Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በመጤው ተምች ሳቢያ ፈተና ላይ ወድቀናል››

ኢያን ቼስተርማን፣ የፊድ ዘ ፊውቸር

ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ዋና ኃላፊ

ኢያን ቼስተርማን የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤኣይዲ) ፋይናንስ በሚያደርገውና የ‹‹ፊድ ዘ ፊውቸር›› ኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ የእሴት ሥራዎች ላይ ለሚካሄደው እንቅስቃሴ ዋና ኃላፊ ወይም ቺፍ ኦፍ ፓርቲ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ በቆሎን ጨምሮ በስድስት ዋና ዋና ሰብሎች ላይ የእሴት ሰንሰለት የማስፋፋት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአብዛኛው በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ውስጥ የሚተገበር ፕሮግራም ነው፡፡ በግብርና መስክ ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱት ሚስተር ቼስተርማን፣ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በኬንያ፣ በዛምቢያ፣ እንዲሁም በዚምባብዌ ሠርተዋል። የእሴት ሰንሰለት ማስፋፊያ ፕሮግራምን እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ እንዲመሩና እንዲያስተገብሩ በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፉት ሚስተር ቼስተርማን፣ በኢትዮጵያ የተከሰተውንና መነሻው ከአሜሪካ፣ ከማዕከላዊ አሜሪካና ከካሪቢያን አገሮች የሆነውና በአሁኑ ወቅት መጤ ተምች እየተባለ የሚጠራውን የተባይ ወረርሽኝ መከላከል ስለሚቻልባቸው መንገዶች ይናገራሉ፡፡ ከመጤው ተምች ባልተናነሰ በኢትዮጵያ የእርሻ ሥራ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ገበሬውን ዋጋ እንደሚያስከፍሉት የሚጠቅሱት ሚስተር ቼስተርማን፣ በድኅረ ምርት አሰባሰብ ሳቢያ በበቆሎ ሰብል ላይ ብቻ እስከ 20 በመቶ የሚገመት የምርት ብክነት እንደሚታይ ያብራራሉ፡፡ ጥሩ የግብርና ዘዴዎች በማሳ ውስጥ በአብዛኛው አለመተግበራቸው የምርት ዘር እጥረት፣ የማዳበሪያ፣ የአፈር ጥበቃ ችግሮችና ሌሎችም መጤው ተምች ከሚያደርሰው ጉዳት ያልተናነሰ ፈተና መደቀናቸውን ይናገራሉ፡፡ ብርሃኑ ፈቃደ መጤው አረም በአገሪቱ የሰብል ምርት ላይ ስለደቀነው አደጋ፣ በዚህ ዓመት ሊደርስ ስለሚችለው ጉዳት፣ መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄና ስለሌሎችም ጉዳዮች ሚስተር ቼስተርማንን በማነጋገር የሚከተለውን ቃለ ምልልስ አጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- መነሻውን ከአሜሪካ አገሮች ያደረገው መጤ ተምች አፍሪካን በከፍተኛ ደረጃ በመውረር ችግር ፈጥሯል፡፡ እንዴት ነው ወደ አፍሪካ ሊመጣ የቻለው?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- የተምቹ ዋና መገኛ የካሪቢያንና የማዕከላዊ አሜሪካ አካባቢዎች ናቸው፡፡ የተምቹ ሥርወ መነሻ እነዚህ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለፉት በርካታ መቶ ዓመታት ውስጥ ተምቹ በዩናይትድ ስቴትስ ተንሰራፍቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ‹‹ፎል አርሚዋርም›› የሚል ስያሜ ያገኘው፡፡ ‹‹ፎል›› ወይም ‹‹መጸው›› የሚለው ቃል ከአሜሪካ ቋንቋ የተወሰደው፣ ተምቹ በዚህ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ስለሚራባ ነው፡፡ ወደ አፍሪካ የተዛመተው እ.ኤ.