Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክክልል ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አዲስ አበባ የመዳኘት ኢሕገ መንግሥታዊነት

ክልል ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አዲስ አበባ የመዳኘት ኢሕገ መንግሥታዊነት

ቀን:

በውብሸት ሙላት 

በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው የተከሰሱ እንዲሁም ጥፋተኛ ተብለው ፍርደኞች የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ ከማረሚያ ቤት ወጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉትና መደበኛ አድራሻቸው በየክልሉ የሆኑት በርካታ ናቸው፡፡ ለነገሩ ክሳቸው ያልተቋረጠ ወይም በይቅርታ ያልተለቀቁ ነገር ግን የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመዋል በተባለበት ወቅት አድራሻቸው ክልሎች ውስጥ የነበሩ በርካታ ተከሳሾች ጉዳያቸው አዲስ አበባ በሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ በተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር በፌዴራል ፍርድ ቤት መታየት ያለባቸው የፌዴራል ወንጀል ሆነው ነገር ግን በክልሎች የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን በውክልና የመዳኘት ሥልጣን የክልሎች በመሆኑ በተለይ በሽብር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ምርመራውም የተከናወነውም የክስ ሒደቱም በመታየት ላይ ያለው አዲስ አበባ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓቢይ ዓላማ ይህ ዓይነት የወንጀል ምርመራና የክስ ሒደት ሕገ መንግሥታዊ መሆን ወይም አለመሆኑን መፈተሽ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የክልሎችም ይሁኑ የፌዴራልም መንግሥታት በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ዝርዝር ሕጎች እንደተገለጸው የፍትሐ ብሔርም ይሁን የወንጀል ጉዳይን አከራክሮ የመወሰን ወይም የመዳኘት ሥልጣን አላቸው፡፡ መርሁም የፌዴራልን ጉዳይ በፌዴራል ፍርድ ቤት፣ የክልልን ጉዳይ በክልል ፍርድ ቤቶች ዳኝነት መስጠት ነው፡፡

የፌዴራሉ መንግሥት የራሱ የሆነ የተከለለ ብቻውን የሚያስተዳድረው ግዛት ስለሌለውና የሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ድምር ውጤት ስለሆነ በሁሉም ቦታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት በግዛት ሳይወሰን የጉዳዮቹ ዓይነት ላይ የተመሠረተ ሥልጣን አለው፡፡ ለክልሎች በግዛታቸው ውስጥ የሚያከናውኗቸው፣ የሚያዙባቸው፣ የሚናዘዙባቸው ጉዳዮች አሏቸው፡፡ 

ለፌዴራሉ ፍርድ ቤቶች ብቻ የሚቀርቡ፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ብቻ የሚወሰኑ የወንጀልም የፍትሐ ብሔርም ጉዳዮች አሉ፡፡ ጉዳዮቹ የተከሰቱት፣የተፈጸሙት፣ አልያም ባለመፈጸማቸው የክርክር መነሻ የሆኑት በክልሎችም ይሁን በሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች ከግምት ውስጥ ሳይገባ የጉዳዮችን ዓይነት መሠረት በማድረግ ብቻ የፌዴራል የሆኑ አሉ፡፡

የጉዳዮቹን ዓይነት ለመለየት በመሥፈርትነት የሚያገለግሉት በፍርድ ቤት ታይቶ እልባት የሚሰጠውን ጉዳይ ለመዳኘት በሥራ ላይ የሚውለውን ሕግ ያወጣው የፌዴራል ወይም የክልል መንግሥት መሆኑ፣ ጉዳዩ የተፈጸመበት ቦታና የተከራካሪ ወገኖቹ ማንነት (ዜግነት፣ መኖሪያ ቦታ፣ የሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ወዘተ) ናቸው፡፡

ጉዳዮቹ የተፈጸሙት በዘጠኙ ክልሎች ውስጥ ሆነ የመዳኘት ሥልጣኑ ግን የፌዴራል ፍርድ ቤት ሊሆንም ይችላል ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በመደበኛነት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የሚገኙት አዲስ አበባና ድሬዳዋ  ብቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ አዲስ አበባ፡፡

የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በየክልሉ ስለሌሉና ላይኖሩ እንደሚችሉ ቀድሞም ከግምት ስለገባ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78(2) ላይ እንደተገለጸው የየክልሎቹ ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ፍርድ ቤቶቹን ወክለው የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሥልጣን የሆነውን የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን የሆነውን ጉዳይ ደግሞ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በውክልና የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ የድጋፍ ድምፅ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ወይም የከፍተኛ ፍርድ ቤቶችን ወይም ሁለቱንም በተወሰኑ ወይም በሁሉም ክልሎች እንዲቋቋሙ ሊወስን ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ እስካልተወሰነ ድረስ በቅርንጫፍ መልክም ክልል ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤት መክፈት አይቻልም፡፡ በተዘዋዋሪ ችሎት ወይም በኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች በመጠቀም ክልል ላይ የተፈጸሙ ጉዳዮችን ከአዲስ አበባ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት በሕግ አልተፈቀደም፡፡ በእርግጥ ይህ አሠራር በሰበር ወይም በይግባኝ የመጡትን ጉዳዮች ለማስተናገድ ከሆነ ቅርንጫፍ፣ ተዘዋዋሪ ችሎት ወይም በሌላ መንገድ ማስቻል ክልክል አይደለም፡፡

ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ውጭ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በክልሎች የሚደራጁት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ውክልናው በተነሳበት ክልል ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ አመቺ በሆነ ቦታ የፌዴራሉ ከፍተኛም ይሁን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሊያስችል እንደሚችል ከአዋጅ ቁጥር 25/1988 ከአንቀጽ 24 መረዳት ይቻላል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78(2) ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስካልወሰነ ድረስ የፌዴራል ጉዳዮችንም የክልል ፍርድ ቤቶች በውክልና ደርበው ይሠራሉ፣ ዳኝነት ይሰጣሉ፡፡ ይህንን ውክልና ሊያነሳ የሚችለው ምክር ቤቱ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ውክልናቸው እስካልተነሳ ድረስ የክርክሩ መነሻ የሆነው ጉዳይ ክልል ላይ ከተፈጸመ አከራክሮ የመወሰን ሥልጣኑ የፌዴራል ፍርድ ቤትም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ መሠረት በተሰጣቸው ውክልና በክልል ፍርድ ቤት ይታያል እንጂ አዲስ አበባ ወይም ድሬዳዋ ባሉ ፍርድ ቤቶች እንዲታይ አይመጣም፡፡

እንደሚታወቀው፣ የፌዴራሉም ይሁን የክልል ፍርድ ቤቶች አወቃቀራቸው ሦስት እርከን ያለው ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ (የወረዳ)፣ የከፍተኛና የጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በመሆን፡፡ እንደየጉዳዮቹ ዓይነት አዲስ ክስ የሚቀርበው ለመጀመሪያ ደረጃ ወይም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት እንጂ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት አጋጣሚ ወደ ዜሮ የተጠጋ ነው፡፡ በውክልና ወደ ክልል ፍርድ ቤትም የተዛወሩት የመጀመሪያና የከፍተኛ ፍርድ ቤቶቹ ሥልጣን እንጂ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አይደለም፡፡

ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 80(4) እና (5) ላይ እንደተገለጸው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚታይን የክልል ከፍተኛ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚታይን ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ይዳኙ ዘንድ በውክልና ተሰጥተዋል፡፡ ይግባኝን በተመለከተ በክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የታየ ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ይሄዳል፡፡ ክርክሩን ያስተናገደው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሆነ ማለትም ስለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆን፣ ይግባኙ ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይመጣል፡፡

የክልል ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ጉዳዮች በማከራከር የዳኝነት አገልግሎት ከሰጡ የበጀት ማካካሻ ከፌዴራል መንግሥት እንዲተላለፍላቸው የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌም አለ፡፡ በተጨማሪም የክልል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራል ጉዳዮችንም የሚያስተናግዱ ስለሆነ በእነዚህ ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ ዳኞችን ክልሎች ከመሾማቸው በፊት ለፌዴራሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቅርበው አስተያየት መጠየቅ አለባቸው፡፡ በሦስት ወራት ውስጥም አስተያየቱን መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ሳይሰጥ ቢቀር ግን ያው እንደተወው ስለሚቆጠር የሹመት ሒደቱ ይቀጥላል፡፡ ይህ የሆነው የፌዴራል ጉዳዮችንም ስለሚዳኙ ነው፡፡

