Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአገር የሚያስፈልጋት ከውድመትና ከጥቃት የፀዳ ትግል ነው

አገር የሚያስፈልጋት ከውድመትና ከጥቃት የፀዳ ትግል ነው

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ላለፉት 26 ዓመታት ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ በሐሳብና በምናብ፣ አንዳንዴም እዚህ ጋዜጣ ላይ በሚወጣ ጽሑፍ ኢሕአዴግን ‹‹በላ ልበልሃ!›› እያልኩ የምሞግትበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ግንቦት 20 ለኢሕአዴግ ከሞላ ጎደል አልፋና ኦሜጋው ነው፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የተመሠረተችበት፣ ታሪኳ መጻፍ የጀመረበት፣ ወዘተ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያለውን ቢልም አንድ ነገር ግን እውነት ነው፡፡ ግንቦት 20 የወታደራዊ አምባገነንነት እንዳይሆን የፈረሰበት፣ ፈላጭ ቆራጮች እምቧጮ የሆኑበት፣ ወታደራዊ ኃይላቸው፣ የፀጥታ መረባቸውና ፓርቲያቸው የተበጣጠሰበት ዕለት ነው፡፡

ኢሕአዴግ እስከ ዛሬም ድረስ ደርግን ማሸነፉን፣ በዓለም አቀፍ መድረክም ዕውቅና (ብድርና ዕርዳታ ጭምር) መሰጠታቸውን፣ ከዚህም አልፎ ያለ ጠንካራ ተቃዋሚ መገኘቱን የትክክለኛነቱን ማስረጃ አድርጎ ይቆጥር ገባ፡፡ ከደርግ ‹‹መብለጡ›› ወይም ‹‹መሻሉ››ን ደግሞ ብቸኛውና አስፈላጊው የሥልጣን ‹‹የብቃት ማረጋገጫው›› እያደረገ አቀረበ፡፡ ራሱን ከደርግ ጋር ከማወዳደር በቀር በሌላ ነባራዊ መሥፈርት ተገቢነቱን ጠይቆ የማያውቀው ኢሕአዴግ ግን ከአካዳሚ ነፃነት አኳያ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት፣ ከከተማ መሬት አስተዳደርና የመኖሪያ ቤት ግንባታ አንፃር የደርግ መንግሥት እንደሚበልጡትና እንደሚያስከነዱት አንዴም ታይቶት አያውቅም፡፡

ከመሸፋፈንና ራስን ከማታለል ተላቆ የተሳካና የተሻለ ነገር መሥራቱን መመዘንና ለሕዝቡም በኩራት ሪፖርት ለማድረግ የሚፈልግ መንግሥትም ከደርግ በስንት በለጥኩ እያለ ከማስላትና ራስን ከደርግ ጋር እያወዳደሩ ከመዋረድ ወጥቶ ዋናውን ጥያቄ መጠየቅ አለበት፡፡ ደርግን ማስወገድ ያስፈለገው ለሕዝብ ጥያቄና ቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን ደም መቃባት በሌለበት በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ሥርዓትና አሠራር ለመመሥረት ነው፡፡ የፖለቲካ ጠቦች፣ የሕዝብ ቅሬታዎች ወደ ጠመንጃ የሚሄዱበትን ዕድል እያጠበቡ ለመዝጋት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶና ስብስቦሽ እንዲያብብና እንዲነግሥ በዚህ መሠረትም አጠቃላይ የእሰይታና የአዲስ አገር ግንባታ ሥነ ልቦናዊ ምልዓት እንዲፈጠር ለማድረግ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የአገሪቱ የፖለቲካ ሰላም ፈተና የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚዎች ትግል/ትንቅንቅ ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ትግል በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ክልል ውስጥ እንዲቆይና በዚያው እንዲገታ የሚያደርግ አያያዝ ከመከተልና ከማጎልበት ይልቅ፣ የተለያዩ ሥውርና ግልጽ ደባዎችን እስከ መጠቀም ልቅ ስለወጣ ነፃ እንቅስቃሴዎችና መሰባሰቦች ተኮላሹ፡፡ በዚህ ምክንያት ኢሕአዴግ ራሱ የትርምስና የተቃውሞ ዋና መራቢያ ሆኖ በመቆየቱ የቁጣ እሳት አልጠፋ ብሎ፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት ያስመዘገቡትና ይበልጥ እየከፋ የመጣ አደጋ ውስጥ ገብተናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህን የሥርዓቱን ችግር በቅጡ አስተንትኖና አስተውሎ ከሕዝብና ከዴሞክራሲ ወገኖች ጋር መፍትሔ በመፈለግ ፋንታ ብቅ ያለ ተቃውሞን ሁሉ ፀረ ሰላም፣ ጽንፈኛ፣ አሸባሪ እያሉ በድቆሳ ለማሸነፍ የተያዘው የተለመደው መንገድ የሌላ ተቃውሞ ማስፋፊያና የአገዛዝም መዋረጃ እየሆነ ነው፡፡

