- የ36 ቦታዎች ጨረታ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ተሰረዘ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየወሩ መሬት በሊዝ ለማስተላለፍ ጨረታ እንደሚያወጣ የደነገገ ቢሆንም፣ ላለፉት ስድስት ወራት አንድም የመሬት ሊዝ ጨረታ አልወጣም፡፡
በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ለመጨረሻ ጊዜ የመሬት ሊዝ ጨረታ ያወጣው፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡
በ28ኛ ዙር ሊዝ ጨረታ 236 ቦታዎች ለጨረታ የቀረቡ ቢሆንም፣ የ36 ቦታዎች ደግሞ የጨረታ ሒደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ተሰርዟል፡፡ ‹‹አሸናፊ መሆናችን በጋዜጣ ከወጣ በኋላ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ጽሕፈት ቤቱ ጨረታውን ሰርዞብናል፤›› ያሉ አሸናፊ ተጫራቾች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጀማል ካልይ ፊርማ የወጣው ደብዳቤ፣ ጨረታው የተሰረዘበትን ምክንያት በድፍኑ አስቀምጧል፡፡
‹‹የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆነውን ውስን የመሬት ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር የሚገባ በመሆኑና የመንግሥትና የሕዝብን ጥቅም ከማስቀደምና ከማስከበር አንፃር ታይቶ ቦታው ተሠርዟል፤›› በማለት ደብዳቤው ያመለክታል፡፡
ነገር ግን አሸንፈው እያለ ማሸነፋቸውም በጋዜጣ ጭምር የተገለጸላቸው ተጫራቾች፣ ይህንን ድፍን ያለ ምክንያት እንዳልተቀበሉት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ 28ኛ ጨረታ በኋላ በወሩ 29ኛው ዙር ጨረታ ይወጣል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ጨረታው ግን እስካሁን ድረስ አልወጣም፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ንጉሥ ተሾመ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጨረታው በየወሩ መውጣት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ለጨረታ የተዘጋጁ ቦታዎች ለሌሎች ሥራዎች በመዋላቸውና ክፍላተ ከተሞች በሚፈለገው ደረጃ ቦታዎችን አዘጋጅተው እያቀረቡ ባለመሆኑ ጨረታ ሊወጣ አልቻለም፡፡
የነበሩ ችግሮችን አርሞ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 102 ቦታዎችን አዘጋጅቶ ለአልሚዎች ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ በጨረታው የሚተላለፉት ቦታዎች ለቢዝነስ፣ ለመኖሪያና ለቅይጥ አገልግሎት እንደሚውሉ፣ በኮልፌ 12፣ በቦሌ 37፣ በአራዳ ስድስት፣ በአቃቂ ቃሊቲ ሰባት፣ በአዲስ ከተማ ሁለት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ደግሞ ዘጠኝ ቦታዎች በ29ኛው ሊዝ ጨረታ እንደሚወጣ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