እንግዲህ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ውጭ የተፈጸሙ የፌዴራል ጉዳዮች የሚዳኙት በዚህ አኳኋን ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን የዳኝነት ውክልና ሊያነሳ እንደሚችልም ከላይ ተመልክተናል፡፡ በዚህ መሠረት ውክልናቸው የተነሳባቸውን የክልል ፍርድ ቤቶች አሉ፡፡ ይህ የሆነውም በ1995 በወርሃ መጋቢት መገባደጃ ሲሆን፣ የተወሰነውም በአዋጅ ቁጥር 322/1995 ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት በአፋር፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም በመወሰኑ ለእነዚህ ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ የነበረው ውክልና ተነስቷል፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚመለከታቸውን ጉዳዮች በሚመለከት ውክልናው አልተነሳም፡፡ ስለሆነም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ በተጨማሪ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎች ውስጥ የሚነሱ ጉዳዮችን በእነዚህ ክልሎች በመገኘት የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡ ቀሪዎቹ ክልሎች ግን አሁንም ቢሆን ማናቸውም የፌዴራል ጉዳዮች ቢሆኑ በክልል ፍርድ ቤቶች ይታያሉ፡፡

ይህን አደረጃጀት መሠረት በማድረግ ለፍትሐ ብሔርም ለወንጀል ክርክሮችም የዳኝነት ሥራ ይከናወናል፡፡ በዚህ መንገድ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት ወለም ዘለም የሚባልበት እንዳለሆነ ይልቁንም በጥብቅ መከበር ያለበት መሆኑን ከሚከተሉት የሰበር ውሳኔዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው በቅጽ 6 ላይ የታተመ ሲሆን የሰበር መዝገብ ቁጥሩ 20465 የሆነውን እንመልከት፡፡ በአዋሽ ኢንተርናሽናል ኩባንያና በሕፃን ተመስገን ቱጂ ሞግዚትና አሳዳሪ መካከል የተካሔደው ክርክር ነው፡፡ አስቀድሞ ጉዳዩን የተመለከተው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራሉን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመወከል ሲሆን፣ ይግባኝ ባይ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት  አቤቱታ አቅርቦ ጉዳዩን የፌዴራል ጉዳይ እንዳልሆነ በመወሰን ስለዘጋው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ፡፡

የሰበር ችሎቱም በክልሉ ከፍተኛ ፍርድ የተነሳን የፌዴራል ጉዳይ በይግባኝ መስማት ያለበት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሆኑ እንጂ ጉዳዩ የፌዴራል እንዳልሆነ በመግለጽ በምክንያት ተለይቶ ውሳኔውን አጽንቶታል፡፡ የአከራካሪው ጭብጥ የፍትሐ ብሔር ቢሆንም በክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የታየን የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በማናቸውም መንገድ ቢሆን በይግባኝ ማየት እንደማይችል ሰበር ችሎቱ ወስኗል፡፡ የአምስቱ ክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን በመወከል በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ ጉዳይን ተቀብሎ የመዳኘት ሥልጣን ቀሪ መሆን ማለት በይግባኝ የሚመጡ ሌሎች የፌዴራል ጉዳዮችን አይዳኝም ማለት እንዳልሆነ ወስኗል፡፡