አ. በ2017 ነው፡፡ ስለዚህ ከአንድ ዓመት በፊት ተምቹ በባህር ተጉዞ እንዴት ወደ አፍሪካ እንደመጣ ማንም በእርግጠኝነት መናገር አልቻለም፡፡ ምናልባትም በመርከብ ጭነት አሊያም በአውሮፕላን ተጓጉዞ ሊመጣ እንደቻለ ይገመታል፡፡ ይሁንና የተስፋፋበት መንገድ ገና አልታወቀም፡፡ የምናውቀው ነገር ቢኖር መጀመርያ በምዕራብ አፍሪካ ከታየ በኋላ በፍጥነት በመዛመት ላይ እንደሚገኝ ነው፡፡ በ12 ወራት ውስጥ ብቻ መላውን አፍሪካ አዳርሷል፡፡ እንደ መጤው ተምች ያለ እጅግ አነስተኛ ነፍሳት እንዴት በዚህን ያህል ፍጥነት ሊዛመት ቻለ ካልን፣ በመጀመርያ እንደ እሳት ራት ዓይነት ቢራቢሮ መሰል ፍጥረት ሆኖ ዑደቱን ይጀምራል፡፡ በዚህ ወቅት የአውራ ጣት ጥፍር የሚያህል መጠን ቢኖረውም፣ በጥሩ አኳኋን የሚነፍስ ንፋስ ካገኘ በቀን እስከ 150 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አስገራሚ አቅም አለው፡፡ በዚህ የተነሳም ሰፊ ቦታ በመሸፈን ይጓዛል፡፡ በሕይወት ዑደቱ ወቅት ለመመገብ በሚመርጠው ሰብል ላይ እንቁላሉን ይጥላል፡፡ እንቁላሎቹ ሲፈለፈሉም ወደ አባ ጨጓሬነት ይቀየራሉ፡፡ አባ ጨጓሬውም ከብዙ ሒደቶች በኋላ እየገዘፈ በመምጣት ሰባት የዕድገት ምዕራፎችን ያልፋል፡፡ በመጨረሻም ትልቁ አባ ጨጓሬ ወደ ሙሽሬነት (ፑፓ) በማደግ እንደ እሳት እራት የመሰለ ነፍሳት ሆኖ ይወጣል፡፡ በመሆኑም ባለፉት ወራት ውስጥ መላውን አፍሪካ በማዳረስ አዲስና አሥጊ ነፍሳት በመሆን የአፍሪካን ግብርና የሚፈታተን ለመሆን በቅቷል፡፡

ሪፖርተር፡- መጤው ተምች ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ግብርና ላይ በጣም ከባድ ጥፋት የማድረስ አቅም እንዳለው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ምን ይጠብቃታል? በአሁኑ ወቅት የሚታየው ሁኔታስ ምን ይመስላል?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- መጤው ተምች በኢትዮጵያ የነበረውን መስፋፋት ስንመለከት በመጀመርያ የታየው በደቡብ ክልል ሲሆን፣ በሚያዝያ ወር ገደማ ነበር መኖሩ የታወቀው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቀስ በቀስ ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ ውስጥ ሥርጭቱ እየተስፋፋ መሆኑ በግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና በቆሎ በሚያመርቱ ገበሬዎች እየተለየ ሊመጣ ችሏል፡፡ ከደቡብ ክልል ባሻገርም በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ከነሐሴ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ የተምቹ ሥርጭት መኖሩ ታውቋል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባዘጋጀው መረጃ መሠረትም ተመሳሳይ የሥርጭትና የሰብል ጥቃት መድረሱን ለማወቅ ችለናል፡፡ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የተባይ ጥቃት የታየው በደቡብ ክልል ሲሆን፣ ቁጥሮች እንደሚያሳዩትም እስከ 30 በመቶ የሚሆነው የበቆሎ ሰብል በዚህ ተምች መጠቃቱን ነው፡፡ በኦሮሚያ የተምች ወረርሽኙ ሙሉ ለሙሉ በነበረበት ወቅት 25 በመቶ የበቆሎ ሰብል ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በአማራ ክልል 20 በመቶ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል የጉዳቱ መጠን 12 በመቶ ብቻ እንደነበር ታውቋል፡፡ ይህ የሚያሳያው ተምቹ ገና እንደ አዲስ በገባ ሰሞን የነበረውን ጉዳት ይመስለኛል፡፡ ሰዎች የገመቱት ተምቹ ልክ እንደ ቱሪስት በቶሎ የሚሄድ አድርገው ነበር፡፡ ተምቹ የመጣው ግን ለመቆየት ነው፡፡ ዜጋ ሆኗል፡፡ ተምቹ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተከሰተ መጤ ግን ቋሚ ተባይ ሆኗል፡፡