መሪዎቻችንና የገዥው ፓርቲ ሹማምንት መደበኛው ግንቦት 20 ክብረ በዓልና ዋዜማው ላይ ብቻ ሳይሆን አሁን ድኅረ 2008 ዓ.ም. ጭምር የሚነግሩን፣ በአንዳንድ አገር ለውጡ የተወሰነ ርቀት ሄዶ ይገተራል፡፡ የእኛ ግን ቀጣይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሕዝብ ወጣሪነት ሞጋች ኅብረተሰብ የመፍጠር ትግሎችን ፍሬ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ የሁሉም ልዩነት መፍቻ ኃይል ነበር፡፡ እኛ ግን ልዩነቶችን በሰላም ማስተናገድ የሚያስችል መሠረታዊ ለውጥ አምጥተናል፡፡ የቡድንና የግል መብቶች የተከበሩበት፣ ሙሉ ነፃነት ያላቸው ፍርድ ቤቶች አስተማማኝ ሰላም ያለበት፣ ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብተናል እያሉ ነው፡፡ ይህን የሚለን ነፃ የአደባባይ ሠልፍና ስብሰባ የማካሄድ ነፃነትን በመሰነግ ዋናው ሕግ ጣሽ የሆነው መንግሥት ነው፡፡

ዋናው ሕግ አፍራሽና ሕግ ጣሽ እሱ ሆኖ ክልከላውንና አፈናውን እንቢ ብሎ የገነፈለ ሕዝብን በሕገወጥነት ይከሳል፣ የረባ ሰላማዊ መፍትሔን ሳይሞክር በኃይል ‹‹ሕግ የማስከበር›› ዕርምጃን ያውጃል፡፡ በጥይትና በእስራት ያስተናግዳል፡፡ ዴሞክራሲ ብሶተኛ ለመጮህ መብትና ዕድል የሚያገኝበት ለጩኸትም ጆሮ የሚሰጥበት፣ ከዚያም አልፎ በወከላቸው ሰዎች አማካይነት ከመንግሥት ጋር እስከ መደራደር አክብሮት የሚያገኝበት ሥርዓት ነው፡፡ እኛ አገር ይህ አይሠራም፡፡ እንዲሠራም አይፈለግም፡፡

ሐሳብን የመግለጽና የንግግር ነፃነት ከሥር ከመሠረቱ በመሰነጉ፣ የሕዝብ ቅሬታና ብሶት ጋዜጣ ላይ ፓርላማ ውስጥ መሰማት ባለመቻሉ፣ ተዳፍኖ ለሚንተከተክ ተቃውሞ ዳርጎናል፡፡ መንገሽገሽ ለተዘረገፈበት ደጅ ለወጣና አደጋ ለሚሸተው ተቃውሞ የግድ የሚያጋልጠንም ይኼው ነው፡፡