ከላይ ካየነው በተጨማሪም በቅጽ 12 የታተመ፣ በሰበር መዝገብ ቁጥር  54577 የሆነ ውሳኔም እናገኛለን፡፡ ተከራካሪዎቹ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና ሰለሞን ያዕቆብ ሲሆኑ፣ ክርክሩ መጀመሪያ ላይ ያየው የአላባ ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በዚህ ፍርድ ቤት ከተወሰነ በኋላ ጉዳዩ የፌዴራል ስለሆነ በይግባኝ ማየት ያለበት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወይስ በክልሉ የተቋቋመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚለው ጭብጥ ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የሚነሱ የፌዴራል ጉዳዮችን በይግባኝ ማየት ያለበት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን በድጋሜ አጽንቶታል፡፡ ለውሳኔው በማጠናከሪያነት የቀረበው መከራከሪያም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 80(2) ላይ በክልል ውስጥ የሚነሱ በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የሚዳኙትን የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በውክልና እንዲያዩ ከደነገገ በኋላ በመቀጠልም በእዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ በክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የታዩ የፌዴራል ጉዳዮችን በይግባኝ እንዲዳኙ ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በግልጽ በሁለት ደረጃ ከፍሎ በመሰጠቱ፣ እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 322/95 መሠረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ ሲወስን የተገለጸው የክልሎቹ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በመጀመሪያ ደረጃ በውክልና ሥልጣን የተሰጣቸውን ሥልጣን ቀሪ አደረገ እንጂ በይግባኝ የሚመጡ አቤቱታዎችን የማየት ሥልጣንን እንዳላስቀረ ዘለግ ያለ ሐተታ በማቅረብ ነው፡፡

ከፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአስተዳደር ፍርድ ቤቶችም ክልል ውስጥ እስከተገኙ ድረስ በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ቅር የተሰኘ አካል ለፌዴራል የመጀመሪያ ወይም ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት ካለው የሚስተናገደው በክልል ፍርድ ቤቶች እንጂ ክልል ላይ በተቋቋሙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እንዳልሆነ ቅጽ 20 ላይ ከሰፈረው ውሳኔ መረዳት ይቻላል፡፡ ክርክሩ የተከናወነው በእነ ሚሪንዳ ዋሲሁንና በኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ ቦርድ በወሰነው ውሳኔ ላይ ይግባኝ ማለት የፈለገ ተከራካሪ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት እንዳለው ይታወቃል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በተቋቋሙባቸው ክልሎችም ቢሆን እንኳን ከቦርዱ ውሳኔ የሚነሳን ጉዳይ በይግባኝ ማየት ያለበት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን በድጋሚ አጽንቶታል፡፡

ከላይ ያየናቸው ውሳኔዎች የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ቢሆኑም እንኳን መነሻቸው በክልል እስከሆነ ድረስ የመዳኘት ሥልጣኑ ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው መሠረት በጥብቅ መተግበር ያለበት መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ ለፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በዚህ መልክ ከተወሰነ ለወንጀል ሲሆን ደግሞ እንደውም የበለጠ ሊፈጸም ይገባል፡፡

ይሁን እንጂ የተወሰኑ የወንጀል ድርጊቶች በሚመለከት ምንም እንኳን የተፈጸሙት በክልሎች ቢሆንም፣ ተከሳሾችም መደበኛ ነዋሪነታቸው በክልል ቢሆንም ምርመራውም ሆነ ክሱም አዲስ አበባ ላይ እንደሚከናወን ይታወቃል፡፡ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከሚውሉበት ጊዜ ጀምሮ በክስም ሒደትም በፍርደኝነትም አዲስ አበባ ላይ ማቆየት የተለመደ ነው፡፡

በወንጀል የፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ቢያንስ አራት የመንግሥት ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህም ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤትና ማረሚያ ቤት ናቸው፡፡ የፌዴራል ወንጀል በሚሆንበት ጊዜ ምርመራውን የሚያከናውነው የፌዴራል ፖሊስ ነው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል እንዳይፈጸም የመከላከል፣ ከተፈጸመም ምርመራ የማከናወን ኃላፊነት አለበት፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሥር የሚወድቁ የወንጀል ተግባራትን ይከላከላል፣ ምርመራም ያደርጋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የአገርና በመንግሥት እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ይከላከላል፣ ምርመራም ያከናውናል፡፡

ለክልል ፖሊስ ውክልና እስካልሰጠ ድረስ የፌዴራል ፍርድ ቤት ሥልጣን የሆኑ የወንጀል ተግባራትን የመከታተል ኃላፊነት አለበት ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተገለጸው በፌዴራል መንግሥት በክልሎች ውስጥ በመግባት የፀጥታ ማስከበር ተግባር እንዲፈጽም ሲታዘዝ ሕግና ሥርዓትን ያስከብራል፡፡ በዚህን ጊዜም የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ትብብር የማድረግ ግዴታ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው ምንም እንኳን ዋና መሥሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ቢሆንም ለሥራው አመቺነትና ኃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታው ለማከናወን እንዲመቸው በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ቅርንጫፍ መክፈት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ይህ እንግዲህ ወንጀል ለመከላከልም ለመመርመርም ጭምር ነው፡፡ 