ተምቹ አፍሪካን ይወዳል፡፡ ምክንያቱም አፍሪካ ሞቃት ቦታ ነው፡፡ ብርዳማና ቀዝቃዛ የበጋ ወራት በአፍሪካ የሉም፡፡ ስለዚህ ተምቹ አይሞትም፡፡ በተፈጥሮ ያገኘው ምቹ አጋጣሚ ስላለ ነው በአፍሪካ በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው፡፡ እንደማስበው ሁለት ነገሮች ያሳስቡኛል፡፡ አንደኛው በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሲስፋፋ አስተውለናል፡፡ ከጀምሩ የነበረው የሥርጭትና የሰብል ጥፋት መጠን በጣም ከፍተኛ እንደነበርም ታውቋል፡፡ በዚህ ዓመት የሚኖረው ሁኔታም እንደ ዩኤስኤአይዲ ፕሮጀክት ያሳስበናል፡፡ በርካታ ተቋማትም የእኛን ሥጋት ይጋራሉ፡፡ ተምቹ በአገሪቱ ለመስፋፋት አጋጣሚውን አግኝቷል፡፡ ሌላው አሁንም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ የመስኖ ሰብሎችን የማጥቃት አዝማሚያ እንዳለው እያየን ነው፡፡ በደቡብና በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢያዎች የመስኖ ሰብሎች አሉ፡፡ እነዚህ ውኃና ተፈላጊውን ነገር የያዙ ከአባቢው በተለየ ሁኔታ የሚታዩ እኛ ‹‹ኦይሲስ›› ብለን የምንጠራቸው ናቸው፡፡ በአነስተኛ መጠን በመስኖ የሚለማ የበቆሎ ሰብል የሚገኝባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ የተቀረው አካባቢ ደረቅና ለተምቹ ምግብ የሚሆን ነገር የማይገኝበት በመሆኑ የመስኖው እርሻ ለተምቹ ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጠ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚደርሱ የመስኖ በቆሎ ማሳያዎች ላይ ሲደርስ እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ጉዳት በዋናው የምርት ወቅትም ሰብሎች ላይ ሊደርስ የሚችል ነው ማለት ነው?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- ጉዳቱ በዋናው የሰብል ምርት ወቅት ያጋጥማል ማለት አይደለም፡፡ የመጤው ተምች ተፈጥሯዊ ጠላቶች የሆኑ ነገሮች በሥርዓተ ምኅዳሩ ውስጥ መታየት ጀምረዋል፡፡ የአፍሪካ ተምች ወይም ‹አፍሪካ አርሚዋርም› የሚባለው በአፍሪካ ለዓመታት የኖረ ነው፡፡ መጤው ተምች ለነባሩ የአፍሪካ ተምች የአጎት ልጅ እንደ ማለት ነው፡፡ ከውጭ በቅርቡ የመጣ ዘመድ፡፡ የተፈጥሮ ጠላቶቹ መጤውን ተምች መብላትና ማጥቃት ጀምረዋል፡፡ ሌላኛው የተምቹን ጥቃት ለመቀነስ የሚረዳው ከባድ ዝናብ እንደሆነ እናስባለን፡፡ ከባድ ዝናብ ትንንሽ ነፍሳትን ማጥፋትና መግደል ይችላል፡፡ የመስኖ ሰብሎች ከለላ ባይሰጡም፣ ወደ ዋናው የዝናብ ወቅት ስንገባ ግን የዝናቡ መጠን የተምቹን ሥርጭት ሊቀንሰው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በተምቹ የደረሰው ወረራ ምን ያህል ጥፋት ሊስከትል ይችላል? በዚህ ዓመት ሊደርስ ስለሚችለው ጉዳት የሚያሳዩ ትንበያዎች አሉ?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ጥያቄ እያነሳ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ነው ብሎ ለመናገር ከባድ ነው፡፡ ይህ ነው ብሎ ለመተንበይ የሚያስችል የተራቀቀ የክትትል ሥርዓት የለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓመት የክትትል ሥራውን ለማሻሻልና ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ጋር አብሮ ለመሥራት ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ ምክንያቱም መረጃ ነው እኛንም ሆነ ሌሎች ተቋማት እንዲሁም ዩኒየኖችን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና ገበሬዎችን ሳይቀር የጋራ ጥረታችንን በማዛመድ በትኩረት እንድንሠራ የሚረዳን፡፡ ዘመቻችን በምን ላይ እንዲያተኩር እናድርግ የሚለውን የሚመልስልን መረጃ ነው፡፡ በመሆኑም መረጃ ለመሰብሰብ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እየደገፍን ነው፡፡ ሆኖም ሥጋት አለን፡፡ የምዕራብ አፍሪካን ተሞክሮ ያየን እንደሆነ፣ ለምሳሌ ጋና ውስጥ ሌላ የዩኤስአይዲ ፕሮጀክት አለን፡፡ በዚሁ በተምች ጉዳይ ላይ መረጃ እንለዋወጣለን፡፡ ተምቹ በተከሰተ በሁለተኛው ዓመት የወረራ መጠኑ እስከ 70 በመቶ ሊደርስ ችሏል፡፡ በተጨማሪም 40 በመቶ የግብርና ውጤታቸውን አጥተዋል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ሥጋት በሚደቅነው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ውስጥ አባ ጨጓሬውና የእሳት ራት የምንለው ዓይነት ደረጃ የደረሰው ተምች በዝናብ እስካልተመታ ድረስ፣ ሩቡን የገበሬዎችን ሰብል አሊያም ከዚህ በከፋ ደረጃ ሲሆን ደግሞ ግማሽ ያህሉን ሰብላቸውን ሊያሳጣቸው ይችላል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በእጅ መልቀምና ፀረ ተባይ ኬሚካል መርጨት ውጤት ተምቹን ለመከላከል አስችሎ ይሆናል፡፡ አደጋው ግን በዚህ ውጤት ተኩራርተን ከተቀመጥን ነው፡፡ አሁን ለየት ያለ ጉዳይ እያየን ነው፡፡ በመስኖ የሚለሙ ሰብሎችም እየተጠቁ ነው፡፡ ካለፈው ዓመት የተረፈ ምርት አለ፡፡ መጤው ተምች እንደሆነ ራሱን አላምዷል፡፡ ወደ ሁሉም ክልሎች ተሠራጭቷል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓመት የከፋ ጉዳት ለማድረስ የሚችልበት ዕድል አለው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት ያሠራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሦስት እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት በአፍሪካ ሊከሰት እንደሚችል፣ ከ30 በላይ የሰብል ዓይነቶችም በዚህ ተምች መጠቃታቸውን የሚያመላካት መረጃ ወጥቷል፡፡

ሚ/ር ቼስተርማን፡- ይህንን ጥያቄ በሁለት መንገድ እወስደዋለሁ፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው የተምቹ ወረርሽኝ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን የኢኮኖሚ ጉዳት የሚያመላክት ትክክለኛ ትንበያ አላየንም፡፡ እርግጥ ሌሎች በአፍሪካ ደረጃ የደረሰውን ጉዳት የሚቃኙ መላምቶች በጥናት ተቋማት ይፋ ተደርገዋል፡፡ መረጃዎቹ በአፍሪካ የተከሰተው ተምች ያስከተለውን አስደንጋጭ ኪሳራ ያሳያሉ፡፡ ተመሳሳይ ወጪ በኢትዮጵያም ሊከሰት የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ በኢትዮጵያ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በበቆሎ አምራችነት እንደሚተዳደር የታወቀ ነው፡፡ ከምግብ ዋስትና አኳያ በቆሎ ትልቁ የእህል ምርት ነው፡፡ በመሆኑም እንደ የኢኮኖሚና የምግብ ዋስትና ይዘቱ ካየነው፣ ተምቹ በበቆሎ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ለዚህም ነው እንደ እኛ ያለው ፕሮጀክት ውስጥ ያሉ ሰዎችን በማስተባበር ተምቹን ለማጥፋት የምንንቀሳቀሰው፡፡ ብዙ መረጃ መውጣት አለበት፡፡ ሕዝብ ትክክለኛው መረጃ ሊደርሰው ይገባል፡፡ ውጤታማ የተግባቦት ሥራ በማከናወን ስለተምቹ ግንዛቤን ማስፋፋት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን መረጃ በሚዲያው በኩል ለሕዝብ ማድረስ ይገባል፡፡  