ይኼው ራሱ ብቻ በጥፋት ላይ ጥፋት እያደራረበ መንግሥትን ተቃውሞን በኃይል የመደፍጠጥ የማይገረሰስ ሥልጣን አጎናጽፎኛል ባይነት ላይ እንኳን ያለ ፍርኃትና ኃፍረት እንዲናገር አድርጎታል፡፡  ተቃውሞን በኃይል ለመደፍጠጥ መድፈር፣ ደፍሮና ደፍጥጦም ሳይጠየቁ መቅረት ብቻ ሳይሆን ይህንን በአደባባይ፣ በየክብረ በዓሉና በየመንግሥት መግለጫው የ‹‹ሕግ የበላይነት›› ተግባር ተደርጎ ቡራኬ እየተሰጠው ይነገራል፡፡ በዚህ ግዳጅ ሒደት ውስጥ ሕይወት ይጠፋል፡፡ ሰው ይገደላል፡፡ በገፍም ይታሰራል፡፡ ኢሕአዴግ ካሰረ በኋላ ክስ በማቋረጥም ሆነ በይቅርታ ለመልቀቅ ‹‹ንቃት››ና ወይም ‹‹ተሃድሶ›› ሲሰጥም መብት መድፈሩና ሕግ መተላለፉ ሳይሆን የመሪነት ኃላፈነቱን ማሟላቱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በሕይወት የመኖር መብትን ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ሰው ሕይወቱን አያጣም ይላል፡፡ መንግሥት ይህን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ለማክበርና ለማስከበር፣ ከአደጋ እጠብቃችኋለሁ፣ ከግድያና ከገዳይ እከላከላችኋለሁ ብሎ በየአቅጣጫውና በየዘርፉ ዝርዝር ሕጎችን አውጥቷል፡፡ እንዲያወጣም ይገደዳል፡፡ ሕፃናት እንዳይሞቱ፣ የሕፃናት ሞት በተቻለ መጠን እንዲቀንስ፣ ማንም እናት በወሊድ እንዳትሞት፣ ረሃብ  ሰውን እንዳይገድል፣ የመኪና አደጋ፣ በኤችኤቪ ኤድስ ሞት ሰው እንዲተርፍ መንግሥት ግዴታ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ ግብር ሰነዶች በዚህ ሁሉ ዘርፍ የኢትዮጵያን ጥረቶችና ትጋቶች ይዘረዝራሉ፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን በመንግሥት ሕግ አስከባሪዎችና በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች  እጅ የሚሞተው ሰው ቁጥር ከምንነጋገርበት ጉዳይ አንፃር አስደንጋጭና አሳሳቢ ሆኖ መጥቷል፡፡ ሠልፍ የማድረግ፣ በሠልፍና በስብሰባ መንግሥትን መቃወም ጨምሮ ሐሳብን የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ በሕይወት ከመኖር መብት እኩል ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡

መንግሥት የአደባባይ ሠልፍና ስብሰባ ጥያቄ ሲመጣ እየከለከለ መብትነቱን ደፈቀው፡፡ ከዚያም በላይ ‹‹አደገኛ›› አደረገው፡፡ ክልከላው እየተጠናወተው  ከመምጣቱ የተነሳ የአደባባይ ሠልፍና ስበሰባ ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ሁሉም ከከተማ/ወረዳ አስተዳደር እስከ ፖሊስ  ያለ ሁሉ ‹‹የቀለም አብዮት መከላከያ›› ዘብ ቋሚ ሆነ፡፡ በዚህ መካከል ሕግን አክብሮ ድምፅ የማሰማት ጨዋነትንና ምግባርን የምንማርበትና የምንለማመድበትን መድረክን ጭምር ተነጠቅን፡፡ መንግሥት የስብሰባና የሠልፍ እንዲሁም የመቃወም መብትን ማክበር ማስከበር፣ ያለበት ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ብቻ አይደለም፡፡ ከጉዳትና ከአደጋ በመከላከል ጭምር ነው፡፡   