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን የሆኑ ወንጀሎችን ክስ የሚመሠርተው የፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የክስ ሒደቱን የሚከናወነው በክልሎቹ በመገኘት በክልል ፍርድ ቤቶች ስለሆነ ይኼንኑ ኃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ አለበት ማለት ነው፡፡ ይህንን ግዴታ ታሳቢ በማድረግም ነው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዋና መሥሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ላይ ሆኖ በክልሎች ላይ ቅርንጫፍ ሊከፍት እንደሚችል በማቋቋሚያ አዋጁ (943/2008) አንቀጽ 4 ላይ የተገለጸው፡፡

ቅርንጫፍ መክፈት ሳያስፈልገውም የክሱን ሒደት ሊከታተል ይችላል፡፡ ቁምነገሩ በክልል የተፈጸመን በክልል ላይ ምርመራና ክስ መመሥረትን አክብሮ መሥራቱ ላይ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች ውስጥ ሁለቱ ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበርና ማስከበር›› እንዲሁም ‹‹የሕግ የበላይነትን ማስከበር›› መሆናቸው በአዋጁ አንቀጽ 5 (1) እና (2) ላይ በግልጽ  ሰፍሯል፡፡

ከዳኝነት ሥልጣን አኳያ ሕገ መንግሥታዊ አሠራርና ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል ታስቦ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረው ከላይ ባየነው መልኩ ነው፡፡ ይህንን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ተከትሎ አለመተግበር የሕግን ልዕልና ወይም የበላይነት አለመተግበርና አለማስፈን ከመሆን አይዘልም፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሲጀምርም ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም የመከታተል በሕግ የተጣለበት ኃላፊነት አለበት፡፡ የዘወትር ተግባሩም ነው፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከላይ የሚለውን ከሆነ በክልል ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ሲኖሩ ተጠርጣሪዎቹን ፖሊስ አዲስ አበባ በማምጣት ምርመራ ማከናወኑ የሕግ መሠረት የለውም ማለት ነው፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግም ክሶቹን በፌዴራል ፍርድ ቤት አዲስ አበባ ላይ መመሥረቱ ተገቢነት የለውም፣ ሕጋዊም አይሆንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዓቃቤ ሕግ በዚህ መንገድ የወንጀል ምርመራ እንዳይከናወን የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

በዚህ በተጨማሪ ፖሊስ የሚያደርገውን የምርመራ ሒደትም በአግባቡና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ብቻ እንዲሆን የመከታተልና ስህተት ሲፈጸምም የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ አለበት፡፡ ማንኛውም መርማሪ ፖሊስ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚወስነውን ውሳኔ የማክበርና የመፈጸም የሕግ ግዴታ አለበት፡፡ የዓቃቤ ሕግን ትዕዛዝና ውሳኔ ሳያከብር የቀረ ፖሊስም የወንጀል ተጠያቂነት አለበት፡፡ ለነገሩ ከፖሊስ ውጭ የሆነ ማንኛውም ሰው (ባለሥልጣን፣ የፀጥታና የደኅንነት ወዘተ) ደግሞ የዓቃቤ ሕግ ሥራና ተግባር ላይ ጣልቃ ቢገባ፣ ቢደናቅፍ፣ ባይተባበር በወንጀል እንደሚጠየቅ የቅጣቱም መጠን ሳይቀር ሁሉ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 24 ላይ ሰፍሯል፡፡

በአጭሩ፣ ክልል ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ምርመራዎቹም ክሶቹም በክልል ውስጥ መከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሥልጣኑም የክልሎች ፍርድ ቤት በመሆኑ ፌዴራል ፖሊስም፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ፍርድ ቤቶችም ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተዓማኒ በመሆንና በማክበር ተምሳሌት መሆን ተገቢ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...