ሪፖርተር፡- የተምቹን ጉዳት ለመከላከል እንዲቻል ምን ዓይነት አማራጮች እንዲወሰዱ ይመከራል? በእጅ መልቀምና የኬሚካል ርጭት ባለፈው ዓመት ውጤት እንዳመጡ ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን እንደተጠበቀው ውጤታማ አልነበሩም፡፡ በዚህ ዓመት ተምቹ ከሚጠበቀው በላይ ከባድ ሥጋት ከደቀነ፣ ምን ዓይነት ተጨማሪ የመከላከያ ዘዴዎች እንዲኖሩ ይመክራሉ?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- እንደማስበው በሁለት አማራጮች ላይ ድጋፍም ምክረ ሐሳብም እየሰጠን ነው፡፡ አንደኛው መከላከል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ከቀላል መልዕክት የሚነሳ ነው፡፡ ገበሬዎች ማሳዎቻቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጥሩ የእርሻ ሥልቶችንና ዘዴዎችን መከተል አለባቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መጤው ተምች በሰብሎች ላይ ስላደረሰው ጥፋት እናወራለን፡፡ ነገር ግን በሚገባ ያልተዘሩ ዘሮች፣ ዘር እንዲዘራበት የታረሰው መሬት ላይ የሚታየው ሰፊ ክፍተት አለመጣጣም፣ ዝቅተኛ ጥራት ያለው ዘር መጠቀም፣ የማዳበሪያ እጥረትና መጥፎ የአፈር ጥበቃ ሳይሻሻል ሰዎች በተምቹ ላይ ሲያማርሩ ይታያሉ፡፡ መልካምና ጤነኛ የበቆሎ ሰብል የምታመርት ከሆነ፣ ይህ በራሱ በጣም ወሳኝ ሊባል የሚችል የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ትኩረታችን በገበሬዎች መሠረታዊ የበቆሎ ኤክስቴንሽን ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ በመሠረታዊነት የምታከናውናቸውን ነገሮች በትክክለኛው መንገድ መወጣት ይኖርብሃል፡፡ የሰብል አስተዳደርን ማሻሻል ይጠበቅብሃል፡፡ ተምቹን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ካየን፣ በእጅ መልቀምና የኬሚካል ርጭት መልዕክቶች ሲሠራጩ እናያለን፡፡ ሆኖም የተቀናጀ የተባይ ቁጥጥር ሥርዓት ግን መኖር አለበት፡፡ ይህ ሥርዓት በእጅ መልቀምንም ሆነ የኬሚካል ርጭትን የሚያካትት ቢሆንም፣ ሌሎችም በገበሬው ደረጃ የሚከናወኑ የተባይ ቁጥጥር ዘዴዎችንም ይይዛል፡፡ ገበሬዎች እንዴት ተባይ መከታተል እንደሚገባቸው ሥልጠና ያገኙበታል፡፡

የእኛ ትኩረት ገበሬው መቼ ርጭት ማከናወን እንዳለበት መንገር አይደለም፡፡ የእኛ ትኩረት ገበሬው ርጭት የማያካሂድባቸውን ወቅቶች ለይቶ እንደሚያውቅ ማድረግም ጭምር ነው፡፡ ዝናብ እየጣለ ከሆነ ፀረ ተባይ ኬሚካል መርጨት አይጠበቅብህም፡፡ ምክንያቱም ዝናቡ ከሚረጨው ኬሚካል የተሻለ ሆኖ ተባዩን ሊከላከል ስለሚችል ነው፡፡ በዚህ የመኸር ወቅት ቀደም ብሎ መዝራትም ጥቅም አለው፡፡ ሌሎች ተምቹ ሊመገባቸው የሚችሉ አማራጭ ሰብሎችን መዝራት ከተቻለም፣ በበቆሎ ሰብል ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል፡፡ ኬሚካል መርጨት ግድ ከሆነም በሚረጨው ሰው ላይ ያን ያህል ጉዳት ወይም ተፅዕኖ የማያደርሱ፣ አደገኛነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ውጤታማ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች አሉ፡፡ ከማኀበረሰቡ ተመልምለው የመጡ የርጭት ባለሙያዎችን እያሠለጠንን ነው፡፡ ፀረ ተባይ ኬሚካሉ ውጤታማ የሚሆነውም በባለሙያ እንዲረጭ ሲደረግ በመሆኑ አገልግሎቱን የገበሬውን ኪስ በማይጎዳ ገንዘብ እንዲያቀርቡ ማድረግ ይገባል፡፡ ርጭቱን የሚያካሂዱት ገበሬዎች ያለ በቂ ሥልጠናና ብዙ በመርጨታቸው የሚጠፋ እየመሰላቸው፣ አሊያም ጥቂት ሲረጩ ተባዩ አልጠፋ እያላቸው ነው መሰል ደጋግመው ሲረጩ ይውላሉ፡፡ የኬሚካል ርጭት ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡ የሚረጩት ሰዎች የመደካከም፣ የመዝለፍለፍ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ኬሚካል መርጨት እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ተገቢው የኬሚካል መከላከለያ አለማድረግም አንዱ በርጭት ወቅት የሚታይ ችግር በመሆኑ በርካቶች ለኬሚካል ንክኪ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ በባለሙያ ርጭቱን ማከናወኑ የተሻለ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከሳይንስ ተቋማት ጋር እየሠራን በመሆናችን፣ አንዳንድ መጤውን ተምች መቋቋም የሚችሉ አገር በቀል ዝርያዎች እንዳሉ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ምርምሮቹ በሒደት ላይ ናቸው፡፡ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም ይህም አንዱ የመከላከያ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡    