መንግሥት ቁጣ ባለበት ሠልፍና ስብሰባም ውስጥ የመግደል መብት የለውም፡፡ በአገራችን ቅሬታዎችና ችግሮች ታጅለው ስለኖሩ ቁጣ ሊፈነዳ ይችላል፡፡ የሕዝብ ቁጣም በተለያየ መልክ ይከሰታልም፡፡ እንዲህ ያለና ከዚያም የባሰ ጠመንጃ ይዞ ለጩኸት የወጣ፣ ሲከፋም የተኮሰ/የሚተኩስ ቢኖር እንኳን ኃላፊነት የሚሰማውና ሕዝብን የሚያከብር መንግሥት ዝም ብሎ የድፍጠጣ በትር አይጠቀምም፡፡ መንግሥት ቁጣን ያበርዳል፡፡ ወደ ሰላማዊ የውይይት መፍትሔ ለማምጣት የሚስችል በሽምግልናም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲ በኩል መማለድን የሚጨምር ማናቸውንም ዘዴ ተጠቅሞ የሕዝብ ቁጣን ያበርዳል፡፡ ይህ እኛ አገር ተራራ ነው፡፡ ውርደት ነው፡፡ ተራ የሕዝብ ተቃውሞና መንግሥት ‹‹ውጊያ›› ላይ ናቸው፡፡ በአገራችን እንኳንስ ከገነፈለ ተቃውሞ ተወካይ ጋር መወያየት ይቅርና ያልታፈቀደ ሠልፍን መታገስ፣ በዚህ ላይ ቃታ አለመሳብ ለብጥብጥ መልዕክተኞች መሸነፍና እጅ መስጠት ነው፡፡

መንግሥት ሕግ በማስፈጸምና በማስከበር ስም የተጠናወተውን ሕገወጥነትና ከሕግ በላይ የመሆን አደጋ የአገሪቷን ዴሞክራሲ ትግል ሲበዛ ጎድቶታል፡፡ አጨናግፎታል፡፡ በሌላው ወገን ደግሞ የሕዝብ የትግል ሥልትም ከዚሁ እኩል አገር የማትወጣበት አዘቅት ውስጥ ለዘለቄታው እንድትኖር እያደረገ ነው፡፡ እስካሁን ስንል የቆየነው ሕዝብ ፍላጎቱንና ብሶቱን በይፋ ለመናገርና ለመግለጽ፣ በደልን ለመጋተርና መብቱን ለማስከበር የማይፈራበት የእኔ የሚለው የነፃነት አየር የለም፡፡ መንግሥት ይህንን ከልክሏል፡፡ ለመቃወም የሚወጣውን ይቀጣል፣ ያስራል፣ ይገድላል የሚለው የችግራችን አንደኛው ገጽታ ነው፡፡ ሌላው የችግራችን ገጽታ በደልን የመከላከል፣ የማጋለጥና ተጋፍጦ የመፋረድ ወይም ይህንን የማሰማትና የማስተጋባት የትግል ሥልታችንን የሚተናነቀው አፍራሽነት ነው፡፡ የትግል ሥልቱ በልማትና በለውጥ ላይ ማኩረፍን ይጨምራል፡፡ ከእሱም ይነሳል፡፡

ለደርግ አምባገነንነት ተቃውሞ መገለጫና መጉጃ ሆነው ሥር እየሰደዱ የመጡት ኩርፊያ፣ ከዳር ቆሞ ማየት፣ ችሎታን መሸፈጥና አውቆ ማጥፋት በኢሕአዴግ አስተዳደር ለአጭር ጊዜ ተደናግጠው ነበር፡፡ ይህ ግን ለአጭር ጊዜ ብቻ ሆኖ አብቅቷል፡፡ መፍትሔ የተነፈገው ፖለቲካዊ ብሶተኛነት ኢሕአዴግን ወድቆ የማየት ፍላጎ ህሊና ከማሳጣቱ የተነሳ፣ በግብርና ምርትና ለተወሰነ ጊዜም በወጪ ንግድ የታየውን ዕድገት አንዳች ድርቅ መጥቶ ድራሹን ቢያጠፋለት እስከመመኘት የደረሰ ሰው እናገኛለን፣ የባሰም አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደባ ቢሠራበትም፣ ፀብ ቢለኮስበትም አይለያይም የሚል መከራከሪያ ይዞ ‹‹አሁንም የፈለገው ዓይነት ቀውስ መጥቶ ድብልቅልቁ ቢወጣ›› የሚልና ኢሕአዴግን በዚህ ዓይነት መንገድም ለመገላገል የሚመኝ ሰው ሲያጋጥም አዲስ አይደለም፡፡ ዛሬም በዚሁ ቀውጢ ወቅት እንዲህ ባለ ድብልቅልቁ የወጣ ነገር ኢሕአዴግን ‹‹እንዲገላግለን››ም የሚመኝ አለ፡፡

