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ሳያስፈልግ እዚያው ባሉበት እንዲሸጋሸጉ እየተመቻቸ ነው፡፡
የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳደር መቀመጫና የአካባቢው የንግድ ማዕከል የሆነችው ሻሸመኔ ከተማ፣ ባለፈው ሳምንት ከተቀሰቀሰው አመፅ ወጥታ መረጋጋት ላይ እያለች፣ የማረሚያ ቤቱ ቃጠሎ ዓርብ ማለዳ ላይ መከሰቱ ነዋሪዎችን አስደንግጦ ነበር፡፡
አቶ ናዶ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓርብ በሻሸመኔ ሁሉም የንግድ ቤቶች ተከፍተው ሥራ በመጀመራቸው የቀድሞው ሰላማዊው እንቅስቃሴ ቀጥሏል፡፡