ሪፖርተር፡- መጤው ተምች በተነሳባቸው አካባቢዎች ስለሚደርሱ ጉዳቶች ያን ያህል አልሰማንም፡፡ በአንፃሩ በአፍሪካ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመስፋፋት እንዲህ ያለውን ጉዳት እንዲያደርስ ምን ምቹ ሁኔታ ቢያገኝ ነው? አብዛኞቹ የእርሻ ማሳቸውን በአግባቡ መንከባከብ የማይችሉ አነስተኛ ገበሬዎች በመሆናቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- የትኛውም እኛ የምንለግሰው ምክረ ሐሳብ እውነታውን የሚያሳይና ተግባር ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ አነስተኛ ገበሬዎች ካላቸው የመሬት ይዞታ አኳያ፣ ከሚያገኙት ዓመታዊ ገቢና ከሚገኙበት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሐሳብና ምክር መስጠት ይገባል፡፡ የሚነደፉት መፍትሔዎችም ገበሬው ላይ አላስፈላጊ ወጪ የሚያስከትሉ ሳይሆኑ፣ እውነታው ላይ የተመረኮዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ እንደ አገር መረበሽ የሚያስፈልገን አይመስለኝም፡፡ በዚህ ዓመት ሊኖር የሚችለው የመጤው ተምች ወረርሽኝ ከፍተኛ ሊሆን የሚችልበት ሥጋት አለ፡፡ ይህ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ጥናታዊ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት መጤው ተምች ልክ እንደ ሌሎች ተባዮች ሁሉ የሚያልፍባቸው ዑደቶች አሉ፡፡ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች እንደገለጹልን ከሆነ፣ በአምስት ወይም በስድስት ዓመት አንዴ ተምቹ መጥፎ ጊዜ እንደሚያሳልፍ ሐሳባቸውን አካፍለውናል፡፡ በሌሎቹ ዓመታት ደግሞ ጥሩ የዝናብ መጠንና የተፈጥሮ ጠላቶቹ ሊቋቋሙት እንደሚችሉ ተስፋ አለ፡፡ በመሆኑም ተምቹ እንደ ማንኛውም ተባይ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚው አለ፡፡ በመደበኛ መንገድ መቆጣጠር የሚቻልባቸው ዕድሎች አልጠፉም፡፡ እንደማስበው ነገሮችንና አካሄዳችንን መለየት ይጠበቅብናል፡፡ ከፍተኛ ወረርሽኝ የሚያጋጥመን ከሆነ፣ ያለንን ነገር ሁሉ በማንቀሳቀስ ለመቆጣጠር መጣር አለብን፡፡ ሆኖም በቆሎን የማያጠፋበት ወቅትም አለ፡፡ ተምቹን በተፈጥሮ መቆጣጠር የሚቻልባቸውና ገበሬዎችም ይህንን በመረዳት አሠራራቸውን የሚያስተካክሉበት መንገድ ይኖራል፡፡ በቆሎ ግን አነስተኛ ዋጋ ያለው ሰብል መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ ምንም እንኳ ለብዙዎች ቋሚ የምግብ ሰብልም ቢሆን፣ አነስተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ በመሆኑም ገበሬዎች ምርታቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተሻለ ዋጋ የሚያስገኙላቸውን ሰብሎች መዝራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለራሳቸውና ለከብቶቻቸው የሚስማሙ ሰብሎች በርካታ ናቸው፡፡ ይህም ለማስተላለፍ ከምንፈልጋቸው መልዕክቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ መጤ ተምች ወደ አገሪቱ የመጣው ከ7.8 ሚሊዮን ያላነሱ ሰዎች ለአስቸኳይ የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ በተዳረጉበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት በጣም አስከፊ ድርቅ ሲከሰት በመቆየቱ ሚሊዮኖች ለምግብ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት የተምች ወረርሽኝ መከሰቱ ተደራራቢ ችግር ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ምን ያህል ቁርጠኝነቱን እያሳየና የሚፈለገውን ጥረት በማድረግ የተምቹን ጉዳት ለመከላከል እየሞከረ ነው ማለት ይችላል?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- መጤ ተምቹን የመከላከል ኃላፊነት የተሰጠው ብሔራዊ ግብረ ኃይል በመመሥረቱ የእኛ ግንኙነት ከዚህ ግብረ ኃይል ጋር በመሆን ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ግብረ ኃይል የሚያስተባብረው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሲሆን፣ የሰብል ጥበቃ ዳይሬክቶሬትም በዚሁ ሥራ ውስጥ ተሳታፊ ነው፡፡ እነዚህ የመሪነት ሚናውን እንዲጫወቱ ኃላፊነቱ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የዚህ ሥራ ሙሉ ኃላፊነት አለበት፡፡ ተምቹን መከላከል ስለሚቻልበት አግባብ ስትራቴጂ ነድፈዋል፡፡ ሰፊ የግንኙነት ኔትወርክ በመፍጠር ከዩኤስኤአይዲ፣ ከዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት (ኤፍኤኦ) እና ከሌሎችም ጋር ሰፊ ግንኙነት አላቸው፡፡ እኛ ባለን አነስተኛ አቅም ብሔራዊ ስትራቴጂውን ለማገዝ እየሞከርን ነው፡፡ በስትራቴጂው ውስጥ በሰፊው ለተቀመጡ ሥራዎች የሚያግዙ ድጋፎችን በመስጠት በቅርበት ተባብረን እየሠራን ነው፡፡ እንደማስበው ውጤታማ ስትራቴጂ ተነድፏል፡፡ ሆኖም ከሚዲያውም ጋር በመሆንና ውጤታማ የተግባቦት ሥራ በማከናወን ለገበሬው አስፈላጊውን መረጃ ማድረስ ይገባናል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ተገቢው የቴክኒክ መልዕክት ለገበሬውና ለሚመለከታቸው ሁሉ እንዲተላለፍ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በእርስዎ አስተያየት በአጭር ጊዜ፣ በመጪዎቹ ወራት ውስጥ በኢትዮጵያም ሆነ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ውስጥ የተምቹን ወረርሽን ለመከላከል ሲባል ሊወሰድ የሚገባው ዕርምጃ ምንድን ነው?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- የመጀመርያው ሰፊ የግንዛቤ ሥራ ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲወጡ የነበሩ መልዕክቶችን ማጠናከርና በሚገባ ማሠራጨት ያስፈልጋል፡፡ መረጃው ለገበሬዎች በተገቢው ጊዜ እንዲደርሳቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ተምቹን ተቀብሎና ተመቻችቶ የመቀመጥ ስሜት እንዳይፈጠር ማድረግም ወሳኝ ሥራ ነው፡፡ የሚተላለፈው መልዕክት በሁለትዮሽ መንገድ የሚካሄድ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ከገበሬዎች የሚመነጨውን መልዕክትም መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ የሚገጥማቸው ፈተና ምን እንደሆነ፣ ሥጋታቸውና የመፍትሔ ሐሳባቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ይገባል፡፡ ገበሬዎች እጅግ በርካታ ሐሳቦችን ያመቁ በመሆናቸው የትኛው አካሄድ ውጤት እንደሚያመጣና የትኛው እንደማይሠራ ያውቃሉ፡፡ ይሁንና እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች ለመቀበል የሚያስልች የሁለትዮች የመልዕክት ልውውጥ ማካሄድ የሚቻልበት ሥርዓት በዚህ አገር አልተመሠረተም፡፡ በመሆኑም ገበሬዎች ያላቸውን ሐሳብና መልክዕት ወደ ተቋማት ማድረስ የሚቻልበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- መጤው ተምች በቀላሉ የማይጠፋና ለረዥም ጊዜ ለመቆየት እንደ መጣ ገልጸዋል፡፡ የተምቹን ጉዳት ለመከላከል በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎች ምንድን ናቸው ይላሉ?