ሰብዓዊ መብቶች ሰጪና ተቀባይ የላቸውም፡፡ በተፈጥሮና ሰው በመሆናችን ምክንያት ብቻ የተቀናጀናቸው ናቸው እየተባለ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ እኛ የምንገኘው ግን በሥልጣን ላይ ያለ አካል ሲያሻው ሊነጥቅን በማንችልበት ማኅበራዊ ልማት ውስጥ አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ዝርዝርን ለሚያስተውል ሰው እንደ ኢትዮጵያ ደሃ ከሆኑ አገሮች ይልቅ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ምድር ለ ሰው ሰፊና ከስም ያለፉ ነፃነቶች እንዳሉት ይረዳል፡፡ ይህን የተረዳ ሰው ለልማት የሚደረግ ትግል በሌላ ፈርጅ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መሟላት የሚደረግ ትግል መሆኑ አይጠፋውም፡፡ ስለዚህም በልማት ላይ ማኩረፍ የትግል ሥልት አይደለም፡፡ በዚህ ግንባር የሚደረገው ትግል ግን ፍዝ ኩርፊያ ብቻ አይደለም፡፡ ‹በኢትዮጵያ አየር መንገድ አትሳፈሩ፣ ለኢትዮጵያ ዕርዳታ አትስጡ፣ ወደ ኢትዮጵያ ዘመዶቻችሁ ዶላር ወይም ሌላ መገበያያ እየላካችሁ የኢሕአዴግን ዕድሜ አታራዝሙ . . . › ማለት የማያሳፍር የትግል ዘዴ ሆኗል፡፡

በአገርና በልማት ዙሪያ ኩርፊያ የለም የሚለው ቅስቀሳና መከራከሪያ ግን፣ ለአገርና ለልማት ተብሎ ተቃዋሚዎችን ማቅረብ የሚለውን ቁም ነገር ማካተትና በተቃዋሚዎች ዙሪያ ያለውን ኩርፊያ የማምከንንም አስፈላጊነት ማስታወስም አለበት፡፡

ሰላማዊ ስላልሆነ ትግል በሰፊው ተነግሯል፡፡ በሕግም የተከለከለ ነው፡፡ የትጥቅ ትግል ረዥም ጊዜ ይወሰዳል፡፡ ከመንግሥት ጋር አገርንም ያደቃል፡፡ በዚህ ዓይነት ትግል ውስጥ ሲተኩሱ፣ ፈንጂ ሲዘሩና መሠረተ ልማት ሲያወድሙ ኖረው ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ መልሶ ግንባታ ማለት ዛሬ እብደት ነው፡፡ ይህ የተዘጋ፣ በሕግም የተከለከለ አማራጭ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ይህንን በዛሬው ዓለም ደረጃ ከቁጥርና ከአማራጭነት ውጪ የወጣውን የትግል ሥልት እንከተላለን ያሉና ስለዚህም ከ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት›› የጨዋታ ሕግ ራሳቸውን ያስወጡ ቡድኖች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ የእነዚህን ቡድኖች ምርጫ፣ አቋምና መከራከሪያ ያገዘውና ‹‹ጥብቅና›› ቆሞ የሚገለግለው ራሱ የገዥው ፓርቲ የኢሕአዴግ ፖሊሲና አሠራር ነው፡፡