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- እንደማስበው የተፈጥሮ ሚዛኑን እንደሚጠብቅ በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ገበሬዎች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ በዩኤስኤአይዲም ሆነ በሌሎች ተቋማት በኩል እየተከናወኑ ያሉ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ምርታቸውን በእጥፍ ለመጨመር የሚያስችሉ ጥራት ያላቸውን ዘሮች መጠቀም፣ ወይም ደግሞ ጥሩ የእርሻ ዘዴዎችን በመተግበር ውጤታማ መሆን የሚችሉባቸው መንገዶች አሉ፡፡ በግርድፉ እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የበቆሎ ሰብል በድኅረ ምርት አሰባሰብ ወቅት በብክነት ሳቢያ እንደሚጠፋ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ያለውን የምርት ብክለት በቀላሉ መከላከል የሚቻልባቸው ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የፒፒ ከረጢትን በመጠቀም ድኅረ ምርት ብክነቱን ከ20 በመቶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች ከመጤው ተምች ጋር አይዛመዱም፡፡ አይገናኙም፡፡ በመሆኑም ገበሬዎች በመጤው ተምች ሳቢያ የሚደርስባቸውን የኢኮኖሚ፣ የቴክኒክና የእርሻ ሥራ ጉዳት መቀነስ የሚችሉባቸው መንገዶች አሉ፡፡ የተምቹን ወረርሽን በተገቢው ማዕቀፍ ውስጥ በማስቀመጥ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ሰው ስለመጤው ተምች የሚያወራው ልክ የሰይጣን ሥራ እንደሆነ አድርጎ ነው፡፡ እንዲህ ባለው አመለካከት ውስጥ ካለን ጥሩ የእርሻ ዘዴዎችን ከመከተል በድኅረ ምርት ለሚባክነው ምርት ያለንን ትኩረት እናጣለን ማለት ነው፡፡ አንደኛው መልዕክት ሌላኛውን እየዋጠው ነው ማለት ነው፡፡ በበቆሎ ሰብል ላይ ሊኖር ስለሚገባው የእሴት ሰንሰለት መነጋገር አለብን፡፡ የምርት፣ የክምችት፣ የገበያና ሌሎች ጉዳዮች በተገቢው መንገድ መካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ አዎን በመጤው ተምች ሳቢያ ፈተና ላይ ወድቀናል፡፡ ነገር ግን መቋቋም የምንችልባቸው መንገዶች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓመት ሊኖር ስለሚችለው ጉዳት የሚያሳዩ አኃዞችን ወይም ትንበያዎችን ማወቅ አልታቸለም ማለት ነው?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- በዚህ ወቅት መተንበይ ከባድ ነው፡፡ እንደማስበው የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥርዓቱ ስለተዘረጋ ተጨማሪ መረጃዎች መውጣት ይጀምራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ሊመጣ የሚችለው ጉዳት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል የምናውቅበት ዕድል ይኖራል፡፡ መረጃው ለሁሉም የሚቀርብበት አጋጣሚ ስለሚፈጠር ወደፊት እንጂ አሁን ላይ መናገርም ጉዳቱን መተንበይም ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቃለ ምልልስ በመነሳት መጤው ተምች በኢትዮጵያ ላይ ከባድ አደጋ ስለመደቀኑ መደምደም እንችላለን?

ሚ/ር ቼስተርማን፡- አዎን እንደዚያ ነው እኛም የምናምነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...