ኢሕአዴግ የውስጥ ተቃውሞን በማኮላሸቱና በማዳከሙ ለራሱ ጥንካሬ አልፈጠረለትም፡፡ ተቃዋሚዎች ተመርረው ወደ ስደት ወይም ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደ ተገላገላቸው መቁጠሩም በራሱና በአገር ላይ የባረቀ ሆኗል፡፡ በሕጋዊነት መቀጠል ወይም ወደ ሕገወጥነት መዞር እያለ የጫካን መንገድ በሚያመላክት ፕሮፓጋንዳ ድቆሳ ሲሠራ መቆየቱም ለኢሕአዴግ ‹‹መበስበስ›› እንጂ ጥንካሬ አልሆነውም፡፡ እንዲያውም ከሕገወጡ ይልቅ ሕጋዊውን መንገድ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ የፖለቲካ፣ የሕግና የአሠራር ባህል ላይ ደንቃራ በመሆኑ በሰላምና በሕጋዊ የጨዋታ ሕግ ውስጥ ማደር ያልቻለው የውስጥ ተቃውሞ ከጎረቤት አገር ባለጋራነትና ከውጭ ጠላትነት ጋር እንዲሸራረብ አድርጓል፡፡

ከጥንት ከጠዋቱ አበሳ የበዛበት ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ደግሞ ከዚህ የተነሳ እንደተደናገጠና እንደታፈነ ነው፡፡ የምንገኝበትን ወቅታዊውን ሁኔታ በመሰለ የሕዝብ ብሶትና ግፊት የመንግሥትን የእኔ ብቻ ልክ ዳፍንት ባናወጠበት ጊዜ እንኳን የሕዝብ ትግል ትክክለኛ ምሪት አላገኘም፡፡ የደሃ አገርን ተቋማት፣ ንብረትና የልማት ሥራዎች ማውደም በትግል ዘዴነት መርቆና ባርኮ ለወጣቱ መስጠት ዛሬም ኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበ አደጋ ነው፡፡ በቁጣ ታውሮም ሆነ ፖለቲካ ተብሎ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ማድረስና ንብረት ማውደም የትግል ሥልት አይደለም፡፡ ፖለቲካም አይደለም፡፡ ንብረት ማውደምና ሕይወት ማጥፋት የዜጎችን መብት የሚጥስ በመሆኑ መጀመርያ የትኛውንም በደል፣ የመብት ረገጣና ኢፍትሐዊ ተዛነፍ የማይቃወም የትግል ሥልት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል አዋላጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥፋትንና ውድመትን ይዞ የሚመጣ ተቃውሞ ውስጥ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ድል አይገኝም፣ ይህ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ ዓይቱ የትግል ሥልት ሌላም ጠንቅ፣ አደጋና ጣጣ አለበት፡፡ አውዳሚ የትግል ሥልት በገዛ ራሱ ምክንያት አውዳሚ ነው፡፡ ጥፋትንና ጥቃትን ይዞ በሚመጣ ትግል ውስጥ መሳተፍ የአንዱን ወይም የሌላውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ትግል ከጥፋት ጋር ተዛምዶ እንዲታይ ያደርጋል፡፡ ሌሎች አሻጥረኞች ሊያቀናብሩትና ሊያደርሱት ለሚችሉት ውድመት ሁሉ ማላከኪያ ይሆናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአንዱን ማኅበረሰብ ትግል ከውድመት ጋር መዛመዱ ቀሪው ወይም ሌላው ማኅበረሰብ የዚያን ማኅበረሰብ ትግል በሥጋት እንዲያይ ያደርጋል፡፡ ይህ ራሱ ለዴሞክራሲያዊ ትግሉ ከፍተኛ ስብራትና አደጋ ነው፡፡

አገራችንን ፖለቲካዊ ሰላምና ነፃነት ከልማት ጋር የተገናኙበት ሕይወት ውስጥ የሚያስገባውን የትግል መንገድ የመፈለግና የዚህን ፈር ቀዶ ጥርጊያ መንገዱን የማንጠፍ ውዝፍ ሥራ ተደቅኖባታል፡፡ ከዚህ አንፃር ቀደም ሲል እንደገለጽነው፣ በፈላና በደፈረሰ ስሜት መታወርና እልህን በዜጎችና በዜጎች ንብት ላይ መወጣት በጭራሽ ፖለቲካ አይደለም፡፡

ፖለቲካ፣ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ከአፈና መዳፍ የመፈልቀቅና ዕድሜ የመስጠትም ሆነ የመቅጨት ውጤቶች የሁለት ወገኖች ድርጊታዊ መስተጋብር የሚወስኑ መሆናቸውን መቼውንም አለመዘንጋት ነው፡፡ መንግሥት ማነቆ አላልቶም ሆነ የተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ‹‹አደንዝዞት›› ለአደባባይ ሠልፍ ዕድል ሲሰጥ፣ ከቁጥጥር በወጣ ግልፍታ ታውሮ የጥፋት ድርጊት ውስጥ መግባት ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች መብት ይጥሳል፣ የእነሱን ሥጋትና ጥርጣሬ ያስከትላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የገዛ መብትን ያባርራል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ኃላፊነት በተሞላበት አኳኋን መብትን መጠቀም፣ ያ መብት ለነገም ውሎ አድሮ እንዲገኝ አርቆ ማሰብ ነው፡፡ መብት እንዲሰፋና ሥር እንዲይዝ የመሥራት ብልህነት ነው፡፡ ያለፉት 27 ዓመታት ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ክራሞታችን የነፈገን ይህን የመሰለ የፖለቲከኝነት ትንሹን እውቀት ነው፡፡

ስለሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ደጋግመን አንስተናል፡፡ አደባባይ ወጥቶ ታቃውሞን ከመግለጽ ጀምሮ በዴሞክራሲ ውስጥ የሚታወቁት ፍላጎትንና ጥቅምን የመግለጽና የመጠየቂያ መንገዶች እንደ ፍጥርጥራቸው በመረጥናቸው ዘዴዎችና እነሱንም በሚገዛቸው ሕጎች ይወሰናል፡፡ ሕጋዊነታቸው፡፡ ሕዝብ ፍላጎቱን፣ ብሶቱን፣ ጥያቄውን በይፋ የሚናገረው መብቱን የሚያስከብረው በደሉን የሚጋተረው በተቋማዊ መንገዶች አቤቱታ እያቀረበ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሠልፍ በስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ተቃውሞን ይገልጿል፡፡ አቋምን ያሳውቋል፡፡ ቅሬታን ያስመዘግቧል፡፡ ይህ ከጥቅም የመነጨ ፍላጎትን የማስመዝገቢያና የማስታወቂያ (በመንግሥት ፖሊሲና አመራር ላይ ተፅዕኖን የማሳረፊያ) ዘዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭምር በሕግ የተደነገገ ነው፡፡ ጥያቄን በማስታወቅ ሐሳብን በመግለጽ ከፍ ሲልም በደልን በመከላከል፣ በማጋለጥና ተጋፍጦ በመፋረድ የትግል ሕጎች ላይ ሳይሳካልን የቀረው በሕጎቹ ጉድለት ሳይሆን፣ ከሕጉ በላይ መሆን የቻሉ ገዥዎች በመኖራቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ገና ከችግር አልወጣም፡፡

ሥልጣንንና ትክክለኛነት የእኔ ብቻ ነው ብሎ መሰሪ መንገዶችንና በሥልጣን መባለግን የትግል መሣሪያው አድርጎ ያለተጠያቂነት የዘለቀበት ገዥው ፓርቲ ዋናውን ተጠያቂነት ቢሸከምም፣ የተቃውሞው ጎራ መብቶችና ኃላፊነቶች ለተግባቡበት የትግል ዘዴ አለማለማመዱ ጥፋት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ትግል ከውድመት መፅዳት፣ ዴሞክራሲያዊ ግቢ ውስጥ መዋልና ማደር አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ትልቁ ድርሻና ግዴታ የገዛ ራሱን ‹‹ትንቅንቅ›› ከሕጋዊው መድረክ ውጪ ያደረገው መንግሥት ነው፡፡        

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...